መነሻ ገጽአምዶችማኅበረ ፖለቲካንጉሥ ዳዊት ያፈሰሰው ውኃ!

ንጉሥ ዳዊት ያፈሰሰው ውኃ!

ኢትዮጵያ ስለነጻነቷ ሲባል በተለያየ ዘመን ውድ የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት የተከፈለላት፣ ስለልጆቿ በደኅና መኖርም አባቶች የተሰዉላት አገር ናት። በመስዋዕትነት ተገኝቶ የተሰጠ ስጦታ በክብር ሊያዝ እንደሚገባ፣ ኢትዮጵያን የሚረከብ ትውልድም እንዲያ ያለ አደራን ይቀበላል። አሁን ያለውና ተከታዩ ትውልድም፣ አገሩ ላይ በነጻነትና በደኅና እንዲኖር ዋጋ ሲከፈልለት ከቀደመው ይልቅ በቅርቡ ዐይቷል፤ ሰምቷል። መቅደስ ቹቹ ይህን ነጥብ መነሻ በማድረግ የተከፈለልንን ዋጋ ማወቃችንን በተግባር እንግለጥ ትላለች፡፡ ብዙ የቤት ሥራም አለብን በማለት ሐሳቧን እንዲህ አጋርታለች።

ኢትዮጵያ ውሽንፍርና ማዕበል የበዛበት ባህር ላይ እንደተገኘ መርከብ በከባድ ፈተና ውስጥ የቆየችበትና አሁንም ያለችበት ወቅት ላይ ነን። በሰሜኑ ክልል የነበረውና ያለው ጦርነት እጅግ ብዙና አስከፊ ውድመቶችን አድርሷል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምጣኔ ሀብት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ተጠንቶ ሳያልቅ የተከሰተው ጦርነትና ተያያዥ ጦሱ፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ አይቀሬ ነው።

‹ኢትዮጵያን ማፍረስ አጀንዳዬ ነው› ያለው የአጥፊዎች ስብስብ የሆነ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ የለየው የ‹ህወሓት› ቡድን፣ በተለያዩ የአማራና አፋር ክልል ከተሞች አሳፋሪና አሳዛኝ ውድመቶችን አድርሷል። እነዚህ ውድመቶች ከማይመለስ የሰው ልጅ ሕይወት ጀምሮ፣ ዕርምጃዎችን ወደኋላ ሊመልሱ የሚችሉ የሀብትና ንብረት ጥፋቶችን የሚያካትቱ ናቸው።

ነገሩ ዕቃ ሲጠፋብን ወይስ ስንሰረቅ፣ አልያም ብርጭቆ ሲሰበር ‹ጦሳችሁን!› እንደሚባለው አይደለም። በእርግጥ የኢትዮጵያ መከራ ተሸክመው፣ የኹላችንን ጦስ ይዘው፣ አደራን ተቀብለው ሕይወታቸውን አስይዘው እየተዋጉ ያሉ፣ ተዋግተው የተሰዉ፣ እንዲሁም ለአገር የመጣ ዱላ አርፎባቸው ሕይወታቸውን የተነጠቁ ንጹኃን፣ ወዳጅ ዘመዳቸውን የተለዩ ዜጎች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው። ኹላችንስ ልባችን በሐዘን፣ አእምሯችንም በደረሰው ጥፋት ኹሉ ሳይታመም መች ቀረ!?
የኔ ጥያቄ ወዲህ ነው፤ የተከፈለልንንና የሚከፈልልንን ዋጋ እያወቅንና እየተረዳን ነው ወይ? የሚለው ነው። ያም ብቻ አይደለም፤ ካወቅን ደግሞ ቀጥሎ ምን ልናደርግ አስበናል?

ስለንጉሥ ዳዊት ከሚነገሩና በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚገኙ ታሪኮች መካከል አንዱን ላንሳላችሁ። እንዲህ ነው፤ ንጉሥ ዳዊት ጠላቶቹ ተነስተውበት በነበረበት ከባድና አስቸጋሪ ወቅት ነው። ታድያ በዛ ኹኔታ በአንዱ ቀን በምሽጉ ውስጥ ሳለ ‹ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ?› ብሎ ተመኘ። ወደ ቤተልሔም እንደልብ እንዳይሄድና የተመኘውን እንዳያገኝ ደግሞ በሰዓቱ በጠላቶቹ ዙሪያው ተከብቦ ነበር።

ነገር ግን፣ ዳዊት የተናገረውን የሰሙ ሰዎች ዝም አላሉም። ተነስተው፣ የጠላትን ሠራዊት በውጊያ አልፈው ከቤተልሔም የምንጭ ውኃ ቀድተው ዳዊት ሊጠጣ የተመኘውን አመጡለት፤ አቀረቡለት።

ዳዊት ታድያ ያንን ውኃ አልጠጣውም፤ እንደውም አፈሰሰው። ‹በነፍሳቸው ደፍረው የሔዱ ሰዎች ደም አይደለምን?› አለ። ይህን በማድረግ ዳዊት የሰዎቹን መስዋዕትነት እንደሚያከብርና እርሱ ውኃ ይጠጣ ዘንድ የተከፈለለትን ዋጋ እንደሚያውቅ አሳየ። እንደውም ይህ እንደ ጽድቅ የተቆጠረለት ሥራው ሆነ። እንግዲህስ ኢትዮጵያዊያን የሚከፈልልን ዋጋ ትልቅ መሆኑን ማወቃችንን በተግባር የምንገልጥበት መንገድ እንዴት የላቀ ሊሆን ይገባ?

መቆም እንኳ አይቻልም!
ለአገር መስዋዕትነትን ለሚከፍሉ፣ ለራሳቸው አይደለ ግን ልጆቻቸው በነጻነትና በደኅና ይኖሩ ዘንድ፣ አንድ ሕይወታቸውን ለሚገብሩ ሽልማታቸው ምንድን ነው? የተቀረጸ ሐውልት? በሥማቸው የተሰየመ አደባባይና ጎዳና? በሥማቸው የሚገጠም ግጥምና የሚሠራ ሙዚቃ? በእርግጥ ይህ ቢሆንስ ብቻውን ችሎ ዋጋቸውን የሚመልስ ነው? በፍጹም!

ንጉሥ ዳዊት የተከፈለለትን ዋጋ ዐይቶ፣ ስሜቱን ነክቶት የወሰነው ውሳኔ ውኃውን ማፍሰስ ነበር። የኢትዮጵያውያን ውሳኔስ ምን ሊሆን ይገባል?

እንደሚታወቀው በዚህ አስከፊ ጦርነት እጅግ ብዙ ጥፋቶች ደርሰዋል። የወደሙ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ማዕከላት፣ ማምረቻዎችና የተለያዩ ተቋማት…ብዙ ናቸው። የአገርን ጦስ ይዘው ያለፉ ሕይወቶችም ብዙ ናቸው። ብዙ ቤተሰብ ተበትኗል፤ ብዙ ልጅ ወላጅ አልባ ሆኗል፤ የተጠፋፋው ቤተሰብ ዕልፍ ነው፤ የማኅበረሰብ ሕይወት ተናግቷል…ብዙ ብዙ።

እነዚህን ኹሉ ልብ ብሎ ለተመለከተ ከአሁንና ከዛሬ፣ ከትላንትናም ይልቅ ነገ አስፈሪ ሆኖ ሳይታየው አይቀርም። እርግጥም እንዲያ ነው! ይህ ኹሉ ማለፉ አይቀርምና ካለፈ በኋላ የሚጠብቀን የቤት ሥራ ቀላል እንደማይሆን ማወቅ ያስፈልጋል። የፈረሰውን ዳግም መገንባት፤ የወደቀውን ማንሳት፤ የተበተነውን መሰብሰብ፤ የተቋረጠውን መቀጠል ከማናውቃቸውና ጊዜ ከሚያመጣቸው ተጨማሪ ፈተናዎች ጋር ቀጣይ የቤት ሥራዎቻችን ናቸው። እነዚህ ኹሉ ታዲያ ገና የጦርነቱ ፍጻሜ ባላየንበት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም በእርግጠኛነት የምናውቃቸው የቤት ሥራዎች ናቸው።

ሕይወታቸውን ገብረው ኢትዮጵያን ለማዳን የሚደክሙትን የምናመሰግነው ጊዜያችንን፣ ዕውቀትና ጉልበታችንን በመስጠት ነው። ልክ ንጉሥ ዳዊት ያመጡለትን ውኃ እንዳፈሰሰ ሁሉ፣ ለአገራቸው ሰማዕትነትን የተቀበሉ ብርቱዎች ሕይወታቸውን ሰጥተው ያተረፉልንን ጊዜና አገር በመቀናጣት ሳይሆን ተግቶ በመሥራት በተግባር ዋጋቸውን ልንከፍል ያሻል።

አሁን ወደኋላ መራመጃ ጊዜ የለም፤ ለመቆም እንኳ ፋታ ሊኖር አይገባም። የሆነብንን በማሰብና በማዘን የሚባክንም አፍታ ሊገኝ አያሻም። እንደወትሯችን የአንድ ሰሞን ሆሆታ ሆኖ በቶሎ የምንዘነጋው፣ እንደ አዲስ ሙዚቃ አንድ ሰሞን ዘፍነን ሌላ ሙዚቃ ስንሰማ የምንቀይረው አይደለም። የአገራችንን የመከራ ጦስ የወሰዱ፣ በእርሷ ላይ የተሰነዘረውን ዱላ አጎንብሰው የተቀበሉ ወገኖቻችን ዕዳ በኹላችን፣ በየአንዳንዳችን ላይ ነው።

ዘፈን ማሞቂያ እንዳይሆን!
የግጥምና ዜማ ሥራዎችን የሚሠራው ድምጻዊ እሱባለው ይታየው የሺ ‹ዘፈን ማሞቂያ አይደለም!› እያለ ስለአገር ያቀረበው ሙዚቃ አለ። ይህ ሙዚቃ ስለአገር የተሠሩ የሙዚቃ ሥራዎች ኹሉ መቋጠሪያ የሆነ ወይም መሆን እንዳለበት ይሰማኛል። ወደነገሬ ከመግባቴ በፊት ጥቂት እንድል ፍቀዱልኝ፤
‹ዘፈን ማሞቂያ አይደለም…እወድሻለሁ ማለቴ፣
ሳልጠራሽ ውዬ አላድርም…በቀን ውስጥ ሦስት አራቴ
ኧረ እኔስ እወድሻለሁ…ኧረ እኔስ እወድሻለሁ
ንግግሬ ላይ እንኳ…መች ለይቼስ እኔ አውቃለሁ!› ብሎ ይጀምራል።

በዚህ ሙዚቃ ቪድዮ መግቢያ ላይ አዝማሪ ሆኖ የሚጫወተው ገጸ ሰብዕ ከአንድ መለስተኛ መጠጥ ቤት ሆኖ ግጥም እየተቀበለ በማስንቆው እየተጫወተ ታዳሚውን ያጫውታል፤
‹አገሩ ሸውከኛ…ሰዉ ነገረኛ…ዳኛው ነገር ሰሚ
እኛስ እንሄዳለን ይብላኝ ለከራሚ!› ይላል አንዱ ጠጪ፣ አዝማሪውን ተቀበል ይለዋል። አዝማሪው ‹‹እኛስ እንሄዳለን…›› ብሎ መጨረስ ይሳነዋል።

በሥፍራው ታዳሚው ጥቂት ነው። አዝማሪው በዛ ቦታ ተቀበል የተባለውን ስንኝ ቢቀበልም ባይቀበልም ብዙም ለውጥ ላይመጣ ይችላል። ‹ለእኛ ታምኖ አልቀበልም ብሏልና የበለጠው ሹመት ይሰጠው!› ብሎ የሚመሰክርለት የለም። ግን አዝማሪው መምረጥ ያለበትን ያውቅ ነበር። አልቀበልም ብሎ ከሥራ ገበታው ይፈናቀላል። ይሄኔ ነው እሱባለው ‹ዘፈን ማሞቂያ አይደለም…› ብሎ ሙዚቃውን የሚቀጥለው።

- ይከተሉን -Social Media

ይህ ሙዚቃ በተከፈተና የተሠራለትን ቪድዮ በተመለከትኩኝ ቁጥር የዚህ ገጸ ሰብዕ ነገር ይደንቀኛል። ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ብዙ ታዳሚና ሰሚ ሊኖር አያስፈልግም ነው ነገሩ። ቅንጣት ቢመስል እንኳ እያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ነገር ዋጋ እንዳለው ማወቅም ማመንም ተገቢ ነው። የምንጠቅም እያስመሰለን እንኳ ቢሆን ትክክለኛውን ነገር ማድረግ!

የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚሠራው ሰዓቱን ቢያከብር ቀላል ነገር ያደረገ ይመስላል አይደለ? ግን ትልቅ ዋጋ አለው። የመንግሥት ሠራተኛ ባለጎዳዮችን በአግባብ ቢያስተናግድ፣ ነጋዴ ለደንበኞቹ ቢታመን፣ መምህር ለተማሪዎቹ ቢቆረቆር፣ ሐኪም ለሕሙማኑ ቢሳሳ፣ ትራፊክ ፖሊስ በአግባብ ሕግ ቢያስከብር፣ ዳኛ በእውነት ቢመዝን፣ ተራ አስከባሪ ተራውን በአግባብ ቢያቀናጅ፤ ከሰዓትና ጊዜ ጀምሮ ኹሉም እያንዳንዱ ለተሰየመበት ታማኝ ሆኖ ቢገኝ፤ ይህ ለአገር ትልቅ ዋጋ አለው። አልያ በአፍ አገሬን እወዳለሁ ብቻ ማለቱ ዘፈን ማሞቂያ ከመሆን የዘለለ አይሆንም።

እንደ ዳዊት የምናፈስሰው ውኃ ባይኖርም፣ እንደየድርሻችን ግን ስለተከፈለልን መስዋዕት ዋጋውን በተግባር በሥራ ልንመልስ ተገቢ ነው። አሁን ላይ የመከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች፣ እንዲሁም ፋኖ በጦር ግንባር ተገኝተው ሕይወታቸውን ሰጥተው እየተዋጉ ይገኛሉ። ከዛ በተጓዳኝ በርካቶች ድጋፎችን በማድረግ፣ ደም በመለገስ፣ ለዘማቾች ስንቅ በማቀበል፣ በመንፈስ በማበርታት፣ በድምሩ በየመስኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአቅምን በማድረግ ላይ ተጠምደዋል።

ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው፣ እያንዳንዷ ጠብታ ድርሻ ዋጋ አላትና የሚናቅ ሚና አይኖርም። ግን ይህም የአንድ ሰሞን እንዳይሆን አደራ በየልባችን ብናኖር መልካም ነው። ተጨማሪ የምንሰጠው ባይኖር እንኳ ለያዘነው እንታመን፤ ባንችል እንኳ ቢያንስ አንስረቅ። በመዋጮ፣ በልገሳ፣ በድጋፍና በመሳሰለው የሰጠነውን ከአገራችን ኪስ መልሰን አንንጠቅ።

አሁንም ጦርነቱ ገና አላለቀም። ገና የሚጠብቀን የቤት ሥራ ተሰልቶ አልተለየም። ግን አሁን በእርግጥ የምናውቀው እውነት አለ። ብዙዎች የምንወዳትን ኢትዮጵያ ሊያቆዩልን፣ የምንመኛትን ነጻነት ሊያስጎነጩን ውጊያ ላይ ናቸው። ያንን እውን እንደሚያደርጉት ጥርጥር የለም። የእኛ መልስ ከወዲሁ ሊዘጋጅ ይገባል። ይህም በተግባር፣ በሥራ የሚገለጽ ነው። አሁንና ከዚህ በኋላ ለመቆም እንኳ ፋታ ሳይኖር ወደፊትና ወደፊት ብቻ!


ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች