መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብነገረ ጤናየኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የቆይታ ዘመን

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የቆይታ ዘመን

በቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘውና ዓለምን ያዳረሰው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መዛመት ከጀመረ አሁን ላይ ኹለት ዓመታትን ቢያስቆጥርም፣ መቼ ወረርሽኝ መሆኑ ያበቃል የሚለውን ለማወቅም ሆነ ለመገመት እስካሁን አልተቻለም። ቫይረሱ በወረርሽኝ መልክ የተከሠተ ሰሞን ብዙዎች በዚህ በሠለጠነ ዘመን በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ሥር ይውላል በማለት እምብዛም አስጊ እንደማይሆን ይገምቱ ነበር። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ቀነሰ ሲባል እንደአዲስ እያገረሸ አሁንም ድረስ አስጊነቱ እንደነበረ ይገኛል።

ወረርሽኙ በከፍተኛ ፍጥነት እንደሠሞኑ ተስፋፋቶ ባያውቅም፣ የአሁኑ ገዳይነቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ሥጋቱ መቀነሱን የሚናገሩ አሉ። አንዳንዶች እንዲህ ተሠራጭቶ ከቆየ በጊዜ ሒደት የሚያመጣው ለውጥ ስለማይታወቅ መጠንቀቁ አይከፋም በሚል ሥጋት እንዳላቸው ይናገራሉ። በአዲሱ የኦሚክሮን ዝርያ ሳቢያ የተከሠተው በሽታ እንደቀድሞዎቹ ዝርያዎቸች ገዳይ አይደለም ቢባልም፣ የመጀመሪያዎቹ ሟቾችን ማስመዝገብ መጀመሩ ይፋ ተደርጓል። ለምሳሌ፣ በደቡብ ኮሪያ ከኦሚክሮን ጋር በተገናኘ የመጀመሪያዎቹ ሟቾች በያዝነው ሣምንት መጀመሪያ ተመዘገቡ መባሉን ‹ዮናፕ ኒውስ ኤጀንሲ› ዘገበ ብሎ ‹ዘ ስትሬትስ ታይምስ› አስነብቧል።

አዲሱ ኦሚክሮን የተሠኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ኢትዮጵያ ውስጥም ሳይቀር በከፍተኛ ፍጥነት ተዛምቶ ያልያዘው እንደሌለ እየተነገረ ይገኛል። አብዛኛው ሰው ሳይመረመር በሽታው ይዞ እንደለቀቀው ከምልክቶቹ በመነሳት ቢናገርም፣ ከወረርሽኙ ሥርጭትና ኢትዮጵያ ካላት አቅም አኳያ ለኹሉም ምርመራውን ማድረግ እንዳልተቻለ እየተነገረ ነው። እኛን በመሳሰሉ ድሃ አገራት ብቻ ሳይሆን፣ አቅሙ ያላቸውም ምርመራ ማድረጊያውን ቁስ በተፈለገው ፍጥነት ማሠራጨት አለመቻላቸው እየተዘገበ ይገኛል። ግለሰቦች በየቤታቸው በመውሰድ ራሳቸውን የሚመረመሩበት መሣሪያም ዕጥረት በማጋጠሙ ችግሩ እየጎላ መምጣቱን የሚናገሩ አሉ።

ኮሮና ቫይረስ ዝርያውን እየቀያየረ እንዲህ ዓለማችንን እያመሰ የሚቀጥልበት ጊዜ ምን ያህል እንደሚሆን ብዙዎች መላምታቸውን ሲያስቀምጡ ቆይተዋል። ከችግሩ አጀማመር አኳያ በአጭር ጊዜ ይጠፋል ያሉ የመኖራቸውን ያህል፣ እንደኤች አይ ቪ ወረርሽኙ ሳይጠፋ የሚዘልቅ ነው የሚሆነው እያሉ ምልከታቸውን ያስቀመጡም ነበሩ። ከወረርሽኙ ሥርጭት እንዲሁም ከቫይረሱ ተለዋዋጭነት አንፃር በዚህ ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ይውላል ብሎ መናገር እንደማይቻል ባለሙያዎች ይመሰክራሉ።

በቆይታ ጊዜው ላይ አስተያየታቸውን የሠጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይህን የሚወስነው የዓለም ጤና ድርጅት እንደሆነ ይናገራሉ። ወረርሽኝ ተከስቷል ብሎ መጀመሪያውኑ ዕውቅና የሠጠው ዓለም አቀፉ ተቋም፣ ወረርሽኝ መባሉ ከእንግዲህ ያበቃል ብሎ በይፋ እስካልተናገረ ድረስ አገራትም ሆኑ ባለሙያዎች በተናጥል ቢናገሩ ጥቅም እንደሌለው ይናገራሉ። ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተሄደበት መንገድ ወሳኝ ቢሆንም፣ የታማሚ ቁጥር፣ ሆስፒታል የገቡና ያገገሙት ቁጥራቸው ከአጠቃላይ የሥርጭት መጠኑ ጋር ተጣጥሞ ሲታወቅ ይፋ እንደሚደረግ ‹ሚንት› በድረ ገጹ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ማንኛውም በወረርሽኝ መልክ የተከሠተ በሽታ፣ ወረርሽኝ መሆኑ የሚያበቃበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ ጊዜው አጠረም ረዘመም ሕብረተሰቡ ከበሽታው ጋር አብሮ የመኖርን ጥበብ ሊላበስ እንደሚገባው ይመክራሉ። እንደማብሪያ ማጥፊያ አቆመ ተብሎ በአንድ ጊዜ ሥርጭቱ የሚቆም ባለመሆኑ፣ ሥራው የሒደት ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ በተስፋ እየተጠነቀቁ መቆየት እንደሚገባ ይናገራሉ። ወረርሽኙ ለረጅም ጊዜ ቢቆይ እንኳን እንዴት ራስን ከበሽታው ተከላክሎ መቆየት እንደሚገባ ማወቅ ይገባል ተብሏል።

ከኮቪድ ጋር በተገናኘ አዲሱ ኦሚክሮን የተባለው ዝርያ ስለበሽታው ሥርጭት ይገመት የነበረ የመቆያ ጊዜን እንዳራዘመውና ሒደቱን እንዳወሳሰበው የሚናገሩት የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ አዲሱ ክስተት በቋፍ ላይ የነበረውን የሕብረተሰቡን ዕምነት ጥርጣሬ ውስጥ የከተተ በመሆኑ፣ አሁን ላይ ሆኖ በዚህ ጊዜ ወረርሽኝ መሆኑ ያበቃል ማለት እንደማይቻል ያስገነዝባሉ።

አዲሱ ዝርያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የበሽታው ሥርጭት እንዲያሻቅብ ቢያደርግም፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ ሥራቸውን ከመጀመሪያው “ሀ” ብለው ስለማይጀምሩ በአንፃሩ ለአዲሱም ዝርያ ዕልባት ለማግኘት ረጅም ጊዜ እንደማይወስድ የሚናገሩ አሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ኦሚክሮን በባህሪው ያን ያህል ጉዳት የማያመጣና የጉዳት መጠኑ ዝቅተኛ ዝርያ በመሆኑ፣ ሰዎች በከባባዶቹ ዝርያዎች ተይዘው ጉዳት እንዳይጨምርባቸውና ሰውነታቸው እንዲለማመደው በማድረጉ ለወደፊት ጠቀሜታው ትልቅ እንደሚሆን እየተነገረም ነው። ይህ ላለፉት ከባባድ ዝርያዎች ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ባሕሪያቸውን ቀይረው ለሚከሠቱ አዳዲስ ዝርያዎችም የአሁኑ ጠቀሜታ ሊኖረው ስለሚችል የወረርሽኙ የቆይታ ጊዜ ይራዘማል ብሎ ለመገመት አዳጋች ያደርገዋል ተብሏል።

በየል ዩኒቨርስቲ የማኅበረሰብ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑ ዶክተር አልበርት የተሰኙ የተላላፊ በሽታዎች ስፔሻሊስት እንደሚሉት፣ እስካሁን ባለው ሒደት ኮቪድ ለዘላለም አብሮን የሚኖር ይመስላል። እንዴት ማቆም ይቻላል በሚለው ላይ በመረባረብ ከፍተኛ ትኩረት ተሠጥቶ ካልተሠራበት በሽታውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት አይቻልም ባይ ናቸው። ወረርሽኝ መሆኑ አብቅቷል ብሎ የዓለም ጤና ድርጅት የሚወስንበት የሥርጭት መጠንም ይህ ነው ብሎ መናገር ስለማይቻል ጊዜውንም ለመገመት አስቸጋሪ እንደሚሆን ባለሙያው ተናግረዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች “ኢንደሚክ” የሚሉት ወቅት፣ በሽታው በተወሠነ ደረጃ ሥርጭቱን ቀንሶ ሳይዋዥቅ የሚቀጥልበት ሒደት እንደሆነ በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ (ኤክስፐርት) ስቴፈን ኪስለር አስረድተዋል። ይህ ወቅት በዚህን ጊዜና መጠን ላይ ሲሆን ነው ብሎ መስመር ማስመር የማይቻልበት አወዛጋቢ ጉዳይ እንደመሆኑ፣ ዋናው የባለሙያዎች ሥምምነት መኖሩ ነው ይላሉ።

የኦሚክሮን መከሠት ጊዜውን ለመገመትም ሆነ ለማሳጠር የነበረ ዕቅድን ቢያስረዝመውም፣ ከሳርስ እና ከመደበኛው የጉንፋን ቫይረስ ሥርጭት አንፃር የኮቪድም መቀነሱ እንደማይቀር እርግጠኛ መሆን ይቻላል ይላሉ። የሥርጭቱ መጠን እንደአገራት አቅም ሊለያይ ይችላል የሚሉት ባለሙያው፣ ዓለማችንን ለምን ያህል ጊዜ ሥጋት ላይ ይጥላታል የሚለውን ሳንቲስቶች ሳይሆኑ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች የሚመልሱት ነው የሚሆነው ብለዋል።

በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች የወረርሽኙ ጊዜ ቢራዘምም እንኳን ከኹለት ዓመት በፊት ወደነበረው ውዥንብርና ሥጋት ዓለማችን መመለስ እንደሌለባት ይናገራሉ። በክልከላዎችና በቁጥጥሮች ሳቢያ የሕብረተሰቡ ማኅበራዊ ኑሮ እንዳለፉት ዓመታት ሊናጋ እንደማይገባው ይናገራሉ። ከበሽታው ጋር አብሮ ተስማምቶ መኖር ብቻ ሳይሆን፣ የዓለምን ኢኮኖሚ በማይጎዳና ሕብረተሰቡ በሠላም ሠርቶ የሚኖርበትን ኹኔታ በማይለውጥ አኳኋን ከቫይረሱ ጋር አብረን መኖር መቻል እንዳለብን ያስገነዝባሉ።

ኦሚክሮን ባሕሪውን የቀየረ አዲስ ዝርያ ሆኖ እስካሁን የተመረቱ መከላከያዎችን መቋቋም መቻሉ ለብዙዎች ሥጋት መሆኑ ይታወቃል። ለዚህም ዝርያ ክትባት ማዘጋጀት ቢቻል እንኳን አሁንም ዝርያውን ለውጦ እንደአዲስ የመከሰቱ አዝማማያ ስለሚኖር ወረርሽኝ መሆኑ ያበቃል የሚለውን ግምት ብዙዎች ያጣጥሉታል።

በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተላላፊ በሽታዎች ክፍል አጥኚ ዊሊያም ሞስ (ዶክተር) ግን ከዚህ የተለየ ኃሳብ አላቸው። ቫይረሱ ራሱን እየቀያየረ ቢመጣም አሁን በሚሠራጭበት ፍጥነት ሁሌ እየጨመረ መሔድ እንደማይችል ነው የተናገሩት። የሆነ የከፍታ መጠን ይኖረውና ከዛ በላይ መሔድ ስለማይቻለው ማሽቆልቆሉ አይቀርም ባይ ናቸው። አዲስ ዝርያ ቢከሠትም ሰውነታችን ከነባሮቹ በሚያገኘው አቅምን የማጎልበት ብቃት አኳያ እስካሁን እንደነበረው አስጊ አይሆንም ይላሉ። ምንአልባት በየጊዜው እንደሚለዋወጠው ዓይነቱ፣ የተለያዩ ክትባቶችን እያዘጋጁ በየተወሰኑ ጊዜዎች እንደጉንፋን ክትባት መከተብ አሊያም የሰውነት መከላከል አቅምን ማጎልበት ሊያስፈልግ እንደሚችል ጠቁመዋል። የሰውነታችን የተፈጥሮ በሽታን የመቋቋም ብቃት እያደር እየጠነከረ ይመጣል የሚሉት እኚህ ተመራማሪ፣ የወረርሽኙ ሒደት የማይቀለበስ አዙሪት ይሆናል የሚል ሥጋት እንደሌላቸው አሳውቀዋል።

ሳንቲስቶቹ እንደሚሉት፣ አጠቃላይ የሕብረተሰቡ በሽታውን የመቋቋም ብቃት አድጓል። ከኹለት ዓመት በፊት የነበረው ማኅበረሰብ አይደለም አሁን ያለው የሚሉት እነዚህ ባለሙያዎች ፣ ለወደፊትም ይበልጥ ጠንካራና በቀላሉ ሥጋት ላይ የማይወድቅ ትውልድ ይኖራል ይላሉ። እንደማንኛውም ጉንፋን ታሞ በአንድና በኹለት ቀናት ውስጥ መነሳት የሚቻልበት ጊዜ ይሆናል በሚል ምልከታቸውን ከሠደድ እሳት ጋር ያነጻጽሩታል። እሳት ነክቶት በማያውቅ ዱር ውስጥ ሰደድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከሰት የሚስፋፋውን ያህል በቀጣይ ዓመት እዛው ቦታ ላይ ተመሳሳይ አይሆንም። እኩል የሚነድ ምግብ ካለማግኘቱ ባሻገር፣ ተፈጥሮም መቋቋምን የሚሰጣቸው ተክሎችም ሆኑ እንስሳት ስለሚኖሩ አውዳሚነቱ እየቀነሰ ይመጣል።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች