መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን ትምህርት ቢሮ ባደረገው ሽግሽግ ላይ ቅሬታ አቀረቡ

በአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን ትምህርት ቢሮ ባደረገው ሽግሽግ ላይ ቅሬታ አቀረቡ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከአንዱ ወደ ሌላኛው ክፍለ ከተማ ባደረገው የመምህራን ሽግሽግ ላይ ቅሬታ እንዳደረባቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ትምህርት ቢሮው ባደረገው ሽግሽግ ቅሬታ አለን የሚሉት መምህራኑ፣ እስከ ዛሬ ከአንድ ትምህርት ቤት ወደ ሌላኛው ትምህርት ቤት ዝውውር ሲያደርጉ በፍላጎታቸው መሠረት አመልክተውና ተገቢውን ዝግጅት አድርገው ይፈጸም እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ግን እየሆነ ያለው በተቃራኒው እንደሆነ ነው ለአዲስ ማለዳ አሰተያየታቸውን የሰጡት።

ሽግሽግ እንደሚደረግ የሰማነው በትዕዛዝ መልኩ፣ ለዛውም በአንድ የስልክ ጥሪ አማካይነት ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ አንድን ትምህርት ቤት ለቆ ወደ ሌላው ለመሄድ የሚያስፈልጋቸውን ዝግጀት እንዳላደረጉና ሽግሽጉም ፍላጎታቸውን ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በ2014 የትምህርት ዘመን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከአንዱ ትምህርት ቤት ወደ ሌላኛው ክፍለ ከተማ ትምህርት ቤት ያደረገው የመምህራን ሽግሽግ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተቃራኒ ነው የሚሉት መምህራኑ፣ ተግባሩ የመምህራንን ፍላጎት መሠረት ያላደረገ ከመሆኑም በላይ በቅድሚያ ምክክር ያልተደረገበት ነው ሲሉነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

መምህራኑ ከሽግሽጉ አስቀድሞ ምክክር ማድረግ ተገቢ እንደነበርና ይህም አለመሆኑ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፣ ሽግሽጉም የመምህራንን የግል ሕይወት እና ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ አያይዘውም ከአንደኛው ወደ ሌላኛው ትምህርት ቤት መምህራኑ ሽግሽግ ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት እንዳልገባቸውና ሒደቱም ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ነው ለአዲስ ማለዳ ያብራሩት።

አዲስ ማለዳ የቅሬታውን ዝርዝር ምላሽ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ያቀናች ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የመምህራን ልማት ዳይሬክተር ተወካይ የሆኑት ብዙነህ ዘለቀ ጉዳዩን በተመለከተ በሚከተለው መልኩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ብዙነህ በቀለ እንደሚሉት ከሆነ፣ የመምህራን ሽግሽጉ የተደረገው በትምህርት ቢሮው መመሪያ መሠረት ሲሆን፣ ይኸውም በየትምህርት ቤቱ የሚገኙ ርዕሳነ መምህራን በሚያደርጉት ኦዲት መሠረት አንድ መምህር በቀን ማስተማር ከሚገባው ክፍለ ጊዜ ብዛት በታች ይዞ ከተገኘ አዲስ ወደሚከፈቱ ትምህርት ቤቶች እንዲሸጋሸግ ስለሚያዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሽግሽጉን በመመሪያው መሠረት ነው የተፈጸመ ነው የሚሉት ብዙነህ፣ የተከናወነውም “የመምህራን፣ የርዕሳነ መምህራን፣ የምክትል ርዕሳነ መምህራን እና የሱፐር ቫይዘር ዝውውር አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 69/2013” በተሰኘው መመሪያ መሠረት መሆኑን ነው ያብራሩት።
ብዙነህ አያይዘውም፣ የሽግሸግ መመሪያው ለመጀመሪያ ጊዜ በ2014 የትምህርት ዘመን ተግባራዊ የሆነ እንደሆነና የጸደቀውም ባሳለፍነው መስከረም 6/2014 መሆኑን አመላክተዋል።

የቢሮው ተወካይ እንደሚለት ከሆነ፣ አንድ የትምህርት ዓይነት ብቻ የሚያስተምር መምህር በአምስት ቀን እስከ 21 ክፍለ ጊዜ ማስተማር አለበት። ከዚህ የክፍለ ጊዜ ጫና በታች የያዙ መምህራን ትርፍ ስለሆኑ አዲስ ወደ ተከፈቱና የመምህራን ዕጥረት ወዳአለባቸው ትምህርት ቤቶች ይሸጋሸጋሉ ነው ያሉት።

በዚህም መሠረት፣ በመዲናዋ በሚገኙ ክፍለ ከተሞች የመምህራን ሽግሽግ እንደተደረገና ለአብነትም በጉለሌ ክፍለ ከተማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 66፣ በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 41 ትርፍ መምህራንን አግኝተናል ያሉ ሲሆን፣ እነዚህንም ወደ ለሚ ኩራና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ወደሚገኙ ትምህርት ቤቶች አሸጋሽገናል ብለዋል።

ሸግሽጉ የመምህራንን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አይደለም ለሚለው የመምህራን ቅሬታ፣ የዳይሬክተሩ ተወካዩ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ይኸውም “በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ የትምህርት ዓይነት የሚያስተምሩ ሦስት መምህራን ካሉና መያዝ ከሚገባቸው የክፍለ ጊዜ ጫና በታች ይዘው ከሆነ፣ በኦዲት መሠረት ትርፍ የሆነው መምህር ቅድሚያ በፍላጎት እንዲነሳ ይደረጋል ብለዋል። ፍላጎት ከሌለው ደግሞ ዝቅተኛ አገልግሎት ያለው ሽግሽግ እንደሚያደርግ መመሪያው ይጠቅሳል” ሲሉ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ ስለጉዳዩ አልሰማንም ለሚለው የመምህራኑ ቅሬታ፣ “አዲስ የወጣውን መመሪያ በየ ክፍለ ከተማው ለሚገኙ ት/ቤቶች እንዲደርስ ካደረግን በኋላ ነው የተካሄደው” ብለዋል። እንዲሁም ቅድሚያ አልተነገረንም ለሚለው የመምህራኑ ቅሬታም “ቀድሞ በሚሠራው ኦዲት መሠረት ዝቅተኛ የክፍለ ጊዜ ጫና ያለው እንደሚነሳ የታወቀ ነው፤ ለ30ሺሕ መምህራን ኦረንቴሸን አይሰጥም” ብለዋል።

ብዙነህ በመጨረሻም፣ መመሪያውን የጣሰ አሠራር አለ የሚሉ መምህራን ካሉ ቅሬታቸውን ለመቀበል በራቸው ክፍት እንደሆነና መምህራኑ ቅሬታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ አመላክተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች