የሕዝብ እና ምጣኔ ሀብት አጣብቂኝ

0
1260

በርካታና የተለያየ ዓይነት ችግር የተደራረበባት ኢትዮጵያ፣ ከፈተናዎቿ መካከል አንደኛው የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ነው። ምንም እንኳ ቁጥሮች እዛና እዚህ እየተጠቀሱ እድገት ታይቷል ይባል እንጂ፣ ማኅበረሰቡ ውስጥ ግን ኪሳራና እጦቱ በዝቶ ይታያል። የኑሮውን ጫና በሚመለከት ብዙውን ጊዜ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ድምጻቸውን ሲያሰሙ ይደመጣል። በተጓዳኝ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች፣ በእለት ያገኟት የነበረች ገቢ ሳትጨምር በአንጻሩ ወጪው በከፍተኛ መጠን ከፍ በማለቱ እጃቸውን ለምጽዋት ለመዘርጋት ተገደዋል።

ይህን ማኅበረሰቡ ውስጥ ዘልቆ የገባውን ችግር ለመፍታት በርካታ እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉ እሙን ነው። ባለሞያዎችም መንግሥት የምጣኔ ሀብቱን ጉዳይ ቸል እያለ ነው፤ ለማስተካከል የሚያግዙ አካሄዶች ሊወሰዱ ይገባል ሲሉ ደጋግመው በማሳሰብ ላይ ናቸው። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ጦርነት እንደተራበ አንበሳ፣ ሳይሰስት በጀቱን ቀርጥፎ እየበላ ይገኛል። በየቦታው ያሉ አለመረጋጋቶችና ያንን የተከተሉ መፈናቀሎችም ሠርቶ አዳሪዎችን ወደ ለምኖ ማደር አድርሷቸዋል። ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ ባለሞያዎችን በማነጋገርና የተለያዩ ዘገባዎችን በማጣቀስ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ ሐብታም ሳጃው የተባሉ አንዲት እናት ይጠቀሙበት የነበረውን የእንጀራ መሶባቸውን “የሚሸጥ” የሚል ጽሑፍ ለጥፈው ለመሸጥ መንገድ ላይ ወጥተው መገኘታቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ከተሰራጨ በኋላ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የእንጀራ መሶባቸውን ለሽያጭ ያቀረቡት እናት ለምን መሶባቸውን ለመሸጥ እንደተገደዱ ሲጠየቁ ‹‹የሚበላው ይገኝ እንጂ በሳህንስ አልበላውም? እኔ ጦሜን እያደርኩ እቤት ተቀምጦ ምን ይሠራልኛል? በዚህ ጊዜስ ተርፎ በመሶብ የሚያድር እንጀራ አለ ብለህ ነው?›› የሚል ተደራራቢ ጥያቄ አዘል ምላሽ መስጠታቸው ከተሰማ በኋላ ጉዳዩ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል።

ከእያንዳንዱ ቤት ጓዳ የማይጠፋውን የእንጀራ መሶባቸውን ለገበያ ያቀረቡት እኚህ እናት፣ የመጨረሻ ያሉትን እራስን መግቦ የማደር ትግል አካል ነው። የእኚህ እናት ችግር አደባባይ ወጥቶ ብዙዎች አዝነው እየረዷቸው ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ካለው ዋጋ ንረት ካስከተለው የኑሮ ውድነት ማምለጥ የማይችሉ ሚሊዮን እናቶች በየቤታቸው ልክ እንደ ሀብታም ጓዳቸው መግባቱ አይቀሬ ነው። አሁን ላይ የኑሮ ውድነት የብዙ እናቶች ጓዳ ስለማንኳኳቱ እምብዛም አጠራጣሪ ነገር አይመስልም።

የብዙዎችን የእለት ከእለት ሕይወት እየፈተነ የሚገኘው የዋጋ ንረትን ተከለትሎ የተከሰተው የምጣኔ ሀብት ቀውስ አሁን ላይ እንደ አገር በምጣኔ ሀብቱ ላይ እያሳደረ የሚገኘው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አለመሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በየጊዜው ይገልጻሉ። የዋጋ ንረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሰ መቀጠሉ፣ የሕዝብን የኑሮ አጣብቂኝ ውስጥ ስለመክተቱ የሕዝቡን ምሬት መስማትና በየጊዜው በገበያ ላይ የሚታየውን ዋጋ ጭማሪ የኑሮ ውድነት አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉ ማሳያ ነው።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዘርፈ ብዙ በሆነ አጣብቂኝ ውስጥ ስለመግባቱ የዘርፉ ባለሙያዎች በየጊዜው የተለያዩ ማሳያዎችን በማንሳት ያስረዳሉ። ምጣኔ ሀብቱን በየአቅጣጫው አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱ እነዚህ ተግዳሮቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መቀጠላቸውን ተከትሎ የሕዝብ እና ምጣኔ ሀብት ፈተና አሁንም እንደቀጠለ ነው። በተለይ ካለፉት ኹለት ዓመታት ወዲህ ተከስተው የሚታዩ እንደ ጦርነት፣ ማዕቀብ፣ የኑሮ ውድነትና የውጭ ምንዛሬ እጥርት የመሳሰሉትን ፈተናዎች ማንሳት ይቻላል።

በየአቅጣጫው ፈተና የበዛበት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አጣብቂኝ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዜጎች የእለት ከእለት ኑሮ እና ምጣኔ ሀብት ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ አልቀረም። የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላለፉት ኹለት ዓመታት በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎችም ይገልጻሉ። በእነዚህ ኹለት ዓመታት ምጣኔ ሀብቱ ካስተናገዳቸው ከፍተኛ ፈተናዎች መካከል የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና አሁንም የቀጠለው ጦርነት ተጠቃሽ ናቸው።

በተደራራቢ ችግሮች እየተፈተነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግሮቹን ተቋቁሞ እንዲያልፍ ከወትሮው የተለየ ሥልት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ቢጠቁሙም፣ የኢኮኖሚው ፈተና አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል። በተለይ የሰሜኑ ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ ለመሆኑን፣ በጦርነቱ የወደመው በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብት፣ በ10 ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ሀብት ንብረቱን አጥቶ ተረጂ መሆኑ እና በጦርነቱ ምክንያት የተባባሰውን የዋጋ ግሽበት እንደማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።

በጦርነቱ ከወደመው ሀብት በተጨማሪ ለጦርነቱ የሚወጣው የመንግሥት በጀት እና ከሕዝብ የሚሰበሰበው ሀብት በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ የሚባል ጫና እያሳደረ ይገኛል። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የመንግሥት በጀት ወደ ጦርነት ወጪ መዞሩ፣ በመንግሥት የሚለሙ ፕሮጀክቶች እንዲቋረጡ እና የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዳይቀጥሉ ማድረጉ በኢኮኖሚው ላይ የረዥም ጊዜ ጠባሳ እንደሚሆን እየተገለጸ ነው። የሰሜኑ ጦርነት ቀጥተኛ ሰለባ ከሆኑት ከትግራይ፣ ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች መካከል፣ አማራ ክልል በጀቱን ለጦርነቱ ማዞሩን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በክልሉ መንግሥት የሚለሙ የተመረጡ ፕሮጀክቶችን እስከማጠፍ የደረሰ እርምጃም ወስዷል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፖለቲካ ጥገኝነት የተለየ አለመሆኑን ተከትሎ፣ በየጊዜው በሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ሰለባ እንደሚሆን እና ጉዳቶችን እንደሚያስተናግድ ብዙዎች ይስማማሉ። ባለፉት ኹለትና ሦስት ዓመታት ብቻ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ኪሳራ እያስተናገደ ነው።

ዋጋ ናረ ወይስ ተሰቀለ?

የኢትዮጵያ የኑሮ ወድነቱ ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት በየጊዜው ማሻቀቡና ተባብሶ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየጊዜው የሚያወጣቸው መረጃዎችና በማኅበረሰቡ ላይ የሚታየው የኑሮ ጫና ያመላክታል። በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የዋጋ ንረት አሁን ላይ ዝቅተኛ ገቢ ካለው የማኅበረሰብ ክፍል አልፎ መካከለኛ ገቢ እስካለው የማኅበረሰብ ክፍል ድረስ የማኅበረሰቡን ኑሮ እየፈተነ ይገኛል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የኑሮ ወድነት ተከሰተ የሚባለው የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም ወይም ገቢ ማነስ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተደምሮ የሚፈጥረው የመግዛት አቅም ሲዳከም ነው። በኢትዮጵያ ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ድረስ የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እያሻቀበ ቢሆንም፣ የአብዛኛው የማኅበረሰቡ ክፍል ገቢ ወይም የመግዛት አቅም ግን ከዋጋ ግሽበቱ እኩል ማደግ አለመቻሉን የዘርፉ ባለሙያዎቸ ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቶ አሁን ላይ ደግሞ ተጨማሪ አባባሽ ሁኔታዎች ገጥመውታል። ከሰሜኑ ጦርነት መከሰት በኋላ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ በሳምንት ልዩነት እያሻቀበ ሄዶ የአብዛኛውን ማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ እየፈተነ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በዩክሬን እና በሩስያ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከውስጣዊ ችግሮች በተጨማሪ ለዋጋ ግሽበት ሌላ ምክንያት መሆኑን መንግሥት እየገለጸ ነው። የጦርነት መራዘምም የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ እንደሚያደርግ እና የማኅበረሰቡን ኑሮ እንደሚፈታተን የዘርፉ ባለሙያዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን ያመላክታል። ይህ በየዓመቱ እያደገ የመጣው የዋጋ ግሽበት ከ10 ዓመት በፊት ማለትም 2005 ላይ ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 20 በመቶ ነበር።

ባለፉት አራት ዓመታት በየዓመቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በአመዛኙ በየወሩ የመጨመር እንጂ የመቀነስ አዝማሚያ አያሳይም። ከአራት ዓመታት በፊት ማለትም የ2011 ነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 17.9 በመቶ ነበር። አሁን ላይ ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት እየጨመረ የ2014 ነሐሴ ወር ዋጋ ንረት 32.5 በመቶ ደርሷል።

ይህም ሆኖ አሁን ያለው የዋጋ ንረት ገበያ ላይ ካለው እውነታ ጋር የማይገናኝና መንግሥት ከሚያወጣው መረጃ የበለጠ መሆኑ ይነሳል። የነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ንረት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር  ሲነጻጸር 32.5 በመቶ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች የዋጋ ንረት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጻር የ31.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በኢትዮጵያ የተከሰተው የኑሮ ውድነት በየጊዜው እያሻቀበ ቢመጣም፣ አሁንም ኹነኛ መልስ እየተሰጠው አለመሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ። በየጊዜው እያሻቀበ የመጣው የኑሮ ውድነት ላለፉት ተከታታይ ዓመታት በፍጥነት እያደገ ቢመጣም፣ መንግሥት የኑሮ ወድነቱን ባለበት የሚገታ መፍትሔ አለመስጠቱም ይነሳል።

የኑሮ ወድነት ተከሰተ የሚባለው የዜጎች የመግዛት አቅም ከጊዜ ወጊዜ እየተዳከመ ሲመጣ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ጊዜያዊ ወይም የእለት ሥራ ላይ ኑራቸውን መሠረት ያደረጉ ዜጎች ላይ የኑሮ ውድነት መከሰቱን ይገልጻሉ።

የዋጋ ግሽበቱ የእድገት መጠኑ ይለያይ እንጂ ከምግብ እስከ ቁሳቁስ፣ ከአልባሳት እስከ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ሆኖ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮው እየፈተነ ነው። ዋሲሁን በመንግሥት በኩል በቂ የመፍትሔ ምላሽ አለመሰጠቱን ይገልጻሉ። ‹‹የዜጎች ኑሮ የተሻለ እንዲሆን መንግሥት ኃላፊነት አለበት›› የሚሉት ዋሲሁን፣ መንግሥት የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት የማሟላትና የተሻለ ገቢ እንዲኖራቸው የማድረግ ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ ለችግሩ በቂ ምላሽ እየሰጠ አይደለም ይላሉ።

‹‹መንግሥት ከማኅበረሰቡ እኩል ነው እየሰማ ያለው›› የሚሉት ባለሙያው፣ መንግሥት ችግሩን ልብ እንዲለውና አስቀድሞ መፍትሔ እንዲያስቀምጥ የዘርፉ ባለሙያዎች ብንወተውትም፣ ጠብ የሚሉ የመፍትሔ ሐሳቦች አላቀረበም።›› ይላሉ። መንግሥት ከማኅበረሰቡ ቀድሞ ችግሩን መረዳትና መፍትሔ ማበጀት ካልቻለ፣ ዜጎች ምን ያድርጉ ወደሚለው መግባት አስፈላጊ ነውም ብለዋል። ማኅበረሰቡ መዘጋጀት አለበት የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን፣ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም ሲሉም አሳስበዋል።

አሁን ባለው ወቅታዊ ኹኔታ የኑሮ ውድነቱ በውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የተወጠረ መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው የሚገልጹት ባለሞያው፣ ማኅበረሰቡ ከወዲሁ ራሱን ማዘጋጀትና ወጪ ቆጣቢ አኗኗር ሥልትን መከተል መለማመድ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ከዚህ በፊት በኑሮ ወድነት ዙሪያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ኹኔታ ‹‹ኅብረተሰቡ የአኗኗር፣ የአበላል፣ የአመጋገብ ዘይቤውን መቀየር አለበት።›› የሚል መልዕክት አስተላልፏል። መንግሥት በየጊዜው እያደገ ለመጣው የዋጋ ግሽበት በመግለጫው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ከገበያ ሥርዓት ቁጥጥር፣ ከውጭ የተገዙ ሸቀጦችን ማስገባትና አዲስ ፈጣን ግዢ ማካሔድ፣ የአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ብሎም ማኅበረሰቡን የመፍትሔ አካል ማድረግ የሚሉ ናቸው።

ጦርነት እና ምጣኔ ሀብት

የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረበት ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ እስካሁን በዘለቀበት ኹለት ዓመት ሊሞላው የአንድ ወር ዕድሜ በቀረው ጊዜ፣ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መጥቷል። ባልዳበረ ኢኮኖሚ ላይ የተከሰተው ጦርነት፣ ቀጥተኛ ሰላባ በሆኑት ክልሎች ላይ ከፍተኛ የሀብት ውድመት አስከትሏል።

ጦርነቱ እስካሁን በተካሄደባቸው በአፋር እና በአማራ ክልል አካባቢዎች የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ መውደሙን የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ጦርነቱ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ከመስፋፈቱ በፊት ትግራይ ክልል ውስጥ በሚካሔድበት ወቅት ከመንግሥት ሀብት እስከ ግለሰብ ፋብሪካዎች ድረስ የክስተቱ ሰላባ መሆናቸው መገለጹ የሚታወስ ነው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት በበርካታ ፈተናዎች የተወጠረበት ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይ በአሁኑ ሰዓት የኢኮኖሚው ዋነኛ ፈተና ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነት መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው፣ ከጦርነቱ በፊት የነበሩ የኮቪድ-19 ተጽዕኖ፣ የዋጋ ግሽበትና የውጪ ምንዛሬ እጥረት ከጦርነቱ መከሰት በኋላ ተባብሰው መቀጠላቸው፣ ጦርነቱ ኢኮኖሚውን አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል ይላሉ።

ጦርነት በኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ መካከል የመንግሥት ሀብት አጠቃቀም ማዛባት እና የሕዝብ ሀብት አጠቃቀም ላይ ችግር መፍጠር መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ደምስ ይገልጻሉ። ባለሙያው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነት የመንግሥትን የልማት በጀት ወደ ጦርነት እስከማዞር የሚደርስ ነው። በጦርነቱ ካጋጠመው የሀብት አጠቃቀም መዛባት በተጨማሪ፣ የችግሩ ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት ውድመት እንዲሁም የዜጎች ከመኖሪያ ቦታ መፈናቀል በኢኮኖሚው ላይ የረዥም ጊዜ ጠባሳ የሚጥል ነው ብለዋል።

በጦርነቱ የተከሰተውን የሀብት ውድመት እና የመሠረተ ልማት መስተጓጎል ተከትሎ ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ ችግሮች እንደሚከሰቱ የሚገልጹት ባለሙያው፣ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ አለመጠናቀቁን ለአጭር ጊዜ የሕዝብ ኑሮን ከማስተጓጎሉ በተጨማሪ፣ የረዥም ጊዜ እድገትን እንደሚገታ እና ለዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የሰሜኑ ጦርነት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ በተጨማሪ፣ የጦርነቱ ሰለባ በሆኑት አካባቢዎች የሚኖረው እና ሀብቱን ያጣው የማኅበረሰብ ክፍል ግንባር ቀደም የችግሩ ተጋላጭ እንደሚሆን ደምስ ጠቁመዋል። በተከሰተው ጦርነት ሀብቱን ያጣው ሕዝብ ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር መጋለጡን ተከትሎ ረሀብ ሊከሰት የሚችልበት ኹኔታም ሊያጋጥም እንደሚችል ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ከገጠማት የጦርነት የምጣኔ ሀብት ችግር ልትወጣ የምትችለው ባለድርሻ አካላትን ያካተተ እና የተቀናጀ የመልሶ መቋቋሚያ እቅድ በማዘጋጀት ነው የሚሉት ባለሙያው፣ የመልሶ ግንባታ ተዋንያን በግልጽ መለየት አለባቸው ብለዋል። መንግሥት የኢኮኖሚ መልሶ ግንባታውን ብቻውን የሚወጣው አይደለም የሚሉት ባለሙያው፣ የመልሶ ግንባታ ተሳታፊዎችን በግልጽ በእቅዱ ውስጥ ማካተት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመሻገር ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ከአጭር እስከ ረዥም ጊዜ እቅድ አዘጋጅቶ መሥራት ያለበት ቢሆንም፣ አሁን ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ ስሜታዊ ይመስላል ሲሉ ባለሙያው ጠቁመዋል። ‹‹በዚህ ረገድ የገዘፈ እንቅስቃሴ አይታይም›› የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ በባለሙያዎች የታገዘ ኹሉን አካታች እቅድ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

ባለሀብቶች በመልሶ ማቋቋም የሚኖራቸው ሚና ጉልህ መሆን አለበት የሚሉት ደምስ፣ ድርሻቸውን በእቅድ አካቶ የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል።

የጦርነቱን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋም በአጭር ጊዜ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውን ዜጎች መልሶ ማቋቋም እና በአካባቢው ረሀብ እንዳይከሰት በፍጥነት የማገገሚያ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። እንዲሁም መሠረታዊ የሚባሉ መሠረተ ልማቶችን እና ተቋማትን ወደ ሥራ ማስገባት እና የጉዳቱ ሰለባ የሆነው ማኅበረሰብ ወደማገገም የሚገባበትን ሥራ መሥራት እንደሚገባም መክረዋል።

የጉዳት ሰለባ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በደረሰበት የንብረት ውድመት ራሱን ችሎ መቋቋም አይችልም የሚሉት እኚህ ምሁር፣ ‹‹የሚያርስበትን በሬ ያጣን ማኅበረሰብ እንዴት ወደ ምርት ማምረት እንደሚገባ በሚገባ አስቦ በአስቸኳይ መደገፍ ይገባል›› ብለዋል። ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የእርሻ በሬውን ያጣ ገበሬ እንዴት ወደ ግብርና ሥራው መመለስ ይቻለዋል የሚለው ጉዳይ ትኩረት እንዳልተሰጠው እና ቀላል ነገር አድርጎ የማየት ሁኔታ መኖሩን ባለሙያው ገልጸዋል።

ጦርነቱ ለረዥም ጊዜ ካልቀጠለ ለጦርነት የተገነባውን መከላከያ ኃይል ጭምር ወደ መልሶ ግንባታ እና ወደ መሠረተ ልማት በማስገባት ከችግሩ ማገገም ይቻላል የሚሉት ባለሙያው፣ ‹‹ጦርነቱ ከቀጠለ አሁንም ችግር ውስጥ ነው የምንወድቀው›› ብለዋል። ባለሙያው አክለውም፣ በታቀደ እና በተቀናጀ ኹኔታ ውጤታማ ሥራ ካልተሠራ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል አሳስበዋል።

የሰሜኑ ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ ካስከተላቸው ጉዳቶች መካከል የውጪ ምንዛሬ እጥረት እና የዋጋ ግሽበት መባባሶች ይገኙበታል። ከጦርነቱ መከሰት በኋላ የኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሬ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እና የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው ፕሮጀክቶች እንዲስተጓጎሉ ምክንያት እየሆነ መምጣቱ እየተገለጸ ነው።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ወትሮም የነበረ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በኋላ እየተባባሰ ስለመምጣቱ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያነሳሉ። በውጭ ምንዛሬ እጥረቱ እንደ አገር፣ በግሉም ሆነ በመንግሥት በኩል ቀላል የማይባል ችግር መፍጠሩም ይነሳል።

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ምንጮች ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ የውጭ ብድር፣ የእርዳታ ድርጅቶች እና በውጪ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሐዋላ ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩት ገንዘብ ዋና ዋናዎቹ ናቸው የሚሉት ደምስ፣ በጦርነቱ ምክንያት ከውጪ ምንዛሬ ምንጮች የሚገኘው ገንዘብ የቀነስበት ሁኔታ መኖሩ አንድ ችግር ነው ሲሉ ይገልጻሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ለመሠረታዊ ልማት እና ለተገቢው አገልግሎት በአግባቡ እየተጠቀመችበት አይደለም።

በዚህም የውጪ ምንዛሬ በጥቁር ገበያ እና በባንኮች ኮሚሽን ቁጥጥር ስር መውደቁ፣ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የውጪ ምንዛሬ በአግባቡ እንዳትጠቀም በማድረግ ለውጪ ምንዛሬ እጥረት እንዳጋለጣት ደምስ ይናገራሉ። አሁን ላይ የውጪ ምንዛሬ እጥረቱን ተከትሎ በባንክ 52 ብር የሚመነዘረው አንድ ዶላር በጥቁር ገበያ 92 ብር እየተሸጨ ይገኛል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ የውጪ ንግዶች የምታገኘውን ምንዛሬ ለማሳደግ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የምርት መጠን ማሳደግ ይገባል ሲሉም ባለሞያው መክረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here