አዲሱ የምጣኔ ሀብት መርሃ ግብር ምን ያመጣ ይሆን?

0
1064

በኬሚካል ማስመጣት ንግድ ላይ የተሰማራዉ ፍሬዘር አበበ በአስመጪነት ዘርፍ ከተሰማራበት ጊዜ አንስቶ ያለምንም እንቅፋት ሥራ የሠራበት ጊዜ አልነበረም። ከተጓተቱ የአሠራር ሒደቶች አንስቶ እስከ የጉምሩክ የአሠራር መርዘም ድረስ ትልቅ እንቅፋት እንደሆነበት ይገልፃል። ይህም፤ ለተጨማሪ ወጪ እንደዳረገዉና አንዳንዴም ኪሳራ ላይ እንደሚወድቅ ይናገራል።
ይሁን እንጂ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ የኢትዮጵያን የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን ለማሻሻል የሚያስችል ብሄራዊ መርሃ ግብር ተከትሎ፤ ፍሬዘር አሁን ላይ ተስፋን ሰንቋል። የስራ ፈጠራ መርሃ ግብር አካል የሆነዉ እና በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ያግዛል የተባለዉ ይህ መርሃ ግብር በ10 አስፈፃሚ ተቋማት የሚተገበሩ 80 ተግባራትን ያካተተ ነዉ። ዓላማውም፤ ባለፈው የዓለም ባንክ ሪፖርት መሠረት፤ ለንግድና ኢንቨሰትመንት ምቹ በሚል መለኪያ ከ190 አገራት 159 ያለውን የአገሪቷ ደረጃ ማሻሻል ነው።
በመርሃ ግብሩም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር ይፋ የተደረጉት የሕግና የአሠራር ማሻሻያዎች ማድረግ ፣ የተፋጠነ የመንግሥት አገልግሎት መስጠት፣ የብድር አቅርቦትን ማሻሻል የሚሉት ዋነኞቹ ናቸዉ። ይህንንም መርሃ ግብር ተግባራዊ በማድረግ በ2020 ኢትዮጵያን ወደ ቀዳሚዎቹ መቶ ከፍ ማድረግ ግብ ይዟል። መርሃ ግብሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቆጣጣሪነት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚያስተባብረዉ ይሆናል ተብሏል።
በኢትዮጵያ የለዉጥ ንፋስ መንፈስ ከጀመረበት ካለፈዉ መጋቢት 2010 ጀምሮ በርካታ ማሻሻያዎችና ስር ነቀል ለዉጦች በመንግሥት ተቋማት ላይ ተከናዉኗል። ይህንም ተከትሎ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለሕዝብ ጥራት ያለዉ እና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ረገድ እመርታ አሳይተዋል ተብሎ ይነሳል።
ምን ምን ያካትታል?
አሁን ላይ ደግሞ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ዙሪያ በጠቅላይ ሚንስትሩ ይፋ የሆነዉ መርሃ ግብር ለአዲስ ንግድ ጀማሪ፣ በግንባታ ዘርፍ ለተሰማሩ ከፍቃድ ጋር በተያያዘ እና የዉጭ ንግድን አካቶ የያዘ ነዉ። ይህ መርሃ ግብር የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ ጊዜ እና የረጅም ጊዜ በሚል የተከፋፈለ ሲሆን ለዉጥ እንደሚያመጣም እንደ ፍሬዘር ባሉ ነጋዴዎች ተጠብቋል።
ከዚህ በፊት በንግድ ፍቃድ ማዉጣት ሂደት ላይ አዲስ ንግድ ጀማሪዎች እንደ ቅድመ ሁኔታ ማሟላት የሚጠበቅባቸዉ ነገሮች እንደ ኪራይ ዉል፣ የድርጅት ስም እና ማኅተም ማሳወጅ እንዲቀሩ ተደርጓል። አንድ ሳምንት በላይ ይፈጅ የነበረዉንም የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ማግኘት ሂደት ወደ 3 ቀናት ዝቅ ለማድረግ በአጭር ጊዜ ወስጥ ለመተግበር ታቅዷል።
በአንድ መስኮት የሚያልቅ የንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደት በንግድና ኢንዱሰትሪ ወይም በክፍለ ከተማ እንዲያልቅ የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ እንዲሆንም የአጭር ጊዜ እቅድ ተይዞለታል። የንግድ ምዝገባ ሂደቱም ዘመናዊ እንዲሆን እና የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ አትሞ የሚያወጣ ሶፍትዌር ተግባራዊ እንዲሆን የታቀደ ሲሆን ይህም ተጨማሪ እሴት ታክስ የተመዘገበ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ግዴታ መሆን እንደሚያስቀርና በመካከለኛ ጊዜ እቅድ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።
በረጅም ጊዜ እቅድ በፌደራል እና በክልሎች ያሉ የንግድ ተቋማትን እርስ በርስ እና ከሚመለከታቸዉ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ጋር በመረጃ መረብ እንዲገናኙ የሚያደርግ አሰራር ይፋ ሆኗል። በግንባታ ዘርፍ ላይ በመርሃ ግበሩ እንደተቀመጠዉ የግንባታ ፈቃድ ማግኘትና የክፍያ አፈፃጻም ሂደትን ዘመናዊ በማድረግ ይወስድ የነበረዉን ጊዜ የሚያሳጥር ነዉ። ንብረት ለማስመዝገብ እና የካርታ ምዝገባዉን በቴክኖሎጂ በማዘመን ቀልጣፋ አሰራርን ተግባራዊ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀዉ መርሃ ግብር ዘርፉ ለሚያስፈልገዉ የኤሌክትሪክ ኃይል ጥያቄ ደግሞ ማሟላት የሚኖርባቸዉን መረጃዎች እንዲቀነሱ የሚያደርግ ሲሆን በወቅቱ አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛል። በመረጃ መረብ የሚታገዝ የአከፋፈል ታሪፍም ተግባራዊ ይሆናል። የሚጠየቀዉም አገልግሎት በአጭርና በተገቢዉ ጊዜ እንዲያገኙ የሚያስችል ነዉ።
ኢትዮጵያ ከዉጭ ሃገራት ጋር የሚያገናኛት የገቢ እና የወጪ ንግድ ላይም አዲሱ መርሃ ግብር በርካታ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህም በዘርፉ ለተሰማሩት ባለሀብቶች ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረዉ ይጠበቃል። በዚህም ረገድ በጉምሩክ ዉስጥ አዳዲስ ሕግና ደንቦችን በሥራ ላይ በማዋል (custom clearance) በኮፒ ማስረጃዎች እንዲከናወን እና አዲስ የጉምሩክ አገልግሎት ክፍያም እነደሚጀምር ታዉቋል።
ዕቃዎቹም ሃገር ዉስጥ ከመድረሳቸዉ በፊት የቀረጥ አከፋፈል ሂደቱ መጨረስ የሚቻልበትም ሁኔታ ይመቻቻል።በዋና ዋና ደረቅ ወደቦች ላይም (ሞጆ እና ቃሊቲ) በቀን 24 ሰዓት እና 7 ቀናት በሳምንት አገልግሎት እንዲሰጡና የጉምሩክ ሂደቱንም ለማሳጠር የአጭር ጊዜ እቅድ ተይዞለታል። ከኢትዮጵያ ጅቡቲ ድረስ በተዘረጋዉ የገቢ እና ወጪ ንግድ ሂደቱ ላይ ከነበሩት 4 የፍተሻ ጣቢያዎች ወደ 2 እንዲቀነስ በ መካከለኛ የጊዜ እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ተወስኗል። በረጅም ጊዜ እቅድም መርሃ ግብሩ በወጪ እና ገቢ ንግድ ላይ ሊያጋጥሙ ይችላሉ የሚባሉትን ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ታቅዷል።
በዚህ መርሃ ግብር ዉስጥ የብድር ሁኔታም የተካተተ ሲሆን በተለይም ለአዲስ ንግድ ጀማሪዎች ብድር የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች አዳዲስ አሰራሮች ይተገበራሉ። በዚህም ረገድ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት እነዲሰፉና እነዲያድጉ ብሎም በዋስትና የብድር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ብዙኀኑን መድረስ እንዲችሉ ይታገዛሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ የዋስትና ምዝገባ ሂደት ተግባራዊ ይሆናል።
የመርሃ ግብሩ ጠቀሜታ ለነጋዴዉ
ለባለፉት ስምንት ዓመታት የጉምሩክ አስተላላፊ የሠራው ሳሙኤል መረሳ አብዛኛዉን ጊዜ ጥራት ያለዉ ሥራ መስራት እንደሚቸገሩ እና በጉምሩክ በኩልም የሥራ ሰዓት ስለማይከበር ለዕቃዎች አላስፈላጊ የወደብ ኪራይ እንደሚከፍል ይናገራል። ይህ መርሃ ግብርም መፍትሄ እንደሚያመጣለት ይጠብቃሉ።
ሌላዉ በቅመማ ቅመም ወደ ዉጭ በመላክ ሥራ ላይ የተሰማራዉ ሚካኤል ተፈራ እንደሚናገረዉ ደግሞ ዕቃዎች ወደ ወደብ በሚጓጓዙበት ጊዜ የሚፈጠሩ ችግሮች በርካታ ናቸዉ። መርሃ ግብሩም ይህን ከመቆጣጠር አኳያ አካታች መሆኑ ጠቃሚ ነዉ ይላሉ።
ከአገራዊ የምጣኔ ሀብት ጠቀሜታዉ አንፃር ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር አጥላዉ አለሙ (ዶ/ር) እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የነበረዉ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መር ኢኮኖሚ ጨርሶ መጥፋት ያለበት ነዉ።
የእኔን ደጋፊ ብቻ በኢኮኖሚ ላጎልብተዉ የሚል እና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የነበረበት ነዉ። ‹‹ይሄ መርሃ ግብር የመንግሥት ድጋፍ በግሉ ዘርፍ ላይ የሚስተዋልበት ነዉ ይህም ትክክለኛ የማኅበራዊ ምጣኔ ሀብት አካሄድ ነዉ›› ይላሉ።
አያይዘዉም እንደተናገሩት፤ ከዚህ በፊት ንግድ ለመጀመር የተንዛዛ አካሄድ ስለነበር ሰዎች ለመሥራት አይበረታቱም ነበር። ‹‹ይህም ሰርተዉ ግብር በመክፈል ለአገር ምጣኔ ሀብት እድገት የሚጠቅሙትን ሰዎች ያስቀራል›› ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ስለተጠቀሰዉ ብድር ሁኔታ አጥላዉ ሲናገሩ የብድር ሁኔታ ለሁሉም ንግድ ጀማሪ አስፈላጊ ነዉ ይላሉ። እንዲያዉም ዋስትና ሳያስፈልጋቸዉ የስራዉ አዋጭነት ታይቶ በኢትዮጵያዊ ዜግነታቸዉ ብቻ ብድር ሊመቻችላቸዉ ይገባል ብለዋል።
አያይዘዉም ‹‹ከዚህ በፊት አዋጭነታቸዉ በግልፅ ለማይታወቁ ንግዶች ከፍ ያለ ገንዘብ ብድር ሲመቻችላቸዉ እንደነበርም ገልፀዉ አገራዊ የምጣኔ ሀብት ኪሳራ ወስጥ የሚከት አሠራር ነዉ ሲሉ ተናግረዉ በፓርቲ ባለቤትነት ሥር የሚገኙት ድርጅቶች መወገድ አለባቸዉ›› ሲሉ አክለዋል።
ነገር ግን ማስተካካያው ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ተጽዕኖ ውጭ መሆን አለበት ይላሉ ባለሙያው። ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፤ ሁልጊዜም ጥቅማቸዉን መሠረት አድርገዉ ስለሆነ የሚሰሩት ጥቅማቸዉን ከማስጠበቅ አንፃር በአገራት ላይ አቅጣጫ የማስቀየር ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ ብለዋል።
በሌላ በኩል፤ ተኬ አለሙ (ዶ/ር) የተባሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ከመርሃ ግብሩ ጋር በተያያዘ የሚያስፈራቸው ነገር የአስፈጻሚ አካለት ደካማ መሆን ነው። አስፈጻሚ አካላት በሰው ኃይልም ሆነ በዕውቀት ክፍተት ስላለባቸው፤ መርሃ ግበሩ አፈፃፀሙ ላይ ከፍተት ሊኖረው ይችላል ይላሉ። ስለዚህም የእነዚህን አካለት አቅም ግንባታ ላይ መሠራት አለበት ብለዋል።
በተጨማሪ፤ በዚህ መርሃ ግብር አተገባበር ላይም አንዳንድ ፍራቻዎች ይስተዋላሉ። ከፍተሻ ጣቢያዎች ጋር በተያያዘ ቁጥራቸዉ መቀነሱ አሁን ካለዉ የሕገ ወጥ መሣሪያ ዝዉዉር ጋር ስጋት ሊሆን ይችላል ተብሏል። ሌላዉ ደግሞ ከዚህ በፊት የወጡት ሕግና ደንቦች የአፈፃፀም ሁኔታ ደካማ ስለነበሩ ያሁኑ መርሃ ግብርም ላይ ሥጋት አለባቸዉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here