በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ “ኦነግ ሸኔ” 256 ቤቶች ማቃጠሉ ተገለጸ

0
1340

በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ወረጃርሶ ወረዳ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው “ኦነግ ሸኔ”፣ 256 የግለሰብ ቤቶችን እንዳቃጠለ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ባሳለፍነው ሳምንት (የጥቅምት ወር ሦስተኛ ሳምንት 2014) ከጎሐ ጽዮን ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የጁ መድኃኒዓለም ተብሎ በሚጠራው የገጠር አካባቢ የሚገኙ 256 የግለሰብ ቤቶችን “የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ኃይል” እንዳቃጠላቸው ነው አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ መረዳት የቻለችው።

አዲስ ማለዳ ተፈጸመ የተባለው የቤቶች ቃጠሎ ወንጀል የተሠነዘረበትን ሰዓት ለማጣራት የሞከረች ሲሆን፣ ከምንጮቿ ባገኘችው መረጃ መሠረትም ጥቃቱ የተፈጸመው ከንጋቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እንደሆነ ነው። በአደጋው ለሕልፈተ ሕይወት የተዳረጉ ሰዎች እንደሌሉም ተመላክቷል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ እና ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ የሚኖሩ ግለሰብ የተናገሩትም፣ በቃጠሎው ወቅት ወደ አራት የሚሆኑ ሰዎች ጉዳት የደርሰባቸው ቢሆንም የሞተ ሰው አለመኖሩን ነው።
“ታጣቂ ቡድኑ” የግለሰብ ቤቶችን ባቀጠለበት ወቅት ምንም እንኳን ሰዎች ለሞት ባይዳረጉም፣ ንብረታቸውን ከቤታቸው ማውጣት ባለመቻላቸው በ256ቱ ቤቶች ውስጥ የነበሩ ዕቃዎች ሙሉ ለሙሉ ተቃጥለዋል። ይህን ተከትሎም ቤታቸው በእሳት የወደመባቸው ግለሰቦች በአጎራባች ቦታዎች ተጠግተውና በየጫካው ተበታትነው እንደሚገኙ ነው ከመረጃ ሰጪ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ መረዳት የተቻለው።

በወረዳው በ“ኦነግ ሸኔ” በተፈጸመው ቤት የማቃጠል ወንጀል 256 አባውራዎች ቤት አልባ መሆናቸውን እና ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ፣ በጠቅላላው ከ5ሺሕ 54 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ከቤታቸው መፈናቀላቸውን ነው፣ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የአካባቢው ነዋሪ ወጣት ከሰጡትው ዕማኝነት መረዳት የተቻለው።

ወጣቱ አክለውም፣ “ኦነግ ሸኔ” በአካባቢው ጥቃት መሠንዘር የጀመረው ከ2013 ጀምሮ መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ መከላከያ ሠራዊት በአካባቢው እንደሌለ ገልጸዋል። የሚመለከተው አካል ያሉበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት መከላከያ ሠራዊቱ ገብቶ ከለላ እንዲያደረግላቸው በማድረግ እንዲታደጋቸው ነው ያሳሰቡት።

“ታጣቂ ኃይሉ” ጥቃት የሠነዘረው ሰዎች እንቅልፍ ላይ በነበሩበት ወቅት በመሆኑ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች የተሰነዘረባቸውን አደጋ ለመከላከል ከባድ ሆኖባቸው እንደነበርም ነው ለአዲስ ማለዳ ያመላከቱት።
ጥቃቱ የተፈጸመው የየጁ መድኃኒዓለም አካባቢ ነዋሪዎች በተዘናጉበት ወቅት በመሆኑ፣ ቃጠሎው እንደተፈጸመ ተነስተው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከመፋጠን በዘለለ ዕቃዎችን ለማውጣትና ቤቶቹን ለመታደግ የነበራቸው ጊዜ ትንሽ እንደነበር ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
“የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ኃይሎች” በወረ ጃርሶ ወረዳ እንዳሉ ነዋሪዎቹ ጠቁመው፣ መንግሥት ዕርዳታ እንዲያደርግላቸው በተስፋ እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ተሰነዘረ የተባለውን የቃጠሎ አደጋ አስመልክቶ ምን እየተሠራ እንደሆነ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የወረ ጃርሶ ወረዳ አስተዳደር ወደ ሆኑት አየለ መንግሥቱ ብትደውልም፣ ስልካቸውን ሊያነሱ ባለመቻላቸውና በመጨረሻም ስልካቸው ጥሪ መቀበል ባለመቻሉ ለጉዳዩ ያላቸውን ምላሽ የማግኘት ሙከራዋ ሳይሳካላት ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here