መነሻ ገጽአምዶችማኅበረ ፖለቲካፌደራሊስቶች ወይንስ ትናንሽ ንጉሦች?

ፌደራሊስቶች ወይንስ ትናንሽ ንጉሦች?

ፌደራሊዝምን ከመንግሥት አገልግሎት ጋር ማስተሳሰር ያቃተው አገራዊውን የተቋማትና የመንግሥት መዋቅሮችን ስርጭት በመተቸት አዲሱ ደረሰ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ከገጠመኛቸውና የተሠሩ ጥናቶችንና ሰነዶችን በማገላበጥ ከመፍትሄ ምክረ ሐሳብ ጋር አዘጋጅተዋል።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ አዲስ አበባ ሊዘዋወር እንደሆነ በቅርቡ ተሰምቷል። ፍርድ ቤቱ በስድስት ኪሎ አካባቢ በባለ 13 ወለሎች ፎቅ እንደሚኖሩት እንዲሁም 1.8 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተነግሯል። እሁድ፣ ታኅሣሥ 11/2013 የመሰረተ ድንጋዩ ሲቀመጥ፥ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አበዲሳ እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዐዛ አሸናፊ ተገኝተዋል።

የፍርድ ቤቱ የመሰረተ ድንጋይ ሲቀመጥ አንድ ታሪክ አስታወሰኝ። ከሦስት ዓመታት በፊት ከአለቃዬ ጋር ለአንድ ሥራ ወደ ወላይታ ተጉዤ ነበር። ወላይታ እንደደረስን፥ ጓዜን በተዘጋጀልኝ የሆቴል ክፍል ውስጥ ወርውሬ፤ ሻወሬን ወስጄ ቴሌቪዥን እያየው ኢንተርኔት ለመጠቀም ወደ እንግዳ መቀበያው አመራው። በእንድግዳ መቀበያው ውስጥ ለአንድ ልጅ ገንዘብ እየተሰበሰበ ነበር። ለምን እንደሆነ ጠጋ ብዬ ጠየኩ። የታሪኩን ሙሉ በሙሉ እውነተኛነት በገለልተኛ መንገድ ማረጋገጥ ባልችልም፥ ገንዘብ የሚሰበሰብለትን ወጣት ታሪክ ግን እንዲህ ሲሉ አጫወቱኝ።

ወጣቱ ለዘመናት የአባቴ ነው የሚለውን ቦታ በጉለበተኛ ተቀምቷል። ቀሚውም በቦታው ላይ የቀርከሃ (ይመስለኛል?) ምርት እያመረተ በትርፉ ዓለሙን መቅጨት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ድሃው የመሬቱ ባለቤት እኔ ነኝ የሚለው ቤተሰብ፤ በወላይታ ፍርድ ቤቶች ቢንከራተቱም፤ ልጁ እንደሚለው ጉልበተኛውን ፍራቻ፤ አሊያም በጉልበተኛው ገንዘብ በመማለላቸው የተነሳ የድሃውን ቤተሰብ እውነት ሊያደምጡ ሳይፈልጉ ቆይተዋል።

ቤተሰቡ ጉዳዩን ወደ ደቡብ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይዞ እንዲሄድ እና እዚያ አቤት እንዲል ተመክሯል። ልጁም ቤተሰቡን ወክሎ ሃዋሳ በሚገኘው የደቡብ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለመሄድ ቆርጦ ተነስቷል። ችግሩ የሃዋሳውም ፍርድ ቤት በትንሹ ለሦስትና ለአራት ጊዜ በ15 ቀናት ልዩነት እየቀጠረ እንደሚያንገላታው ገብቶታል። የቻለውን ያክል ምግብ በገጠራማው ወላይታ ከሚገኘው ቤተሰቡና ጎረቤቶች ይቋጠርለታል። የፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ግን በተቋጠረ ምግብ የሚገፉት እንዳልሆነ ገምቷል። ስለዚህ አገልግሉ ስታልቅ ሆቴል የሚመገብበት ገንዘብ ያስፍልገዋል። በተቻለ አቅም ሆቴል አልጋ ይዞ የሚያድርበትንም ገንዘብ እየሰበሰበ ነበር።

ለሆቴል መክፈል ከሚችለው በላይ ቀጠሮው ቢዘገይስ የሚል ጥያቄ ለተሰበሰቡት ሰዎች አቀረብኩ። ያለምንም ማመንታት “በሃዋሳ አስፓልቶች ላይ እያደረ ጉዳዩን ያስጨርሳል” አሉኝ ቆፍጠን ብለው። የልጁን መጨረሻ ለማወቅ የሚያስችል ቆይታ በወላይታ አልነበረኝም። እንደው ተሳክቶለት ይሆን ለመሆኑ? በሃዋሳ አስፓልቶች ላይ ምን ያክል ቀን አድሮ ይሆን? የሰበሰበውን ገንዘብ በሙሉ ጨርሶ ወደልመና ገብቶ ይሆን? ተሳክቶለትም ይሁን ሳይሳካለት ወደ ቀየው ለመመለስ ቢፈልግ ሌላ ገንዘብ ደግሞ ከየት ያመጣል? ቤተሰቡ ጉዳዩን በሃዋሳው አይደለም በወላይታው ፍርድ ቤት ለመከታተልም የሚያስችል አቅም አልነበረውም። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ ግብግቡ በንግድ ከደለበ ጥጋበኛ ጋር ነው። በዚህ ዓውድ ፍትሕን ይፈጸማል ብሎ ማሰብ ከቶ እንዴ ይቻላል?

ስለፍትሕ ጥራት ያሉ ጽንሰ ሐሳቦችን ከማንሳቴ በፊት የጥቁር አንበሳውን ምሳሌ ላክል። በእኔ አሊያም ከእኔ እድሜ በላይ ላለ እና አዲስ አበባን እና የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ለሚያውቅ የሆሰፒታሉ በረንዳ ላይ የሚተኙ በሽተኞችን ትዕይንት ይዘነጋል ብዬ አልገምትም። ሆስፒታሉ ለዘመናት በአገሪቱ ያለ ብቸኛ የሪፈራል ተቋም ሆኖ ማገልገሉ ይታወቃል። በክልሎች ያሉ የጤና ተቋማት የበሽተኞች ቁጥር ካላቸው የባለሞያ ቁጥር ሲበልጥባቸው አሊያም የበሽተኛው ጉዳይ ከአቅም በላይ ነው ብለው ሲያስቡ ወደ ጥቁር አንበሳ ይልካሉ።

በሆስፒታሉ በረንዳ ላይ በሽተኞች በረንዳ ላይ አሊያም በግቢው ውስጥ አንዳንዴም ውጪ ተኮልኩለው ይውላሉ ያድራሉ። ምስኪን ዜጎች በሽታው የሚደቁሳቸው ሳያንስ መሬቷን እፍ ብለው ቅዝቃዜው ላይ ይተኛሉ። ጉሉኮስ የተሰካላቸው በሽተኞች ጭምር ውጪ ተኝተው ማየት የተለመደ ነበር። ዐሥርታትን በዘለለ ጊዜ በተሠራ ሥራ በርካታ የሪፈራል ሆስፒታሎች በየክልሉ ተገንብተዋል። እርሱን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ የሚደረግ የስቃይ ጉዞ እየቀነሰ ይመስላል። አሁንም እንዲህ ዓይነት በሽተኞች በጥቁር አንበሳ እና ጳውሎስን በመሳሰሉ ሆስፒታሎች ቢታዩም፤ አብዛኛዎቹ ከቅርብ አካባቢዎች የሚመጡ እና ሁኔታቸውም ከዚህ ቀደሙ እጅግ የተሻለ ነው ቢባል ከእውነታው የራቀ አይሆንም።

ለነገሩማ የፌደራሊዝም ጥቅሙ ይሄ ነበር። ዜጎች በምርጫቸው ለመዝናናት፤ ዘመድ ለመጠየቅ አሊያም ለንግድ ካልሆነ በስተቀር ተገደው የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲሉ የሚያደርጓቸው ስቃይ የበዛባቸው ጉዞዎች በማስቀረት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እና የመንግሥት መዋቅሮችን በተሻለ ቅርበት የመገንባት ፍይዳው። ይሁንና ይህ እውን የመሆን ተስፋው ሩቅ ይመስለኛል።

የኢትዮጵያ የፍትሕ ስርዓት በወፍ በረር
በዓለም የፍትሕ ፕሮጀክት የተዘጋጀውና የዓለም አገራት የፍትሕ ስርዓትን ገምግሞ በ2019 (እ.ኤ.አ.) ለመጀምሪያ ጊዜ በሚል የታተመ አንድ ሰነድ አለ። የሰነዱ አዘጋጆች በ101 አገራት ውስጥ የሚኖሩ ከ100 ሺሕ በላይ ዜጎችን አናግረናል ብለው ባዘጋጁት ሰነድ ላይ የኢትዮጵያ የፍትሕ ስርዓትን በጥቂቱም ቢሆን አሳይተዋል። የሰነዱ አዘጋጆች አናግረናቸዋል ካሏቸው ኢትዮጵያውያን መካከል ከ74 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰነዱ ከመታተሙ በፊት በነበሩት ኹለት ዓመታት ፍትሕን ፍለጋ ሲንቀሳቀሱ እንቅፋት እንዳጋጠማቸው ተመልክቷል።

ሰነዱ በፍትሕ መጓተት፤ አሊያም ማጣት ምክንያት ዜጎች ደረሰብን ያሏቸውን ችግሮችም ሳያመነታ ዘርዝሯል። የሰነዱ አዘጋጆች አናግረናቸዋል ካሏቸው ኢትዮጵያውያን መካከል በፍትሕ መዘግየት አሊያም እጦት ምክንያት 42 በመቶው ለጤና እክል፤ 43 በመቶው ለገቢ መቀነስ፣ ሥራ እጦት አሊያም የመኖሪያ አካባቢን ለመቀየር መገደድ፤ 26 በመቶው ለተበላሸ የቤተሰብ ግንኙነት እንዲሁም 19 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ለሱሰኝነት ተዳርገናል ሲሉ ነግረውናል ይላሉ።

በተጨማሪም ሰነዱ ኢትዮጵያውያን የፍትሕ ጥያቄያቸውን ለማስመለስ በአማካኝ 5.4 ወራት ይፈጅባቸዋል ያለ ሲሆን 26 በመቶ የሚሆኑት ያነጋገሯቸው ደግሞ ፍትሕን ለማግኘት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት እጅግ በጣም አዳጋች እንደሆነባቸው አመላክቷል። እንደሰነዱ ከሆነ ከ73 በመቶ በላይ የሚሆኑት በጥናቱ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን የሕግ ምክር የሚያገኙት ከቤተሰብ አሊያም ከጓደኛ ሲሆን 18 በመቶው ጉዳያቸው የተፈታላቸው ቢሆንም 21 በመቶ የሚሆኑት ግን መፍትሄ ሳያገኙ በመቅረታቸው ተስፋ ቆርጠው እንደተውት ተገንዝበናል ይላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዘለቄታዊ የልማት እቅዱ ውስጥ ፍትሕ ለሁሉም በእኩል አቅርቦት ላይ ሊተገበር እንደሚገባው በማመን አንዱ የልማት እቅዱ እንዳደረገው ይታወቃል። የዓለማቀፉ ድርጅት አባል አገራት ፍትሕን በአገር ዐቀፍ እና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተቀዳሚ ተግባራቸው እንዲያደርጉት በወተወተበት እቅዱ፥ ፍትሕን ለሁሉም በእኩል አቅርቦት ላይ ማቅረብ አለመቻል ዜጎችን ከሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚገታ አስምሮበት አልፏል።

ከዓለም ሕዝብ መካከል ኹለት ሦስተኛ የሚሆነው ሕዝብ ለዕለት ተለት ኑሮው ከሚያስፈልገው ከፍተኛ የሕይወት ቀውስ እስከሚዳርግ የፍትሕ እጦት ጋር አብሮ እንደሚኖር የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዓለም ከሚገኘው ሕዝብ 1.4 ቢሊዮኑ ያልተሟላ የዜግነት እና አስተዳደራዊ የፍትሕ እጦት ጋር አብሮ የሚኖር ነው መሆኑን ይጠቁማሉ።

በአገሬ ያለው የፍትሕ አገልግሎት መልከዓ ምድራዊ ስርጭት አሳስቦኛል የሚሉት ደግሞ ጄሚ ባክስተር እና አልበርት ዩን ናቸው። ከናዳውያኑ በ2014 (እ.ኤ.አ.) ባሳተሙት ጥናታቸው መንግሥታት የፍትሕ አቅርቦት ስርጭትን ከዜጎች ማኅበራዊ፤ ምጣኔ ሀብታዊ እና የቋንቋ መሰረት ጋር ብቻ እያነጻጸሩ ሲገመግሙ መኖራቸው፥ የሕዝብን መገኛ ቦታ መሰረት ያደረገ የፍትሕ አገልግሎት አቅርቦት ደካማ እንዲሆን ሳያደርገው እንዳልቀረ ይገምታሉ። የፍትሕ አገልግሎት እና የዜጎች መኖሪያ ቦታ ግንኙነት ላይ ብዙ ጥናቶች አለመገኘታቸውም የዚህ ማሳያ ነው የሚሉት ካናዳውያኑ፤ በገጠር እና ከተሜው ካናዳ መካከል እየሰፋ የመጣ የፍትሕ አገልግሎት አቅርቦት ልዩነት አስተውለናል ይላሉ።

መፍትሄው ምን ይሁን?
የአጼ ኃይለሥላሴን እና የደርግን መንግሥት አሃዳዊ ብለን መቃወማችን ትክክል ነው ያልነው ዜጎችን በቅርበት በሚያገለግል ስርዓት ለመቀየር በሚል ተስፋ ነበር። የንጉሡን ፍትሕ ፍለጋ ድሃ ዜጎች አዲስ አበባ ድረስ እንዲመጡ በማስገደድ የሚያንገላታ የነበረን ስርዓት በመሆኑ አንድ ድሃ የወለጋ ገበሬ የኦሮሚያ ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ፍለጋ አዲስ አበባ ድረስ እንዲመጣ በሚያስገድድ ስርዓት መቀየር ፖለቲከኞቻችን ስለፌደራል ስርዓት ያላቸውን እውቀት እንድንጠራጠር አድርጎናል። ባህር ዳር ተቀምጦ ወልዲያን ማስተዳደር፤ አዲስ አበባ ቦሌ ተቀምጦ ለጅማ ፍትሕ መስጠት፤ መቀሌ ተቀምጦ የአክሱም ሕዝብ የውሃ ጥማት ይሰማኛል ማለት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዜጎች ለሚያነሱት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ይሰጣል የሚል እምነት ማሳደር አያስችልም።

- ይከተሉን -Social Media

ሲሆን ሲሆን አማራ እና ኦሮሚያን የሚያካክሉ ክልሎች የራሳቸው የመወሰን ጡንቻ ወዳላቸውና ለሕዝባቸው የመንግሥትን አገልግሎት በቅርበት ማቅረብ ወደሚችሉ አነስ ወዳሉ የመንግሥት መዋቅሮች መቀየርን ማሰብ ተገቢ ነበር። የፍትሕን ጥራት ከሚወስኑ ነገሮች አንድኛው የፍትሕ አገልግሎቶች ቀረቤታ መሆኑን ጠንቅቀው በሚያውቁት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳት መዐዛ፥ ፍትሕን ከኦሮሚያ ልጆች ለሚያርቀው ማዕከል ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ሲያስቀምጡ ማየት ግርምትን ያጭራል።

አርባ ሚሊዮን እና ሰላሳ ሚሊዮን ሕዝብ ይዘዋል የሚባልላቸውን ክልሎች በአንድ አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ጠርንፎ ማስተዳደርን ለመቀጠል ያለው ፍላጎት መነሻ ጽንሰ ሐሳቡ፤ ከፌድራሊዝም ይልቅ ለትናንሽ አሃዳዊነት ይቀርባል። ጨፌው የኦሮሚያን፤ የባህር ዳሩ ምክር ቤት የአማራን ከተሞች ከንቲባዎች እየሾመ እና እየሻረ የሕዝብን ጥያቄ ዘመኑን በሚመጥን መልክ እመልሳለው ብሎ ማሰብ አውቀው ከተኙ ሹማምንት ህልምነት በዘለለ ለዜጎች ጠብ የሚያደርገው አንዳችም ነገር አይኖረውም።
አዲስ ደረሰን በኢሜል አድራሻቸው addisuderesse@gmail.com ማግኘት ይቻላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች