ደራሼ – በጥምቀት ሰሞን

0
1639

ከአዲስ አበባ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ከሚገኘው የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ደጅ ተነስተን አርባ ምንጭ እየዘለቅን ነው። እናንተ እነማን ናችሁ? ላለ፣ በደቡብ ክልል ጊዶሌ ከተማ በደራሼ ወረዳ የሚከበረውን የፊላ ፌስቲቫል ተመልክቶና ቃኝቶ ለተመልካች፣ ለአድማጭ እንዲሁም ለአንባቢ ለማድረስ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት፣ ከየመገናኛ ብዙኀኑ የተውጣጣን ጋዜጠኞችና የካሜራ ባለሞያዎች። እነሆ እኔም ከተጓዦቹ መካከል ነበርኩና፣ ከደርሶ መልስ በሰው አእምሮ አድሮ ለትውስታ ከሚቀረው መካከል ይህን የጉዞ ማስታወሻ ላካፍላችሁ ወደድኩ፤ ልምላሜ የማይለየው ደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል በፀሐይዋ ንዳድ የተበገረ አይመስልም። ከተራሮች አናት አንስቶ ዳርቻ የሌላቸው የሚመስሉ መሬቶች አረንጓዴ ምንጣፍ ለብሰዋል። ረጃጅምና ባለሰፋፊ ቅርንጫፍ፣ የጎልማሳ እድሜ እንዳስቆጠሩ ግንዳቸው የሚያሳብቅ ዛፎች ስብሰባ የተቀመጡ አልያም ሰልፍ የወጡ ይመስላሉ። አሻግረን ስንመለከት ከሰማይ ጋር የገጠሙ የሚመስሉት ሐይቆች የተሳፈርንበት መኪና ጎማ ከረገጠው መሬት ውጪ ምድር ሁሉ በውሃ የተመላች የሚመስልን ስሜት ይፈጥራል።

በነገራችን ላይ፣ የካሜራ ባለሞያ እንዲህ ያለውን የተፈጥሮ ትዕይንት በምስል ቀርጾ ሲያቀርብ ዳኝነቱን ለተመልካች ይተዋል። ወዲህ ግን፣ ለአንባቢ አልያም ለአድማጭ ብቻ ‹ይህን ውበት ዐየሁ› ብሎ መንገር አስቸጋሪና ከባድ ነው። ቃላት በአንድ ወገን ግነት ሊመስሉ አልያም ሊያሳንሱ ይችላሉ። እንግዲህ ማየት ማመን፣ ሳያዩ ማመን ደግሞ ብጽዕና ነውና፣ መልክዓ ምድሩ፣ የሰዉ እንግዳ ተቀባይነት፣ ውበትና ድምቀቱ እንዲህ ነው ብዬ ስጽፍ፣ ከአገላለጽ አሳንሼ እንጂ አብዝቼ እንዳልሆነ እንድትረዱኝ አደራ እላለሁ።

ወደ ነገራችን እንመለስ፤ አዳራችንን አርባ ምንጭ አድርገን ረፈድፈድ ሲል ወደ የደራሼ ወረዳ ማእከል ወደ ሆነችው ጊዶሌ ከተማ ደረስን። የከተማዋ መግቢያ ጀምሮ መንገዱ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ሰንደቅ ዓላማዎች ደምቋል። የደረስንበት እለት የጥምቀት ዋዜማ ወይም ከተራ ነበር። የገባንበትን ጨምሮ በሦስት አቅጣጫ የሚታዩት የከተማዋ ዋና ዋና የሚባሉ መንገዶች በሕዝብ ለመመላት አፍታ አልወሰደባቸውም። እኛም እግራችን አካባቢው እንደደረሰ ማረፊያችንን ከመፈለግ በኋላ የዚህ ሁነት አካል ለመሆን ተጣደፍን።

ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ በደራሼም ይሠራል፤ ቆነጃጅቱ ሁሉ አደባባዩን መልተውታል። ነጠላ ደርበው በዝማሬና በእልልታ ከተጠመዱት ኋላ ፊላ ከሚጫወቱት በኩል በውብ የልጅነትና የወጣትነት ለዛ የሚጫወቱና የሚሳሳቁ የደራሼ ቆነጃጅትና ጉብሎች ይታያሉ። እርሱ ትከሻዋ ላይ፣ እርሷ ወገቡ ላይ እጃቸውን አሳርፈው ወዲያና ወዲህ እያሉ፣ ወንዶቹም እየተቀያየሩ ሴቷን እያቀፉ የእግር ምታቸውን ከፊላው ጋር አስተካክለው ይጨፍራሉ። ጥር በደራሼ እንዲህ በወጣቶችና ልጆች ቡረቃ፣ በአዋቂዎች ፈገግታ ደምቆ ይዘልቃል።

ጥቂት ስለ ደራሼ
ደራሼ ከአርባ ምንጭ ሃምሳ ኪሎሜትር አካባቢ ርቀት ላይ በከፍታ የሚገኝ፣ አራት ብሔረሰቦችን ያካተተ ወረዳ ነው። እንደዛሬ ሳይሆን ለወትሮው ‹የሰገን አካባቢ ሕዝቦች› በሚባል ዞን ስር ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች መካከል ነበር። ታዲያ ባለብዙ ታሪክና የበርካታ ታሪካዊ ኹነቶች አውድ የነበረው ይህ አካባቢ፣ የጋርዱላ መገኛ ነው።

ጋርዱላ የተራራና የመስተዳድር መዋቅር ሥም ነው። ከአርባ ምንጭ ወደ ደቡብ ኦሞ በሚወስደው የስምጥ ሸለቆ መንገድ ላይ፣ ከጫሞ ሐይቅ ማብቂያ አርባ ኪሎሜትር አካባቢ በስተምዕራብ ነው፤ መገኛው። ይህ ስፍራ ደግሞ በመስተዳድር መዋቅርነት ያገለገለው ከ1883 ጀምሮ ለአርባ ዓመታት ያህል ነው። አሁን ላይ ታደያ ተራራው በአገር ዐቀፍ ደረጃ ተከልሎ በተመዘገበ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ደን ተሸፍኗል።

ስለጋርዱላ ከተነሳ ከመልክዓ ምድራዊ ሥሪቱ ጀምሮ በመስተዳደርነት የነበረው መልክ ሰፊ ጊዜን የሚሻ በመሆኑ ይቆየን። አንድ ጉዳይ ብቻ ግን ለጉዳያችን ማንደርደሪያ ይሆነን ዘንድ እናክል፣ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ፣ ልክ በዓመቱ ማለትም በ1929 ነው ጋርዱላን ‹የተቆጣጠረው›። ታድያ አርበኞች በሽምቅ ውጊያ እረፍት ቢነሱት፣ ጋርዱላ የአርበኞች የስንቅና የመረጃ ምንጭ ነው በሚል ግምት በአውሮፕላን ቦንብ አጋየው። እና ከተራራው ወረድ ብሎ አዲስ ከተማን ቆረቆረ።
አጋጣሚ ደግሞ ይህ አዲስ ይቆርቆር የተባለው ከተማ የተሰየመበት ስፍራ የደራሼ ብሔረሰብ የባህል መሪ ግራዝማች ሰማ ሳይሌ ‹ቤተመንግሥት› ይዞታ የነበረ ነው። ታድያ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ኪቶሌ እያሉ ነበር መኖሪያ ስፍራቸውን የሚጠሩት፣ ሲውል ሲያድር ጊዶሌ ተባለ። ኪቶሌ ትርጉሙ ‹ወይና ደጋ› እንደማለት ነው።

ታድያ የደራሼ ወረዳ ማእከል የሆነው ጊዶሌ ከተማ፣ ከጠላት የጣልያን ጦር አገር ለቅቆ መውጣት በኋላ ያረፈው በአርበኞች እጅ ላይ ነው። ጋርዱላ መቃጠሉን ተከትሎ ከስፍራው የተፈናቀሉ የአጼ ምኒልክ ሠራዊት ቤተሰብ አባላትም ኑሮአቸውን በጊዶሌ ከተማ አድርገው ነበር። በአካባቢው ለአስተዳደር የተሰየሙ ባለሥልጣናት፣ የቤተክርስትያን አባቶች፣ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ የንግድ ሰዎች ተሰባስበው ነበር።

ይህ ሁሉ ተዳምሮ ደራሼ ወረዳ ከአራቱ ብሔሮች በተጨማሪ ብዝኀነትን የተላበሰ አካባቢ ሊሆን ችሏል። ለምሳሌ ‹ድራይታት› ወይም ‹ዲራሽታት› ተብሎ የሚጠራው ቋንቋ በደራሼ አካባቢ ቢነገርም፣ አማርኛን ጨምሮ ሰፊ የሆነ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ይገኛል። ጋርዱላ ከተማ ከመቃጠሉ አርባ ዓመታት አስቀድሞ በአካባቢው ሰፍሮ የነበረው የምኒልክ ሠራዊት አባላት አብዛኛዎቹ ኦሮምኛ ተናጋሪ ነበሩ። ይህም በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ሰዎችም ቋንቋን እንዲለምዱትና እንዲናገሩት አስችሏል።

የደራሼ ወረዳ 78 ሺሕ 718 ሔክታር የቆዳ ስፋት አለው። በሰሜን የጋሞ ጎፋ፣ በደቡብ የኮንሶና አሌ ወረዳ፣ በምሥራቅ የኮንሶና አማሮ ወረዳ እንዲሁም በምዕራብ የጋሞ ጎፋና የአሌ ወረዳ ያዋስኑታል። በዚህ አካባቢ ጥቂት የማይባሉ ታሪካዊ ኹነት የተፈጸመባቸው መስህቦች እንዲሁም ድንቅ የተፈጥሮ ሀብቶች ይገኛሉ።

ፊላ ፌስቲቫል
በተለያየ መጠን ከቀርከሃና ሸንበቆ የተዘጋጁት ባለቀዳዳዎቹ መሣሪያዎች፣ የሰዎችን ትንፋሽ ሲያገኙ ሊገመት የማይችል ድምጽ ያወጣሉ። አዛውንትም፣ ጎልማሳም የሆኑ ደራሼዎች እንደ ጎረምሳና ወጣቶቹ ለፊላ መሣሪያ ትንፋሽ ሳያጥራቸው በእግራቸው ዜማውን የተከተለ ምት ይመታሉ። መሣሪያውን መጫወት የሚችሉ ሴቶች በትንፋሽ፣ የቀሩት ደግሞ በእግራቸው መሬቱን እየደለቁ ከወዲያ ወዲህ ተያይዘው ይጫወታሉ።

የጊዶሌ ከተማ መሃል ሜዳ የፊላ ጨዋታ አደባባይ ነው። የከተማው ሰው አደባባዩ የሚገኝበትን አደባባይ ‹ፒያሳ› ወይም ‹መስቀል አደባባይ› ብሎ ሲጠራው፣ የገጠሩ ሰው ደግሞ ‹የባህል ጨዋታ አደባባይ› ብሎ ሰይሞታል። ለፊላ ጨዋታ እንዲህ በጥር ወር፣ በጥምቀት ማግስት በአራቱ የከተማዋ ማዕዘናት ተምሞ የሚሞላው ይህን የጊዶሌን መኻል አደባባይ ነው።

ለወትሮ ማኅበረሰቡ በተገኙ መልካም አጋጣሚዎች ይጫወት የነበረውን የፊላ ጨዋታ ለአገር ለማስተዋወቅና ለዓለምም ለማሳየት፣ ዓመታዊ ፌስቲቫል እንዲዘጋጅ የሆነው ከኹለት ዓመት በፊት ነው። በዚህ አጋጣሚም ለደራሼ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች መታየት ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል።

ፊላ ፌስቲቫል ዘንድሮ ማለትም 2013 ለሦስተኛ ጊዜ ነው የተካሄደው። ፊላ ምንድን ነው? ብሎ ለጠየቀ፣ ፊላ የሙዚቃ መሣሪያ ነው። ይህ መሣሪያ አራቱም በወረዳው የሚገኙ ብሔሮች የሚጠቀሙት ሲሆን፣ እነዚህም ደራሼን ጨምሮ ኩሱሜ፣ ማሾሌ እና የሞስዬ ብሔረሰብ ናቸው።

የፊላ ጨዋታ መች ተጀመረ የሚለው ከአፈ ታሪክ የተቀዳ መልስ አለው፣ ይህም ኅብረተሰቡ በአካባቢው መኖር ከጀመረበት ጊዜ የሚነሳ ነው። ታሪኩ ደግሞ እንዲህ ነው አሉን፣ ‹‹ሀልላ የሚባል የቆላ ዛፍ አለ፣ እሾህ ረዘም ያለና ከስሩ ክብ ሆኖ ከጎኑ ክፍተት (ስንጥቅ) ያለው። ነፋስ በሚነፍስበት ጊዜ ታድያ ለጆሮ የሚስብ ድምጽ ያወጣል። እረኞችም ይህን ድምጽ ሰምተውና በድምጹ ተማርከው ተመሳሳይ ድምጽ ለማውጣት የሚችል መሣሪያ ሠሩ።

ይህን ተመሳሳይነት ያለው ድምጽ የሚያወጣ መሣሪያ የሠሩት ከጉሎ እንጨት ነው። እነርሱም በእርሻ ቦታቸው እየነፉ ይጫወቱበት ቀጠሉ። እንዲህ እያለ ተስፋፍቶ፣ በዜማና በአጨዋወት ስልት፣ በምጣኔ፣ በውዝዋዜ ታጅቦ፣ ፊላ ከሙዚቃ መሣሪያነት ብቻ ከመሆን የላቀ የደራሼ ሀብት ሊሆን ቻለ። ከቀርከሃ እና ሸንበቆም እያዘጋጁ ይጫወቱ ቀጠሉ።

የጃዝ አባት ክቡር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ በዚህ ፊላ በተባለ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ዙሪያ ጥናት አድርጓል። በዚህም ጥናት መሠረት ፊላ የጃዝ ሙዚቃ መሠረትና አንድ ግብዓት ሆኖ ሲያገለግል፣ ባለ ሰባት ኖታ የሙዚቃ መሣሪያ መሆኑም ታውቋል።

ፊላ በወረዳው በሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል እንደ ቋንቋ መግባቢያም ጭምር ነው ቢባል ማግነን አይሆንም። ታድያ ከጥምቀትና በማግስቱ በድምቀት በአደባባይ ከሚከበረው የፊላ ጨዋታ በተጨማሪ፣ የተለያዩ ምክንያቶች ለፊላ ጨዋታ ምክንያት ናቸው። እንግዳ ለመቀበል፣ በግጭት ወቅት ድል ሲገኝ፣ በእርቅ ጊዜ ፊላን ይጫወታሉ። ፊላን ለመጫወት እድሜ አልያም ጾታ መስፈርት አይደሉም፣ ስልቱን ማወቅ ብቻ በቂ ነው፤ ቀላል ነው ማለት ግን አይደለም።

በተጨማሪ ፊላን በሰርግ፣ በሚያዝያ ወር ለእርሻ ሥራ ወደ በረሃ በሚወጣበት ጊዜ፣ የመኸር ምርት በሚሰበሰብ ወቅት እንዲሁም በተለያዩ ሐይማኖታዊ ክብረ በዓላት ላይ ይጫወቱታል።

አፍታ ቆይታ ከመምህር ሰይድ መሐመድ ጋር
ሰይድ አሕመድ፣ የጊዶሌ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ከእርሳቸው ጋር ግማሽ ሰዓት የተጠጋ ቆይታ አድርገናል። በግሩም የአተራረክና አገላለጻቸው ካካፈሉን ውስጥ፣ ይልቁንም በአካባቢው የመጀመሪያ ስለሆነው ጥንታዊ ትምህርት ቤት ያወጉን ይገኝበታል። መምህር ሰይድ በዚህ ትምህርት ቤት ተምረዋል፣ አስተምረዋልም።
‹የፊታውራሪ ገበየሁ መታሰቢያ ትምህርት ቤት› ይባላል። ከመግቢያው በር ላይ ተጽፎ የሚገኘው ሥም ግን ‹የጊዶሌ መጀመሪያ ደረጃ 1ኛና 2ኛ ሳይክል ትምህርት ቤት› የሚል ነው። የትምህርት ቤቱ ሥያሜ የተቀየረው በደርግ ዘመነ መንግሥት እንደነበር ነው ሰይድ ያወሱት።

‹‹ሸሽቼ ከኋላዬ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ፤ ከፊት ለፊት ስፋለም ከወደቅሁ ግን እሬሳዬን ትውልድ ቦታዬ ውሰዱልኝ›› ያሉት ፊታውራሪ ገበየሁ፣ በአድዋ ጦርነት ከፍተኛና አስደናቂ ግድል የፈጸሙ የአገር ባለውለታ ናቸው። በተያያዘ ደግሞ የአድዋ ጦርነት ላይ ከዘመቱት መካከል የሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ጦር የተነሳው ከጋርዱላ ነበር።

ታድያ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ፊታውራሪ ገበየሁ አስቀድሞ በጠየቁት መሠረት አካላቸው በትውልድ ስፍራቸው አረፈ። በጋርዱላ ደግሞ መታሰቢያቸው የሚሆን ትምህርት ቤት እንዲገነባ አጼ ምኒልክ አዘዙ። ይህም ትምህርት ቤት በ1938 ተሠርቶ ዘመናዊ ትምህርት በአካባቢው እንዲጀመር ምክንያት ሆነ።
ብሩ ስማሎ የተባሉ ሰው ‹የጋርዱላ ታሪክ› በሚል ርዕስ የአካባቢውን ሁለንተናዊ ታሪክ የሚዳስስና በ2008 ለህትመት የበቃ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ሲሉ ስለትምህርት ቤቱ ሥያሜ ጠቅሰዋል፤ ‹‹…ይህ ትምህርት ቤት የእውቀት ማዕድ በመሆን በገጠርና ከተማ መካከል ዘላቂ ትስስርን የፈጠረ ብቻ ሳይሆን የአገር ፍቅርንና የጀግንነት መንፈስን በትውልድ ውስጥ ያበቀለ ልዩ ሠርቶ ማሳያ ነበር። ዳሩ ግን በ1975 ገደማ የተደረገው የትምህርት ቤቱ የሥም ለውጥ ምክንያት ሲመዘን ቁምነገሩ ሚዛን የሚደፋ አይመስልም።››

ሰይድ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ጥንታዊ እንደመሆኑና ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ጨምሮ አንጋፋ ምሁራንን ያፈራ ከመሆኑ ጋር ሲነጻጸር፣ አሁን ያለበት ደረጃ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ‹‹እድገቱ ባለበት ነው።›› ብለዋል። ምንም እንኳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ለጨረሱ ተማሪዎች በ1962 የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በዛው እንዲከታተሉ ለማስቻል ትምህርት ቤት ቢገነባም፣ በዘርፉ በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ ሰይድ ከልምድና ከዕይታቸው አካፍለዋል።

ስለ አድዋ ከተነሳ…
ሰይድ ከትምህርት ቤቱ በተጨማሪ አያይዘው ካነሱት ኹነት አንዱ ከዛሬ 125 ዓመት በፊት ወደ አድዋ የሚወስደን ታሪክ ይገኝበታል። በነገራችን ላይ በደራሼ የአድዋ ጦርነት እንዲሁም የጣልያን ወረራ ጉዳይ በስፋት አሻራ ያሳረፉ ክስተቶች ናቸው። አካባቢው የአድዋ ድል በድምቀትና በልዩ ክብር ታስቦ ከሚውልባቸው አካባቢዎች መካከልም ነው።

የመጀመሪያው ታሪክ እንዲህ ነው። የአድዋ ጦርነት ላይ ከሠራዊቱ ጋር አብረው የዘመቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ታቦታት ይገኙበታል። ታድያ ከድል በኋላ በአድዋ የተገኙ ታቦታት ወዴት ይሂዱ ሲባል፣ አንደኛው የቅድስት ሥላሴ ታቦት ወደ ወረኢሉ ተንተአ ከተማ እንዲሄድ ተባለ። በዛም ‹ደብረ ሠላም› በሚል መጠሪያ የቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያን እንዲታነጽ ሆነ።

ኹለተኛው የጊዮርጊስ ታቦት ደግሞ ወደ አዲስ አበባ፣ አሁን ፒያሳ የሚገኘው አራዳ ጊዮርጊስ እንዲሄድ ተባለ። ሦስተኛው የጊዮርጊስ ታቦት ደግሞ የሀብተ ጊዮርጊ ዲነግዴ ሠራዊት ከጋርዱላ ተነስቶ ነውና አድዋ ዘምቶ ድል ያደረገው፣ በጋርዱላ እንዲሄድ ተባለ። እናም በ1888 በጋርዱላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ታነጸ፣ ታቦቱም በክብር ገባ።

ከአድዋ ድል አርባ ዓመታት በኋላ፣ ጣልያን በበቀል ስሜት ኢትዮጵያን ሲወር፣ ከላይ እንደተጠቀሰው የሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ሠራዊት መነሻ የነበረውን ጋርዱላን ለማጋየት አላንገራገረም። ያም ብቻ አይደለም፣ በባንዳዎች ጠሪነት በአካባቢው የነበሩ የተለያየ የጦር ሥልጣን ያላቸውን ኢትዮጵያውያን እንዲሰበሰቡ በማድረግ፣ በቦንብና ከባድ መሣሪያ በአንድ ጊዜ እንዲጨፈጨፉ አድርጓል። በደራሼ ይህ የሰማዕታት መቃብር አሁን ድረስ ሰማዕታቱን እያወሳ ይገኛል።

ታድያ ሰማዕታቱ እንደሚታሰቡት ሁሉ የአድዋ ድልም ይዘከራል። ብሩ ስማሎ ከላይ በጠቀስነው መጽሐፋቸው ይህን፣ ይልቁንም ከትምህርት ቤቱ ጋር በማያያዝ ጠቅለል አድርገው እንዲህ ሲሉ አስፍረውታል፤ ‹‹ተማሪዎች ለክብረ በዓላቱ ተሰልፈው የየካቲት 23 ቀን 1888ን የአድዋ ድል ዲስኩር ሲነበብ፣ ትምህርት ቤቱ በሥሙ የተሰየመውና የድሉ ቋያ የነበረው ፊታውራሪ ገበየሁ ገድል ይነሳ ስለነበር ነው። ሌላው የጀግንነት ወኔ መቀስቀሻ የ1933 ሚያዝያ 27 የድል በዓል ሲነሳ ደግሞ፣ ለአገራቸው በዱር በገደል ሲዋጉ ጋርዱላ ላይ በፋሽስት ጣልያን የተጨፈጨፉ አርበኞች ስለሚታወሱ ነው።››

እናም ለደራሼዎች ኢትዮጵያ የተከፈለባት ናት። በመስዋዕትነትም፣ በድልም የኢትዮጵያዊነትን ድርሻ ቀምሰዋል። የብዝኀነት መናኽሪያ ቢባል የሚያንሰው የኢትዮጵያ ደቡብ ክፍል፣ ‹መዋቅር› በሚባል ጦሰኛ የፖለቲካ አስተዳደር ጉዳይ፣ ከብዙኀን ፍቅርና ሰላም የሚበልጥ በሚመስል መንገብገብ በታወሩ በጥቂት ሹመት ስጡን ባዮች እረፍትና ሰላም ይጣ እንጂ ኢትዮጵያዊ መልኩ አልደበዘዘም።

‹ጎመን ለምኔ!› የሚያሰኘው ሀለኮት
የደራሼ ሕዝብ የራሱ መገለጫ የሆነ በርካታ ባህላዊ እሴቶች ያሉት ነው። ከእነዚህም መካከል ከላይ የተጠቀሰው የፊላ ጨዋታ አንዱና ዋነኛው ነው። ያ ብቻ ግን አይደለም፤ ከእርሻ ጋር በተገናኘ ማኅበሰረቡ የመሬት ለምነትና እርጥበትን ለመጠበቅ የሚጠቀመው መንገድ ድንቅ የሚባል እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክራሉ። ይህም ‹ታርጋ› ብለው የሚጠሩት የአስተራረስ ዘዴ ሲሆን፣ ጥንታዊና ኋላቀር ተብሎ ሳይተው አሁን ድረስ በዚህ ጥበብ አርሰው አደሮች ከመሬት አብቅለው እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ነገሩስ በእጅ ያለ ወርቅ ሆኖ እንጂ የደራሼን የአስተራረስ ጥበብ ለድፍን አገር ትልቅ ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው።

ታድያ በዚህ ጥበብ በደጋውና ወይናደጋው የደራሼ ክፍል እንሰት፣ ድንች፣ ጎመን፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ አተርና ሽንኩርት የመሳሰሉ ምርቶች ይገኛሉ። እንዲሁም ‹ሀለኮታ› ብለው የሚጠሩት በከተማ ‹ሞሪንጋ› ወይም ‹ሽፈራው› የሚባለው ዛፍም የደራሼ ምድር ላይ በስፋት የሚታይ ነው። ይህም በተለያየ መንገድ የየእለት ምግብ የሚዘጋጅበት ነው። ሀለኮትን መመገብ ለደራሼ አዲስ አይደለም።

ደራሼዎች የሀለኮትን ወይም ሀለኮ ብለው በአጭሩ የሚጠሩትን ይህን ተክል ባህርያት በሚገባ ያውቃሉ። ለምሳሌ በዝናብ ወራት ተክሎች ውሃን ሲያገኙና ሲለመልሙ፣ ሀለኮ ግን ቅጠሉን ያራግፋል፣ በትልም ይጠቃል። እንደው ትላትሎች ባያጠቁት እንኳ በስሎ ገበታ ላይ ሲቀርብ ያለው ጣዕም ‹እንደ ፀሐይ ወራት የሚያረካ አይደለም› ሲሉ ይናገራሉ።

በተለያየ መልክ ተሠርቶ ይበላል፤ ሀለኮ። እንደ ጎመን በእንጀራ፣ አልያም በሾርባ መልክ። የወለደች ሴት ስትታረስ ሀለኮ አይጠፋም። ‹ፓርሾት› ወይም ‹ሂባ› የሚባል ባህላዊ መጠጥ ለማዘጋጀትም ይውላል። ከዚህ ባሻገር እንደ ጠላ እንደ ጠጅ ኃይል ያለው ‹ጨቃ› የሚባል መጠጥ በአካባቢው የተለመደ ነው።
ደራሼዎች ከምግቡ ከመጠጡ ሳይሰስቱ፣ ለጉልበታቸው ሳይሳሱ፣ ከፈገግታ አቀባበላቸው ሳያጎድሉ፣ ከጨዋታቸው ጨምረው፣ አካባቢያቸው እንዲታወቅላቸው ያላቸውን ጉጉት አክለው በፍቅር አስተናግደውናል። የጉዞአችን ማስታወሻ ይህ ብቻ አይደለም፤ ይቆየን።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here