“ዴልታ ፕላስ” በመባል የሚታወቀው አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ከቀደመው የመጀመሪያ ዝርያ ዓይነት የበለጠ እንደሚስፋፋ ቢነገርም፣ ምን ያህል ይሠራጭ እንደነበር በእርግጠኝነት ለማወቅ አዳጋች ነበር። ከሠሞኑ የእስራኤል ሳይንቲስቶች በምርምር አረጋገጥን እንዳሉት አዲሱ “ዴልታ ፕላስ” የተባለው ዝርያ ከነባሩ መሰሉ “ዴልታ” ይባል ከነበረው ዓይነት ዝርያ በ15 በመቶ የበለጠ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድል እንዳለው ነው።
‹ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ› ላይ በወጣው ዘገባ መሠረት፣ ሳይንቲስቶቹ ‹ማሳቹሴት› ውስጥ ያሄዱት የበሽታው ዝውውር ጥናት፣ አዲሱ “ዴልታ ፕላስ” ከዴልታ ዝርያ ጋር ያለውን ልዩነት ለማወቅ አስችሏቸዋል። ከዚህ ቀደም የ“ዴልታ” ዝርያ፣ “አልፋ” ከሚባለው የቀደመ ዝርያ በ60 በመቶ የበለጠ መተላለፍ ይችላል። “አልፋ” የሚባለው ዝርያ ደግሞ መጀመሪያ በቻይና ከታወቀው ከዋናው ዝርያ በ50 በመቶ ይበልጥ ሊሠራጭ እንደሚችል ታውቋል።
ይህ የሥርጭት መጠን የሚያሳየው፣ ቫይረሱ ዝርያውን እየቀየረ ለሕክምና ማስቸገሩን ብቻ ሳይሆን፣ በጣም በፍጥነት መሠራጨት እየቻለ እንደሆነ ነው። “ዴልታ” የተባለውና ይበልጥ ይሠራጫል የተባለው ዝርያ ከታወቀ ወዲህ ደግሞ፣ አሁን “ዴልታ ፕላስ” የተሰኘ በመጠኑ ልዩነት ያለው ዝርያ ተገኝቷል።
እንደ እስራኤል የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት፣ “AY.4.2.” የተሰኘው ይህ አዲስ ዝርያ ቀድሞ ከታወቀው በ15 በመቶ ይበልጥ የመሠራጨት አቅም እንዳለው ነው። የሥርጭቱ ፍጥነትን ማወቅ ቢቻልም ግን፣ ዝርያው የበለጠ ገዳይ ስለመሆን አለመሆኑ፣ እንዲሁም እስካሁን የተመረቱ ክትባቶችን የበለጠ የመቋቋም ብቃት ስለመኖር አለመኖሩ የበለጠ በጥናት እንደሚጣራ መነገሩን ‹ታይምስ ኦፍ እስራኤል› ይፋ አድርጓል።
ከ3 ወር በፊት በተካሄደ ጥናት፣ “ዴልታ” የተሰኘው ዝርያ፣ “አልፋ” ከተሰኘው በ60 በመቶ የበለጠ ይተላለፋል ተብሎ የነበረ ሲሆን፣ ይህም መጀመሪያ ከተገኘው የኮቪድ ዝርያ በ50 በመቶ የበለጠ የሚሠራጭ ነው ተብሎ ነበር።
“ዴልታ” የተሰኘውና በመጀመሪያ እንግሊዝ ውስጥ የተገኘው ዝርያ፣ እስካሁን ዓለማችን ላይ ከተመዘገቡት የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች በ6 በመቶው ላይ የታየ እንደሆነ ታውቋል። ይህ ዝርያ አሜሪካ ውስጥ ከተገኘባቸው 5 ግዛቶች አንዷ ማሳቹሴት ስትሆን፣ ዝርያውም አይነቱን ቀይሮ መገኘቱ ተነግሯል። ከ53 ሺሕ 884 የኮቪድ -19 ናሙናዎች ውስጥ ስድስቱ አዲስ ዝርያ በመሆናቸው ጥናቱ መካሄዱ ታውቋል። በካሊፎርኒያ፣ ዋሽንግተንና ሰሜን ካሮላይናም ዝርያው በመገኘቱ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በምርመራ ላይ ያለ ዝርያ ነው በማለት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በአሜሪካ የተመዘገበው የአዲሱ “ዴልታ ፕላስ” ዝርያ ይበልጥ እየተስፋፋባት ያለችው በመጀመሪያ የ“ዴልታ” ዝርያ የተገኘባት እንግሊዝ መሆኗ ታውቋል። አዲሱ ዝርያ ያለው እሾህ የመሰለው ፕሮቲን አይነት የተለየ በመሆኑ እስካሁን ካሉ ክትባቶች ጋር የሚኖረው መስተጋር ምን እንደሚሆን ገና አልታወቀም። በእስራኤል ሳይንቲስቶች የበለጠ እንደሚተላለፍ ቢረጋገጥም፣ ክትባቶችን የመቋቋም አቅሙ ምን ያህል እንደሆነም ሆነ የገዳይነቱ መጠን ገና መረጋገጥ አለበት ተብሏል።
የዝርያው የስርጭት መጠን የበለጠ ነው ቢባልም፣ አሁን በብዙ አገሮች እየቀነሰ ነው የተባለውን የቫይረሱን የሥርጭት መጠን በመቀልበስ ወደ ወረርሽን ደረጃ እንደበፊቱ የማሳደግ ብቃት ይኖረዋል የሚል ፍራቻ እንደሌላቸው ባለሙያዎቹ መናገራቸው ተዘግቧል። ዋናው የሥርጭት መጠኑ ከፍተኛነት ሳይሆን ክትባትን የመቋቋም ብቃቱ ምን ያህል እንደሆነ ሲታወቅ እንደሆነ የሚናገሩት ሳይንቲስቶቹ፣ ይህ እስከሚታወቅ የወደፊቱን መተንበይ አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል።
እስካሁን የተፈበረኩ የክትባት አይነቶች “ዴልታ” የተሰኘውን ዝርያ የመተላለፍ አቅም ይቀንሳሉ ተብሎ በመረጋገጡ፣ የአዲሱ “ዴልታ ፕላስ” ዝርያም ዕጣ ፈንታ ከዛ የተለየ አይሆንም በሚል ተስፋ የሚሰጡ ቢኖሩም፣ በጥናት እስኪረጋገጥ መጠበቅ ግድ እንደሚል ይናገራሉ።
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭቱ በአፍሪካ
ከመጀመሪያው የኮቪድ-19 ሥርጭት ጀምሮ ወረርሽኙ በአፍሪካ ላይ የበለጠ ጉዳት ያስከትላል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ተሰግቶ ነበር። ከአፍሪካውያን ይበልጥ የውጭ አገራት ዜጎች በተለያየ ሚዲያዎች ጭምር “አፍሪካውያን ሊያልቁ ነው” በማለት ትንበያዎችን ሲያስተጋቡ ነበር። ከተተነበየው በተቃራኒ ምዕራባውያኑ በወረርሽኙ ሲደቆሱ፣ ኢኮኖሚያቸውም እየወረደ ሲመጣ በአፍሪካ የተፈራው ግን ሳይደርስ ቀርቷል።
የብዙዎች ሥጋት የነበረው የአፍሪካ ይበልጥ አለመጎዳት ሲታወቅ፣ ብዙዎች ምክንያት ያሉትን መላምታቸውን ሲያስቀምጡ ቆይተዋል። ከሕዝቡ ድህነት አኳያ፣ እንዲሁም በተለይ በከተሞች የሚኖረው ሕብረተሰብ ተፋፍጎ ከመኖሩ አኳያ ያን ያህል አደጋ አለመከሰቱ እንዳያዘናጋና ለከፋ ወረርሽኝ እንዳያጋልጥ እያሉም የሚወተውቱ ነበሩ።
አፍሪካ ካላት 1.4 ቢሊዮን ዜጎች እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው 8.5 ሚሊዮን ብቻ ናቸው። ከሌላ አህጉርም ሆነ ከአንዳንድ አገሮች ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ በጣም አነስተኛ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ።
በአህጉሪቱ ኮቪድ አለባቸው ተብለው የተመዘገቡ ቁጥራቸው አነስተኛ ነው ቢባልም፣ የዓለም ጤና ድርጅት ይህ የሆነበት የሚለው የተለየ ምክንያትን ያስቀምጣል። ቁጥሩ ያነሰው ከ15 በመቶ በታች ያሉት ብቻ ስለሚመዘገቡ ነው ቁጥሩ ያነሰው እንጂ እውነታው ሌላ ነው ይላል። 60 ሚሊየን የሚሆኑ አፍሪካውያን ቫይረሱ ይዟቸዋል የሚለው ይህ ተቋም፣ ይህ ቁጥር በአህጉሩ ካለ የምርመራ መጠን አኳያ በጣም አነስተኛ ነው ብሏል።
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ በአህጉሩ የተደረገ የኮቪድ ምርመራ 70 ሚሊየን ገደማ ነው። ይህም ከአጠቃላይ የሕዝቡ መጠን 6 በመቶውን የሚሸፍን ነው ተብሏል። ከአፍሪካ አገሮች ብዙ ዜጎቿን የመረመረችው ጋቦን 50 በመቶ ምርመራ አድርጋለች የተባለ ሲሆን፣ ቀጣዩዋ ደቡብ አፍሪካ 30 በመቶ ዜጎቿን ብቻ ነው ያስመረመረችው። ለንጽጽር ያህል የአውሮፓዋ ኦስትሪያ ከ1ሺሕ በመቶ በላይ ምርመራ አድርጋለች። እንግሊዝም ከ400 በመቶ በላይ ምርመራን በማድረግ ዜጎቻቸውን ደጋግመው መርምረዋል። በእነዚህ አገሮች በቫይረሱ የተያዘ
ሰው ቁጥር ከፍተኛ ቢሆን አይገርምም የተባለ ሲሆን፣ አስር በመቶ ነዋሪዎቿን መመርመር ያልቻለችው አፍሪካ ግን የተያዙባት ቁጥር አነስተኛ ነው ማለት እንደማይቻል ኳርተዝ አፍሪካ አስነብቧል።
የቫይረሱ የሥርጭት ወቅት
የኮቪድ-19 ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገኘ ወዲህ ወረርሽኙ ሲጨምር፣ አንዴም ጋብ ሲል ሌላ ጊዜም ደግሞ መልሶ ሲያንሰራራ ቆይቷል። ይህ የሆነበት ምክንያት ከሚወሰደው የጥንቃቄ ዕርምጃ አኳያ ነው ቢባልም፣ ከሠሞኑ ግን የተለየ መረጃ ወጥቷል። የቫይረሱ ሥርጭት ከአየር ፀባይ ጋር በተገናኘ ወቅቶችን ጠብቆ እየተፈራረቀ ነው የሚል ግኝት ላይ መድረሳቸውን ‹ጆርናል ኔቸር ኮምፒዩቴሽናል ሳይንስ› የተሰኘ መጽሔት አስነበበ ብሎ ‹ፋይናንሺያል ኤክስፕረስ› ይፋ አድርጓል።
የስፔን ሳይንቲስቶች ቫይረሱ በመደበኝነት አመቱን ሙሉ በተመሳሳይ ይሰራጭ እንደሆነ አሊያም እንደእንፍሉዌንዛ ጊዜን ጠብቆ ይበልጥ እንደሚስፋፋ ለማወቅ ባካሄዱት ጥናት የሥርጭት መጠኑ ወቅታዊ መሆኑን ለማወቅ ችለዋል። ከዚህ ቀደም የቫይረሱ ሥርጭት ከአየር ንብረት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለውና በየትኛውም የአየር ጸባይ ሊተላለፍ እንደሚችል ተነግሮ ነበር።
የኮቪድ ቫይረስ በማንኛውም የአየር ሁኔታ ሊተላለፍ እንደሚችል ቢታወቅም አሁን ግን ይበልጥ የሚስፋፋበትን ሁኔታ ለማወቅ መቻላቸውን ተመራማሪዎቹ ይፋ አድርገዋል። ከ5 እስከ 11 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ዝቅተኛ ሙቀት ባለበትና ሒውሚዲቲው ወይም የአየር እርጥበታማነቱ ዝቅተኛ በሚሆንበት ወቅት በመጀመሪያ በቻይና እንደመከሰቱ በተመሳሳይ ሁኔታ አሁንም በፍጥነት ይተላለፋል ብለዋል።
የ162 አገራትን መረጃ በመውሰድ ይበልጥ በተላለፈባቸው ወቅቶች የነበረውን የአየር ፀባይ በማነጻጸር ከድምዳሜ ላይ መድረስ መቻላቸውን አሳውቀዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነና ተመሳሳይ የሥርጭት መጠን ነበረው ማለት ቢከብድም፣ ከሙቀት መቀነስና ከአየር እርጥበታማነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ማወቅ አስችሎናል ብለዋል።
የቫይረሱ ሥርጭት ከአየር ሁኔታው ጋር ቁርኝት ስለነበረው በወረርሽኝ መልክ የተከሰተው መስፋፋት በየጊዜው እንዲቀንስና እንዲጨምር አድርጎታል ይላሉ። በብዙ አገራት ለሦስተኛ ዙር አገረሸ የሚባለው ሥርጭቱ በአየር መለዋወጥ ሳቢያ የሚሆን ነው ብለዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014