በፋሽን ሳምንቱ ከ30 አገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ አምራቾች ይሳተፉበታል ተብሏል
ማክሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) መሴ ፍራንክፈርት ኤግዚቢሽን ከኢንዱስትሪ ሚንስቴርና ከኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማኅበር ጋር በመተባበር ስምንተኛውን የአፍሪካ ሶርሲንግ እና የፋሽን ሳምንት በአዲ አበባ ስካይላይት ሆቴል ከጥቅምት 25-28 እንሚያካሂድ አስታውቋል፡፡
ለመላው አፍሪካውያን አምራቾች ትስስር ይፈጥራል በተባለው በዚሁ መድረክ፤ ከ30 አገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ አምራቾች ይሳተፉበታል ያሉት የኢንዱስትሪ ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፣ 39 አገር በቀል ኩባንያዎች በመድረኩ እንሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡
ይህ የአፍሪካ ሶርሲንግ እና የፋሽን ሳምንት በዘርፉ የአፍካ ትልቁ መድረክ ነው ያሉት ታረቀኝ ከ6000 በላይ ዓለም ዓቀፍ ገዢዎችም ምርቶችን እንሚጎበኙ ተናግረዋል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ በአልባሳት ምርት ላይ የተሰማሩ የአፍሪካ አገራት የጥጥ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የአልባሳት፣ የቴክኖሎጂ፣ የቆዳ ውጤቶች፣ የቤት ማስጌጫዎች እንሁዲም የፋሽን ዲዛይኖቻቸውን ለእይታ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡