የበዓል ትውስታዎቼ!

0
844

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በዓልን ጓግቼ እንድጠብቀው የሚያደርገኝ ምክንያት በየጊዜው ይቀያየራል፤ ተቀያይሯል። አንድ ጥርት ብሎ ትዝ የማይለኝ እድሜዬ ላይ ቤተሰቦቼ ለእኔና ለእህት ወንድሞቼ የሚገዙልን ጫማና ልብስ ነበር። ጥቂት ከፍ ስል በዓል ሲደርስ ለቤት ውስጥ ፍጆታ የሚገዙ የቤት እቃዎች ሳይቀር የበዓል ትርጓሜዬ ሆኑ።
ያ ጊዜ ማለት በዓል ሲደርስ አንዳች አዲስ ነገር ለማየት የምፈልግበት ነበር። እንደው አዲስ የተገዛ የቡና ሲኒ ሳይቀር ብቻውን ከበዓል ድባብ ጋር ተዳምሮ ተወልጄ ያደግኩበትና የኖርኩበት ቤት አዲስ የሆነ ያህል እንዲሰማኝ ያደርግ ነበር።
ከፍ ስል መንፈሳዊ ዓለም የበለጠ አዘንብሎብኝ በዓላትን ሰማያዊ አድርጌ ተመልክቻለሁ። ፈጣሪን ‹ለዚህ ስላደረስከን እናመሠግናለን› ብሎ ማመስገን የበዓል ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በማመን ብዙ በዓላትን አክብሬ አሳልፌአለሁ። ያም ሁሉ አልፎ ደግሞ በዓል ከላይ ያልኳቸው የሁሉም ድምር ሆኖ ማግኘቴንም አልረሳም።
ቀጥዬም ሠርቼ በማገኘው የምፈልገውንና በዓል ያደምቃል ያልኩትን ለቤትም ሆነ ለራሴ መግዛትን ልምድ አደረግሁ። ከዘመድ፣ ቤተሰብ፣ ከጓደኛና እህት ወንድሞቼ ጋር መሰባሰብ የበዓል ወግ ሆነኝ። ማልጄ ወደ ፈጣሪ ለምስጋናም ለጸሎትም ጎንበስ ቀና ማለትን አወቅሁ። ለተቸገሩ የሚደርሱ ማኅበራት ጋር ጠጋ ብዬ የድርሻዬን ማበርከትን ተማርኩ። ይህም ሁሉ በዓልን በዓል ያደረገው ምስጢር ሆነልኝ።
በዚህ መካከል አንድ እውነት ፈጽሞ አልተቀየረም። በሁሉም በዓላት እናታችን ያለእረፍት ስታገለግለን ነበር። የበዓሉን ሥራ ቀድማ የምትጀምረው፣ በዓሉን በማክበር ግን መጨረሻ የምትሆነው እርሷ ናት። ጉድ ጉዷ የሚያልቀው ሁላችንን ካበላችና ካጠጣች፣ ‹በቃን› ማለታችንን ካረጋገጠች በኋላ ነው።
የበዓል ሰሞን ከመሥሪያ ቤቷ ፈቃድ ትወስዳለች፤ ለሥሙ የምትወስደው ፈቃድ ‹እረፍት› ይባላል እንጂ የባሰ ሥራ የምትይዝበት ሰሞን ነው። ግን ከፍቷት ዐይተናት ወይም ደከመኝ ብላ አታውቅም። ‹ኤጭ! ደግሞ በዓል ደረሰ› ስትልም ሰምተናት አናውቅም። ግን’ኮ ይደክማል! የበዓል ቅድመ ዝግጅቱ፣ ደርሶ መንጎዳጎዱ፣ እንግዳ ማስተናገዱ፣ ቤተሰብን መንከባከቡ ቀላል አይደለም።
ለካ እናት ናት በዓልን ትርጉም የምታሰጠው፤ ሴት ናት የበዓልን ትዝታ የምታትመው።
ትዳር የመሠረቱና ልጆች የወለዱ እህቶቼ ልክ እንደ እናታችን ሆነው ሳይ፣ የሕይወትን ቅብብሎሽ አስባለሁ። ድካምንም ለካ እንዲህ ይወራረሱታል! ግን ደግሞ እህታችን እንደ እናታችን ሥራ አይበዛባትም፤ ያንን ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች አሉላት። የገበር ምጣድና ኩበት፣ የዶሮ ሽንኩርት እጅ እስኪግል መላጥና መክተፍ፣ ከሰልና እንጨት እያራገቡ ወጥ መሥራት ወዘተ ይህ እህቴ የምታደርገው አይደለም።
ዘመናዊ ምጣድ፣ የተዘጋጁ ግብዓቶች ገበያ ላይ መገኘት፣ የሽንኩርት መፍጫ መኖር፣ የኤሌክትሪክ ምድጃና ወዘተ የእህቴን ሥራ አቅልሎላታል። ከባድ ሥራን ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችና መሣሪያዎች አጋዥነታቸው ጥርጥር የለውም።
እናቶቻችን የበዓል ሥራ በዛብን ብለው የሚያማርሩ አይደሉም። ግን ቢያንስ ከባዱን ሥራ፣ ብዙ ጉልበት የሚወስድና የሚያደክመውን የበዓል ጉድ ጉድ ቀለል እንዲልላቸው ማድረግ ይቻላል። አሁን በዓል ሲባል የትዘታዬ ሁሉ መቋጠሪያ የሆነችው እናቴ ወደ ሐሳቤ ትመጣለች። እርሷን እያመሠገንኩም ሴትነት አስባለሁ።
መቅደስ ቹቹ
mekdichu1@gmail.com


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here