የኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎና ወጣቱ ትውልድ

0
1398

የአድዋ ድል በዓል የአፍሪካውያን ሁሉ ምሳሌና በዓለም ፊት የማይረሳ ታሪክ መሆኑ እሙን ነው። ኢትዮጵያውያን ከአድዋ ድል ውጪም ሌሎች የተለያዩ ወረራዎችን በተለያዩ ጊዜ መክተዋል። ለዚህም ብዙ መስዋዕትነትን ከፍለዋል። ከእነዚህ ድሎች መካከል ከ1928 እስከ 1933 የጣልያንና የኢትዮጵያ አርበኞች ጦርነት ተጠቃሽ ነው።
ይህ በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን የሚከበረው የአርበኞች ቀን፣ የአርበኞች ተጋድሎና ድል የሚወሳበት ነው። አገርና ትውልድ የእዚህ አርበኞች ባለውለታ መሆኑም እሙን ነው። ታድያ የዛሬው ወጣትና ትውልድ ስለዚህ የድል በዓል ምን ያህል ያውቃል? አርበኞችስ ለትውልድ ምን የሚሉት አላቸው? የሚያዝያ 27/1933 ታሪክስ ምን ይመስላል? የአዲስ ማለዳዋ እየሩሳሌም አለሙ እነዚህን ጥያቄዎች በማንሳት አባቶችን እንዲሁም በዓሉን ለማክበር ታድመው ያገኘቻቸውን ሰዎች በማነጋገር፣ መዛግብትን በማገላበጥ ጉዳዩን የአዲስ ማለዳ ሐተታ አድርጋዋለች።

በ1888 ጣልያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛቷ ስር የማድረግ ሕልሟን እንደምታሳካ እርግጠኛ ነበረች። ግን አልሆነም። አድዋ ላይ ከሸፈ። ታድያ ይህ ከሆነ 40 ዓመታት በኋላ በ1928 የጣልያን የጦር ሠራዊት በአዲስ ትውልድ የጦር ሠራዊት ኢትዮጵያን ወረረ። ይሄኔ የጣልያን ሕልም ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዢ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአድዋ የገጠማትን ሽንፈት መበቀያ ነው።

ይህኛው እንደ አድዋ በብዙ ቀናት ጉዞና በጥቂት ሰዓታት ውጊያ ያለቀ አልነበረም። ለአምስት ዓመታት እጅ ያለመስጠት ተጋድሎ ነበር። አርበኞች ለራሳቸው ሕይወት ሳይሳሱ፣ የአገራቸውን ክብር አስቀድመው ኢትዮጵያን ዛሬ ለምትባለው ለእያንዳንዱ ቀን ትደርስ ዘንድ መስዋዕትነትን ከፍለዋል።

ዘንድሮ ሚያዚያ 27/2013 ዕለተ ረቡዕ 80ኛው ዓመት የአርበኞች ቀን አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሀውልት ስር ተከብሯል። አዲስ ማለዳም በእለቱ በስፍራው በመገኘት የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር እና የኮሪያ ዘማቾች ማኅበር አባላትን አነጋግራለች።
የአርበኞች ተጋድሎና የዛሬ ዕይታ

የ80ኛው የአርበኞች ቀንን ማክበርና ማሰብ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን የበለጠ እንዲያውቅና የወደፊቷን ኢትዮጵያ እጣ ፋንታ፣ ሰንደቅ ዓላማዋን ይዞ የተሻለ ኢትዮጵያ እንዲፈጥሩ ለማስቻል ነው ይላሉ፤ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ጆቴ መስፍን።

‹‹አገራችን አሁን በብዙ ችግር ውስጥ ነው ያለችዉ፤ ድንኳን በደንብ ሊያስጠልል የሚችለው ያሉት ችካሎች በሙሉ በደንብ ተወጥረዉ ሲዘረጉ ነዉ።›› ያሉት ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ አሁን ላይ ያንን መጠለያ ድንኳን ሊዘረጋ ያሰበውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመከፋፍል እየተሯሯጡ ያሉና ዶላር እየተከፈላቸዉ በፌስቡክ ሕዝቡን ለማበጣበጥ የሚፈልጉ አሉ ብለዋል።

በተያያዘም ኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ መሆኗን በማውሳት፣ ይህም በጥንቃቄ መካሄድ እና ሕዝቡም የሚፈልገውን፣ ይሠራልኛል የሚለውን አገናዝቦ መምረጥ እና አገራችን ወደሰላም የምትሄድበትን መንገድ መፈለግ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።
‹‹የቆጡን አወርድ ብለን የብብታችንን ደግሞ እንዳናጣ መጠንቀቅ አለብን። ኢትዮጵያ የምትፈልገዉ ጠንካራ መንግሥት እና አገሪቷን ከዓለም መንግሥታት ጋር እኩል ቆሞ መከራከር የሚችል ነው። ከዛም ባሻገር ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚፈልጉትን በትዕግስትም ሆነ በተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩና እንዳያጠፉ መከላከል ያስፈልጋል። በአገራችን ላይ ያሉ ብዙ ችግሮች ሊጠፉ የሚችሉት የተገነባውንና እየተገነባ ያለውን አፍርሰን ሌላ በመገንባት አይደለም። ይልቁንም እየተገነባ ያለውን አጠናክረን ወደፊት ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከሚፈልጉት ስንላቀቅ ነው። ያኔ ስለወደፊቱ መነጋገር እንችላለን።›› ሲሉ አክለዋል።

‹‹ወጣቱ ትውልድ ይህን የአርበኞች የድል በዓል በደንብ አያውቀውም። ስለዚህ ስለበዓሉ ምንነት በትምህርት ፖሊሲ ውስጥ የታሪክ ትምህርት ላይ በትኩረት መሠራት አለበት።›› ያሉት ደግሞ ፍርድያውቃል ምርኩዜ ናቸው። በሙያቸው የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሱፐር ቫይዘር (ተቆጣጣሪ) ሆነው የሚያገለግሉት ፍርድያውቃል፣ ልጆቻቸው ከአሁኑ ታሪኩን እንዲያውቁ በዓሉ ላይ ይዘዋቸው እንደሚታደሙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

እንደውም ገና የሦስት እና አራት ዓመት ልጆች ሳሉ የአርበኞች ቀን እንዲሁም የድል በዓል ልጆቻቸውን ወደ አደባባይ ትርዒቶች ይዘዋቸው እንደሚሄዱ አውስተዋል። ይህንንም የሚያደርጉት ልጆቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ ለአገራቸው ፍቅር እና ተስፋ እንዲኖራቸው ነው ብለዋል።

‹‹በልጆቼ ላይም ለውጥ ዐይቻለሁ፤ ሌሎችም እንደእኔ ልጆቻቸውን እያመጡ እና እያስተማሩ ነው። ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም። ይህን በዓል ሁሉም ጋር እንዲዳረስ የአርበኞች ማኅበር፣ ባህልና ቱሪዝም በጥልቀት መሥራት ይኖርባቸዋል። ወጣቱ የአድዋ ድል ያህል ይህን የአርበኞች ቀን በዓልን አያውቀውም። ስለዚህ በተለይም የታሪክ ትምህርትን በትኩረት እና በሰፊዉ ለትዉልዱ መሰጠት አለበት።›› ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
ይህን ማድረግ ከተቻለ ከዉስጥም፣ ከዉጪም ሆነዉ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሠሩትን የኢትዮጵያ ጠላቶች ማጥፋት እንደሚቻል ያምናሉ።

አዲስ ማለዳ የስድስት ዓመቱ ልጃቸውን አናግራለች፤ ናታን ፍርድያውቃል። እርሱ በበኩሉ በልጅ አንደበት ኮልተፍ እያለ በቦታው የተገኘው የአርበኞችን ቀን ለማክበር እንደሆነ ተናግሯል። የስምንት ዓመቱ ወንድሙ አድያምሰገድም፣ የኢትዮጵያ አርበኞች በጦር በጎራዴ ጣሊያንን ያሸነፉበት እለት ነው በማለት ይናገራል። አያይዞም እንዲህ አለ፤ ‹‹እዚህ የመጣሁት አባቶቻችን ጣሊያንን ያሸነፉበትን ቀን ለማክበር ነው። እኔ ደግሞ ሳድግ ጎበዝ የአዉሮፕላን አብራሪ ሆኜ አገሬን ማስጠራት ነው የምፈልገው።››
ጌጡ በቀለ የአርበኞች ቀን በድል ሀውልት ስር በዓሉን ለማክበር ከተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ናቸው። አዲስ ማለዳም ቀርባ አናግራቸዋለች። እርሳቸውም ሲናገሩ የአርበኞች በዓል ወጣቱ በስፋት አያውቀውም ብለዋል። እርሳቸውም የፍርድያውቃልን ሐሳብ በመጋራት፣ በትምህርት ቤቶች ላይ የታሪክ ትምህርት ላይ በስፋት አለመሠራቱ ትልቅ ችግር እንደሆነ ነው የሚያምኑት።

‹‹ይህን ቀን አባቶቻችን ዋጋ የከፈሉበት ነው። ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል ያለፈው ትውልድ በርካታ ያልተነገረላቸውን ዋጋ ከፍሏል። ስለዚህ ከአራት ኪሎ የድል ሀውልት ስር ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወጣቶችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ይህንኑ ሐሳብና ታሪክ በመውሰድ በስፋት መዳረስ አለበት።›› ሲሉም ተናግረዋል።

ታሪኩንና የመጣበትን መንገድ የማያውቅ ትዉልድ ምን እንደሚሠራ እንዲሁም ወዴት እንደሚሄድ አያዉቅም ያሉት ጌጡ፣ አባቶቻችን ኢትዮጵያ ነጻነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል ያደረጉ በመሆናቸው ሲከበሩና ሲታወሱ መኖር አለባቸው ባይ ናቸው። ይህ ትውልድ የአርበኞችን ተጋድሎ ጠንቅቆ አያውቅም ብለውም ይሞግታሉ።

አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተዉ የሚገኙ ወጣቶችን ሚያዝያ 27 ስለሚከበረዉ በዓል ያላቸው ግንዛቤ ምን እንደሆነ ለመጠየቅ ሞክራለች። በዛ መሰረት የላብ አደሮች ቀን ይመስለናል፣ የአድዋ ድል በዓል ነው ያሉ የሚገኙ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ በዚህ ቀን የሚከበር በዓል ስለመኖሩም እንደማያውቁ ገልጸዋል። በአንጻሩ የኢትዮጵያ አርበኞች የድል መታሰቢያ ቀን ስለመሆኑም የገለጹም ነበሩ።

ታሪክን ስናወሳ
የኢትዮጵያ ኃይል የንጉሡ ክቡር ዘበኛን ጨምሮ ማይጨዉ ላይ ከወራሪዉ ኢጣሊያ ጋር የመልሶ የማጥቃት እርምጃ ወሰደ። ሆኖም ከባድ መሣሪያ ታጥቆ የመጣውን የኢጣሊያን ጦር ማሸነፍ አልቻለም።
ንጉሡም ይህን በመገንዘብ አገር መወረሩን ጠቅሰው እርዳታ ለመጠየቅ ወደ አውሮፓ አመሩ። ንጉሡ ከሄዱበት ጊዜ አንስቶም የኢትዮጵያ አርበኞች ወራሪዉን የኢጣሊያ ጦር ለመመከት ሴት ወንድ ሳይሉ በዱር በገደሉ የሽምቅ ውጊያ በማድረግ ፋታ መንሳት ጀመሩ። የኢጣሊያ ጦርም በአየርም ጭምር የታገዘ ድብደባ ማድረጉ ደግሞ ጦርነቱን የከፋ አድርጎት ነበር።

የኢጣሊያ ጦርም አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አዉርዶ በምትኩ የኢጣሊያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀለ። በእዚህ ሁኔታ የተቆጡ ጀግና አርበኞችም ትግላቸውን አጠናክረዉ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ተነሱ። ይሄኔ ንጉሡ የኢጣሊያን ወረራ በጄኔቭ ስብሰባ ላይ በመገኘት ለዓለማቀፉ ፍርድ ቤትም መፍትሄ ለማግኘት ሲጠይቁ ነበር።

ወቅቱ ደግሞ የኹለተኛው የዓለም ጦርነት ሊጀመር አገራት እርስ በእርሳቸዉ የተከፋፈሉበት ወቅት በመሆኑ ሰሚ አጡ። በአገር ውስጥም የኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን ተቆጣጥሬአለሁ ብሎ ካወጀበት ጀምሮ የአርበኞች ተቃዉሞ ቀጥሎ፣ ለአገሩ የሚሞተዉም በዛው ልክ ጨምሮ ነበር።

ሙሉቀን ታሪኩ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ – ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 1993 በሚል በተረጉሙትና በሳምፕሰን ጄሪ በተጻፈው ‹Early History of Ethiopia› በተሰኘ መጽሐፍ ተጠቅሶ እንደሚገኘው፣ የኢትዮጵያዊያን ተቃዉሞ የበለጠ በመቀጣጠል የካቲት 12/1929 (እ.ኤ.አ በ1937) ግራዚያኒ ላይ የግድያ ሙከራ ተደረገ። ይህንንም ተከትሎ ወራሪው ጦራ በወሰደዉ የበቀል እርምጃ በአንድ ቀን ከ30 ሺሕ በላይ የአዲስ አዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ አደረገ። በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችም ሰማዕትነትን ተቀበሉ።

ወራሪው የኢጣሊያ ጦር ይህ አልበቃ ብሎት ገዳማትን እና አብያተ ክርስቲያናትን፣ ምዕመናንን ሳይቀር ማቃጠልና መግደል ጀመረ። እርምጃው ኢትዮጵያን ከማረጋጋት ይልቅ ወደ ባሰ የተቃዉሞ ትግል ሲያስገባት ነበር። የጣሊያን መንግሥት በኢትዮጵያ አዲስ አስተዳደር በመሾም ከቀድሞ የተሻለ አስተዳደር ለማስፈን ሞከረች። ይህ ሁሉ ሲሆን አይበገሬዎቹ የኢትዮጵያ አርበኞች ተስፋ ባለመቁረጥ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምዕራብና በምሥራቅ ኢትዮጵያ የፋሺስቱን ኢጣሊያ ጦር ማጨናነቅ ቀጠሉ፤ እረፍት ነሱት።

አዲስ የተሾመው አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ መጠነ ሰፊ የመንገድ ግንባታ ጀመረ። ጎን ለጎንም ጣሊያናዊያን ከኢትዮጵያ ልጆች እንዳይወልዱና መኖሪያ መንደራቸውንም ከአገሬው ሕዝብ እንዲለዩ ሕግ አጸደቁ። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደርም ቅሬታ የነበራቸውን የአገር ውስጥ ተቃዋሚዎችንም ከአገሬዉ ሕዝብ በመለየት ከጎናቸው አሰለፋ።

ግራዚያኒ ላይ የግድያ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ወደ ጎጃም ያመለጡ የተማሩ ወጣቶች እ.ኤ.አ በ1938 መጀመሪያ ላይ ሰፊ የተቃዉሞ ዉጊያ አደረጉ። ንጉሡም በውጪ እርዳታ የመፈለግ ጥረታቸውን ቀጥለው ነበር። ሆኖም እ.ኤ.አ በ1939 የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመጀመሩ ጣሊያን ከጀርመን ጎን ተሰልፋ እንግሊዝን ለመውጋት ስትነሳ፣ እንግሊዝ በበኩላ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የኢጣሊያንን ጦር ከኢትዮጵያና ከምሥራቅ አፍሪካ ጠራርጋ ለማስወጣት ወሰነች።

በዚህም አጋጣሚ ለአምስት ዓመታት በየጫካውና ጉድጓድ ውስጥ እየተሹለከለኩ ጠላትን ከሕዝቡ ጋር በመሆን እረፍት ሲነሱ የነበሩት ጀግኖች የኢትዮጵያ አርበኞች፣ በስተመጨረሻ የእንግሊዝ ጦር እርዳታን በተለያየ አቅጣጫ ንጉሡ አስተባብረው ብቅ አሉላቸው። እንግሊዝም በአፍሪካ ያላትን ጦር ከደቡብ በኩል በኬንያ፣ በምሥራቅ ከእንግሊዝ ሶማሌ ላንድ፣ በሰሜን ደግሞ በሱዳን ያላትን ጦር በማንቀሳቀስና በጎጃም የሽምቅ ተዋጊዎች ጋር በመጣመር የወራሪዉ የኢጣሊያ ጦር ላይ ጥቃት ፈጸመ።

አገራቸውን ከጠላት ለማላቀቅ በርካታ ተጋድሎዎችን የፈጸሙና አርበኞችን ይመሩ ከነበሩት መካከል ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ራስ አበበ አረጋይ፣ ሸዋረገድ ገድል (የሸዋ አርበኛ)፣ ደጅ አዝማች በላይ ገብረማሪያም ጋሪ፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ (በጅማ)፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፣ ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ደጃዘማች ወንዲራድ ድፋባቸዉ፣ ፊታዉራሪ ዘዉዱ አባኮራን፣ ልጅ ኃይለማሪያም ማሞ እና ሌሎችም ሥማቸውን ጠርተን የማንጨርሳቸውና የሥም ዝርዝራቸው በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ በክብር ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ አርበኞች ሕይወታቸውን በመገበርና ዋጋ በመክፈል በስተመጨረሻ ከእንግሊዝ ጦር ጋር በመሆን የፋሺስቱን የኢጣሊያ ጦር ጠራርጎ በማስወጣት ሰቅሎት የነበረውን የኢጣሊያ ባንዲራ ልክ በአምስት ዓመቱ አውርዶ በምትኩ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውለበለበ። ንጉሠ ነገሥቱም ወደ ዙፋናቸው የተመለሱት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ነበር።

ታሪክ ሌላ የሚነግረን ነገር አለ። ይህም የአምስት ዓመቱ ጦርነት ማብቂያና የድል ቀን መጋቢት 28 ይከበር የነበረበት ወቅት እንደነበር ነው። መምህርና የታሪክ ተመራማሪዉ አበባው አያሌው እንደሚያስረዱት፣ ደርግ ወደ ሥልጣን እንደመጣ ከንጉሡ ጋር ተያይዞ በብሔራዊ ደረጃ ይከበሩ የነበሩ በዓላት በአብዛኛው ተሰርዘዋል። ይህም የንጉሡን የልደት ቀን ጨምሮ ሚያዝያ 27 ይከበር የነበረው የአርበኞች የድል በዓልን ወደ መጋቢት 28 ቀን እንዲከበር ተወስኖ ነበር።

ምክንያቱ ደግሞ በደቡብ በኩል ከእንግሊዝ ጦር ጋር የመጣው በእነ ገረሱ ዱኪ፣ በቀለ ወያ እና ሌሎች የደቡብ አርበኞች የሚመራው ቡድን አዲስ አበባ የገባዉ መጋቢት 28/1933 ስለነበር ነው። ጣሊያንን ቢያባርሩም ነገር ግን ተመልሶ የእንግሊዝ ባንዲራ በጣሊያን ባንዲራ መተካቱ በሕዝቡና በአርበኞቹ መካከል እንዴት ነጭን በነጭ እንተካለን በሚል ቅሬታ ተፈጠረ።

በወቅቱ ንጉሠ ነገሥቱ ደብረማርቆስ ላይ ከእንግሊዝ ጦር ጋር እና ከእነ በላይ ዘለቀ ጋር በመሆን መንገድ በማጽዳት ጊዜ ፈጅቶባቸው ነበር። ዘግይተው ሚያዝያ 27/1933 አዲስ አበባ ደረሱ። ንጉሠ ነገሥቱ ከገቡ በኋላ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ብዙ አለመግባባቶች ተፈጥረዉ የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን በንጉሡ እና የንጉሡን ጦር ተከትሎ የመጣዉ የራስ አበበ አረጋይ ጦርም ባለመስማማቱ ችግሩ በስተመጨረሻ ተፈትቶ ሚያዝያ 27/1933 ወደ ዙፋናቸው ተመለሱ። ከዚህ በኋላ የእንግሊዝ ባንዲራ ወርዶ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሰቀለ፤ አሉ አበባው አያሌው። ሕዝቡም ይህን ሲያይ የአገር ክብር መመለሱን ተቀበለ። ይህም ቀን የድል ቀን ሆኖ እንዲከበር ተደረገ።

ታድያ ደርግ ወደ መጋቢት 28 አድርጎት የነበረ ቢሆንም፣ እንደገና ደርግ ከሥልጣን ከወረደ በኋላ በ1984 በርካታ የታሪክ ምሁራን የተሳተፉበት ክርክር ተካሄደ። በዛም መጋቢት 28 ተሽሮ ወደ በፊቱ ሚያዝያ 27 እንዲመለስ ተደርጓል።
ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት የመከራና የግፍ ጊዜያት በኋላ በጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ ድል አገኘች። የኢጣሊያም ጦር ለኹለተኛ ጊዜ ሽንፈቱን ተከናንቦ ተሰናበተ። ይህ የአርበኞች ቀን ብሔራዊ በዓል ሆኖ መከበር የጀመረው ከ1934 ጀምሮ ነው።

ወደፊትስ?
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ጆቴ መስፍን ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፣ አሁን በአገር ውስጥ መግባባት ሳይኖር ሲቀር የሚኖረው ውጤትና መልስ አገር ማጥፋት ነው። ስለሆነም ጥንታዊ አባቶችና እናቶች ለአገር መስዋዕት እንደሆኑ ሁሉ አሁን ላይ ያለው ወጣትም ከመንግሥት ጋር ዘብ በመቆም አገር ያለችበትን ከባድ ሁኔታ ማሸጋገር ይኖርበታል ብለዋል።
‹‹ይህንን ያላደረገ ትውልድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መሥራት አይችልም። አገሪቷ አሁንም ድህነት ውስጥ ነው ያለችው። በጋራ ተባብረን ካልሠራን ደግሞ ወደፊትም አገራችንን ከድህነት ማላቀቅ አንችልም። አሁን ላይም ያለነው ድህነት ላይ ነው።›› ሲሉም የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አክለዋል።

በጋራ ተባብሮ መሥራት ካልተቻለ ወደፊትም ኢትዮጵያን ከድህነት ማላቀቅ አይቻልም ያሉ ሲሆን፣ ወጣቱ ትውልድ ያለፈው ትውልድ ለአገሩ የከፈለውን ዋጋ እንዲገነዘብና ታሪኩንም አዉቆ የተሻለ እንዲሠራ ታስቦ የአርበኞችን የድል በዓል መታሰቢያ እንደሚከበር አሳስበዋል።

‹‹የዘንደሮውም በዓል ሲከበር የመጡት ወጣቶች ናቸው። እኛም እንዲመጡ የምንፈልገው ተተኪ ወጣቶችን ነው፤ እኛ አቅማችን ደክሟል። ይህ የአርበኞች የድል በዓል እንደ አድዋ ወጣቱ እንዲያከብረውና ነገ እነሱም የየራሳቸውን የትዉልድ አሻራ ለአገራቸዉ ሠርተዉ እንዲያልፉ የተለያዩ ሚዲያዎች እና ትምህርት ቤቶች ኃላፊነት አለባቸዉ።›› ሲሉም ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በበዓሉ ታድመው ያገኘቻቸው አስተያየት ሰጪዎችም ሲናገሩ፣ ይህንን ክፍተት ከትምህርት ቤቶች ባሻገር በየጊዜው የሚመጡ መንግሥታት የመሙላት ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
በመታሰቢያ በዓሉ ላይ የታደሙ ተማሪዎች እና ሌሎች ወጣቶችም በበኩላቸዉ ‹‹አባቶቻችን አገራችንን ከጣሊያን ወረራና ግኝ ግዛት አዳኑ። እኛ ደግሞ አሁን ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ጠንክረን በመማር፣ በመሥራትና በጋራ በትብብር፣ የእምነትና የሃይማኖት ልዩነቶቻችን እንዳሉ ሆነው አንድ በምታደርገን አገራችን ጉዳይ ላይ ለዓለም ምሳሌ በሚሆን ደረጃ መሥራት አለብን።›› ብለዋል።

‹‹ትዉልዱን በማንቃትና በማስተማር እንደ አድዋ ድል ይህ የአርበኞች የድል ቀን በስፋት እንዲከበር የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ኃላፊነት አለባቸው።›› ሲሉ አስተያየት የሰጡት ደግሞ ከአዲስ ማለዳ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት መምህርና የታሪክ ተመራማሪ አበባው አያሌው ናቸው።


ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here