ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ታግያለሁ ቢልም በተግባር ያልተገለጠ ነበር የሚሉት አዲሱ ደረሰ፥ በተለይ በኦሮሞ እና በአማራ ማኅበረሰብ መካከል አለመተማማን እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር አጋር የሚላቸውን ደግሞ ሌሎቹን ከሥልጣን ያገለለ ስርዓት አንብሮ ማለፉን ማስረጃዎችን በማጣቀስ በመጣጥፋቸው አስታውሰዋል። ድኅረ ሕወሓት፥ በተለይ በኦሮሞ እና በአማራ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ልኂቃን መካከል የተፈጠረው የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የቃላት ትግትግ ውጤቱ ዳግማዊ ሕወሓትን ከማዋለድ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም አምባገነን እንዲሆኑ መደላድል ከመፍጠር የዘለለ ፍይዳ አይኖረውም ሲሉ ከታሪክ አጣቅሰው መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ሹማምንቶቻቸው ከመገናኛ ብዙኀን አጋራቾቻቸው ጋር ተባብርው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ብለው የጠሩት፤ ነገር ግን “ጦርነት” ለመባል ብቁ የሆነው የማዕከላዊው መንግሥትና የሕወሓቶች ግብግብ ወደ መገባደጃው የደረሰ ይመስላል። የቡድኑን የአንድ ወቅት አድራጊ ፈጣሪ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋል ተከትሎ፤ ደስታም ሃዘንም የሚያንጸባርቁ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ክርክሮች እየተነሱ ይገኛሉ። ከምንም በላይ ውሃ የሚያነሱት ግን የአማራና የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት ዳግማዊ ሕወሓት እንዳይሆኑ መልዕክት የሚያስተላልፉት መልዕክቶች ሆነው አግኝቻቸዋለው።
እነዚህ በኹለት ቡድን ውስጥ የተደራጁ ባለሥልጣናት እጃቸው ላይ የወደቀውን ኀላፊነት መረዳታቸውን ከመፈተሻችን በፊት፤ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የክርክር ነጥብ እንዲሆን አንድ ነገር ላይ መስማማት ያሻል። ሕወሓት ይዘውረው ነበር ተብሎ በሚታማው ኢሕአዴግ ዘመን የተተከለው ስርዓት “የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት በማስፈን ቅንነት ታስቦ የተተገበረ ነው ወይ?” የሚለው ጥያቄን መመለስ ነው። በአጭሩ ይህ ጽሁፍ ለመነሻው ስርዓቱ የብሔር ብሔርቦችን እኩልነት የማምጣት ቅንነት ያልነበረው ነው በሚል ይመልሳል።
ምላሹን ለማብራራት ያክል፡- አንደኛ ያንን እኩልነት ለማምጣት ቅንነት የነበረው ስርዓት ለምን የሶማሌን፣ አፋርን፣ ቤኒንሻንጉል ጉሙዝን፣ ሐራሪን፣ ጋምቤላን፣ አዲስ አበባን እና ድሬዳዋን ሕዝቦች በራሳቸው ጉዳይ ላይ እንዲወስኑ ማድረግ አልፈለገም? ደቡብ ክልል ተብሎ በተጠራው ክልል ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች የክልሉ አወቃቀር አልተስማማንም ለሚለው ጥያቄያቸው ምላሽ ለምን በፌደሬሽን ምክር ቤት በኩል ሳይሆን በመከላከያ በኩል ሲደርሳቸው ኖረ? በሕወሓት፣ በብአዴን፣ በኦሕዴድ እና በደሕዴን መካከል እኩል የመወሰን ሥልጣን ነበረ ብለን ብንስማማ እንኳን እነዚህ አራቱ ብቻቸውን በጋምቤላ፣ በሶማሌ እና መሰል ክልሎች እጣ ፋንታ ላይ እንዲወስኑ የሚያስችላቸው የብሔረሰቦች እኩልነት ጽንሰ ሐሳብ የትኛው ነው?
ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት ባለመቻሉ፥ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ መልሱ ኢሕአዴግ የብሔረሰቦችን እኩልነት ለማምጣት ተግባሩ ቀርቶ ሐሳቡም እንኳ አልነበረውም ብሎ ይነሳል። ይህንን ተከትሎ ከኢሕአዴግ የብሔረሰቦች እኩልነት ጀርባ የነበረው፤ የውስን አድራጊ ፈጣሪዎች ገዢ አስተሳሰብ ታዲያ ምን ነበር? ሲል ይጠይቃል። የዚህ ጽሁፍ መላምት፤ የብሔረሰቦች አኩልነት ትርክት፤ ለመላው ብሔረሰቦች እኩልነት ያልታሰበ እና በቀጥታ የአማራ እና የኦሮሞ ማኅበረሰቦች ግንኙነት ላይ ያነጣጠረ ነበር የሚል ነው። መላምቱን በተወሰኑ ጥናታዊ ድርሳናት እናስደግፍ።
ጣሊያን በኹለተኛው ወረራ እንዴት ተሳካላት?
ጣሊያኖች በአድዋ ላይ ሽንፈትን ቀምሰው ከተባረሩ በኋላ እስከሚቀጥለው ወረራ ድረስ እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። “እንዴት ተሸነፍን? በሚቀጥለውስ ለማሸነፍ ምን መደረግ አለበት?” በሚል በሮም ሹማምንት እና በፊታውራሪዎቻቸው መካከል ጠንከር ያለ ውይይት ሲደረግ ነበር የከረመው። የእነዚህ ውይይቶች እና የውስጥ ለውስጥ ጥናቶች ያመጧቸው ውጤቶች ላይ ተመስርተው ስለተገበሩት ፖሊሲ በጨረፍታ የሚያስቃኘን አሕመድ ሃሰን ኦማር ነው።
አሕመድ የጣሊያኖች ተጽዕኖ በብሔረሰቦች ግንኙነት ላይ በሚል ባጠናውና በ2000 (እ.አ.አ.) በኢትዮፒክ የጥናትና ምርምር ኅትመት ላይ ባሳተመው ጽሁፉ ስለጉዳዩ ጥቂት አካፍሎናል። ጣሊያኖች በኹለተኛው ወረራቸው ወቅት ኢትዮጵያን በቀጥታ በኀይል ከማንበርከክ በፊት ከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ሊተገበር እንደሚገባው ተማምነው መምጣታቸውን ያሳያል። ለዚህ ፖሊሲ ደግሞ የኢትዮጵያ በሃይማኖት እና የጎሳ ልዩነት መስመሮችን በሚገባ መጠቀም እንዳለባቸው በፖሊሲያቸው መያዛቸውን አሕመድ ያነሳል።
ከኢትዮጵያ ሁሉ ደግሞ ሸዋ፤ በልዩ ሁኔታ ደግሞ ሰሜን ሸዋ የመጀመሪያ ዒላማ ነበር። ሰሜን ሸዋ የተመረጠው በኹለት ምክንያት ነው። አንደኛ ግዛቱ የአገሪቱ ጥንካሬ የስህበት ማዕከል መሆኑ ነው። የስህበት ማዕከል ያደረገው ምክንያት እራሱ ደግሞ ደካማ ጎኑ ነው። ሰሜን ሸዋ የአማራ እና የኦሮሞ ጎሳዎች ተሰባጥረው የሚገኙበት ከመሆኑ በተጨማሪ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች እንዲሁ ተሰባጥረው የሚኖሩበት በመሆኑ ነው። የእነዚህ ማኅበረሰቦች በአገራዊ ስሜት መንቀሳቀስ ለአገሪቱ ጥንካሬ ሊውል ሲችል፤ እነዚህን የልዩነት መስመሮችን ፈልፍሎ መግባት ለቻለ ደግሞ ዋንኛውን የአገሪቱን ደካማ ጎን አገኘ ማለት ነው።
ስለዚህ ሸዋን፤ በተለይ ሰሜን ሸዋን ማጥቃት መላው ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ዋንኛ ፖሊሲ እንዲሆን ታቅዷል- ከኀይል እርምጃም በፊት። ግን ሸዋ ሳይደርሱ ሸዋን ማጥቃት እንዴ ይቻላል? በወሬ፣ በትርክት! ለመሆኑ ሸዋን/ሰሜን ሸዋን ለማንበርከክ የተነዛው ወሬ ምን ነበር?
የአጼ ኃይለ ሥላሴ የግዛቱ ጠቅላይ ገዢ የነበሩት ከበደ መንጋሳ ጦራቸውን አሰባስበው በማይጨው ጦርነት ለመሳተፍ በ1928 ወደ ሰሜን ይጓዛሉ። ከመጓዛቸው በፊት የክልሉን ጸጥታ እንዲያስተዳድሩ ዲንጎ ኦመርን ሾመው ይሄሉ። ዲንጎ ኦመር ከአጼ ሚኒሊክ ጀምሮ የጂሌ ኦሮሞዎች መሪ የነበሩ ሰው ነበሩ። ዲንጎ በሥራቸው ያሉትን የኦሮሞ ወታደሮችን ከአማራ ማኅበረሰብ ከተውጣጡ ወታደሮች ጋር ደምረው የግዛቱን ጸጥታ የማስጠበቅ ኀላፊነት ይሰጣቸዋል። ሹመት ካለ በሹመት የሚከፋም አይጠፋምና የገደም ባላባት የነበሩት ወርቁ ማሳ በጉዳዩ ደስ ያላቸው አይመስልም።
የማይጨው ጦርነት ባልተጠበቀ ሁኔታ በሽንፈት ተጠናቀቀ። ለጣሊያኖቹ ይህን የመሰለ አጋጣሚ አልተገኘም። ወሬው በአፋጣኝ ተቀነባበሮ ለባላባት ወርቁ እንዲደርሰው ተደረገ። “የማይጨው ሽንፈት የተከሰተው አካባቢው ላይ የነበረው የኦሮሚኛ ተናጋሪ ተገልብጦ የኢትዮጵያን ጦር በመውጋቱ ነው፤ እንዲያውም እርምጃው የጂሃድን የሚመስሉ ምልክቶችም ነበሩት” የሚል ነበር። ወትሮም ሹመቱ ያልጣመው ወርቁ፤ ሰሜን ሸዋን እየዞረ ወሬው ለሁሉም ሹማምንት እንዲደርስ አደረገ።
የሸዋ መበተን፤ የአገሪቱ እጅ መስጠት መሆኑ የገባቸው አዲሱ ተሽዋሚ ዲንጎ፤ አሉባልታው ሸዋን እንዳይበታትን ከአንዱ ባላባት ወዳንዱ ባላባት እየተመላለሱ መምከርን ያዙ። የእሳቸው ልፋት ፍሬ እንዲያፈራ እንኳን እድል ሳይሰጠው ወርቁ ወትሮም አላማሩኝም ያላቸው ባላባቶችና ጦሮቻቸው ላይ ጦሩን ያዘምት ጀመር። ዲንጎም አልተሳካላቸውም። አማራ ነኝ ባዩ ቀስ እያለ ወደሰሜን ሸዋ ከፍተኛ ቦታዎች ማፈግፈጉን ጀመረ፤ ኦሮሞ ነኝ ባዩም ነገሩ አልጣመውም፤ ጦሩን ይዞ ወደ ረባዳማ ስፍራዎች ሸሽቶ ነቅቶ መጠበቅን መረጠ።
መሃል መንገዱ ወለል ብሎ ለጣሊያኖች ተከፈተ። የጣሊያኑ የጦር መሪ ፔትሮ ባዶግሊዮ አዲስ አበባ የገባበት መንገድ ምን ያክል ቀላል እንደነበር ሲያስረዳ “የጠላት ጦር በሕይወትም ያለ አይመስልም፤ መንገዱ ሁሉ አልጋ ባልጋ ነበር” እንዳለ የአሕመድ ጥናት ማስረጃ አጣቅሶ ያሳያል። ጣሊያን በኹለተኛው ወረራ እንዴት ተሳካለት ብሎ ለሚጠቅይቅ፤ ሸዋ በሚል መዋቅር ውስጥ በአንድነት ተጣምረው የአገር አንድነትን የማስጠበቅ ስትራቴጂካዊ እና ፖለቲካዊ ኀላፊነታቸውን ሲወጡ የነበሩት ኦሮሞ እና አማራ ነን ባይ ሹማምንት መተማመን ስላቃታቸው ተሳካለት ብላችሁ አስደረዱ።
ታዲያ ይሄ ከብሔረሰቦች እኩልነት ጋር ምን አገናኘው?
የብሔረሰቦች እኩልነት ሻምፒዮና ነኝ የሚለው ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ ከነበረባቸው 27 ዓመታት ምን ያክል የባህል፣ የቋንቋ እና የትውፊት ጥናቶች ተካሄዱ? ለመሆኑ የብሔረሰቦች እኩልነት፣ የተለያዩ ጎሳዎች በየዓመቱ ኅዳር 29 በየከተሞቹ እየተዟዟሩ ከሚያሳዩት ዳንስ ባሻገር ምን ፈየደ? ክልል የተሰጣቸው ብሔረሰቦች እንኳን፤ አይደለምና እስከመገንጠል መብት ሊኖራቸው፤ የራሳቸውንም ፕሬዝዳንቶች ሲመርጡ እንዳልነበር ማስረጃዎችን ማግኘት አይቻልም ወይ?
በአንጻሩ በአማራና በኦሮሞ ነን ባይ ማኅበረሰቦች መካከል አለመተማመንን ሊፈጥሩ የቻሉ ምን ያክል መጻሕፍት ተጻፉ? ምን ያክል ጥናቶችስ ተሰሩ? ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ማስታወሻ ሳይገነባ፤ የአኖሌ ሃውልት የተገነባበትስ እንድምታ ምንድን ነው? የብሔረሰቦች እኩልነት ሻምፒዮና የነበረ ስርዓት፥ እንደው ግፋ ቢል ኦሮሚኛን እንኳን የፌደራል ቋንቋ ማድረግ ለምን ተሳነው? በእርግጥስ የብሔረሰቦች እኩልነት ትርክት፤ በኹለቱ ማኅበረሰቦች መካከል ቋሚ አለመተማመንን አስፍኖ በተሳካ ሁኔታ ሸዋን ከመበታተን ውጪ ሌጋሲው ምን ነበር?
በርግጥ የኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ መምጣት ቀጥተኛ ምክንያቱ የኹለቱ ማኅበረሰቦች አለመተማማን ነው ማለት አይቻልም። ከዚያ ይልቅ ለስርዓቱ መንገስ ዋንኛ ተጠያቂው የደርግ ስርዓት ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጠረው ምሬት ነው የሚለው ትንታኔ ያደላል። ታዲያ ኢሕአዴግ አይደለምና የሁሉንም የብሔረሰቦች ይቅርና አራቱ ፓርቲዎች በሚወከሏቸው ብሔረሰቦች መካከል እንኳን እኩልነት ሳያመጣ እንዴት 27 ዓመታት ተሳክቶለት በሥልጣን ላይ ቆየ? ለሚሉት ጥያቄዎች ከጣሊያኖች መጽሐፍ ተቀድቶ በመንግሥት መዋቅር ጭምር ተደግፎ የተተገበረው እና በኹለቱ ማኅበረሰቦች መካከል አለመተማመንን የፈጠረው ፖሊሲ ነው።
ለዚህም ማስረጃው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ወደ ሥልጣን በማምጣት የተጠናቀቀው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ነው። በ2005 የአዲስ አበባን መስፋፋት እንደ ቅድመ ምክንያት አድርጎ በዋንኛነት በወጣቶች ተሳታፊነት በኦሮሚያ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተቀጣጠለ። ወትሮም ከፍቶን ነው የኖርነው ያሉት የአማራ ክልል ወጣቶች ሰንበትበት ብለው ተቀላቀሉ። አምስት ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የኢሕአዴግን ብሎም አገሪቱን ፖለቲካ ግልብጥብጡን ባወጣ መልኩ ለውጦች ይተገበሩ ጀመር። የኹለቱ ማኅበረሰቦች ካብ ለካብ መናበብ ግዙፉን ስርዓት እጁን ጠምዝዞ ወደ ለውጥ አምጥቶታል ካልን፤ በኹለቱ መካከል የነበረው አለመግባባት ደግሞ ስርዓቱን ለ27 ዓመታት አሰንብቶታል ቢባል ከእውነታው የራቀ አይሆንም።
ድኅረ ሕወሓት/ኢሕአዴግ፡ ኹለቱ ማኅበረሰቦችና የተወካዮቻቸው ኀላፊነት
አሁንም በኹለቱ ማኅበረሰቦች ዘንድ ለየብቻ የሚደረጉ መጉረመረሞች እንዳሉ ለማስተዋል ብዙ እርቀት መጓዝ አይጠይቅም። ለየብቻ የተጨቁኛለው ድንኳን መጣል የጠቅላዩን ስርዓት ንቅንቅ እንደማያደርገው፤ እንዲያውም አምባገነን መሆን ካሰቡ መንገዱን እንደጣሊያኖች አልጋ ባልጋ ከማድረግ ውጪ ምንም የሚፈይደው ነገር ይኖራል ተብሎ አይገመትም።
ኹለቱ ማኅበረሰቦች ያላቸው ቁጥር እና የሰፈሩበት አካባቢ የአገሪቱን ፖለቲካዊ እጣ ፋንታ ለመወሰን ስትራቴጂያዊ እና ፖለቲካዊ አቅምን ያጎናጽፋቸዋል። ይህን አቅም አቀናጅቶ መምራት ካልተቻለ ለየብቻ የሚደረግ ለቅሶ፤ ነጥሮ ወደ ራስ እንደሚመለስ ጥይት ከመሆን ያለፈ ትርጉም አይኖረውም።
ኹለቱን ማኅበረሰቦች እንወክላለን የሚሉት የፖለቲካ ቡድኖች ደግሞ ይህንን በደምብ የተገነዘቡ ሊሆኑ ይገባቸዋል። ሸዋን በተሳካ ሁኔታ ከማፍረስ የዘለለ ትርጉም ካልነበረው የብሔረሰቦች እኩልነት ትርክት ‘ሃንጎቨር’ በጥዋቱ ከተላቀቁ፤ አረፋፍደውም ቢሆን የሚወኩሏቸውን ማኅበረሰቦች ወደ “ብልጽግና” ማማ ሊወስዱ ይችላሉ። ከጣሊያን መጽሐፍ፤ ቀጥሎም ከእርሱ ከተቀዳው የኢሕአዴግ መጽሐፍ ጭቃ ውስጥ፤ ከወዲያኛው ደግሞ የአጼዎቹ ኢትዮጵያ ትርክት ጭቃ ውስጥ የተቀረቀሩ ሐሳቦች፤ የብልጥግናዎች አዲሷ መኪና ከመነሳቷ በፊት ብዙ ግፊ እንዳትጠይቅ ያሰጋል።
የኹለቱን ብልጥግናዎች የማኅበራዊ ሚዲያ መጎሻሸም ላየ፤ አሊያም የጎጥ ፌደራሊዝሙን ለማስቀጠል ያለውን ፍላጎት ላስተዋለ፤ እውነትም ይህን የተገነዘቡ ሹማምንት ስለመኖራቸው ሊጠራጠር ይችላል። የኦሮሞና የአማራ ማኅበረሰቦች ለአገሪቱ ያለባቸውን ስትራቴጂያዊና ፖለቲካዊ ኀላፊነት የተገነዘቡ ሹማምንትን ወደ ቦታው ማምጣት፤ አገሪቱን ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ወረራ ሊታደጋት እንደሚችል መገንዘብ ያሻል። ይህንን ኀላፊነት የዘነጋ አካሄድ፤ ዳግማዊ ሕወሓትን ከመፍጠርና ጠቅላዩንም አምባገነን ከማድረግ በዘለለ አንዳችም ፍሬ አያፈራም። ባስ ሲል ደግሞ የኹለቱ አለመተማመን መጀመሪያ ጣሊያንን ጋብዟል፤ ከዚያም ኢሕአዴግን ለ27 ዓመታት አንግሷል፤ ቀጥሎ የቱን ሴይጣን እንደሚያመጣብን ምን ይታወቃል?
አዲሱ ደረሰ የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ አጋር የሆነው የ‘ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው’ መጽሔት የቀድሞ ተባባሪ አርታዒ የነበሩ ናቸው።
በኢሜል አድራሻቸው አድራሻቸው addisuderesse@gmail.com ማግኘት ይቻላል።
ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013