ከውጪ ለሚገዛው ኹለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር 110.4 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተፈቀደ

1
1362

በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ ይገባል ለተባለው ኹለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ110.4 ሚሊዮን ዶላር ብድር እንደተፈቀደ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሆነው የስኳር ምርት ዋጋ እየናረ መምጣቱን ተከትሎ፣ ከኑሮ ውድነት ጋር ተደማምሮ ከፍተኛ ጫና በመፍጠሩ የኹለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ግዢ በሂደት ላይ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው።

አዲስ ማለዳ የስኳር ግዢ ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሕዝብ ግንኙነትና ተሳትፎ ክፍል ኃላፊ ረታ ደነቀን የጠየቀች ሲሆን፣ ስኳሩን ለማስገባት ብድር መፈቀዱን ኃላፊው ጠቁመዋል።

የስኳሩ ዓለም ዐቀፍ የጨረታ ሂደት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ግዢውን ለመፈጸምም የባንክ ሂደት እንደተጀመረ ገልጸዋል። ስኳሩን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንከ በተገኘ የ110.4 ሚሊዮን ዶላር ብድር እንደሚገዛም ተናግረዋል። ስኳሩን ወደ አገር ውስጥ በማስገባቱ ሂደት ውስጥ ወሳኝ የሆነው ዓለም ዐቀፍ የብድር ደብዳቤ (Letter of Credit) በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ኃላፊው አስታውቀዋል። አጠቃላይ የስኳር ምርቱን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባትም ከአንድ ሳምንት ጊዜ በኋላ የሚታሰብ የ45 ቀናት ጊዜ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

መስከረም 6/2015 የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ በግዢ ሂደት ላይ ያለው ስኳር በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ ይገባል ማለቱ የሚታወስ ነው። ይህንንም ተከትሎ በተቻለ ፍጥነት ስኳሩን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሥራዎች እየተሠሩ እንደነበርና መስከረም 26/2015 የብድሩ ሂደት መጠናቀቁን ረታ አስታውቀዋል።

ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ስኳር ከደረሰ በኋላም የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በፍጥነት ለክልልና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች እንዲከፋፈል እንደሚያደርግ የገለጹት ኃላፊው፣ የንግድ ቢሮዎች ደግሞ ስኳሩን በሸማች ማኅበራት በኩል ለሕዝብ እንደሚያደርሱ አመላክተዋል።

የስኳር ምርት እጥረት ለብዙ ጊዜ ሲንከባለል የቆየ ችግር እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ መንግሥትም ችግሩን ለመፍታት በተደጋጋሚ በዓለም ዐቀፍ ጨረታዎች ግዢ በመፈጸም ጊዜያዊ የአቅርቦት መፍትሄ ለመስጠት ሲሞክር ይስተዋላል። ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስከረም 6/2015 በሰጠው መግለጫም ከዚህ የግዢ ሂደት በተጨማሪ በክረምቱ ለጥገና የተዘጉ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲመለሱ የአቅርቦት ችግር እንደሚቀረፍ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ሥራ ይጀምራሉ የተባሉትን ፋብሪካዎች አስመልክቶም ረታ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ በጥገና ላይ ያሉት ፋብሪካዎች እስከ አሁን ሥራ እንዳልጀመሩ ተናግረዋል። ለዚህም ምክንያት የሆነው ከድንገተኛ ብልሽቶች ውጪ ፋብሪካዎቹ ለስምንት ወራት በቀን ለ24 ሰዓት ያለ እረፍት ስለሚሠሩና በክረምት ወራት ያልተመጠነ የዝናብ ውሀ የሚያገኘው ሸንኮራ አገዳ ስኳር የመስጠት አቅሙ ትንሽ በመሆኑ የፋብሪካዎቹ የጥገና ጊዜ በክረምት ወራት እንደሚሆን ጠቁመዋል። ፋብሪካዎቹም ጥገናቸወን ጨርሰው ከጥቅምት እስከ ህዳር ወር መጀመሪያ ቀናት ድረስ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚመለሱ ገልጸዋል።

አሁን ላይ አንድ ኪሎ ስኳር እስከ 150 ብር ድረስ እየተሸጠ ሲሆን፣ የዋጋ ንረቱ የተከሰተበት ዋና ምክንያት ስኳር አቅርቦት እጥረት መሆኑ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

አስተያየት

  1. አዲስ ማለዳ ኢትዮጵያ በርከት ያሉ የስኳር ፋብሪካዎች እያላት ለምን ከዉጪ እንደምታስገባ የምርመራ ዘገባ መስራት አለበት። የምርመራ ዘገባዉ ስታስቲክስን ያካተተ፣ ማለትም የኢትዮጵያ የስኳር ፍጆታ የሚመረተዉ ምን ያህል ነዉ? ፋብሪካዎቹ በከፍተኛ የዉጪ ብድር ተሰርተዉ ከተጠናቀቁ በኋላ በቂ ምርት ለምን ማምረት አልቻሉም? የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ስኳር ከዉጪ ማስገባት ታቆማለች ሲል የነበረዉ ከምን መነሻ ነዉ? ችግራቸዉ ከአገሪቱ የብቃትና ማኔጅመንት ችግር ጋር የተያያዘ ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ የስኳር ፍጆታዉ እጅግ አነስተኛ ከሆኑ አገሮች ይካተታል። ስኳር ከዉጪ ማስገባት ያሳፍራል። የአስተዳደር፣ የሙስና፣ የብቃት ችግሮች የስኳር ኢንደስትሪዉ ማነቆ መሆን አለመሆኑን በምርመራ ዘገባ ሁሉንም አካላት አካታችሁ ብታስነብቡ ለብዙ ዜጎች ጥያቄ አርኪ ምላሽ መስጠት ትችላላችሁ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here