መንገደኞችን የሚያማርሩ የትራንስፖርት ውስብስብ ችግሮች

0
943

በመዲናዋ አዲስ አበባ የነዋሪዎች ፈተና ከሆኑ ብዙ ነገሮቸ ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው የትራንስፖርት ችግር ነው። ከቤት እንደወጡ የፈለጉትን የትራንስፖርት አማራጭ ማግኘት መቻል ቀላል አይደለም። ጊዜን እና ገንዘብን አላግባብ ከሚያባክኑ የነዋሪው ፈተናዎች ውስጥ የትራንሰፖርት ችግር በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አንዱ ነው። ይህም በየጊዜው የሚጨምረው የከተማዋ የነዋሪዎች ቁጥር ካለው የትራንስፖርት አማራጭ እና ብዛት ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑም ነው።
በከተማዋ ያለው የትራንስፖርት ችግር አንድ ወይም ኹለት ብቻ ሳይሆን ውስብስብ እና ዘርፈ ብዙ ነው። አንዱ ቢፈታ እንኳን በጎን ሌላ ችግር ይፈጠራል።

በየቀኑ በተለይም በሥራ ቀናት መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ላይ ረዣዥም የታክሲ ሰልፎችን ማየት የተለመደ ነው። በዚህም ብዙዎች ሥራቸው ላይ ቀድሞ መገኘት እና ምሽት ከሥራ በጊዜ ቤት መግባት ሲቸገሩ ይስተዋላል።
ከተማዋ ያላት የመንገድ መሠረተ ልማት አናሳ መሆኑም እንዲሁ ለትራንስፖርት ችግሩ መባባስ እንደ መንስኤ ሊወሰድ ይችላል። አዲስ አበባ እንደ ርዕሰ ከተማነቷ ያላት መንገድ ሊኖራት ከሚገባው 20 በመቶ ብቻ እንደሆነ ይነገራል። ይህም ነዋሪዎች የቅርብ ዕርቀት ጉዞዎችን በቀላሉ በእግራቸው መጓዝ እንዳይችሉ እና የትራንስፖርት ችግሩም እንዳይቃለል ምክንያት ሆኗል።

እንዲሁም ደግሞ አማራጭ መንገዶች በብዛት ባለመኖራቸው፣ አንድ አውራ መንግድ ላይ የትራፊክ አደጋ ቢከሰት ተሽከርካሪዎች ለብዙ ሰዓት ተሰልፈው በመቆም ሊጠብቁ ይችላሉ።
በቂ መንገድ አለመኖሩ እና ያሉትም ጠባብ መሆናቸው ሳያንስ የመንገድ ዳር ንግዶች፣ እንዲሁም አንድ ሕንፃ ሲገነባ የተለያዩ የሕንፃ ግንባታ መሣሪያዎች መንገድ ላይ መከማቸት እና መሰል ችግሮች በተዘዋዋሪም ቢሆን ለሚፈጠረው የትራንስፖርት ችግር እንደ መንስኤ ይሆናሉ። በሕዝብ ሀብት ለሕዝብ መገልገያ በተገነቡ መንገዶች ላይ መጠጥና ምግብ ቤቶች መንገዶች ላይ ወንበር ደርድረው ሲሸጡ ማትየም ያልተለመደ ትዕይንት አይደለም። ይህ ሁሉ ተደማምሮ የነዋሪዎችን የትራንስፖርት ችግር ዘርፈ ብዙና ዘላቂ ያደርገዋል።

ይህ ሁሉ ችግር ባለበት በትራንስፖርቱ ላይ እንደ ዋና ችግር ሆኖ ነዋሪዎችን ያማረረው ግን፣ በሰበብ አስባቡ ያለአግባብ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች እና በትራንስፖርት ሰጪዎች የሚደርጉ የመልስ ገንዘብ ያለመመለስ ችግሮች ናቸው።
የዋጋ ጭማሪው በተለይ በታክሲዎች ላይ ሀይ ባይ ያጣ ችግር ነው። እሁድ ቀን እንዲሁም በተለያዩ የበዓላት ቀናት ኹለት ወይም ሦስት ብር የነበረውን አምስት ብር፣ አምስት ብር የነበረውን ደግሞ ዐስር ብር ያደርጉታል። ከታሪፍ ውጭ አንክፍልም የሚሉት ተሳፋሪዎች እንዲወርዱ ወይም በጉልበት እንዲከፍሉ ይደረጋል።
በብዙ ቦታዎች መመልከት እንደሚቻለው ደግሞ አንዳንዶች ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ፣ ሌሎች ደግሞ ከምሽት ኹለት እና ሦስት ሰዓት ጀምሮ በኹሉም ቀናት ከዕጥፍ በላይ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ። በአንዳንድ መንገዶች ላይም እንደሰዓቱ ኹሉም ቦታ ይህን ያህል ነው እያሉ እስከ 5 እጥፍ ያስከፍላሉ። ይህ የተለመደ የየቀን ችግር መሆኑ ደግሞ በመንግሥት ችላ የተባለ ወይም ይሁንታ ያገኘ ያስመስለዋል። በዚህም ምክንያት መኖሪያ ቤታቸው ከሥራ ቦታቸው ሩቅ የሆኑ ሰዎች የሚደርሳባቸውን ስቃይና እንግልት ከወዲሁ ማሰብ አያዳግትም።
ሌላው ነዋሪዎችን በየቀኑ የሚያበሳጨው እና ያማረረው ተያያዥ ጉዳይ ደግሞ የመልስ መከልከል ነው። ይህ ችግር በዋናነት ጎልቶ የሚታየው በባቡር ትራንስፖርት ላይ ነው።

በዚሀ ጉዳይ ላይ አንድ ስሜ እንዳይጠቀስ ያሉ የባቡር ተጠቃሚ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ‹‹ባቡር ስንጠቀም በአብዛኛው አራት ብር መክፈል እያለብን አምስት ብር ነው የሚቀበሉን። አስር ብር ከሰጠንም ስድስት ብር ሊመለስልን እየተገባ አምስት ብር ነው የሚመልሱልን። ለኹለት ሰው ብለን አስር ብር ስንሰጣቸውም ብዙ ጊዜ ኹለት ብር ለመመለስ ፈቃደኞች አይደሉም። መልስ ብለን ስንጠይቅ የለንም በማለት ያመናጭቁናል። የሚገርመው ዝርዝር ሳንቲም የሚከፍሉ ሰዎች እንኳን ቢኖሩ ሳንቲሙን በመደበቅ የለንም የሚሉ ትኬት ቆራጮችን ተመልክቻለሁ። ሕዝብ በየቦታው የሌቦች መጫዎቻ ሆኗል፤ የሚመለከታቸው አካላት ችግሩ እንዳለ በደንብ ያውቁታል፤ ነገር ግን አንድ ብር ለብዙዎች ዋጋ እንዳላት ቢያውቁ እና አዲስ አበባ አብዛኛው ሕዝብ ድሃ እንደሆነ ቢገነዘቡ ኖሮ በታማኝነት ያገልገሉን ነበር። ሆኖም እነሱ የሕዝብ መቸገር ስለማያሳስባቸው ለመቅረፍ ፈቃደኞች አይደሉም›› ሲሉ ነው የተናገሩት።

አዲስ ማለዳ ከሌሎች ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሰማችው ደግሞ፣ ለባቡር ትራንስፖርት አግልግሎት ትኬት ቆራጭ መሆን የሚፈለጉ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ነው። ይህም የመልስ ሳንቲም የለንም በማለት ከሕዝቡ በየቀኑ የሚሰበስቡትን ገንዘብ በማሰብ ነው ይላሉ። በዚህም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በቀን በብዙ ሺ ለሚቆጠር ሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ በትንሹ ከመቶ ሰዎች አንድ አንድ ብር ቢቆርጡ በተቋሙ በወር ከሚከፈላቸው ደሞዝ ውጭ ሦስት ሺሕ ብር አላግባብ መሰብሰብ ይችላሉ ሲሉ ነው ቅሬታ አቅራቢዎች የተናገሩት።
በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን አሰፋ፣ ‹‹ለሠራተኞች ትኬት ሲሰጣቸው ዝርዝር ሳንቲምም አብሮ ነው የሚሰጣቸው፣ ካነሳቸው ደግሞ ከንግድ ባንክ 1000 ዝርዘር ሳንቲም እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው›› ብለዋል። ተሳፋሪ በሚበዛባቸው እንደ ጦር ኃይሎች፣ ሐያትና መገናኛ ለሠራተኞች የሚሰጠውን ዝርዝር ሳንቲም ቁጥሩን ለማሳደግ እየሠራን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም፣ ‹‹መልስ የማይመልሱ ሠራተኞች ካሉ ተሳፋሪዎች ትኬት ሙቁረጫው ጋር በተለጠፉት ቁጥሮች ቢደውሉልን ወዲያውኑ መድረስ እንችላለን። ተሳፋሪዎች እንዲህ ያለ ችግር ሲፈጠር በየጣቢያው ላሉ ፖሊሶችም በማመልከት ችግሩን እንዲፈታ ትብብር ማድረግ አለባቸው›› ነው ያሉት።
በከተማ አውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይም እንዲሁ ተመሳሳይ ችግር ያለ ሲሆን፣ እዚህኛው ላይ ግን በዋናነት ጎልቶ የሚታየው ችግር ዝርዘር ሳንቲም ካልያዛችሁ አናስተናግድም የሚባለው እንደሆነ ነው ቅሬታ አቅራቢዎች የሚናገሩት።

የትራንስፖርት አማራጭ በሌለበት የሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ላይ “ከፈለጋችሁ ዝርዝር ሳንቲም አምጡ፣ ካልሆነ ሳንቲም የለንም” በማለት ወደ አውቶብሱ ውስጥ አያስገቡም። ሌሎች ደግሞ የመልስ ሳንቲም በመከልከል ትርፍ የሚያጋብሱ አገልግሎት ሰጭ አውቶብሶች መኖራቸውን ነው ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

አዲስ ማለዳ በተለያዩ ቦታዎች ተንቀሳቅሳ እንደታዘበችውም፣ ችግሩ በስፋት የሚስተዋል ሲሆን፣ የችግሩ ፈጣሪዎችም በማን አለብኝነት ሕዝቡን እንደፈለጉ ሲያመናጭቁ ነው የሚስተዋለው። በተለይ አንድ ‹‹ሸገር ባስ›› ላይ የምትሠራ ትኬት ቆራጭ አውቶብሱ ውስጡ ባዶ ሆኖ ሳለ ዝርዝር ከሌላችሁ ትኬት አልቆርጥም በማለት ሰዎችን ስታጉላላ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

ሰው የሚበዛባቸው እንደ መገናኛ ባሉ ቦታዎች ደግሞ ነዋሪዎች ከከተማዋ ጫፍ መጥተው ለሥራ የሚውሉበት በመሆኑ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት እና ረዣዥም ሰልፎች የሚስተዋሉ ሲሆን፣ የአውቶብስ አሽከርካሪዎች እና ሥምሪት ሰጭዎች ቁጭ ብለው ሲያወሩ ይታያሉ። ከተሰለፉት ብዙዎች ሰሚ በማጣታችን ለዚህ ኹሉ ስቃይ እየተዳረግን ነው በማለት በግልጽ ሲያወሩ፣ ሌሎች ደግሞ አሽከርካሪዎች ከተናደዱ ለባሰ እንግልት ይዳርጉናል፣ ስለዚህ መናገር አያስፈልግም በማለት ዝምታን መርጠው ሲጠባበቁ ይታያል።

በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ሕዝቡን እንዲያገለግሉ የተመደቡ ብዙዎች ይህን ኹሉ ችግር ሕጋዊ አስመስለው ሲሠሩት ማየት ደግሞ ይበልጥ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው። የግል ታክሲዎችም ይሁኑ የመንግሥት ትራንስፖርት ሰጭዎች ከሚያገኙት ገንዘብ በተጨማሪ አገልጋይነትንም እንደ መርህ ቢመለከቱት መልካም ይሆናል። በብዙ የዓለም አገራት ለተማሪዎች፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአረጋውያን፣ በተለያዩ የበዓላት ቀናት እንዲሁም የትራንስፖርት ዕጥረት በሚኖርባቸው ቀናት ለሕዝባቸው ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ። ይህም ማገልገልን ለሕዝባቸው በማስተማር መልካም ዕሴቶቻቸውን ያበዛሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ብዙዎች ማጭበርበር፣ መሸት ሲል እና በበዓላት ቀን ከዕጥፍ በላይ የታሪፍ ጭማሪ በማድረግ መዝረፍ እና ሕዝቡን ማማርር እንጂ፣ ነጻ ማገልገሉ ቀርቶ በተገቢው መንገድ ማገልገልን እንኳን ገና እንደ መልካም ዕሴት የተመለከቱት አይመስልም።

በዚህ ላይ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አረጋዊ ማሩ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ብዙ ችግር መኖሩን ጠቁመው፣ አዲስ አደረጃጀት ተፈጥሮ በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር ለምፍታት እንቅስቃሴ ላይ ነው ብለዋል። በዚህም በቅርቡ በተደረገ እንቅስቃሴ ሰልፍ የሚበዛባቸው እንደ ሜክሲኮ፣ መገናኛ፣ ፒያሳ፣ ጀሞ እና ጦር ኃይሎች ያሉ ቦታዎች ላይ ያለውን እጥረት በተወሰነ መልኩ መፍታት ተችሎ የነበረ ቢሆንም፣ በቅርቡ ትምህርት መከፈቱን ተከትሎ ችግሩ ሊቃልል አልቻለም ብለዋል።

ምሽት እና በበዓላት ቀን የታሪፍ ጭማሪ የሚያደርጉ አሽከርካሪዎችን በተመለከተ፣ ‹‹ማንኛውም አገልግሎት ለመስጠት የወጣ አገልግሎት ሰጭ ተሽከርካሪ በየትኛውም ሰዓት ከተቀመጠለት ታሪፍ ውጭ መጨመር አይችልም›› ሲሉ ተናግረዋል። ይህን ለመቆጣጠር በእያንዳንዱ ቦታ ተቆጣጣሪ መመድብ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ በነጻ የስልክ መስመር እንዲሁም ለትራፊክ ፖሊሶች ጥቆማ በመስጠት ችግሩን መቅረፍ ይገባል ሲሉ ዳይሬክትሩ ጨምረው ገልጸዋል።

እንዲሁም፣ አምሽተው የሚሠሩ ታክሲዎች የሚያደርጉትን አላግባብ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል ቢሮው ተቆጣጣሪ እየመደበ መሆኑን ጠቁመዋል።
መልስ የማይሰጡና ሳንቲም ካልያዛችሁ አናስተናግድም የሚሉትን በተመለከተም ፣ ‹‹የትኛውም ግለሰብ በያዘው ገንዘብ የመጓዝ መብት አለው። በቂ ዝርዝር መያዝ የባለ ተሽከርካሪው ግዴታ ነው። እንዲህ አይነት ነገር ከፍ ሲል ሌላ ወንጀል እና የመብት ጥሰት ስለሚያስከትል ተሳፋሪዎች በቸልተኝነት መተው የለባቸውም›› ብለዋል።

በሸገርም ሆነ በብዙኃን ትራንስፖርት ሰጭዎች ዘንድ የሚከሰቱ መሰል ችግሮችን አንፀባራቂ የለበሱ ደንብ አስከባሪዎች ስላሉ ለእነሱ ጥቆማ በመስጠት እንዲፈታ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት። በዚህ የማይፈታ ሲሆን ደግሞ ለትራንስፖርት ባለሥልጣን እና ለትራፊክ ፖሊስ በማመልከት ወይም ታርጋ ቁጥሩንና የሚያልፍበትን መስመር በመያዝ ተሳፋሪው መብቱን ለማስከበር እና የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲፈጠር እስከ ወዲያኛው መሔድ አለበት ብለዋል።
በመጨረሻም፣ ዳይሬክተሩ ‹‹በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በዚህ ዓመት በኹለት መልኩ እየተሠራ ነው። ቀዳሚው ያሉትን ትራንስፖርት ሰጭ ተሽከርካሪዎች በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ሲሆን፣ ሌላኛው ያለውን የትራንስፖርት ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም ቢሮው ተጨማሪ አውቶብሶችን ለመግዛት ሒደት ላይ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል።

ከላይ ከተስተዋሉት ችግሮች በተቃራኒው በባቡር ትራንስፖርት፣ በታክሲዎችም ይሁን ከተማ አውቶብሶች ላይ ብዙ መልካም እና የተሰጣቸውን ሕዝብን በቅንነት የማገልገል ኃላፊነት በአግባቡ የሚወጡ መኖራቸው አይካድም። አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝትም ለአረጋውያንና ለእርጉዝ ሴቶች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የሚያደርጉ፣ ሕግ እና ሥርዓት አክብረው የሚያስመሰግን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላት መኖራቸውን ለማየት ችላለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here