የአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የኦሚክሮን አሳሳቢነት

0
601

መነሻውን ቻይና አድርጎ ዓለማችንን ያዳረሰው ኮሮና ቫይረስ እየተስፋፋ በቆየባቸው ላለፉት ኹለት ዓመታት ዓይነቱን እየቀያየረ ለሐኪሞችም ሆነ ለተመራማሪዎች አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ኮቪድ 19 በወረርሽኝ መልክ መከሠቱ ከተረጋገጠ ወዲህ፣ ከኹለት ጊዜ በላይ ዝርያውን ቀይሮም በከፍተኛ ፍጥነት ሲሠራጭ ተገኝቷል።

ለበሽታው ሕክምና ለማግኘት ተመራማሪዎች በሚጣደፉበት በዚህ ጊዜ፣ ዴልታ የሚባል ሌላ አደገኛ ዝርያ ተገኘ ተብሎ ዓለማችን ሕዝብ በድጋሚ ሽብር ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ ነበር። እስካሁን የተገኙት ዝርያዎች ምንነት፣ እንዲሁም በስንት ልፋት የተዘጋጁትን ክትባቶች ስለመቋቋም አለመቋቋማቸው በእርግጠኝነት ሳይታወቅ ሰሞኑን ደግሞ ሌላ አዲስ ዝርያ ተገኘ ተብሎ ጭንቀት ውስጥ ተገብቷል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተገኘ ተብሎ ነበረው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ፣ ኦሚክሮን የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ አገር ውስጥ በመገኘቱ ከፍተኛ የሥርጭት መጠን እንደሚኖረው ተገምቷል። የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት፣ ተመራማሪዎቻችን ባደረጉት ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ አገራችን ተገኘ እንጂ፣ መነሻው እዚህ አፍሪካ አህጉር ስለመሆኑ ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም ብለዋል። ቆየት ብሎ በወጣ መረጃ አዲሱ ዝርያ ቀድሞ ኔዘርላንድ ውስጥ እንደተከሰተ ተገልጿል።

አዲሱ ቫይረስ በእርግጠኝነት ከየት እንደተነሳ ባይረጋገጥም መጀመሪያ ተገኘ የተባለው አፍሪካ ውስጥ በመሆኑ፣ የተለያዩ ምዕራባውያንና የምሥራቅ አገሮች በራቸውን ለአፍሪካ ዝግ ማድረግ ጀምረዋል። በተለይ ከደቡባዊ አፍሪካ አገራት የሚነሱ በረራዎችን እንደማያስተናግዱ የተለያዩ አገራት በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ሰሞን አሳውቀዋል። ይህን ድርጊታቸውን የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንትን ጨምሮ በርካታ አካባቢው አገራ ባለሥልጣናት ተችተውታል። ክልከላውንና እገዳውን ያደረጉት አገራት ውሳኔያቸውን ይፋ ማድረግ የጀመሩት በቂ ምክንያት እንዳላቸው በመናገር ነው። ለሦስተኛ ዙር ወረርሽኙ ከተከሰተ ከባድ ይሆናል በሚል ማስጠንቀቂያዎችንና ክልከላዎችንም ያራዘሙ ብዙ አገራት ናቸው።

ከናይጄሪያ ካናዳ የገቡ ኹለት መንገደኞች ላይ አዲሱ የኦሚክሮን ዝርያ በመገኘቱም ቀድሞ ከተገመተው በይበልጥ ሳይታወቅበት ዝርያው ተስፋፍቶ ይሆናል በሚል ሥጋቱ ጨምሯል። ዝርያው ከተገኘባቸው አገራት የሚገቡ መንገደኞችን ካለማስተናገድ ጀምሮ፣ በመለያ ጣቢያ እንዲቆዩ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ መንገዶችን አገራት በፍጥነት መጠቀም መጀመራቸው እየተነገረ ይገኛል።

ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መነሻው የትም ይሁን የት ጥንቃቄ ያስፈልጋል በሚል ብዙዎች ማስጠንቀቂያቸውን እያሰሙ ይገኛል። ክትባትን መቋቋም ስለመቻሉ ምንም የታወቀ ነገር ስለሌለ፣ ከመረበሽ ይልቅ ጥንቃቄያቸውን አጠናክረው ውጤቱን እንዲጠብቁ ባለሙያዎች እየመከሩ ይገኛሉ።

ስለአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ከሰጡት መካከል የዓለም ጤና ድርጅት ይገኝበታል። ተቋሙ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የአዲሱ ዝርያ የመሠራጨት መጠንም ሆነ ክትባትን የመቋቋም ብቃቱ ምን ያህል እንደሆነ ገና አልታወቀም። ተቋሙ ይህን ቢልም ተመራማሪዎች ግን ክትባትን ወስደው በጨረሱ ሰዎች መካከልም የመተላለፍ ብቃት አለው ማለታቸውን ‹ቢቢሲ› ይፋ አድርጎ ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት የሥርጭት መጠኑ ገና አልታወቀም ማለቱ የዝርያው አሳሳቢነትን ሳይሆን፣ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነና የሥርጭት ፍጥነቱም ሆነ ክትባት የመቋቋም አቅሙ በምርምር መረጋገጥ አለበት ማለቱ ነው። ቢያንስ በከፍተኛ ፍጥነት ስለመሠራጨቱ ከተረጋገጠው ዴልታ ከተሠኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ምን ያህል እንደሚለይ መታወቅ አለበት ሲል ድርጅቱ መናገሩን ‹ዘ ኢኮኖሚክስ› አሳውቋል።

የአዲሱ የኦሚክሮን ዝርያ የመሥፋፋት ደረጃው ብቻ ሳይሆን ያልታወቀው፣ ቫይረሱ ያለባቸውና በበሽታው የተያዙ ሰዎች ምን ዓይነት ምልክት እንደሚያሳዩም ገና አልተረጋገጠም። ዝርያው የተገኘበት ጊዜ አጭር እንደመሆኑ የሚያስከትለው ተጽዕኖም ሆነ ከሌሎች ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥናት ቢያንስ ሳምንታት ሊወስድ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል።

ስለዝርያው የሚደረጉ ምርምሮች መጀመሪያ በተገኘበት ደቡብ አፍሪካ ጨምሮ፣ በተለያዩ አገራት እየተካሄደ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ከሌሎቹ ዝርያዎች የሚለየው ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተገልጿል። በአጭር ጊዜ የተለያዩ አገራት በመገኘቱ ሥርጭቱ ከፍተኛ ነው የሚሆነው በሚል አገራት የሚያደርጉት ጥንቃቄ ተገቢ ቢሆንም፣ ማወቁና መከላከያ መንገዱንም ማስተካከል ሊያስፈልግ ስለሚችል የምርመራ ርብርቡ ተገቢ ነው ተብሏል።

ዝርያው በምን ያህል ፍጥነት እንደሚሠራጭ ባይረጋገጥም፣ ቫይረሱ በተገኘበት ደቡብ አፍሪካና ሌሎች አገራት በኮቪድ እየተያዙ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡ የአዲሱ ዝርያ አስተዋጽዖ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ ተሰግቷል። ይህ ቢሆንም ግን ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ከመጨመሩ ጋር የአዲሱ ዝርያ አስተዋጽዖ ምን ያህል ነው የሚለውም በጥናት መረጋገጥ ያለበት እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አሳውቋል።

አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ እንደዴልታ አሳሳቢ ሊሆን ስለሚችል ወይም የባሰ ተላላፊ ሆኖ ዓለማችንን ሊያስቸግር ስለሚችል ዝርዝሩ እስኪታወቅ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄውን እንዲያጠናክር ተመክሯል። የአዲሱንም ሆነ የነባሩን ዝርያ መስፋፋት ለመገደብ መከላከያ መንገዶችን መጠቀም ጥያቄ ውስጥ የማይገባ አማራጭ እንደሆነ ተነግሯል። በግል ከሚደረጉ ጥንቃቄዎች ባሻገር፣ ክትባትን መጠቀም ለነገ የማይባል አስተዋጽዖ ይኖረዋል ተብሏል። ክትባት ላይ የሚነዙ የተለያዩ አሉባልታዎች ለተከታቢዎች ቁጥር መቀነስ አስተዋጽዖ በማድረጉ አዲሱ ዝርያም እንዲስፋፋ ሚናው ከፍ ያለ መሆኑ ተነግሯል።

ክትባቱን የወሰዱ ግለሰቦች ላይ አዲሱ ዝርያ ተገኝቷል በሚል መከላከያ መንገዱን ይቋቋማል ቢባልም፣ ክትባቱን መውሰድ የበሽታውን የገዳይነት መጠን ስለሚቀንሰው መከተቡ አስፈላጊ እንደሆነ በባለሙያዎች ይታመናል። ካለመከተብ ይልቅ መከተቡ ስለሚጠቅም አሁንም ሕብረተሰቡ በቶሎ እንዲከተብ የመከረው ይህ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋም፣ ክትባቱን ለመስጠት የተራዘመ ጊዜ መውሰዱ ለአዲሱ ቫይረስ መሠራጨት በከፍተኛ መጠን አስተዋጽዖ እንዳደረገ ይገምታል።

አፍሪካና ኦሚክሮን
አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኘ ተብሎ የተነገረው አፍሪካ ውስጥ እንደመሆኑ የዝርያውን ሥርጭት ለመቆጣጠር የሚወሰደውም ዕርምጃ አህጉሪቱን እንዳይጎዳ ሥጋት ፈጥሯል። የበረራ ክልከላን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦች ከአፍሪካ የሚረከቡ አገራት ክልከላቸውን ካጠበቁ አፍሪካውያን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተጠቁሟል። መጠንቀቁ ተገቢ ቢሆንም፣ ሳይንሳዊ ባልሆነ መንገድ ከፍርሃት በመነጨ መንገድ የሚደረግ ጅምላ ክልከላም ሆነ እገዳ በኢኮኖሚውም ሆነ በሌላውም መስክ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተነግሯል።

አፍሪካ ሥርጭቱን ለመቆጣጠር በራሷ የምትወስደው የመከላከል ዕርምጃ እንዳለ ሆኖ፣ ዜጎቿ ክትባትን የመሳሰሉ የመከላከያ መንገዶችን በሚገባ መጠቀም እንዳለባቸው ባለሥልጣኖቿ ሳይቀሩ እያሳሰቡ ይገኛሉ። ክትባት የተከተበው ሕዝብ ቁጥር ከሌላው ክፍለ ዓለም በጣም ዝቅተኛው የሆነባት አፍሪካ፣ አብዛኛውን ክትባት በልገሣ እንደምታገኝ ይታወቃል።

ስለክተባቱ አመጣጥና አወሳሰድ ሕዳር 20 መረጃ ይፋ ያደረገው አፍሪካ ኅብረት፣ ክትባት ለጋሾችም ሊወስዱ የሚገባቸውን ዕርምጃ እንዲሁም የአፍሪካ መንግሥታት ሊያስቀምጡ የሚያስፈልጋቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል። እስከአሁን ከተከተበው አምስት በመቶ የማይሞላ አፍሪካዊ ቁጥሩን በማሳደግ 70 በመቶውን ለመከተብ ዕቅድ መያዙን ያሳወቀው ኅብረቱ፣ ከሌላው አህጉር ያነሰ ቢሆንም ክትባቱን ማዳረሱ አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝቧል።

እስካሁን አፍሪካውያን ከሚያገኙት ክትባት አብዛኛው በልገሳ የተገኘ እንደሆነ የጠቀሰው ተቋሙ፣ የልገሳው መንገድና ጊዜው ተገቢ እንዳልነበር በማስረዳት መስተካከል አለበት ያለውን አስቀምጧል። የአገልግሎት ጊዜያቸው አጭር የሆነ ክትባት ዓይነቶችን አለመቀበል እንዳማራጭ የቀረበ ሲሆን፣ አገራቱ በኹለትዮሽ ሥምምነት ይህን ጠቅሰው እስካልተስማሙ ድረስ ከ 10 ሳምንት ጊዜ ያነሰ ወቅት ያላቸው ክትባቶች አፍሪካ እንዳይገቡ ብሏል። አፍሪካ ካለባት የጤና ዘርፍ ችግርና የአቅም ውሱንነት አኳያ አጭር ጊዜ የቀራቸውን ተረክቦ ለማዳረስ መሯሯጡ አያዋጣም ተብሏል።

በዕርዳታ የሚመጡ ክትባቶችም ስሪንጀን የመሳሰሉ አስፈላጊ የመከተቢያ ቁሳቁሶች የተሟሉላቸው ባለመሆኑ አፍሪካውያንን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገ ነው ተብሏል። ያለዝግጅት በአጭር ጊዜ አሳውቀው ዕርዳታውን የሚልኩም ለአገራቱ ራስ ምታት እየሆኑ ነው ያለው ኅብረቱ፣ ቢያንስ ከሦስትና አራት ሳምንት ቀደም ብለው ዓይነቱንና ብዛቱን በማሳወቅ የሚረከበው አገር ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ የአፍሪካ ኅብረት ጥሪ ያደረገበት “የምክረ ሐሳብ ውሳኔ”፣ የክትባት ሥርጭቱ ፍትሃዊ፣ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ እንዲሆን ያደርጋል ተብሏል። አገራት የተናጥል ሥምምነት ከማድረግና ከመቸገር ይልቅ፣ በጋራ ችግራቸውንም ሆነ ፍላጎታቸውን የሚያሰሙበት መድረክ ቢጠቀሙ እንደሚጠቀሙ ተነግሯል። ለዚህ ለኮቪድ ቁጥጥር ዓላማ ተብለው የተቋቋሙትን COVAX እና AVAT የተሰኙትን ድርጅቶች በመጠቀም አገራት ግዢንም ሆነ ልገሳን እንዲያገኙ ተመክሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here