ኮንትሮባንድ የሚያባትታት አገር

0
1735

ሕገወጥ ንግድ (‘ኮንትሮባንድ’) በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ስለማሳደሩ በመሬት ላይ ያሉ ማስረጃዎችን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። ለመሆኑ ኮንትሮባንድ እንዴት ይከወናል? በአገር ላይየሚያሳድረውስ ተጽዕኖ ምንድን ነው? ሲሉ የአዲስ ማለዳዎቹ ሳምሶን ብርሃኔ እና አሸናፊ እንዳለ መረጃዎችን አሰባስበው፣ የኮንትሮባንድ ተዋናዮችን፣ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን በማነጋገር ከነአማራጭ መፍትሔው ጉዳዩን የሐተታ ዘማለዳ ርዕስ አድርገውታል።

መንደርደሪያ
ከመርካቶ በቅርብ ርቀት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በምትገኘው “ጨረታ የገበያ ማዕከል” ፀሐይ ከመውጣቷ ቀደም ብሎ ያለው እንቅስቃሴ ለተመለከተ ምናልባትም ነገሩ በአዲስ አበባ መሆኑን ሊጠራጠር ይችላል። የከተማው ነዋሪ የዕለት ጉርሱን ለማሟላት ገና ሲዘጋጅ በጨረታ ያለው እንቅስቃሴ ለመገባደድ ይቃረባል።

በተደጋጋሚ ሲጮሁ የማይደክማቸው አገበያዮች፣ በየደቂቃው ለሚገዙት ዕቃ ጮክ ብለው የሚገዙበት ዋጋ የሚናገሩ ገዢዎች፣ በጠዋት ለተገበያዮች ቁርስ ለማቅረብ ደፋ ቀና የሚሉ የምግብ ቸርቻሪዎች የገበያው መገለጫዎች ናቸው። ታዲያ እነዚህ በተለምዶ ጨረታ በሚባለው ገበያ የከተማው ነጋዴዎችና ገዢዎች ገና በጠዋቱ የሚሸጡት ምን ይሆን የሚል ጥያቄ በአዕምሮ ያጭር ይሆናል።

ነገሩ ወዲህ ነው።
በገበያው የሚቀርበው በብዛት በኮንትሮባንድ ወይም በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ያገለገሉ ልብሶች ሲሆን ዋጋቸውም ምናልባትም ከአዲስ አበባ ውስጥ ካሉ ገበያዎች ርካሹ ነው። በአማካይ አንድ ልብስ ከ10 ብር እስከ 120 ብር የሚሸጥ ሲሆን በድኅነት አረንቋ ውስጥ ባለው የኅብረተሰብ ክፍል ተመራጭ ነው።

ታዲያ ይህ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገባ ምርት ያለማቋረጥ በበጋም ሆነ በክረምት በአደባባይ የሚሸጥ ሲሆን ከመንገድ ላይ ቸርቻሪዎች እስከ በከተማው የተንጣለለ ቡቲክ ባለቤቶች ዘንድ ተመራጭ ነው።

በገበያው በ100 ብር የሚሸጡ ያገለገሉ አንዳንድ አልባሳቶች ከጨረታ ተገዝተው በከተማው ባሉ ቡቲኮች እስከ 1 ሺሕ 200 ብር ድረስ ሲሸጡ ማየት በዘርፉ ውስጥ ላሉ ሰዎች ብዙም ላያስገርም ይችላል። ነገር ግን በሕገወጥ መንገድ ገብቶ እንዲህ በአደባባይ ሲሸጥ መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱ የሚያስገርም ነው።

በተለይም በገበያው የሚሸጡ አልባሳቶች በመቶ ሚሊዮን ብሮች ወደ አገር ውስጥ ከመግባቱ አኳያ መንግሥት የሚገባውን ጥቅም በግብር መልኩ አለማግኘቱ ገበያው ከሕግ ጥላ ሥር አለመሆኑን በግልፅ ያሳያል።

በርግጥ የሕገወጥ የወጪና የገቢ ንግድ ካለው ስፋትና የገበያ መረብ እንዲሁም ከሚያንቀሳቀሰው ቢሊዮን ዶላሮች አኳያ ጨረታ የኮንትሮባንድ ንግድ ማሳያ ይሁን እንጂ ያለው ድርሻ እምብዛም ነው።

ከጨረታ ባሻገር፤ እንደ ድሬደዋ፣ ሐረር፣ ጅግጅጋና ሞያሌ ባሉ ከተሞች በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች የገቡ ምርቶች በአደባባይ ከመሸጥም በላይ ያላቸውን ከፍተኛ የሆነ የገበያ ድርሻ ከግምት ውስጥ በማስገባት የከተሞቹ ምጣኔ ሐብት ምሶሶ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በቅርቡ የኮንትሮባንድ ንግድ በስፋት የሚስተዋልባቸው ቀዳሚ የሆነው የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሃመድ ከወር በፊት በተዘጋጀ ውይይት ወቅት እርሳቸው የሚመሯቸው ሕዝቦች ዘንድ ኮንትሮባንድን እንደ ባሕል የመቆጠርና ለብዙዎችም የሕይወት መሰረት መሆኑን አውስተው ነበር።

ኮንትሮባንድ እንዴት ይከናወናል?
ኮንትሮባንድ የተስፋፋባቸው አካባቢዎች በገቢዎች ሚኒስቴር ሳይቀር የተለዩ ሲሆን ከክልሎች ሶማሌ፣ ኦሮሚያና በቤንሻንጉል ቀዳሚ ናቸው።
በኦሮሚያ ቦረና፣ ምሥራቅ ጉጂ፣ ባሌ፣ ምዕራብ ሐረርጌና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ቀዳሚ ሲሆኑ በሶማሌ ፈፈን፣ ጀረር፣ ቶጎ ጫሌ፣ ሸበሌና ዶሎ ዞኖች ዋነኛ ኮንትሮባንድ የመተላለፊያ መስመሮች ናቸው። አሶሳ፣ ከማሺ፣ መተከል፣ ኩምሩክና ሀምዛ በቤንሻንጉል የተለዩ መስመሮች ናቸው።

በሕገወጥ የገቡ ዕቃዎች ለፋብሪካ በተሠሩ መጋዘኖች፣ በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ በተለያዩ ከተሞች በተገነቡ መጋዘኖች እና ለፋብሪካ ተብለው በተሰጡ መሬቶች ላይ በተገነቡ መጋዘኖች በአብዛኛው ይቀመጣሉ። ባቢሌ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞች እና ጎንደር ከፍተኛ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ጊዜያዊ ማስቀመጫ መጋዘኖችን በመያዝ ይታወቃሉ።

ኮንትሮባንድ ዕቃዎች ወደ አገሪቷ መዲናም አዲስ አበባ በሦስት ዓይነት መንገድ ይገባሉ። አንደኛው መንገድ ዕቃው ወደ ድንበር ከደረሰ በኋላ የጉምሩክ ጣቢያዎች የማይኖርበትን መንገድ በሚያውቁ ሹፌሮችና ግለሰቦች ይከናወናል። ታዲያ ይህንን መንገድ የሚጠቀሙ ሕገወጥ አስተላላፊዎች ያላቸው የግንኙነት መረብ እምብዛም ነው።

ይህንንም መንገድ የሚጠቀሙ የሕገወጥ አስተላላፊዎች በብዛት የታጠቁ በመሆናቸው ድንገት በመንገድ ላይ ማንኛውም ሰው ሊያቋርጣቸው ቢሞክር እስከ ግድያ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስዱ መረጃዎች ያሳያሉ።

ሌላው ምርቶች በሕገወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ በመግባት ወደ የተለያዩ ከተሞች የሚሰራጩት በሚገባ የተደራጀ የግንኙነት መረብ በዘረጉ ግለሰቦች ሲሆን ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬዎችንና በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስወጡ ምርቶችን በመሸጥ ይታወቃሉ።

በዚህ ዓይነቱ መንገድ ዕቃ የሚያስገቡም ሆነ የሚያስወጡ ሕገወጥ ነጋዴዎች ከታችኛው እስከ ላይኛው እርከን ካሉ የመንግሥት ኀላፊዎች፣ ከፀጥታ አካላት እና ከጉምሩክ ሠራተኞች ጋር በጥቅም ላይ የተመሰረተ ጥብቅ ግንኙነት በመጠቀም የፈለጉትን የምርት ዓይነቶች ወደ አገር ውስጥ ያስገባሉም፤ ያስወጣሉም።

ዕቃዎቻቸው ታማኝ በሆኑ የጉምሩክ ፈታሾች ቢያዝባቸው እንኳን ከተለያዩ የመንግሥት ኀላፊዎች ጋር በመመሳጠር የይለፍ ወረቀት ያገኛሉ። አንዳንዴም በመረባቸው ሥር በሌሉ የጉምሩክ ሠራተኞች ቢያጋጥማቸው እንደ ምርቱ ዓይነትና ብዛት ከአንድ እስከ ኹለት ሚሊዮን ብር በመክፈል ኬላዎችን ያልፋሉ። ክፍያውም ዕቃው ሲያልፍ ባሳለፈው ኃላፊ አካውንት የሚገባ ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ዕቃው ይወረሳል።

ይህንን ዓይነቱ መንገድ በመጠቀም የሚታወቁት የአልባሳትና የተለያዩ ጨርቃ ጨርቆች ነጋዴዎች ሲሆኑ በተለይም ሶማሌ ክልል የሚኖሩ ሴት ነጋዴዎች በዚህ ንግድ ላይ በመሰማራት ይታወቃሉ።

ሦስተኛው የኮንትሮባንድ ምርቶች ወደ አገሪቷ የሚገባበት መንገድ ለጥቅም ብለው ራሳቸውን በሸጡ የጉምሩክ ሠራተኞችና ሕገወጥ አስተላላፊዎች ሲሆን ንብረቶች ከተወረሱ በኋላ ተሸጠው ለመንግሥት ገቢ መሆን ሲገባቸው በሕገወጥ መንገድ ለጥቂት ነጋዴዎች ይሸጣሉ።

ከሦስቱ መንገዶች ባሻገር፤ ኮንትሮባንድ ምርቶች በአየር መንገድ የሚገቡ ሲሆን በጉምሩክ ሠራተኞች እንኳን የሚያዘው ንብረቶች ቀላል አይደሉም። የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በ2011 በጀት ዓመት ብቻ ከሩብ ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ንብረቶች በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ሲል ተይዘዋል።

ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የውጭ ዜጎች በተለይም ናይጄሪያውያን፣ የበረራ አስተናጋጆች፣ የዕርዳታ ድርጅቶች፣ ኤምባሲዎችና ነጋዴዎችና በዚህ ዓይነቱ ድርጊት ላይ በስፋት ተስተውሏል።

ኮንትሮባንድ በንግድ ላይ ያለው ተፅዕኖ
ዑመር ሽኩር በሞባይል ንግድ ላይ ከተሰማራ ከ10 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ልክ የዛሬ ኹለት ዓመት በአገር ውስጥ የተመረቱ ስልኮች ፍላጎት መጨመሩን ተከትሎ የራሱን መገጣጠሚያ ፋብሪካ በ10 ሚሊዮን ብር ከፍቷል።

ታዲያ ይህ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ከተገነባና ሥራ መስጠት በጀመረ ዓመት እንኳን በቅጡ ሳይሞላው ኢትዮ ቴሌኮም የስልክ ቀፎችን ምዝገባ ስርዓት በ2010 አጋማሽ ላይ በማቆሙ ምክንያት የሞባይል ገበያ ድንገት በኮንትሮባንድ ምርቶች መወረሩንና በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ምርቶች የገበያ ድርሻ ከ90 በመቶ በላይ መሆኑን ተከትሎ ዑመር ፋብሪካውን ለመዝጋት ጫፍ ላይ ደርሷል።

“ከ110 ሺሕ በላይ የስልክ ቀፎዎችን ብንገጣጥምም መሸጥ የቻልነው 10 ሺህ እንኳን አይሆንም” ይላል ዑመር። ይህም ከፍተኛ ገንዘብ ስለያዘብን ሥራ ለማቋረጥ ተገደናል ሲል ዑመር አክሏል።

እንደ ዑመር ያሉ በኮንትሮባንድ ንግድ የተነሳ ፋብሪካቸውንም ሆነ ንግድ ለማቆም የተገደዱ ጥቂት አይደሉም። በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ነጋዴዎች በኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት የተነሳ ምርቶቻቸውን በአግባቡ ለመሸጥ አለመቻላቸውን ሲገልፁ በተደጋጋሚ ይነሳል።

በተለይም ግብር እየከፈሉ በሕጋዊው የንግድ ስርዓት ሥር ያሉ ነጋዴዎች ከሕገወጥ ነጋዴዎች ጋር በገጠማቸው ያልተገባና ኢ-ፍትሐዊ ፉክክር የተነሳ የችግሩ ዋና ገፈት ቀማሽ ሆነዋል። በዚህም የተነሳ ከስረው ከገበያ እስከ መውጣት ይደርሳሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በምሬት ወደ ሕገወጡ የንግድ መረብ ተገፍተው ሲገቡ ይስተዋላል።

በእርግጥ ኮንትሮባንድ ለኢትዮጵያ አዲስ ባይሆንም ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ብዙዎች ይስማሙበታል። የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በመንግሥት ተይዘዋል።

አልባሳት፣ ሲጋራና ትምባሆ፣ ኤሌክትሮኒከስ እና ምግብና መጠጥ ነክ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ የኮንትሮባንድ ምርቶች ቀዳሚ ሲሆኑ የውጭ አገር ገንዘቦች፣ የቁም እንስሳት፣ ጫት እና የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ በተመሳሳይ መልኩ ከሚወጡት መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።

በሕገወጥ መንገድ የሚገቡትና የሚወጡት ምርቶች በዓመት 28 በመቶ ዕድገት ያሳዩ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት በጉምሩክ ኮሚሽን የተያዘው 1.2 ቢሊዮን ብር ኮንትሮባንድ ከ2006 እስከ 2010 ድረስ የተያዘውን ግማሽ ይሆናል።

በ2011 በጀት ዓመት ከተያዘው ኮንትሮባንድ ምርቶች ውስጥ 210 ሚሊዮን ብር የሚያወጡት አልባሳት ሲሆኑ 145 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም 93 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚያወጡት የሲጋራ እና ትምባሆ ምርቶች ናቸው።

በሌላ በኩል፤ 334 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ንብረቶች ወደ ውጭ ሊወጡ ሲል በ2011 በጀት ዓመት የተያዙ ሲሆን 236 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚሆኑት የውጭ አገራት ገንዘቦች መሆናቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ታዲያ እነዚህ በመንግሥት አካላት ተይዘዋል ተብለው ይፋ የሚሆኑት ኮንትሮባንድ ምርቶች ትክክለኛውን ዋጋ እና መጠን አያሳይም ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይሞግታሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚ ኮሌጅ የምጣኔ ሀብት መምህር የሆኑት ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ጥናታቸውን ዋቢ አድርገው እንደገለፁት መንግሥት የሚይዘው የኮንትሮባንድ ምርቶች መጠን በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቷ የሚገባውንና የሚወጣውን 10 በመቶ እንኳን አይሆንም። ለአብነትም ፋንታ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍን ያነሳሉ።

በመንግሥት በየዓመቱ በአማካይ ወደ 250 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አልባሳቶች በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቷ ሲገባ በጉምሩክ ኮሚሽን ቢያዝም አሁንም ከ48 በመቶ በላይ ፍላጎት የሚሸፈነው በኮንትሮባንድ ምርት ነው ሲሉ ፋንታ ይገልፃሉ። ይህም በአገሪቷ አምራቾች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ የሚገልፁት ፋንታ ዘርፉም ሆነ የአገሪቷ ምጣኔ ሀብት አደጋ ላይ መወደቁን ያነሳሉ።

ምጣኔ ሀብት አደጋ ላይ መውደቁን የሚስማሙት ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጌታቸው ተክለማርያም በበኩላቸው፤ የድንበር ንግድ ስርዓቱ ክፍተት ያለበት መሆኑ ለኮንትሮባንድ መስፋፋት ምክንያት ነው ብለዋል። ይህ ሕገወጥ ንግድን መቆጣጠር የሚችል በአገሪቷ ጠንካራና ብቁ የሰው ኀይል ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል ሲሉ ጌታቸው ሥጋታቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ኮንትሮባንድ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ገበያ እንዳይገቡ ተስፋ የሚያስቆሩጥ ሲሆን ፈጠራም እንዲቀጭጭ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ባለሙያዎች ሥጋታቸውን ይገልፃሉ። በተለይም ኮንትሮባንድ ተመሳሳይ እና ሐሰተኛ ምርቶች እንዲበዙ ዋነኛ ምክንያት በመሆኑ ፋብሪካዎች አዳዲስ ነገሮች በመፍጠር አኳያ ተስፋ እንዲቆርጡ እንደሚያደርግ ይነሳል።

ኮንትሮባንድ እና ጤና
ከነጋዴዎች ባሻገር፤ ኮንትሮባንድ የዜጎች ጤና ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ለአብነትም የሲጋራና ትምባሆ ምርቶች መጥቀስ ይቻላል። በኢትዮጵያ ከ40 በመቶ በላይ የሲጋራና ትምባሆ ገበያን የተቆጣጠሩት ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ሲሆኑ ይህም ዜጎች ለተለያዩ የጤና እክሎች እንዲጋለጡ አድርጓል። በየዓመቱ ከ17 ሺሕ በላይ ዜጎች ከሲጋራ ጋር በተያያዙ በሽታዎች ለመሞታቸው የኮንትሮባንድ ንግድ ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ አድርጓል።

በሌላ በኩል እንደ ካናቢስና ኮኬይን ያሉ ምርቶች በሕገወጥ ነጋዴዎች በተለይም በኤርፖርት በኩል የሚገቡ ሲሆን ይህም ኮንትሮባንድ ጤና ላይ የሚያስከትለው ጠንቅ ቀላል እንዳልሆነ ማሳያ ነው።

ችግሩ በዚህ አያበቃም።
በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ያሉ ገበሬዎች በብዛት የሚጠቀሟቸው ፀረ አረም መድኀኒቶች በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር የሚገቡ ሲሆን ይህም የአፈር አሲድነት እንዲጨምርና ለጤና ጠንቅ የሆኑ የግብርና ምርቶች ዜጎች እንዲመገቡ ምክንያት ሆኗል። ይህም ዜጎች ለካንሰርና ለሌሎች በሽታዎች በአስከፊ ሁኔታ እንዲጋለጡ ምክንያት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በተጨማሪም ጊዜ ያለፈባቸውና ሐሰተኛ መድኀኒቶች በስፋት ወደ አገር ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ሲሆን ችግሩ በመስፋቱ በአገሪቷ ወስጥ ከሚሰራጩ ዐሥር መድኀኒቶች አንዱ ሐሰተኛ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።

የኮንትሮባንድ ንግድ እና የመንግሥት ገቢ ተጻርሮ
የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ሕገወጥ ነጋዴዎችን የበለጠ ጠንካራ እያደረጋቸው የታክስ ስወራ እንዲስፋፋ ያደረገ ሲሆኑ ሌሎች በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩ ነጋዴዎች ባልተገባ ፉክክር የተነሳ ተሰላችተው ወደ ሕገወጡ የንግድ ዝውውር እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ኢ-መደበኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ እንዲያድግና የታክስ ገቢ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል።

በተለይ ባለፉት ዐሥር ዓመታት የአገሪቷ አጠቃላይ ምርት በአማካይ 10 በመቶ ቢያድግም የታክስ ከፋይ የሆኑ ድርጅቶች ቁጥር ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ከፍ አላለም። በተጨማሪም መንግሥት የሰበሰበው የታክስ መጠን የአጠቃላይ ምርቱን 10 በመቶ አካባቢ ሆኖ ለዐሥር ዓመታት ቆይቷል። ይህ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት በአማካይ ካስመዘገቡት 17 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ነው።

አዲሱ ካራፎ በተባሉ ምጣኔ ሀብት ባለሙያ 2018 (እ.ኤ.አ) በተደረገ ጥናት በአጠቃላይ ምርት ዕድገት እና በግብር መካከል ያለው ከፍተኛ ልዩነት ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል። ይሔም ለመንግሥት ገቢ አለማደግና ለታክስ ስወራ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ።

በተጨማሪ፤ ወደ ውጪ ከሚላኩ እና ወደ አገር ወስጥ ከሚገቡ ምርቶች የሚሰበሰበው የታክስ መጠን በዓመት 70 ነጥብ 4 ቢሊዮን የሚደርስ ሲሆን የኮንትሮባንድ ንግድ በመስፋፋቱ ዕድገቱ በአማካይ ስድስት በመቶ ብቻ እንዲሆን አድርጎታል። ዕድገቱ ከውጭ አገራት ወደ አገር ውስጥ ከሚገባው ምርት መጠን ዕድገት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ሲሆን የበጀት ጉድለት እንዲሰፋ ምክንያት ሆኗል።

በተጨማሪም፤ በሕገወጥ መንገድ ከሚገባው ምርት ግብር በአግባቡ ቢሰበሰብ የአገሪቷን የልማት ፕሮግራሞችን በመተግበር አኳያ የሚታዩ ክፍተቶችን ሊሞላ እንደሚችል አዲሱ ይገልፃሉ።

ታዲያ መንግሥት ከኮንትሮባንድ ምርቶች ያጣውን ግብር በሌላ መንገድ ማግኘት ስላለበት ሌሎች በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩ ድርጅቶች ላይ ጫና በማድረግ ከፍ ያለ ግብር ጥሏል ይላሉ አዲሱ። በዚህ ምክንያት ድርጅቶች ዋጋ ጭማሪ እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል የሚሉት አዲሱ፣ ይህም ለዋጋ ግሽበት መፈጠር ሰበብ እንደሚሆን ሥጋታቸውን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የግብር ዓላማ የዜጎች የገቢ አለመመጣጠን ማጥበብ እንደመሆኑ መጠን የኮንትሮባንድ ንግድ ከመንግሥት ዕይታ ውጪ በመሆኑ በድሃና ሀብታም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን ልዩነት ሊያሰፋው እንደሚችል ሥጋታቸውን ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

በተለይም በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የተሰማሩት ነጋዴዎች ለሚቀጥሯቸው ሰዎች የሚፈፅሙት ክፍያ ለጥቂት ሰዎች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጥቂቶችን ሀብታም በማድረግ የገቢ አለመመጣጠንን እንደሚያባብስ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ።

ኮንትሮባንድ እና የውጭ ምንዛሬ
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ፍላጎቶቻቸውን ከውጭ አገራት በሚያስገቡት ምርቶች ለሚያሟሉ አገራት፤ የውጭ ምንዛሬ ያለው አስፈላጊነት ከምንም በላይ ነው። በተለይም መሰረተ ልማት ግንባታ ለማካሔድና ወሳኝ የሆኑ የካፒታል ዕቃዎችን ለማስገባት እንዲሁም ዕዳዎችን ለመክፈል የውጭ ምንዛሬ አስፈላጊነቱን ከፍ ያደርገዋል።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት አገሪቷ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ መጠን መጨመር የመንግሥት ዋነኛ ግብ ቢሆንም ላለፉት ዐሥርት ዓመታት ማሳካት ግን አልተቻለም። ለአብነት የማዕድን ዘርፉን መጥቀስ ይቻላል።

የዛሬ ስድስት ዓመት ከ650 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ንግድ ገቢ ያስገኘው የማዕድን ዘርፍ በ2011 በጀት ዓመት ወደ 44 ሚሊዮን ዶላር መውረዱ በማዕድን ሚኒስቴር ይፋ መደረጉ ይታወሳል። ለገቢው መቀነስ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰው የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ሲሆን ችግሩ በየጊዜው እየተባባሰ ነው።

የዛሬ ሦስት ወር ገደማ የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ ወደ ሱማሌ ክልል ጉብኝት ባደረገ ወቅት በየቀኑ ከ1 ሺሕ 600 በላይ የቁም እንስሳት በሕገወጥ መንገድ በሱማሌ ክልል በኩል ከአገር እንደሚወጣ አስታውቆ ነበር። በተጨማሪም ዋሴ ብርሃኑ (ዶ/ር) የተባሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ባደረጉት ጥናት ኬንያ ድንበር አካባቢ ባሉ አንዳንድ ከተሞች ወደ ውጪ የሚላኩ ከብቶች 70 በመቶ የሚሆኑት በሕገወጥ መንገድ ከአገር እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የሰሊጥ ምርት ደግሞ ሌላው በሕገወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት አገራት በተለይም ከሁመራ ወደ ሱዳንና ወደ ሌሎች ጎረቤት አገራት የሚላኩ ሲሆን የቡና ምርትም በተመሳሳይ መልኩ ከአገር እንደሚወጣ መረጃዎች ያሳያሉ።

ታድያ እነዚህና ሌሎች ምርቶች የኮንትሮባንድ ንግድ እየተስፋፋ ሲሔድ በሕጋዊ መንገድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ መጠን እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል። ባለፈው ወር መጨረሻ የወጣው የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት በዐሥር ዓመት ውስጥ ትንሹ የውጭ ንግድ ገቢ (2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር) የተገኘው በ2011 በጀት ዓመት መሆኑን አመላክቷል።

ከዚህ ባሻገር፤ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ረጃጅም እጆቻቸውን በመጠቀም ከባንክ ሥራ ኀላፊዎችና ከትይዩ ገበያ (‘ጥቁር ገበያ’) ነጋዴዎች ጋር በፈጠሩት ትስስር ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ከአገሪቷ ያሸሻሉ።

በየዓመቱ ከአራት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንደሚሸሽ በተባበሩት መንግሥታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፎር አፍሪካ መረጃ ያሳያል። ይህም ከአገሪቷ የሚወጡት ምርቶች ሊያስገኙት ይችሉ ከነበረው ገቢ ጋር ተዳምሮ አገሪቷ የምታጣው የውጭ ምንዛሬ ቀላል እንደማይሆን ያሳያል።

በተጨማሪ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ የኮንትሮባንድ መስፋፋት ለትይዩ የውጭ ምንዛሬ ገበያው ማደግ አንድ ምክንያት ሲሆን የብር ዋጋ እንዲዳከም አድርጓል። በአሁኑ ሰዓት 1 ዶላር እስከ 40 ብር ድረስ ለመመንዘሩ እንደ ዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል።

ኮንትሮባንድን ከሰላምና መረጋጋት ጋር ምን አገናኘው?
በኢትዮያም ሆነ በሌሎች አገራት ከዚህ ቀደም የነበሩ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት፤ ኮንትሮባንድ ኀይል ያላቸው ሕጋዊ ያልሆኑ ጠንካራ ቡድኖች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያላቸው የጥቁር ገበያ ተዋንያኖች፣ ሕገወጥ የገበያ አስተላላፊዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናትን በማገናኘት ሽብር እንዲበዛ ሊያደርግ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ በሕገወጥ ካፒታል ዝውውርና ለሽብርተኝነት በቀላሉ ገንዘብ ማስተላለፊያ መስመር ከሆኑ አገራት ተርታ በመመደቧ በአውሮፓ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ከሰሜን ኮርያና ኢራን ጋር ጥቁር መዝገብ ውስጥ እንድትካተት አድርጓታል።

በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር ኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነሳል። ለአብነትም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መጋቢት 2010 ፓርላማ በቀረቡበት ወቅት፤ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ በፓርላማ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ዋነኛ ምክንያቱ ኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር መስፋፋት ናቸው ብለው ነበር።

የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ፤ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ወቅት በሰጡት አስተያየት በአገሪቷ ለነበሩ አለመረጋጋቶች ጥቅማቸው በተነካ በኮንትሮባንድ ነጋዴዎችና የውጭ ምንዛሬ አዘዋዋሪዎች ድጋፍና በጥፋት ኀይሎች የመጣ ነው ብለው ነበር።

በተጨማሪ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በአገር ደረጃ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ አዲስ ዕቅድ ይፋ በተደረገበት የዛሬ ወር በተደረገ ስብሰባ፤ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከገቢ ባሻገር የሉአላዊነት ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገልጸው ነበር።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በጅግጅጋ የሚኖሩ በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ እንደገለጹት፤ በተለያዩ ቡድኖች መካከል አልፎ አልፎ ፀብ እንደሚነሳና ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች እስከ ሞት የሚያደርስ ግጭት ውስጥ እንደሚገቡ ገልጸዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጌታቸው በበኩላቸው፤ የኮንትሮባንድ መስፋፋት በአንድ አገር አለመረጋጋት፣ ሰላምና ፖለቲካ ላይ ጥርጣሬ መኖሩን ማሳያ ሊሆን ይችላል ሲሉ ሥጋታቸውን ያነሳሉ። ለአብነትም በቅርቡ በመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ የተያዙትን የጦር መሣሪያዎችና የውጭ ምንዛሬዎችን ያነሳሉ። አያይዘውም “የመንግሥት መዋቅሮች በሚገባ ሁኔታ በማይሠሩበት ወቅት እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ” ብለዋል።

በተጨማሪም አገሪቱ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት በመጠቀም ሕገወጥ የንግድ ዝውውር ሊኖር እንደሚችል ሥጋታቸውን ጌታቸው ያጋራሉ። በተለይ መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከገባበት ቀውስ አንጻር ችግሩ ሊስፋፋ ይችላል ሲሉም አክለዋል።

ምን ይሻላል?
የኮንትሮባንድ ንግድ በሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማሳደሩ፤ መንግሥት የኅብረሰተቡን ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንስቶ ስትራቴጂ ቀርጾ ተግባራዊ እስከማድረግ ድረስ የተለያዩ እርምጃዎን ወስዷል። በቅርቡም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቀው አዋጅ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠቃለል ተደርጎ የነበረው የጉምሩክ ፖሊስ ራሱን ችሎ እንዲዋቀር አድርጓል።

በተጨማሪ በቅርቡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ በተገኙበት ኮንትሮባንድ ለመከላከል ይረዳል ተብሎ የታሰበ ዕቅድ ይፋ ተደርጓል። በዕቅዱም መሰረት እስከ ቀበሌ የተዘረጋና ኅብረሰተቡን የሚያሳትፍ ኮንትሮባንድን የመቆጣጠር ሥራ ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባሻገር ችግሩ በስፋት የታየባቸው ክልሎች ይህንን መሰረት አድርገው የራሳቸውን ዕቅድ ይፋ አድርገዋል። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዋነኝነት ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚሠራ የገለጹ ሲሆን፤ ከላይኛው እስከ ታችኛው እርከን ያሉ አመራሮች ተሳታፊ የሚሆኑበት የማስቆሙ ሥራ ወደ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል።

በተመሳሳይ የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ በበኩላቸው፤ ኮንትሮባንድ ረጅም ጊዜ የቆየ ባሕል በመሆኑ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች በቀዳሚነት ይተገበራሉ ያሉ ሲሆን፤ የሕግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አክለዋል።

ታድያ የክልልና የፌዴራል መንግሥታት ሊወስዱ ያሰቡትን እርምጃዎች የተመለከቱ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ መንግሥት ለሁሉም በኮንትሮባንድ ለሚገቡና ለሚወጡ ምርቶች አንድ ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ ማቀዱ ትክክል አይደለም።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ መንግሥት ኮንትሮባንድ ለመቆጣጠር እንደምርቱ ዓይነት የተለያዩ እርምጃን መውሰድ አለበት። ለአብነትም በአገር ውስጥ ከሚመረቱ እቃዎች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ምርቶች በኮንትሮባንድ የሚገቡ ከሆነ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ዓለማየሁ፣ በሌላ በኩል እንደ ከብት እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ለጎረቤት አገራት የሚሸጡት ዜጎች ላይ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ የፖሊሲ ለውጥና ማበረታቻዎች ያስፈልጋሉ ይላሉ።

በሌላ በኩል ከአስተዳደራዊ እርምጃዎች ባሻገር የኮንትሮባንድ ምንጩን በማወቅ የመከላከል ሥራዎች መሠራት አለበት የሚሉት ጌታቸው፤ የመጀመሪያውና ትልቁ ችግር የንግድ ስርዓቱ ነው ይላሉ።

“ንግድ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የኢ-መደበኛ ነጋዴዎች መሆናቸው እና የተቀናጀ ስርዓትና ተቋም እንዲሁም የተደራጀና የሰለጠነ የሰው ኀይል አለመኖሩ ክፍተት መፍጠሩ ኮንትሮባንድ ንግድ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ጌታቸው አክለዋል።

በሌላ በኩል በኮንትሮባንድ ላይ ጥናት ያደረጉት አዲስ በጥናታቸው ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ሕገወጥ የገቢና የወጪ የንግድ እንቅስቃሴን ለመግታት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የአቅርቦት ችግር መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን አገር ውስጥ በማምረት የመተካት ሥራ ያስፈልጋል፤ እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለጻ።

በገቢዎች ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ታክስ ዕቅድና ክትትል ዳይሬክተር ተመስገን ተሰማ በበኩላቸው፤ በፌዴራል ፖሊስ፣ መከላከያ፣ የክልል ፖሊሶችና የጉምሩክ ኮሚሽን መካከል ቅንጅት በመፍጠር እርምጃዎችን መውሰድን ውጤታማ ያደርጋል ይላሉ።

የገቢዎች ሚኒስትር አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃዎችን በመጠቀም የአገር ውስጥ ገቢን ለመጨመር እና ኮንትሮባንድን ለመቀነስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ከወር በፊት በተዘጋጀ ግብር ከፋዮችን ዕውቅና የመስጠት ሥነ ስርዓት ወቅት ቃል ገብተዋል። ይሁን እንጂ፣ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ኮንትሮባንድን መቆጣጠር ይሳካላቸው ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here