መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበአርሲ ዞን ጥቅማጥቅም ለማግኘት የሸኔ አባል ነኝ ብሎ እጅ መስጠት የተለመደ ተግባር...

በአርሲ ዞን ጥቅማጥቅም ለማግኘት የሸኔ አባል ነኝ ብሎ እጅ መስጠት የተለመደ ተግባር እየሆነ መምጣቱ ተነገረ

በኦሮሚያ ክልል የአርሲ ዞን ወጣቶች የኦነግ ሸኔ አባል ሳይሆኑ እንደሆኑ በመግለጽ፣ የክልሉን መንግሥት በማጭበርበር ወደ ካምፕ በመግባት ላይ እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ጠቆሙ።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት ከሆነ፣ ከክልሉ መንግሥት በሚቸራቸው የተለያየ ጥቅማጥቅም የተነሳ፣ በአርሲ ዞን ዙሪያ የሚኖሩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ራሳቸውን የኦነግ ሸኔ አባል በማስመሰል ለክልሉ መንግሥት እጅ እየሰጡ ይገኛሉ ተብሏል።

ግለሰቦቹ ለመንግሥት እጅ ይስጡ እንጂ፣ በአካባቢው በነጻነት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እጅ በመስጠታቸው ጥቅማጥቅም ከክልሉ መንግሥት ስለሚያገኙ በሊስትሮ እና በተለያየ የንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጭምር፣ “ኦነግ ሸኔ ነን” እያሉ በመመዝገብ ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።

የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ ሙሳ ሴሪ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች ባለማወቅ ኦነግ ሸኔን የተቀላቀሉ የክልሉ ወጣቶችን እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረባቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው እንደተናገሩት በተደጋጋሚ ጥሪ የሚደረገው፣ የኦነግ ሸኔ ቡድኖች ከጥፋታቸው እንዲመለሱ፣ የአካባቢው ወጣቶች ሸኔን እንዳይቀላቀሉ፣ መረጃ በመስጠት እንዲሁም የቁሳቁስ (ሎጂስቲክ) ዕርዳታ በማድረግ ሸኔን እንዳይተባበሩ ለማድረግም ጭምር ነው።
ኃላፊው አክለውም፣ የሸኔ አባላት በአርሲ በሦስት ዞኖች መካከል የሚገኝ ረጅም ርቀት ያለው ጫካ ውስጥ እንዳሉ እና በርካታ ዘግናኝ ጥፋት እየፈጸሙ እንደሚገኝም አሳውቀዋል።

እንደ ሙሳ ገለጻ፣ ከኅዳር 19 እስከ 21/2014 ባሉት ቀናት ብቻ 15 ወጣቶች ጥፋታቸውን አምነው ተመልሰዋል ብለዋል። በቀጣይም ብዙዎች ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የአባ ገዳዎችን እና የሀደ ሲንቄዎችን ጥሪ ተከትሎ ከ 200 በላይ የኦነግ ሸኔ አባላት በሕግ ጥላ ሥር ይገኛሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ወጣቶች የክልሉን መንግሥት በማሳሳት የኦነግ ሸኔ አባል ነን በማለት እያጭበረበሩ ነው የተባለውን ጉዳይ ለማረጋገጥ፣ ከቀበሌ ወይም ሲኖሩበት ከነበሩበት አካባቢ ላለፉት 6 ወራት የት እንደቆዩ እንደሚጣራ ጠቁመዋል።

እጅ የሰጡት አባላትም፣ በሕግ ጥላ ሥር እንዲቆዩ በማድረግ የተለያዩ ሥልጠናዎች እንዲወስዱ ይደረጋል ያሉት አስተዳዳሪው፣ ውጤታማነታቸው ሲረጋገጥ ብቻ በነጻነት የሚፈልጉትን ሥራ ሠርተው እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

ጥቅማጥቅም ለማግኘት ወጣቶች እራሳቸውን የሸኔ አባል አድርገው እያቀረቡ ነው ስለተባለው ጉዳይ፣ “ጥቅማ ጥቅም ያገኛሉ የሚለው፣ የበሬ ወለደ እና ፍጹም ከእውነት የራቀ ነው” በማለት አስተዳዳሪው ጉዳዩን አስተባብለዋል። አክለውም፣ ከዞኑ ዕውቅና ውጪ እንደዚህ ዓይነት ተግባር እንዲፈጸም የሚያደርጉ ኃላፊዎች ካሉ፣ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎባቸው ለሕግ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

በኅዳር 19/2014 ለአምስተኛ ጊዜ በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት፣ በአርሲ ከአምስት ዞኖች የተውጣጡ አባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች፣ “ኦሮሞ ሆነህ ከአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ቡድኖች ጋር ጥምረት የፈጠርክ ተመለስ” በሚል ወጣቶቹን እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።
ጥሪው፣ “በስህተት ወይም ባለማወቅ አገር የማፍረሱ ተግባር ላይ የተሠማራችሁ በሠላም ወደ እኛ ተመለሱ” የሚል ነው ብለዋል አስተዳዳሪው። በኦሮሞ ባህል ይህ ጥሪ ሲደረግ፣ ከቡድኖቹ ጋር ግንኙነት ያለው፣ የቡድኑን ዓላማ አስፈጻሚ የሆነና አባል ሆኖ የሚሠራ ሰው፣ ጥሪው በተደረገ በሰባት ቀን ውስጥ በአካባቢው ወደሚገኙ አባ ገዳዎች በመሄድ ጥሪውን መቀበሉን ማሳወቅ አለበት።

ነገር ግን፣ በአካባቢው ባህል መሠረት የተደረገውን ጥሪ ሳይቀበል ከአሸባሪዎቹ ቡድኖች ጋር ግንኙነቱን የቀጠለ ግለሰብና ቡድን፣ በአባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች በጠላትነት ይፈረጃል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች