የኮቪድ 19 ክትባት በግል ተቋማት

0
1363

በኢትዮጵያ አንድ በኮቪድ-19 ቫይረስ የተያዘ ግለሰብ ከተመዘገበበት ዕለት መጋቢት 4/2012 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 10/2014 ድረስ 360 ሺሕ 503 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ ስድስት ሺሕ 287 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘው ሕይወታቸውን አጥተዋል። እስከ ጥቅምት 10/2014 ድረስ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች 23 ሺሕ 393 ሲሆኑ፣ አጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ 330 ሺሕ 821 ነው። ኢትዮጵያ ክትባቱን መስጠት ከጀመረችበት ጊዜ እስከ ጥቅምት 10 ድረስ ማለትም ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ስዓት ድረስ ሦስት ሚሊዮን 77 ሺሕ 505 ሰዎችን ከትባለች።

ዓለምን ያስጨነቀው ኮቪድ 19 ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የዓለም አገራት በወረርሽኙ እየተፈተኑ ይገኛሉ። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለምን የፈተነው ከሕይወት መቅጠፍ እስከ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ በማስከተል መሆኑ ባለፉት ጊዜያት የታየ ጉዳይ ነው።
ኮቪድ 19 ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተገኘው መጋቢት 4/2012 ሲሆን፣ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙን ለመግታት የተለያዩ የመከላከያ ዕርምጃዎችን ቢወስድም ሥርጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቶ አሁን ላይ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።
ወረርሽኙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የዓለም አገራት ለቫይረሱ ክትባት ለማግኘት ሌት ከቀን ሠርተዋል። በዚህም የተለያዩ አገራት ለቫይረሱ ክትባት ማግኘታቸውን ተከትሎ፣ አሁን ላይ የዓለም አገራት ክትባቱን ለዜጎቻቸው እያቀረቡ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም የቫይረሱን ክትባት ከተለያዩ የዓለም አገራት በማምጣት ለዜጎቿ እየሰጠች ትገኛለች። ኢትዮጵያ ክትባቱን እየሰጠች ቢሆንም፣ የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል። እንደ ኢንስቲትዩቱ መረጃ በቫይረሱ የሚያዙ እና የሟቾች ቁጥር አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ ስለመጣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ እንደሚያስፈለግ ይታመናል።

“በኢትዮጵያ ያለው የኮቪድ-19 ሥርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ይህም በበሽታው የሚያዙ፣ በፅኑ የሚታመሙና ሕይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን ቁጥር ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን እየጨምረ ይገኛል” ሲል ኢንስቲትዩቱ መግለጹ የሚታወስ ነው።
በኢትዮጵያ አንድ በኮቪድ-19 ቫይረስ የተያዘ ግለሰብ ከተመዘገበበት ዕለት መጋቢት 4/2012 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 10/2014 ድረስ 360 ሺሕ 503 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ ስድስት ሺሕ 287 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘው ሕይወታቸውን አጥተዋል። እስከ ጥቅምት 10/2014 ድረስ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች 23 ሺሕ 393 ሲሆኑ፣ አጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ 330 ሺሕ 821 ነው። ኢትዮጵያ ክትባቱን መስጠት ከጀመረችበት ጊዜ እስከ ጥቅምት 10 ድረስ ማለትም ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ስዓት ድረስ ሦስት ሚሊዮን 77 ሺሕ 505 ሰዎችን ከትባለች።

መንግሥት ለዜጎች የሚያቀርበው ክትባት በአብዛኛው ተደራሽ የሚሆነው በቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና በዕድሜ ለገፉ ሰዎች መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ይህንኑ ተከትሎ አሁን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በግል ተቋማት የኮቪድ ክትባት ወደ አገር ውስጥ ገብቷል። በግሉ ዘርፍ ትብብር የኮቪድ 19 ክትባት በኢትዮጵያ ለመስጠት ክትባቱ በግዥ ከቻይና እንደገባ ተገልጿል።

የኮቪድ ክትባቱ የቀረበዉ በሜዲቴክ ኢትዮጵያ እና በዋሽንግተን የሕክምና ማዕከል በጋራ ትብብር ሲሆን፣ ክትባቱ ለሚፈልጉ ዜጎች በክፍያ የሚቀርብ መሆኑ ተገልጿል። ተቋሞቹ ክትባቱን ለማቅረብ ከቻይናዉ የክትባት አምራች ሲኖፋርም ጋር የኹለት ሚሊዮን ዶዝ ዉል ተፈራርመዋል ተብሏል። የመጀመሪያ ዙር 200 ሺሕ ዶዝ ክትባት ባሳለፍነው ሰኞ አዲስ አበባ ገብቷል።

ክትባቱን ከቻይናው ድርጅት ለማግኘት ከስድስት ወር በላይ እንደፈጀ የሚዲቴክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር መሐመድ ኑሪ የገለጹ ሲሆን፣ ክትባቱን ሜዲቴክ ኢትዮጵያ በአቅራቢነት እንዲሁም ክትባቱን ለተጠቃሚዎች በማድረስ ደግሞ ዋሽንግተን የሕክምና ማዕከል ሒደቱን ያሳልጠዋል ተብሏል።
የኮቪድ ክትባት በግል የሕክምና ተቋማት የቀረበው በዋናነት ክትባቱን ከፍለው መከተብ ለሚፈልጉ ሰዎች በመንግሥት ከሚቀርበው ክትባት በተጨማሪ እንደ አማራጭ መሆኑ ተመላክቷል። እንዲሁም፣ መንግሥት የሚያቀርበው ክትባት ቅድሚያ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በመሆኑ፣ የክትባቱን ተደራሽነት ለማስፋት የታሰበ ነውም ተብሏል።

ተቋሞቹ ከቻይናው የክትባት አምራች ሲኖፋርም ለኢትዮጵያ የሚያቀርቡት 2 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት የአለም ጤና ድርጅትን መስፈርት ያሟላ ነው ተብሏል። ክትባቱን በግል እንዲያቀርቡ የጤና ሚኒስቴር ለተቋሞቹ ፈቃድ መስጠቱን የገለጸ ሲሆን፣ የክትባቱ አሰጣጥ እና ሥርጭት ከጤና ሚኒስቴር አሠራር ጋር በተናበበ ሁኔታ እንደሚከናወን ተጠቁሟል።

ክትባቱ አዲስ አበባ በገባበት ወቅት የጤና ሚኒስቴር አማካሪው ዶ/ር ሙሉቀን ዩሀንስ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና እንደሚያስፈልግና በተለይም የግሉ የጤና ዘርፍ በዚህ ረገድ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ገልፀዋል። የግሉ የጤና ዘርፍ ከዚህ ቀደም ግብዓቶችን በማስመጣትና በአገር ውስጥም እንዲመረቱ በማድረግ፣ የኮቪድ 19 መመርመሪያና የሕክምና አገልግሎትን በማስፋፋት ለመንግስት ድጋፍ ማድረጉን በማንሳት፣ አሁንም በኮቪድ-19 ክትባት አሰጣጥ ላይ ሕዝቡንና መንግሥትን ለማገዝ ያደረጉትን ጥረት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የሜዲቴክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር መሐመድ ኑሪ ድርጅታቸውና እህት ኩባንያው የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ በጤናው ዘርፍ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎችን በማቅረብና በማምረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፣ አሁንም መንግሥት የግሉ ዘርፍ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያደረገውን ጥሪ በግንባር ቀደምትነት ከተቀላቀሉት ውስጥ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የዋሽንግተን ሕክምና ማዕከል መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀም፣ ተቋማቸው በኮቪድ19 ምርመራና ሕክምና ካበረከተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ፣ ባሉት የተደራጁ ማዕከላት የኮቪድ 19 ክትባትን ከሜዲቴክ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር እንደሚሰጥና ከዚህም በተጨማሪ ማዕከሉ በሚያደርገው ትምህርት እና ቅስቀሳ የክትባቱን ተቀባይነትም ለመጨመር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ማዕከሉም የኮቪድ19 ክትባት ለሚወስዱ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውና በቀላሉ ሊረጋገጥ የሚችል የክትባት ምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ፣ እንዲሁም አገልግሎቱን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጨምሮ በተለያዩ ማዕከላት እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ማዕከሉ የሚሰጠው የክትባት የምስክር ወረቅት በማንኛቸውም የዓለም አገራት ተቀባይነት ያለው እና የምስክር ወረቀት የተሰጠው ሰው መከተብ አለመከተቡን ማረጋገጥ የሚፈልግ ተቋም በቀጥታ (ኦን ላይን) ማረጋገጥ የሚችልበት ነው ተብሏል።

የክትባቱ ተደራሽነት በተለይ የክትባት አቅርቦት ዕጥረት ባለበት አካባቢ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም ማንኛውም ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ሰው መከተብ እንደሚችል ተጠቁሟል። ይሁን እንጂ የጤና ችግር ያለባቸው እንዲሁም ክትባቱን በመውሰዳቸው ሌላ ተጨማሪ ችግር ሊጋጥማቸው የሚችሉ ሰዎች ክትባቱን እንደማይወስዱ ተመላክቷል።

ለዚህም ክትባቱን የሚሰጠው ዋሽንግተን የሕክምና ማዕከል ለክትባት ወደ ተቋሙ የሚመጡ ሰዎችን ጤንነት የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራ ተጠቁሟል። ማዕከሉ ክትባት ከመስጠቱ አስቀድሞ የቅድመ ሁኔታ ማረጋገጥ ሥራ እሠራለሁ ያለ ሲሆን፣ ክትባቱን ለመውሰድ የጤና ሁኔታቸው ለሚገድባቸው ሰዎች ክትባቱን እንደማይሰጥ ጠቁሟል።

ሜዲቴክ ኢትዮጵያ እና ዋሽንግተን የሕክምና ማዕከል የሚያቀርቡት የኮቪድ 19 ክትባት ዋጋ ተመጣጣኝ እና የሕብረተሰቡን የመክፈል አቅም ውስንነት ከግንዛቤ ያስገባ እንደሚሆንም ተገልጿል። የክትባት ዋጋው ክትባቱ አዲስ አበባ እስከገባበት ሰዓት ድረስ ያልተተመነለት መሆኑ ተግልጿል።
በአሁኑ ጊዜ የኮቪድ ክትባት የሚወስዱ ሰዎች የመጀመሪያ ዙር ክትባት ወስደው ተከታዩን ኹለተኛና ሦስተኛ ዙር ክትባት ባለመውሰዳቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ እየሆኑ ነው ተብሏል። የጤና ሚኒስቴር አማካሪው እንደገለጹት ከሆነ፣ በአሁኑ ጊዜ በቫይረሱ ተይዘው በጽኑ ሕሙማን ከፍል ውስጥ የሚገኙ ታማሚዎች በአብዛኛው ክትባቱን ያልወሰዱ ሰዎች ናቸው።

ከዚህ በፊት ቫይረሱ ከያዛቸው ሰዎች ውስጥ ሕመሙ የሚጠናባቸው በዕድሜ የገፉ ሰዎች እና ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው እንደነበሩ ያስታወሱት የጤና ሚኒስቴር አማካሪው፣ አሁን ላይ በኹሉም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች ላይ ሕመሙ እንደሚጸና ተናግረዋል። በመሆኑም ማኅበረሰቡ ቫይረሱ ኹሉንም እንደሚያጠቃ ተገንዝቦ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ መከተብ የቻለችው ካለው የሕዝብ መጠን አንጻር ከሦስት በመቶ የማይበልጥ መሆኑን የጠቆሙት አማካሪው፣ የግሉ ዘረፍ ቫይረሱን በመከላከልም ይሁን ክትባቱን በማቅረብ እገዛ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል። ጤና ሚኒስቴር ቫይረሱን ለመከላከል የሚሠሩ በግሉ ዘርፍ ለተሠማሩ የጤና ተቋማት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ እና በጋራ በሚሠሩ ጉዳዮች ላይ በትብብር እንደሚሠራም ተጠቋሟል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here