መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብነገረ ጤናኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ አደገኛነት

ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ አደገኛነት

በቻይናዋ ዉሃን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኹለት ዓመት ገደማ በፊት ተከሥቶ መላው ዓለምን ያዳረሰው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ዝርያውን እየቀየረ በተደጋጋሚ በመከሠቱ አሳሳቢነቱ እየጨመረ መምጣቱ ይሠማል። ‹ዴልታ› የሚባል በሥርጭቱም ሆነ በገዳይነቱ የባሰ የቫይረሱ ዝርያ ተገኘ ተብሎ፣ ብዙዎች ለሞት ዳርጎ እስካሁንም መሠራጨቱን አላቆመም።

በመጀመሪያ የተገኘው የኮሮና ቫይረስን ዝርያ ለመቆጣጠር ክትባት ተመርቶ ወደ መከላከሉ ቢገባም፣ እስካሁን መቆጣጠር ሳይቻል ቀርቷል። ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የጨረሰው ይህ ወረርሽኝ፣ አሁንም በርካቶችን እያጠቃና እየገደለ እንደሆነ ይታወቃል። ተመራማሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት ወረርሽኙን ለማስቆም የበኩላቸውን ርብርብ ቢያደርጉም፣ አሁን ደግሞ ኦሚክሮን የሚባል ሌላ ዝርያ ተገኝቶ እንደአዲስ የሰውን ልጅ ሥጋትና መከራ አክብዶታል።

ስለወረርሽኙ የነበረ ሥጋት እየቀነሰ ሕብረተሰቡም የሚያደርገውን ጥንቃቄ በመተው እየተዘናጋ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ ኦሚክሮን የተሰኘው አዲስ ዝርያ በቅድሚያ ደቡብ አፍሪካ መገኘቱ ተመዝግቦ ኹሉንም የዓለማችንን ክፍል እያዳረሰ ይገኛል። ባልተረጋገጠ መረጃ ከአፍሪካ ነው ቫይረሱ የተነሳው በሚል ምዕራባውያን አፍሪካን ለማግለል የተጠቀሙበትን መንገድ ብዙዎች ቢተቹትም፣ እስካሁን ለውጥ አልመጣም። ቤተ-እስራኤላዊ የእስራኤል ባለሥልጣንን ጨምሮ አፍሪካ ላይ ምዕራባውያኑ የሚፈፅሙት ተግባር ከዘረኝነት ተለይቶ እንደማይታይ በመጥቀስ አገራት ውሳኔያቸውን እንዲያሻሽሉ ቢጠየቅም ምንም መሻሻል አላመጣም።

አዲሱ ዝርያ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ጭምር ተስፋፍቶ እያለ አፍሪካውያንን ለይቶ ማገዱ ለውጥ እንዳላመጣ የሚገልጹ፣ ዝርያውንም ሆነ ዋናውን ወረርሽኝ ለመግታት የማያዋጣ መፍትሔ እንደሆነ ይናገራሉ። ብራሰልስን የመሳሰሉ የአውሮፓ አገራት መንግሥት የሚያወጣቸውን የጥንቃቄ መመሪያዎች ተቃውመው አደባባይ በመውጣት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በሚጋጩበት በዚህ ወቅት፣ አዲሱ ዝርያን ለመከላከል የሚወሰድን ዕርምጃ ጥያቄ ውስጥ እንደሚከት በርካቶች ሲናገሩ ይደመጣሉ።

አዲሱ የኮቪድ 19 ቫይረስ ዝርያን በተመለከተ የ‹አስትራዜኒካ› ክትባትን ከሌሎች ጋር በጋራ ያገኙ የእንግሊዝ ተመራማሪ የተናገሩት የብዙዎችን ትኩረት ያገኘ ነበር። ፕሮፌሰር ሳራ ጊልበርት የተመራማሪዎች ጉባኤ ላይ ተናገሩ ብለው መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ አዲሱ ኦሚክሮን የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ እስካሁን ከነበሩት ኹሉ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ነው።

እስካሁን በተደረገ ግምገማ አዲሱ ዝርያ ክትባቶችን የመቋቋም ብቃቱ ከፍተኛ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል። የዝርያው አስጊነቱ ክትባትን መቋቋም ከሚችልበት አቅሙ አኳያ ብቻ ሳይሆን፣ የመዛመትና የመግደል ኃይሉም ከሌሎቹ እስካሁን ከተገኙት ዝርያዎች የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ነው። የዝርያው ተለዋዋጭነትም፣ ምርምር ለማድረግም ሆነ የአደገኝነቱን አድማስ ተቀራራቢ በሆነ ልክ ለመገመትም አዳጋች እንዳደረገው ተናግረዋል።

እንደተመራማሪዋ ገለፃ ከሆነ፣ ግኝቱ ዓለማችንን የሚያሰጋ አዲስ ዝርያ እንደመሆኑ ሊሰጠው የሚገባ ትኩረትም ከፍተኛ መሆን እንዳለበት ነው። ዓለማችንን የሚያሰጋ ወረርሽኝ እስካሁን የተከሰተው ብቻ እንዳልሆነ የጠቆሙት እኚህ ሳይንቲስት፣ ለወደፊትም ቢሆን ከእስካሁኖቹ የባሰ ገዳይና የመዛመት ፍጥነቱ ከፍተኛ የሆነ የቫይረስ ወረርሽን ሊከሰት ይችላል ብለዋል። አይከሰትም ብሎ መቀመጥና የቅድሚያ ጥንቃቄ አለማድረግ ያስከፈለውን ዋጋ ከኮሮናው ወረርሽኝ በላይ ያሳየን የለም ያሉ ሲሆን፣ ለወደፊት የሚመጡትንም ሆነ አሁን ያሉትን ወረርሽኞች ለማጥፋትና ጉዳታቸውን ለመቀነስ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን ማጋራት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በዘርፉ ያለውን መረጃ መቀባበል ብቻ ሳይሆን፣ የቀደሙ ተመራማሪዎች የሠሯቸውን ምርምሮችንም ሆነ ለሰው ልጆች ያበረከቱዋቸውን ግኝቶች በአንድ ቋት አስቀምጦ ቀጣይ ተመራማሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች እንዲጠቀሙባቸው ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ‹ኢንዲፔንደንት› አስነብቧል።

በእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የክትባት ዘርፍ ተመራማሪ የሆኑት ሳራ ጊልበርት፣ ባለሙያዎችና ሕብረተሰቡ ከሚጠበቅባቸው ተግባር በበለጠ መንግሥታት አስቀድመው ለእንዲህ ዓይነት የወረርሽኝ አደጋዎች መዘጋጃና መጠንቀቂያ የሚሆን በጀት በየጊዜው መመደብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። አገራት ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ጊዜ ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርጋቸው ኪሳራ ውስጥ ከሚገቡ፣ አስቀድመው ራሳቸውን ቢያዘጋጁ መልካም እንደሚሆን አሁን እየተከሰተ ያለውን ወረርሽኝ በማስረጃነት በማቅረብ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል፣ የአሜሪካ መንግሥት የጤና አማካሪ የሆኑት አንቶኒ ፋውቺ ከእንግሊዟ ተመራማሪ በተቃራኒ የቆሙ የሚያስመስላቸውን ንግግር አድርገዋል። አዲሱ የኦሚክሮን ቫይረስ እንደ ዴልታው ዝርያ ገዳይ ላይሆን ይችላል የሚል መላምታቸውን ተናግረዋል። የአገሪቲን የጤና ተመራማሪዎች የአጭር ጊዜ ግምገማ መሠረት አድርገው እንደተናገሩት፣ አዲሱ ዝርያ በጣም እየተስፋፋ ቢሆንም፣ የዴልታ ዝርያን ያህል ጎጂ ወይም ገዳይ ስለመሆኑ የሚያመላክት ምንም አስረጂ ነገር እንዳልተገኘ ተናግረዋል። ሳይንቲስቶች ስለዝርያው የጉዳት መጠን ከመናገራቸው በፊት በቂ ጊዜና ምርምር እንደሚያስፈልጋቸውም አሳውቀዋል።

አዲሱ የኦሚክሮን ዝርያ በከፍተኛ ፍጥነት መዛመት መቻሉ ቢታወቅም፣ አብዛኛውን ተጠቂ ሆስፒታል እስከማስገባት የሚያደርስ አይደለም በማለት የደቡብ አፍሪካን ምሳሌ በማስቀመጥ ለማስረዳት ሞክረዋል። ይህ ግምት ግን እርግጠኛ ነው ማለት ስለማይቻል፣ እንዲሁም በጊዜ ሒደት ምን ለውጥ እንደሚያስከትል ማወቅ ስለሚያዳግት መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች ከማድረግ ሕብረተሰቡም ሆኑ መንግሥታት መዘናጋት እንደሌለባቸው ተነግሯል።

የኦሚክሮን አስጊነት ያን ያህል አይደለም በሚል አማካሪው መናገራቸውን ተከትሎ በአፍሪካ አገራት ላይ አሜሪካ የጣለችው የጉዞ ገደብ እንዲነሳ ተጠይቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ “የጉዞ አፓርታይድ” ያሉትን ይህን የአሜሪካና የምዕራባውያኑን መሠረት የሌለው ገደብ እንዲያነሱ የጠየቁበትን ምክንያት በማጤን ዕገዳው እንዲሻሻል መደረግ አለበት ተብሏል።

በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲሱ ዝርያ ተገኘ በመባሉ፣ አፍሪካውያን ትልቅ ሥጋትና ከፍተኛ ጭንቀት እንዳደረባቸው የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ተቋም ተናግሯል። አፍሪካውያን መጨነቅ ሳይሆን መጠንቀቅና ተዘጋጅቶ መጠበቅ ነው ያለባቸው ያለው ተቋሙ፣ እስካሁን ከደረሰው የባሰ ነገር ይኖረዋል ተብሎ ሕበረተሰቡን ማሸበር እንደማይገባም አሳውቋል። ‹አፍሪካን ሲዲሲ› በመባል የሚታወቀውን ይህን ተቋም የሚመሩት ጆን ኒኬንካሶንግ እንዳሉት፣ አዲሱን ዝርያ መቆጣጠር ስለሚቻል አፍሪካውያን አላስፈላጊ ከሆነ ሥጋት ሊታቀቡ ይገባል። ማስክ ማድረግን የመሳሰሉ የተለመደ መከላከያ መንገዶችን ይበልጥ በማጥበቅ ማኅበረሰቡ እንዳይዘናጋና በአስፈላጊ ክልከላዎች እንዳይሰላች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎችን ከማድረግ ባሻገር፣ እስካሁን ያልጠቀሙን አላስፈላጊ ክልከላዎችን ባለማድረግ ሕብረተሰቡ ሕይወቱ እንዳይናጋ መሠራት አለበት ተብሏል። አፍሪካ ከሕዝቦቿ 60 በመቶውን ለመከተብ ዕቅድ ይዛለች ያሉት እኚህ ኃላፊ፣ በዕቅዱ መሠረት ክትባቱን ለማዳረስ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊየን ክትባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ኦሚክሮን የተሰኘውን የኮቪድ 19 ዝርያ ያገኙ ተመራማሪ በበኩላቸው፣ ቫይረሱ በተፈጥሮው ላይ የሚያደርገው ለውጥ (ሚውቴሽን) ፍጥነት ለወደፊቱም አስጊ ሆኖ እንደሚቀጥል አመላካች ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ሲኩሊሌ ሞዮ(ዶ/ር) እንዳሉት ዝርያው የሚለወጥበት ፍጥነት ቫይረሱ በምን ያህል ፍጥነት ሊስፋፋ እንደሚችል አመላካች ነው። የተፈጥሮ ለውጥ የሚከሠተው ቀስበቀስ በጊዜ ሒደት በመሆኑ፣ የአሁኑ አዲስ ዝርያ ግን በአጭር ጊዜ መለወጥ መቻሉ በዘርፉ የሚደረገውን ምርምር አዳጋች እንዳደረገው ተመራማሪው አሳውቀዋል።

ይህ ቢሆንም ግን፣ እስከአሁን በተደረገ ምርምር አዲሱ ዝርያ ጉንፋን ከሚያስከትለው ከተለመደው ቫይረስ አሊያም ሳርስ ከተሰኘው ቫይረስ የዘር ማስተላለፊያ ቅንጣትን ሳይወስድ እንደማይቀር ተገምቷል። ከኮቪድ በተጨማሪ ሌላ ቫይረስ ሰውነቱ ውስጥ የነበረበት ሰው ላይ ተቀላቅለው አዲስ ዝርያን ሳያመነጩ እንደማይቀር ግምት የተሠነዘረ ሲሆን፣ ይህንንና ሌሎች መላምቶችን ለማረጋገጥ ጊዜ የሚፈልግ ግምገማና የምርምር ሥራ ይጠይቃል ተብሏል።

ሞዮ እና አብረዋቸው ምርምሩን ሲያደርጉ የነበሩ ባለሙያዎች አዲስ ዝርያ አገኘን ብለው ግኝቱን ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እንዲያት ባደረጉ በሰዓታት ውስጥ የደቡብ አፍሪካና የሌሎች አገራት ተመራማሪዎችም ተመሳሳይ ዝርያ እንዳገኙ ማሳወቃቸውን ይፋ አድርገዋል። በመጀመሪያ ዝርያው ያን ያህል ጎጂ ይሆናል የሚል ግምት ባይኖርም የመለዋወጥ ፍጥነቱ፣ እንዲሁም የሰውነት የመከላከል አቅሙን በቀላሉ የማለፍ ብቃቱ ሲታይ የባለሙያዎች ሥጋት መጨመሩ ተነግሯል።

- ይከተሉን -Social Media

ስለአዲሱ ዝርያ የተለያዩ አገራት ተመራማሪዎች የየራሳቸውን ምልከታ ቢያስቀምጡም፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ሳይንቲስት ኦሚክሮን የበለጠ ጎጂና ገዳይ ስለመሆኑም ሆነ ይበልጥ ስለመተላለፉ በእርግጠኝነት ለመናገር ጊዜው ገና ነው ብለዋል። ይህ ቢሆንም፣ ሕብረተሰቡ ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ ሳይዘናጋ መፈጸም እንደሚገባው ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች