በኦሚክሮን ደጋግሞ የመያዝ ዕድል

0
975

ዓለማችን ላይ ከተከሠተ ኹለት ዓመት ያስቆጠረው ኮሮና ቫይረስ እስካሁን በርካቶችን እየገደለና በሕመም እያሰቃየ ይገኛል። የበርካቶችን ሕይወት ከማመሰቃቀሉ ባሻገር፣ የዓለምን ኢኮኖሚ አናግቶ ብዙዎች ሥራ አጥ ሆነው ለከፋ ድህነት እንዲዳረጉ ምክንያት ሁኗል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዓለማችን አይታው የማታውቀው ምስቅስቅል ውስጥ ከገባች ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ሥጋቱ እስካሁን እንደቀጠለ ነው። በበሽታው የሚሞቱ ቁጥር ብዛቱ በየጊዜው ቢለያይም፣ አሁንም እያሻቀበ ይገኛል። እንደመጀመሪያ ሰሞን ከተማዎች የተወረሩ እስኪመስል ጭር ባይሉም፣ አሁንም ክልከላዎችና ዕገዳዎች ተመላልሰው እየመጡ ይገኛሉ። ለዚህ ምክንያት ደግሞ ቫይረሱ ዝርያውንና ባህሪውን እየቀያየረ በመምጣቱ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ተመራማሪዎች ለፍተው ጥረው ግረው ያገኙት የመከላከያ ክትባት ያን ያህል ጥቅም ሳይሰጥ አዲስ ዝርያ ስለሚሠራጭና ልፋቱን እንደአዲስ ስለሚያስጀምር፣ ሀብትና ጉልበት በተደጋጋሚ እንዲባክን፣ አገራትም ለከፍተኛ ኪሳራ እንዲዳረጉ መንስዔ ሲሆን ቆይቷል።

ሠሞኑን ዓለማችንን እያዳረሰ የሚገኘው ኦሚክሮን የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በመቼውም ጊዜ ከተከሠቱት በይበልጥ የሚተላለፍ በመሆኑ፣ አሁን በዓለም ዙሪያ ተሠራጭተው ከሚገኑ ዝርያዎች ከ95 በመቶ በላዩን ይሸፍናል ተብሏል። ዴልታ የተሠኘው የበለጠ ገዳይ የነበረው ዝርያ እየከሰመ ሲሄድ ኦሚክሮን የተሰኘው ደግሞ ይበልጥ በመተላለፍና ክትባቶችን በመቋቋም ወደር አልተገኘለትም። የመሠራጨት ፍጥነቱ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ይበልጥ ፈጣን ቢሆንም፣ ገዳይነቱና አሰቃይነቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ለመዘናጋት ምክንያት መሆኑ ይነገራል። በእሾሃማው የፕሮቲን ክፍሉ ላይ ባለ ጭማሪ አማካይነት ይበልጥ የሚስፋፋውና ብዙዎችን ታማሚ ያደረገው ይህ ዝርያ፣ ሌሎች ዝርያዎች በቀጣይ እንዳይዙ የማድረግ የመከላከል አቅምን ያዳብራል ቢባልም፣ ሙሉ በሙሉ በማስረጃ ለማረጋገጥ ግን ጊዜ ይፈልጋል ተብሏል።

የኦሚክሮን ዝርያ መከላከያውንም ሆነ የሚያስከትለውን መዘዝ ገና በደንብ መረዳት ሳይቻል ከወደ ፈረንሳይ የባሰ የመሠራጨት ፍጥነት የሚኖረው ሌላ አዲስ ዝርያ ተገኘ መባሉም ሌላ ያልተገመተ ሥጋት አሳድሯል። ከሥርጭቱ ቀጣይነት ጋር በተያያዘ ሳይንቲስቶች ራሱን የመቀያየሩ ሒደት ስለማይቆም ከቫይረሱ ጋር አብሮ ለመኖር መዘጋጀቱ የተሻለ እንደሆነ ስለመምከራቸውም በባለፈው ዕትማችን አስነብበን ነበር።

ኦሚክሮን የተሠኘው ዝርያ እንደቀደምቶቹ አደገኛ የሚባል ገዳይ አይደለም ቢባልም፣ አንዴ ከያዘ መልሶ አይዝም ሲባል የነበረው ግን በምርምር ያልተረጋገጠ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አሳውቋል። ብዙዎች አንዴ ከያዛቸው መልሶ እንደማይዛቸው በመገመት ከጥንቃቄ ሲታቀቡ አንዳንዴም ሌላውን ላለማስያዝ ከሚደረግ ጥንቃቄ ሲዘናጉ በአገራችንም ይታያል። በተቃራኒው አንዳንዶች ደግሞ፣ ቤተሰብ ውስጥ አንዴ ከገባ ከአንዱ ወደአንዱ እየተዘዋወረ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል በሚል ሥጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ ቫይረሱ ዝርያውን የሚቀያይረው በሽታን የመከላከል የሰውነት የተፈጥሮ አቅሙ የተዳከመበት ሰው ውስጥ በሚቆይበት ጊዜ ራሱን ለመቀየር ስለሚመቸው ነው ይላሉ። ሕመም በቶሎ ሊድንለት ያልቻለ ሰው ሰውነት ለቫይረሱ ስለሚመቸው፣ በቆይታው ራሱን መለወጥና ሌላ ሰውን ይበልጥ ለማጥቃት ምቹ ሁኔታ ይፈጠርለታል ሲሉ ያስረዳሉ። ኤች አይ ቪን በመሳሰሉ የሰውነት የመከላከል አቅምን በሚያዳክሙ ቫይረሶችም ሆኑ ሕዋሳት የተጠቁ ሰዎች ላይ በሚቆይበት ጊዜ እንደልቡ ስለሚሆን፣ እነሱም ለረጅም ጊዜ ራሳቸውን አግልለው ስለሚቆዩ የመቀየሩ አዝማሚያ ይጨምራል ይላሉ። ስለኤች አይ ቪ እና ኦሚክሮን ግንኙነት ጥናት ያደረጉ ሳይንቲስቶች ተናገሩ ብሎ ‹ዘ ስታንፎርድ ዴይሊ› እንዳስነበበው፣ ኦሚክሮን እስካሁን ከ50 በላይ ዝርያውን የቀየረበት ኹኔታ ሊኖር እንደሚችል ነው።

በሽታን የመከላከል አቅማቸው ደካማ በሆነባቸው ሰዎች ውስጥ ቫይረሱ ለ10 ያህል ቀናት መቆየት ከቻለ ራሱን ወደሌላ ዓይነት ዝርያ በቀላሉ ሊቀይር እንደሚቻለው ማወቅ ተችሏል። ይህ ግኝት በአነስተኛ ናሙና በተጠና ጥናት መሠረት የታወቀ በመሆኑ እርግጠኛ ስለማያደርግ ሠፊ ጊዜን የሚጠይቅ ተጨማሪ ጥልቅ ጥናትን ይፈልጋል ተብሏል። አንድ ዝርያ ወደሌላ ራሱን የሚቀይርበት ኹኔታ ከታወቀ፣ እንዳይቀየር ለማድረግም ሆነ ቢቀያይርም መከላከል በሚቻልበት አማራጭ ላይ ለመሥራት ምቹ ኹኔታን ይፈጥራል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።

የስታንፎርድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ኤች አይ ቪ ለአዲሱ ኦሚክሮን ቫይረስ መከሰት ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ነው። ዝርያው ደቡብ አፍሪካ ይበልጥ ተሠራጭቶ እንደመገኘቱ በአገሪቱ ካለ የኤች አይ ቪ ሠፊ ሥርጭት ጋር ሳይያያዝ እንደማይቀር ተገምቷል። በዓለማችን ካለ የኤች አይ ቪ በሽታ ተጠቂ ኹለት ሦስተኛው (26 ሚሊዮኑ) ከሠሀራ በታች ባለው የአፍሪካ ግዛት እንደመገኘቱ፣ ከኦሚክሮን ጋር ያለው የሥርጭት ቁርኝት ምልክት ይሰጣል ብለዋል። በኹለቱ በሽታዎች መካከል ያለው ግንኙነት በማስረጃ የተረጋገጠ ባይሆንም፣ ከበሽተኞች በተገኘ መረጃ መሠረት ጠቋሚ ፍንጭ ስለሚሆን ራሱን የቻለ ጥናት ያስፈልገዋል ሲሉ ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል።

የኦሚክሮን ተደጋጋሚነት
ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ አንድን ሰው ደግሞ ሊይዝ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አሳውቋል። እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር የተደረገው ጥናት በጥቂቶች ላይ የተመረኮዘ እንደመሆኑ ያለጥርጥር ደግሞ ይይዛል ማለት እንዳልሆነ የተመላከተ ቢሆንም፣ መረጃው መዘናጋትን እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ያሻዋል መባሉም ተነግሯል። ተቋሙ ያወጣውን ሪፖርት ተመርኩዞ መረጃውን ያስነበበው ‹ኤን ቢ ሲ ቺካጎ› ነው። እንደግኝቱ ከሆነ ደግሞ ይይዛልም ሆነ አይዝም ብሎ አሁን እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ወቅቱ አያስችልም። የትኛውንም ሐሳብ የሚያረጋግጥ ማስረጃ እስካሁን ማቅረብ ባለመቻሉ፣ መጠንቀቁ ይሻላል በሚል መዘናጋት እንዳኖር ተመክሯል።

ኦሚክሮን ከሌሎቹ ዝርያዎች በይበልጥ አንድን ሰው ደግሞ ሊይዝ እንደሚችል አመላካች ኹኔታዎች ስለመኖራቸው የተነገረ ሲሆን፣ እርግጠኛ ባይሆንም እንኳን መዘናጋት እንዳይኖር ሲባል ክልከላዎችና ገደቦች ሊከበሩ ይገባል ተብሏል። የ‹ጆን ሆፕኪንስ› ተመራማሪዎች በበኩላቸው፣ አንድ ሰው በአዲሱ የቫይረሱ ዝርያ ከተጠቃ በኋላ የሰውነቱ የመከላከል አቅም ምን ያህል እንደሚሆን እስካሁን ለማወቅ አለመቻሉን ነው። በጊዜ ሒደት ሰውነት መልሶ በተመሳሳይ ቫይረስ ሊጠቃ እንደሚችል አመላካች ኹኔታዎች ቢኖሩም፣ ይህን መላምት ለማረጋገጥ ለውጡን በጊዜ ሒደት ታግሶ ማየትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል ይላሉ።

ኦሚክሮን ዓለማችን ላይ ከተከሠተ ገና ጥቂት ወራት እንደመሆናቸው በዘላቂነት ምን እንደሚያስከትልም ሆነ ተይዘው የዳኑት ላይ ምን ለውጥ እንደሚያመጣ ለማወቅ ጊዜው አጭር ነው፣ ሲሉ በዘርፉ ላይ ምርምር እያደረጉ የሚገኙ የተለያዩ አጥኚዎች እየተናገሩ ነው። ከወር በፊት በእንግሊዝ በተካሄደ ጥናት በኦሚክሮን የተያዘ ሰው መልሶ የመያዙ ዕድል ከዴልታ ዝርያ በአምስት ዕጥፍ ይጨምራል መባሉን ‹ሬውተርስ› አስነብቦ ነበር። ይህ መረጃ ግን እስካሁን ይህን ያህል ሰዎች ተይዘዋል ተብሎ ማረጋገጥ ባለመቻሉ ለሌላ ማረጋገጫ ጥናት ምክንያት መሆኑ ተነግሯል። በ‹ኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን› አማካይነት ጥናቱን ለማረጋገጥ ተሞክሮ፣ ምንም ዓይነት አመላካች ግኝት እንዳልተገኘ በመጥቀስ ይፋ ተደርጎ የነበረውን ያልተረጋገጠ ግምት ነው በማለት ውድቅ አድርገውታል።

በርካታ ተመራማሪዎች እርግጠኛ ሆኖ እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር ከጊዜና ካለው ማስረጃ አኳያ አይቻልም በሚለው ሐሳብ ቢስማሙም፣ የሚለያያቸው ጉዳይ የተወሠነ ነው። የተወሠኑት አዲስ ለውጥ (ሚውቴሽን) በሚከሰትበት ጊዜ ደጋግሞ ሊይዝ የሚችልበት አጋጣሚ ሠፊ ይሆናል ቢሉም፣ የተወሰኑት ደግሞ የተረጋገጠ ሳይሆን መላምት በመሆኑ አረጋጋጭ ጥናት በሠፊው ሳይደረግ መናገር አይቻልም ይላሉ።

አዳዲስ ዝርያዎች ከቀደሙት ይልቅ በከፍተኛ ፍጥነት መተላለፍ እንደመቻላቸው፣ እንዲሁም በጊዜ ሒደት የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም እየቀነሰ መሄዱ ስለሚታወቅ ኦሚክሮንን የመሳሰሉ ዝርያዎች ደጋግመው ሊይዙ እንደሚችሉ መገመት ያስችላል። ይህ ቢሆንም ግን፣ እንደጉንፋን ቫይረስ በየጊዜው ራሱን እየቀያየረ በመምጣት ደጋግሞ ስለመያዙ በጊዜ ሒደት የሚታይ ይሆናል። በዚህ አጭር ጊዜም ቢሆን ግን በድጋሚ በኦሚክሮን እንደተያዙ የተረጋገጠባቸው ሰዎች መኖራቸውን ባለሙያዎች ጠቁመዋል። ከመሠረታዊ የጥናት ናሙና አወሳሰድ አኳያ የእስካሁኑ በቂ አይደለም ማለቱ ቫይረሱ ድጋሚ አይዝም ማለት ባለመሆኑ፣ ሕብረተሰቡ ቫይረሱ ሳይያዘውም ሆነ ይዞት ከለቀቀውም በኋላ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ኹሉም ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

ተመሳሳይ ርዕስ

የኦሚክሮን ዝርያ አሳሳቢነት – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ አደገኛነት – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

የአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የኦሚክሮን አሳሳቢነት – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here