የኮቪድ ክትባትና ክትባቱ ላይሠራ የሚችልበት ምክንያት

0
746

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ከተከሰተ ኹለት ዓመት ቢያስቆጥርም አሁንም በሕዝብ ላይ የደቀነው ሥጋት እንዳለ ነው። ወረርሽኙ ከምን ላይ ተነስቶ ወደ ሰው ልጅ እንደተስፋፋ እስካሁን ባለመታወቁም ጭምር ሕክምናውን መስጠትና ሥርጭቱንም ማስቆም ሳይቻል ቀርቷል። በቫይረሱ የሚከሰተውን በሽታ ማስቀረት ባይቻልም፣ ወረርሽኙ ነክቷቸው በቫይረሱ የተጠቁ ያለምንም ዕርዳታ እንዳይሞቱ ለማድረግና የሟች መጠኑንም ለመቀነስ መቻሉ ይነገራል።

ኮቪድ 19 በወረርሽኝ መልክ የተከሠተ ሰሞን በሳምንታት ግፋ ቢል በጥቂት ወራት ሕክምናውንና መከላከያውን ማግኘት ይቻላል በሚል ይህን ያህል እንደማይቆይ ሲገመት ነበር። ነገር ግን፣ በጥቂቶች የተፈራው ዕውን ሆኖ እስካሁን ድረስ ቫይረሱ ዓይነቱን እየቀያየረ ዓለማችንን ደጋግሞ እያመሳት ይገኛል።

የኮቪድ ክትባቱ ተገኘ ተብሎ ብዙዎችን የእፎይታ ጊዜ ሰጥቶ የቆየበት ጊዜ እምብዛም ሳይረዝም፣ ሌላ ዝርያ ተገኘ ተብሎ መልሶ ሥጋቱንና ቁጥጥሩን እንዲጨምር አድርጎታል። በርካታ ኩባንያዎች ከብዙ ደጅ ማስጠናት በኋላ በተፋጠነ የሙከራ ዘዴ ያለፈ ክትባታቸውን ለዓለም ለማዳረስ የፈጀባቸው ጊዜ አጭር ቢሆንም፣ ውጤታማነቱ ግን ገና ከመነሻው ብዙ አስብሎ ነበር።

ክትባቱን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚነዙ አሉባልታ ነክ የሴራ ትንተናዎች ሳቢያ አልከተብም የሚለው የሕብረተሰብ ክፍል ብዛቱ እያደር የመጨመሩን ያህል፣ በኹሉም አገራት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን ክትባት አንዳንዶች በግድ ውሰዱ ማለት ጀምረዋል። አፍሪካን የመሳሰሉ ድሃ አገራት 10 በመቶ የሚሆን ዜጋቸውን እንኳን ለመከተብ አቅም አንሷቸው ለግሱን እያሉ በሚማጸኑበት ወቅት፣ ሌላው በእንቢታ አደባባይ ለአመጽ ሲወጣ ሰንብቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ክትባቱ ውጤታማ አይደለም የሚል ስሞታም ሲቀርብ ቆይቷል።

ክትባቱን ወስደው በቫይረሱ የሚያዙ አሉ የሚል በማስረጃ የተደገፈ ስሞታ መቅረብ መጀመሩ የተከታቢው ቁጥር ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቢኖርም፣ የጤና ባለሙያዎች ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማስረዳት ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር። ክትባቱ ሙሉ በሙሉ ከቫይረሱ ይከላከላል ማለት ሳይሆን፣ በበሽታው ተይዞ የመሞት ዕድልን ይቀንሳል ሲሉ ሞግተዋል። ይህ ቢሆንም ግን የክትባቱን ትችት ሊያስቀሩት አልቻሉም ነበር። ክትባቱ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅምን ይቀንሳል ተብሎ ለተሰነዘረ ቅሬታ ምላሽ፣ ሦስተኛ ዙር የመከላከል አቅምን የሚያጎለብት ክትባት ይሰጣል ተብሎ ተጀምሮ ነበር።

ከክትባት ጋር በተገናኘ የሚሠነዘሩ ቅሬታዎችም ሆኑ ምላሾቻቸው ወደ አንድ መደምደሚያ ሳይደርሱ በቅርቡ ደግሞ ሌላ ዱብዕዳ ተከስቷል። አዲሱ የኦሚክሮን ዝርያ በከፍተኛ ፍጥነት መተላለፉና ክትባቱ ለዝርያው መሥራት አለመቻሉ መነጋገሪያ ሆኗል። ቫይረሱ ዝርያውን ቀይሮ ሲመጣ መከላከል ካልተቻለ መከተቡ ጥቅም የለውም የሚሉ ቢኖሩም፣ አሁንም ቢሆን ከከፍተኛ ጉዳት ስለሚከላከል ብትከተቡ ይሻላል በሚል በየአገራቱ እየተቀሰቀሰ ይገኛል።

ክትባቱ ከአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መከላከል አይችልም የተባለው ኦሚክሮን የተሰኘው ዝርያ፣ ክትባቱ በተዘጋጀ ወቅት የማይታወቅ ስለነበር ነው ተብሏል። የሕንድ ‹ብሪሃንሙንባይ ሙኒሲፓል ኮርፖሬሽን› ያወጣውን ሪፖርት ተመርኩዞ ‹አውትሉክ› እንዳስነበበው፣ ክትባቱ መጀመሪያ ተከስቶ የነበረውን የመጀመሪያውን ዝርያ ተመርኩዞ ተዘጋጀ እንደመሆኑ አዲሱን ዝርያ የመከላከል አቅም እንደማይኖረው ነው። ኦሚክሮን ላይ ያሉት እሾህ መሰል ቅጥያዎች ላይ ያለው ፕሮቲን 32 ዓይነት ለውጥን (ሚውቴሽንን) በማስተናገዱ ከቀደመው ዝርያ ጋር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ነው የተነገረው።

የክትባት አምራች ኩባንያዎች፣ ክትባቶቹ ለመጀመሪያው ዓይነት ዝርያ የተዘጋጁ ቢሆኑም፣ በሽታ የመከላከል አቅምን በ25 ዕጥፍ ገደማ ስለሚያሳድጉ መጥቀማቸው እንደማይቀር ነው የሚናገሩት። እነሱ ይህን ቢሉም ሌሎች ከክትባት ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ተመራማሪዎች በበኩላቸው፣ የአምራቾቹ ምክንያት ትክክል አይደለም በማለት ውድቅ ያደርጉባቸዋል። እንደተመራማሪዎቹ ግኝት ከሆነ፣ አሁን ገበያ ላይ ያለ የትኛውም የክትባት ዓይነት ከኦሚክሮን ዝርያ ሙሉ በሙሉ መከላከል የሚችል አይደለም። የበሽታ መከላከል አቅምን የሚጨምር ሦስተኛ ዙር ክትባትም ቢሆን አዲሱን ዝርያ መከላከል እንደማያስችል አንዳንዶቹ ያስረዳሉ። ክትባቶቹ ኦሚክሮንን መከላከል አለመቻላቸውን በማስረጃነት የሚያቀርቡት እነዚህ ተመራማሪዎች፣ በመጀመሪያ ዙር የሚሰጡ ክትባቶች በሽታን የመከላከል አቅም ስለሚያዳክሙም ሊሆን ይችላል በማለት መላምታቸውን ያስቀምጣሉ። ይህ ቢባልም፣ ስለክትባቶች ተፈጥሮም ሆነ በጊዜ ሒደት ስለሚኖራቸው ተጽዕኖ ራሱን የቻለ ጥናት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

በርካታ ተመራማሪዎች ክትባት ለተሠራበት ዝርያ እንጂ ለአዲስ አይነት ውጤታማ እንደማይሆን ይስማማሉ። ክትባት ከአዲስ ዝርያ ከሚመጣ በሽታ መከላከል ባያስችልም፣ የተመሳሳዩን ዝርያ ጉዳት ለመቀነስ፣ እንዲሁም ተጠቂዎች በሽታው ተባብሶባቸው ሆስፒታል መግባት ግድ እንዳይሆንባቸው ለማድረግ ያግዛል ሲሉ ሐሳባቸውን ይሠነዝራሉ።

የክትባቶች የአገልግሎት ጊዜ
ክትባቶች ከተሰጡ በኋላ እስከሕይወት መጨረሻ ከተመሳሳይ የበሽታ ዝርያ እንደሚከላከሉ ይታመናል። ለፖሊዮ በተለምዶ ፀረ-ስድስት እየተባሉ በዓለም ላይ የሚሰጡ ክትባቶች ለዕድሜ ልክ ስለሚያገለግሉ ደግመው አይሰጡም። በተቃራኒው የወባና የጉንፋን ክትባትን የመሳሰሉት ደግሞ ደጋግመው መወሰድ የሚችሉ ናቸው። የኮቪድ ክትባትን በተመለከተ ግን የሚያገለግሉት ለዚህን ያህል ጊዜ ነው ሲባል እስካሁን አልተሰማም ነበር። ሰሞኑን ‹ላንሰንት ጆርናልን› ዋቢ አድርጎ ‹ፋይናንሻል ታይምስ› እንዳስነበበው፣ አስትራዜኒካ የተባለው ክትባት ተሰጥቶ ካለቀ ከሦስት ወር በኋላ አገልግሎቱ እንደሚቀንስ ነው። ክትባቱ የመከላከል አቅሙ ሦስት ወር ከሞላው በኋላ እየተዳከመ ይመጣል ያለው የጥናቱ ውጤት፣ ይህ እንዳይሆን ተከታቢዎቹ የመከላከል አቅሙን የሚያጎለብት ሌላ ክትባትን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ሕንድ ውስጥ ‹ኮቪሺልድ› በመባል የሚታወቅን አቅምን መልሶ የማሳደጊያ ክትባት በመውሰድ ከከባድ ጉዳት ራሳቸውን ማዳን ይችላሉ ተብሏል።

የ44 ሚሊዮን ሰዎችን መረጃ ከእስኮትላንድና ብራዚል አሰባስበው በማጥናት ድምዳሜ ላይ እንደደረሱ የሚናገሩት ተመራማሪዎቹ፣ አስትራዜኒካ የተሰኘውን የእንግሊዝ ክትባት የሚከተቡ ከ3 ወር ቆይታ በኋላ በክትባቱ ብቻ መተማመን እንደማይችሉ ነው። በጥናቱ የተገመገመው ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች የመጨረሻውን ከወሰዱ በኋላ ካለው ኹለት ሳምንት ውስጥ የነበራቸውን የመከላከል ብቃት ከ5 ወር በኋላ ከሚኖራቸው ጋር በማነጻጸር ነው። በዚህም መሠረት ከ5 ወር ቆይታ በኋላ ተከታቢዎቹ በቫይረሱ ተጠቅተው ሆስፒታል የመግባታቸው አዝማሚያ በአምስት ዕጥፍ እንደሚጨምር ታውቋል። ከአራት ወር በኋላ ደግሞ በሦስት ዕጥፍ ስለሚጨምር በቆየ ቁጥር የመከላከል አቅሙ እንደሚዳከም ተረጋግጧል።

የክትባቱ የአገልግሎት ወቅት በጊዜ ሒደት እንደሚቀንስ የታወቀው መጀመሪያ ለተገኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ብቻ ሳይሆን፣ ዴልታና ጋማ ለተባሉት ዝርያዎችም እንደሆነ የኹለቱን አገራት መረጃ እያነጻጸሩ ያጠኑት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይህ የጥናት ግኝት ግን የተከተቡን ካልተከተቡ የሚያነጻጽር ስላልሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ተብሏል። የተከተቡን ብቻ ለይቶ የተመለከተ ጥናት እንደመሆኑ፣ ምንም አይነት ክትባት ካልተከተቡ ያነሰ የመከላከል አቅም ኖራቸዋል ማለት እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ኹለቱን አይነት መረጃዎች አስተያይቶ ለማጥናት አስቸጋሪ በመሆኑ ግኝቱ በጥንቃቄ ታይቶ ማስተካከያ እንዲወሰድ የሚያደርግ እንጂ፣ የክትባቱን ተቀባይነት የሚያሳጣ መሆን እንደሌለበት ጠቁመዋል።

እንደዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ከሆነ፣ ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ ዝርያ የተከተቡትንም ሆነ ያልተከተቡትን ዕኩል የሚያጠቃ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በወረርሽኙ ተጠቅተው ያገገሙትንም እኩል የማጥቃት ዕድል አለው ሲል ተቋሙ አስጠንቅቋል። ከዚህ ቀደም ከተከሠቱት ዝርያዎች በፍጥነት እንደሚስፋፋ ማስረጃ ተገኝቶለታል የተባለለት ኦሚክሮንም፣ ምንም ሳይገድበው የሚሠራጭ በመሆኑ ጥንቃቄዎች ይበልጥ መጠናከር እንዳለባቸውና፣ ከበዓል ጋር በተገናኘ የታሰቡ ሕዝባዊ መርሃ-ግብሮች ሊቀሩ እንደሚገባ ተነግሯል። አዲሱ ዝርያ የመስፋፋት አቅሙ ከፍተኛ ቢሆንም፣ የጎጅነት መጠኑ ግን ዝቅተኛ ነው በሚል የሚሠራጨውን ለማረጋገጥ ጊዜው አጭር ስለሆነም መንግሥታትም ሆኑ ሕብረተሰቡ ይበልጥ እንዲጠነቀቅ ተጠይቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here