መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳከቫይረሱ ክትባቱ ለምን ተፈራ?

ከቫይረሱ ክትባቱ ለምን ተፈራ?

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዉያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እድሪስ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የብጹዕ ወቅዱስ ፖትሪያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤትና የውጪ ጉዳይ መምሪያ የበላይ ኀላፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ(ዶ.ር)፣ እንዲሁም በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስትያን የኢትዮጵያ ዩኒየን ፕሬዝዳንት ፓስተር ታደሰ አዱኛ መጋቢት30/2013 የኮሮና ቫይረስ ክትባት ተከትበዋል፡፡

የሐይማኖት አባቶች ኅብረተሰቡ አሁን ላይ እየተሠጠ ያለውን ክትባት በተገቢው ሁኔታ በመውሰድ ነገር ግን ባለው የክትባት አገልግሎት ሳይዘናጋ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን አጠናክሮ መተግበር እንዳለበት አሳስበው፣ አንዳንድ አካላት በሚነዟቸው የሀሰት መረጃዎች ምክንያት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚወሰዱ የመከላከያ ተግባራትን ለአፍታም ቢሆን ቸል ሊላቸው እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለዓለማችን ቤተኛ ከሆነ ወዲህ የዓለም አገራት አዲስ የኑሮ ዘይቤን እየተላመዱ ይመስላል። ወረርሽኙ በርካታ እንቅስቃሴዎችን የገደበ በመሆኑም ሰዎች ይህን በሽታ አጥፉልን የሚል ተማጽኖ ለሚያምኑት ፈጣሪ እንዲሁም ለቤተሙከራ ባለሞያዎች ሲያቀርቡ ነበር። ታድያ ቫይረሱ ከዚህ ቀደም ተከስተው ክትባት ከተዘጋጀላቸው ወረርሽኞች አንጻር አጭር በሚባል ጊዜ ክትባት ተገኘለት።

ሆኖም ግን ብዙዎች ይህን ክትባት መቀበል የፈለጉ አይመስልም። በእንቅርት ላይ እንዲሉ በአውሮፓ አገራት ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ‹‹የደም መርጋት ገጠማቸው›› የሚል መረጃ መሰራጨቱን ተከትሎ ክትባቱን ከወረርሽኙ ይልቅ የተፈራ አስመሰለው። የዓለም ጤና ድርጅት የደም መርጋት በጥቂት ሰዎች ላይ ያጋጠመና የክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት ይህን ያህል የማያሰጋ እንዳልሆነ ገለጸ።

ኢትዮጵያም በተለያየ መንገድ በሚደረግ ድጋፍ ‹አስትራዜንካ› እንዲሁም ‹ሲኖፋርማ› የተባሉ ክትባቶች ተረክባለች። የጤና ባለሞያዎችን ጨምሮ ባለሥልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶችም አንድም ለራሳቸው አንድም ለሕዝብ ለማሳየትና ተከተቡ ለማለት ተከትበው አሳዩ። ሆኖም ግን ማኅበረሰቡ ክትባቱን በሚመለከት ምን ዕይታ አለው? ክትባቱን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎችስ ምን ያህል ተጽእኖ ፈጥሮበታል? የሕክምና ባለሞያዎችስ ምን ይላሉ? የአዲስ ማለዳዋ ሰላማዊት ሽፈራው የተለያዩ ሰዎች ጋር ቃለመጠይቅ በማድረግ፣ የሕክምና ባለሞያዎችን በማናገርና የተለያዩ ሰነዶችን በማገላበጥ ተከታዩን የአዲስ ማለዳ ሐተታ አሰናድታለች።

በአፍሪካ ደረጃ፣ በኮቪድ 19 ስርጭት ደቡብ አፍሪካ በቀዳሚነት የተቀመጠች አገር ስትሆን እስካሁን ድረስ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በበሽታው ተይዘዋል። ቁጥራቸው ከ50 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿም በዚሁ ወረርሽኝ ሞተውባታል። እንደ ሲዲሲ አፍሪካ ዘገባ ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሞሮኮ፣ቱኒዚያ፣ግብጽ፣ኢትዮጵያ እና ናይጀሪያ ከፍተኛ የተጠቂዎችን ቁጥር በመያዝ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል።

ከአህጉሩ በበሽታው በተያዙ ሰዎች ከተመዘገቡ ቀዳሚ አምስት አገራት አንዷ ሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ ‹አስትራዜኔካ› የተሰኘውን የኮቪድ ክትባት ኹለት ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ብልቃጥ አግኝታለች።
በመጀመሪያው ዙር የሚሰጠውን የኮቪድ 19 ክትባት ከኮቫክስ ዓለም አቀፍ ጥምረት የተተገኘ ሲሆን ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው ለተባሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በመላው አገሪቱ ክትባቱን መከተብ ተጀምሯል።
የጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች፣ እድሜያቸው ከፍ ያሉ እና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን በቅድሚያ እንዲያገኙ እንደሚደረግ የጤና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት አቅርቦት ጥምረት ከተገኘው ኹለት ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ብልቃጥ አስትራዜኒካ ክትባት በተጨማሪ በመጋቢት 21/2013 ደግሞ 300 ሺህ ዶዝ የሲኖ-ፋርማ የኮቪድ19 ክትባት አገራችን ከቻይና ተረክባለች። ከቻይና በድጋፍ የተረከበችውን ክትባት ጨምሮ አስካሁን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶዝ የኮቪድ 19 ክትባት አገራችን አስገብታለች ማለት ነው። በዚህም 20 በመቶ የሚሆነውን የማኅበረሰብ ክፍል እስከሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ድረስ ለማስከተብ እየሰራች እንደሆነ የጤና ሚኒስቴሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።

የክትባቱ አገራችን መግባቱን ተከትሎ፣ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች የሚለቀቁትን እና በከተማችን ስለክትባቱ የሚናፈሱትን ወሬዎች ይዘን አሁን በአገር ውስጥ እየተሠጠ ያለውን የኮቪድ 19 ክትባት አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ያላቸውን ግንዛቤ አዲስ ማለዳ ለመቃኘት ሞክራለች።

ይህ ዳሰሳ ሲሰራ በሙያ ስብጥር እና በዕድሜ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችንና የከተማችንን የተለያዩ አካባቢ •ሪዎችን ያካተትን ሲሆን ጾታንም እንዲሁ ለማካከት ተሞክሯል።
ንጉሴ ዳኛቸው እድሜያቸው ከ 70 በላይ ሲሆን፣ ሾላ ገበያ አካባቢ •ሪ ናቸው። ከሥራ ገበታቸው በጡረታ ከተገለሉበት ጊዜ አንስቶ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ወደ እምነት ተቋማት በመሄድ ነው። የኮረና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኃላ ወደ ቤተክርስቲያን በሚሄዱበት ወቅት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በማድረግ እና የእጃቸውን ንጽህና በመጠበቅ ራሳቸውን ከኮሮና እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

ነገር ግን እርሰቸውን ጨምሮ በዳሳሳችን ካነጋገርናቸው አረጋዊያን መካከል አብዛኛቹ ስለ ኮሮና ቫይረስ በቂ በሚባል ደረጃ እውቀት ያላቸው ቢሆንም ስለ ኮሮና ክትባት ግን ያላቸው መረጃ አነስተኛ እንደሆነ ከምላሻቸው ለመረዳት ችለናል።
ከአረጋዊያኑ አብዛኛዎቹ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት መሰጠት መጀመሩን እንዳልሰሙ እና ከእድሜያቸው ጋር በተያያዘ የተለያዩ የጤና ችግሮች ስላሉባቸው ክትባቱ የሚያመጣባቸውን የጎንዮሽ ጉዳት ስለማያውቁት ለመከተብ እንደሚፈሩ አጫውተውናል። እንዲሁም አሁን የኖሩት እድሜ በቂ በመሆኑ ከዚህ በኋላ የማያውቁትን ባእድ ነገር ለመወጋት ብዙም ፍላጎት እንደሌላችው ገልጸዋል።

ሌሎች አረጋዊያንም በእድሜያቸው መግፋት የተነሳ ካሉባቸው የጤና እክሎች፣ በትምህርት ብዙም ያልገፉ ከመሆናቸው ጋር ተደምሮ፣ ስለ ኮሮና ቫይረስም ሆነ ስለ ክትባቱ በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው አዲስ ማለዳ ለመታዘብ ሞክራለች።
ወደ ትምህርት ቤቶች አካባቢም በመዘዋወር እድሜያቸው ከ15 እስከ 18 የሚሆኑ ከስምንተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ለማነጋገር ሞክረናል። ከአረጋዊያኑ በተሻለ ስለ ኮሮና ቫይረስም ሆነ ስለ ኮቪድ 19 ክትባት እውቀት ያላችው ሲሆን ራሳቸውን ከኮሮና ለመጠበቅ በሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶችም ሆነ በቤት ውስጥ ለኮሮና ቫይረስ የሚደረገውን ጥንቃቄ እንደሚተገብሩ ገልጸውልናል።

የክትባቱን መምጣት ተከትሎ ተማሪዎቹ ክትባቱን ይከተቡ ይሆን በሚል አዲስ ማለዳ ላቀረበችላቸው ጥያቄ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ተማሪዎች፣ የኮቪድ 19 ክትባትን የሚከተቡት ወላጆቻቸው ከፈቀዱላቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
አንዳንዶቹ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ ከአንዳንድ ግለሰቦች የኮሮና ቫይረስ ክትባት ደም ያረጋል የሚል እና ሌላም የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው መስማታቸውን ገልጸው ክትባቱን ለመውስድ ፈቃደኛ አይደለንም በማለት ተናግረዋል።
የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ በአሽከርካሪነት እና በረዳትነት የሚያገለግሉት እንደ ገረመው ክንዴ ያሉ ሰዎችን ያነጋገርን ሲሆን፣ በተለይ በህዝብ ማመላሻ ታክሲ እና በተለምዶ ሀይገር ተብለው በሚጠሩ ተሸከርካሪዎች ላይ የሚሰሩ ረዳቶች ስለ ኮሮና ቫይረስ በቂ የሚባል ግንዛቤ ቢኖራቸውም የስራ ባህሪያችን ግን ለመጠንቀቅ ብዙም አመቺ አይደለም ብለዋል።

በተለይ ደግሞ ማስክ ተደርጎ ከተሳፋሪ ጋር ለመነጋገርም ሆነ ተሳፋሪን ለመጥራት አመቺ አለመሆኑን አስታውቀዋል። በተጨማሪም ማስክ ያደረጉ ተሳፋሪዎች የሚወርዱበትን ቦታ ሲናገሩ ለመስማት አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ረዳቶቹ ገልጸዋል። በዚህም ተሳፋሪ ስንጠራ ማስካችንን አውልቀን እንጠራለን በማለት ይናገራሉ። “የታክሲ ሂሳብ ስንቀበል እና ስንመልስ ከሳንቲም እና ከብር ጋር በየደቂቃው ግንኙነት ስለሚኖረን ለኛ የኮቪድ ጥንቃቄ ለማድረግ እጅግ አዳጋች ሆኖብናል ብለዋል።”

ስለ ኮሮና ቫይረስ ክትባት በተሸከርካሪያቸው ውስጥ በሚከፈት ራዲዮ እና ተሳፋሪዎች ከሚያወሩት ወሬ ተነስተው መረጃ እንዳላቸው የገልጹ ሲሆን፣ ክትባቱ የደም መርጋት እና ሌሎች ችግሮች አሉበት ሲባል መስማታቸውንም ገልጸዋል። ነገር ግን ያላቸው የስራ ባህሪ የበለጠ ለቫይረሱ ተጋላጭ ስለሚድርጋቸው ክትባቱን ካገኙ ለመከተብ ፍቃደኛ እንደሆኑ አብዛኛዎቹ የታክሲ ረዳቶች ገልጸውልናል።

አዲስ ማለዳ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን አስመልክቶ ካነጋገረቻቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በቀን ሰራተኛነት የሚተዳደሩ ወጣቶች እና ጎልማሶች ይገኙበታል። ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አብዛኛዎቹ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁ ሲሆኑ ስለ ኮሮና ቫይረስ በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው ለመገንዘብ ችለናል።

- ይከተሉን -Social Media

ኮሮና አገርችን ውስጥ ገባ ከተባለ ጊዜ ጀምሮ የመጣው ሥራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት እንጂ ሌላ የተለየ ነገር አለመሆኑን ነው የገለጹት። ኮሮና መጣ ተብለን የምንሰራው ስራ አጥተን አብዛኞቻችን ወደ የመጣንበት ክፍለሀገር ተመለስን። ያጠራቀምነውን ጥሪት አሟጠን ከመብላት ባለፈ ሌላ ትርፍ አላገኘንም። ኮሮና ከረሀብ በላይ አይሆንም ፤ ረሀብ ጊዜ አይሰጥም። ኮሮና ገባ ተብሎ ከቤት አትውጡ በተባልንበት ጊዜ ለልጆቻችን የምናበላው እስከምናጣ ድረስ ተቸግረናል። ኮሮና ግን አንድ ዓመት አለፈው እኛም አለን፤ በማለት ተናግረዋል።

ስለ ኮሮና ክትባት ወደ አገር ውስጥ መግባት እና ክትባቱ እየተሰጠ መሆኑን ስንገልጽላቸው ለመከተብ ብዙም ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል። አብዛኛውን ጊዜ የኮሮና ክትባት ከባዕድ አምልኮ ጋ የተያያዘ ነው ሲባል መስማታቸውን ገልጸው፣ የኛ እምነት በፈጣሪ ላይ ብቻ ነው፤ ፈጣሪ ካመጣው ሞት ወደ የትም አይቀርም የሚል አንድምታ ያለው አስተያየት ሰጥተውናል ።

በቅድሚያ ወደ አገራችን የገባው ‹አስትራዜኒካ› የተሰኘው ክትባት የደም መርጋትና ሌሎች የጤና ችግሮችን ያስከትላል በማለት ጀርመንን ጨምሮ 13 የአዉሮፓ ኅብረት አባል አገራት ክትባቱን በጊዜያዊነት ከመስጠት አግደው እንደነበር የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ሲዘግቡ ተሰምቷል። ነገር ግን የአውሮፓ መድኃኒቶች ተቋም ይህን የአገራቱን አቋም በመቃረን፣ ‹አስትራዜኒካ› የተባለዉ ክትባት ጥቅም ላይ ሊዉል የሚችል፣ አስተማማኝነቱም የተረጋገጠ ነው፤ ብሎለታል። ኢትዮጵያ በበኩሏ የክትባቱን ተጓዳኝ ምልክት እያጠናች መከተቧን እንደምትቀጥልና የተባለው የደም መርጋት እንዳላጋጠመ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ነገር ግን አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ስለክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት የተሰጠውን ማሳሰቢያ የሰማ አይመስልም።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የኮቪድ 19 ሕክምና ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ ቀናኢ ፣ ክትባቱ ለሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ከመጋቢት 14/2013 ጀምሮ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይህም አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ኹለት ጊዜ (በዙር) እንደሚሰጥ ይናገራሉ። ክትባቱን መውሰድ የሰውነት ኮቪድን የመከላከል አቅም እንዲያመነጭ ከማድረጉ በተጓዳኝ ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ጽኑ ሕመም ለመከላከል ይረዳል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የክትባቱን አስተማማኝነት በተደጋጋሚ የሚያነሱት ዶክተር ደሳለኝ፣ ነገር ግን እንደ ማንኛውም ክትባት የጎንዮሽ ጉዳት ሊያጋጥም እንደሚችል ይጠቅሳሉ። ‹‹ከ20 እስከ 30 በመቶ ባሉ ሰዎች ላይ ክትባቱን ሲወስዱ ትኩሳት ያጋጥማቸዋል። ይህ ደግሞ ማንኛውም ክትባት ሲወሰድ የሚያጋጥም ነው።›› በማለት ጊዜያዊ ትኩሳትና ድካም ሊያጋጥም እንደሚችል ይጠቁማሉ። የጎንዮሽ ጉዳቱን በሚመለከት በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ያልተጨበጠ መረጃ ሲነገር ይሰማ እንጂ፣ ክትባቱ የሚያደርሰው ከባድ የጎንዩሽ ጉዳት እንደሌለ ነው ባለሙያው የሚገልጹት።
እንደ ዶ/ር ደሳለኝ ሃሳብ ክትባቱን ከመስጠት በፊት ግን መደረግ ያለበት ጥንቃቄ እንዳለ አሳስበዋል። ይህም ሰውነታቸው አለርጂ ያለባቸው፣ ሰውነታቸው እየደማ ያሉ ሰዎች፣ እንዲሁም ነፍሰጡር ሴቶች ክትባቱን መውሰድ እንደሌለባቸው መክረዋል። የሚያጠቡ ሴቶች ግን መከተብ እንደሚችሉ ዶክተር ደሳለኝ ያስረዳሉ።

በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ ክትባት አማካሪ ዶክተር ሙሉቀን ዮሐንስ የኮቪድ 19 ወረርሽኝም ሆነ ክትባት በእኛ እድሜ ያየነው ግዙፍ የሆነ ዓለማቀፋዊ ክስተት ነው ብለዋል። እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ደግሞ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ በጎ ያልሆነ ተጽዕኖ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ስለ ኮሮና ቫይረስ ክትባት በቂ እውቀት እንዲኖረው በሁሉም የመገናኛ ብዙኀን ግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች እንለቃለን፤ ነገር ግን ትልቁ ጉዳይ ህብረተሰቡ ለምንድነው ክትባቱን ለመውሰድ የፈራው የሚለው በመሆኑ ክትባቱን እየተለማመደ ሲመጣ እና የሚከተቡ ሰዎችን ማየት ሲጀምር ሀሳቡን መቀየሩ የማይቀር ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ዶክተር ሙሉቀን ኀብረተሰቡ አልከትብም ሊል የሚችለው ጥቅሙን ባለማወቅ፣ ከ 666 እና ማይክሮ ቺፕስ ጋር በማገናኘት የሚናፈሱ ወሬዎችን በመስማት በመሆኑ ብዙ ሰዎች እየተከተቡ ሲሄዱ እና የክትባን ጥቅም ሲሰሙ ግንዘቤያቸው እንደሚጨምር ተናግረዋል።
የኮሮና ክትባት መሰጠት ቢጀምርም በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ግን በየቀኑ እየጨመረ መምጣቱን የጤና ሚነስቴር አሳስቧል። ለጽኑ ህሙማን የሚረዱ የመተንፈሻ ቬንትሌተሮች እና የኦክስጂን እጥረት በመኖሩ ህብረተሰቡ የበለጠ ራሱን እንዲጠብቅም የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት በግል ስልካችን ጭምር መልዕክት በመላክ እያሳሰበ ይገኛል።

- ይከተሉን -Social Media

ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከገባ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛው የሞት መጠን በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ተመዝግቧል። የጤና ሚኒስቴር ሰኞ እለት 37 ሰዎች በኮሮና ሳቢያ ውድ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ገልጿል።
አሁን ያለውን የኮቪድ 19 ስርጭት ለመቀነስ የመንግስትም ይሁን የግል ሚዲያዎች በበሽታው ዙሪያ አሁን ያለውን አስፈሪ የጉዳት መጠን በደንብ የሚገልፁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችና ማስታወቂያዎች ተከታታይነት ባለው መንገድ ቢሰሩና ለአድማጭ ተልመካቾቻቸው ቢያደርሱ መልካም እንደሆነ አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሀሳብ ተነስታ እንደ አንድ መፍትሄ ትጠቁማለች።

አስተያየት ሰጪዎቻችን አክለውም አሁንም ድረስ በኮቪድ እየተጠቁ ያሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፣ ክትባቱ የሚሰጠውም ለሁሉም ኅብረተሰብ ባለመሆኑ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል። መረጃ ከባለሙያዎች መውሰድ ተገቢ እንደሆነም ዶክተር ደሳለኝ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ተገኝተው ክትባቱን ባስጀመሩ ዕለት፣ በዓለማቀፍ ደረጃ የክትባት ውሱንነት መኖሩን በመግለፅ ኅብረተሰቡ ክትባት ተጀመሯል ብሎ መዘናጋት እንደሌለበት አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች