መነሻ ገጽአምዶችማኅበረ ፖለቲካሥራ አጥነትን ገንዘብ በማሳተም መቅረፍ ቢቻልስ?

ሥራ አጥነትን ገንዘብ በማሳተም መቅረፍ ቢቻልስ?

በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የሥራ አጦች ቁጥር ከፍተኛ እየሆነ በሄደ ቁጥር በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከባድ ነው፡፡የሥራ አጥነት ቁጥርን መቀነስ ለመንግሥት ትልቅ ግቡ ነው፡፡ ምክንያቱም የዜጎች ሥራ አጥ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚያሳድረው የኢኮኖሚ እና ሞራል መላሸቅ አገርን ወደ አልተፈለገ ውጥረት ውስጥ ይከታል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ አዲሱ ደረሰ የመንግሥት የልማት ግቦች እና የሥራ አትነት ቅነሳ ፕግራሞች ከዓለማቀፍ ተመክሮዎችን በማጣቀስ ሊያሳየን ሞክሯል፡፡መልካም ንባብ

…ኢትዮጵያውያን ሥራ አጥነትን እንደተለማመዱት፤ ድህነትን ጽድቅ እንዳረጉት…

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደሥልጣን እንደመጡ ሰሞን በሃምሌ 2010 ካደረጓቸው ንግግሮች መካከል የግዝፍ ፕሮጀክቶችን የተመለከተው አንዱ ነው።
…የጣልናቸውን መሰረተ ድንጋዮችን አይደለም እና ገንብተን ለቅመንም አንጨርሳቸውም። በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት፤ የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች በጥራት እና በወቅቱ ከማጠናቀቅ በዘለለ፤ አንዲህ ዓይነት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን አንጀምርም።
ብለው ነበር ጠቅላዩ።

ጠቅላዩን እንዲያ ያናገራቸው የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ደካማነት ትልቁ ምክንያት ነው። “ካዝናው ባዶ የሆነ መንግሥት ነው የተረከብኩት” ማለታቸው ደግሞ አዲስ ፕሮጀክት ቢያቅዱም የገንዘብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ተገንዝበውም ጭምር ነው ቢባል ከእውነታው የራቀ አይሆንም። ምን አሳሰባቸው ብሔራዊ ባንክን ገንዘብ አሳትሞ እንዲያበድራቸው አያዙም ነበር? እስቲ እውነትም ስለዚህኛው አማራጭ እንነጋገር።

የጠቅላዩ መንግሥት በርትቶ፤ የተጣሉት መሰረተ ድንጋዮቻቸው ከሚገነቡላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ በአለም 7ኛ አንዲሁም በአፍሪካ አንደኛ ይሆናል ተብሎ የተገመተው የህዳሴው የኃይል ማመንጫ ነው። ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈጅ እና ለዜጎች እና ተቋማት በተሸጠ የቦንድ ሰነድ እና ቀጥተኛ የገነዘብ ድጋፍ እየተገነባ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። የህዳሴው ግድብ በግንባታው ወቅት እና ከግንባታው በኋላ 12 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ እቅድ የተያዘለት ነው።

ሌላኛው በተመሳሳይ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ይፈጃል የተባለውና ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የሚደርሰውን ከ756 ኪ.ሜ.በላይ የሚሆነውን ርቀት የሚሸፍነው የምድር ባቡር ፕሮጀክት ነው። በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ዘመናዊ የኤሌትሪክ የምድር ባቡር ፕሮጀክት፤ ከ50 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል። በ2002 አ/ም እ.ኢ.አ. የተጀመረውና አንዴ ሲቋረጥ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲጀመር የሰነበተው የገናሌ ዳዋ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመንግሥት ወጪ የተደረገበት ሌላኛው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ይህ ፕሮጀክት በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድልን እንደሚፈጥርም የተነገረለት ነው።

ላፕሴት በሚል ስያሜ የተጠራውና በኢትዮጲያ፤ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን መካከል የመሰረተ ልማት ግንኙነትን ይፈጥራል ተብሎ የታለመለት ሌላኛው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። በመለስ ዜናዊ፤ ሳልቫ ኪር እና መዋዊ ኪባኪ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት፤ የወደብ አገልግሎት መስጫ፤ ሦስት ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያዎችን፤ የምድር ባቡር አገልግሎቶችን፤ ሪዞርቶችን እና መሰል አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በአንድነት ያቀፈ ሲሆን፤ ይህ ፕሮጀክት ባይጠናቀቅም ከ5000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ግን የሥራ ዕድል እንደፈጠረ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ማግኘት ይቻላል።

ጠቅላዩ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ባሉት ጥቂት ወራት “ባዶውን የተረከብኩትን ካዝና ሮጥ ሮጥ ብዬ በብድር እና በስጦታ የሞላሁት እኔ ነኝ።” ሲሉ ተሰምተዋል። አዳዲስ ግዙፍ እና ወጪያቸው በመንግሥት የሚሸፈኑ ፕሮጀክቶች አይኖሩንም ያሉ የነበረ ቢሆንም፤ የሳቸውን ይሁንታ ያገኙ መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግን መሰረተ ዲንጋይ ተጥሎላቸዋል።

በ35 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ ያርፋል የተባለውና ሲጠናቀቅ ከ100 ሚሊዮን በላይ ተጓዦችን በዓመት ያስተናግዳል የተባለለት የቢሸፍቱ አየር ማረፊያ አንደኛው ፕሮጀክት ነው። ይህ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ይፈልጋል የተባለለት ግዙፍ ፕሮጀክት፤የሚፈጥረው የሥራ ዕድልን በተመለከት ግልጽ ቁጥር ማግኘት አይቻልም። ሆኖም በአመት ከ19 ሚሊዮን በላይ ተጓዦችን ያስተናግዳል የሚባልለት የአዲስ አበባ አየር ማረፊያ ከ13 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ ይታወቃል። በዚህም መሰረት የቢሾፍቱ የአየር ማረፊያ ሲጠናቀቅ ከዚህም አራት እጥፍ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድልን ሊፈጥር ይችላል ቢባል ከእውነታው የራቀ አይሆንም።

በዐቢይ አህመድ የሥልጣን ዘመን ከአፍሪካ ግዙፉ ይሆናል የተባለለትና በ20 ሺሕ ካሬ ላይ ያርፋል የተባለለት የመሶብ ፎቅ ሌላኛው ፕሮጀክት ነው። ይህ ከ680 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይፈልጋል የተባለለት ግዙፍ ፎቅ ሲጠናቀቅ፤ ከ20 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ይላል ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የያዘው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር። የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች በአንድ በኩል በቀጥታ ለዜጎች ሥራን እየፈጠሩ በሌላ በኩል ደግሞ የግል ዘርፉንም በማሳተፍ ተጨማ ገቢና ሥራን እየፈጠሩ ከርመዋል።

አሳምነው ሙሉጌታ በ2005 እ.ኢ.አ. ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የሰርቬይንግ ትምህርቱን አጠናቆ፤ ተቀጥሬ አልሰራም ካሉ አዲስ አበቤዎች አንዱ ነው። ተመርቆ ወደአዲስ አበባ እንደተመለሰ በኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ወቅት ከሚያውቀው ጓደኛው ጋር በአንድ ላይ ሆኖ አነስተኛ ማኅበር ያቋቁማል። ማኅበሩ በዜጎች ቁጠባና በመንግሥት በቀጥታ የገንዘብ ፈሰስ በሚደረግለት የቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ሥራ ይጀምራል።

በመጀመሪያ በኮዬ ፍቼ ሳይት ነበር ሥራ ያገኘሁት። ቀላል የፍጻሜ ሥራዎችን መቀበል ጀመርኩ።… ከዚያ በኋላ ብዙ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፊያለው። ሁሉም በመንግሥት ገንዘብ የሚሠሩ እና በጨረታ ያገኘኋቸው ናቸው።.. በአሁኑ ወቅት እንግዲህ አግብቼ አንድ ልጅ ወልጄ፤ በቤት ኪራይ ውስጥ ነው የምኖረው። ከዚያ ባሻገር ለሥራ እንዲሆነኝም አንድ ፒክ አፕ መኪና ከ500 ሺሕ ብር በላይ በሆነ ወጪ ገዝቻለው። ጓደኛዬም እንዲሁ እራሱን የቻለ ሰው ሆኗል።

ይላል አሳምነው በመንግሥት ወጪ የሚደረግላቸው ፕሮጀክቶች ለሕይወቱ በቀጥታ እንዴት እንደጠቀሙት ሲያብራራ። በእያንዳንዱ ፕሮጀክት ቢያንስ ከአምስት እስከ 20 የሚሆኑ ሌሎች ሰዎችን ደግሞ በጊዜያዊነት መቅጠር አለብኝ። አሳምነው በሥሩ ለብዙ ጊዜ የሠሩ ጊዜያዊ ሠራተኞችን ሁኔታም አጫውቶኛል።
ታዲያ አንደነዚህ ዓይነት ብዙ ፕሮጀክቶችን መንግሥት እያስጀመረ ለምን ዜጎቹን ሥራ በሥራ አያደርግም? አጭር መልስ- ገንዘብ የለውም።

የሠራንበትን ገንዘብ በጊዜው ማስለቀቅ ትልቁ የሥራችን ፈተና ነው። ሙስናን ለመከላከል የተቀመጠው ቢሮክራሲ እና የገንዘብ እጥረት እንዳለ የሚያሳብቁ ሁኔታዎች ተደምረው የሠራህበትን ገንዘብ ካላለቀስክ እንዳታገኝ የሚያደርግ ሁኔታ ነው በዘርፉ ውስጥ ያለው።
ይላል አሳምነው ስለሥራው ተግዳሮቶች ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ።

የኢትዮጲያ መንግሥት በራሱ ወጪ የሚያስገነባቸውን እና ለዜጎቹ በቀጥታም ይሁን የግል ዘርፉን በማነቃቃት በ10ሺዎች ሥራ ዕድልን የሚፈጥሩትን እነዚህን ፕሮጀክቶች ለማስገንባት የሚፈልገውን ገንዘብ ከተለያዩ ምንጮች ያገኛል።

መንግሥት ያለው የገቢ መጠን ከሚሰበስበው ግብር፤ ቀጥተኛ የልማት ድጋፍ፤ እና ከአትራፊ የልማት ድርጅቶቹ ከሚያገኘው ድምር ገቢ እኩል ነው። የሚያቅደውም በዚያችው ልክ ነው። ትንሽ ዘለል ካለም ብድር ይፈልጋል፤ ስለዚህም መንግሥት ቦንድ ይሸጣል። ትርፍ ገንዘብ በባንክ ያላችሁ፤ ማስተማመኛ የቃል ኪዳን ሰነድ ያዙና ገንዘባችሁን አበድሩኝ፤ ግብር ሰብስቤ ከነወለዱ እከፍላለው ይላል። የመንግሥት ጠቅላላ ወጪ፤ መንግሥት ከሚሰበስበው ገቢ ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት የሚለው- ለዘመናት የታመነ የኢኮኖሚክስ ጽንሰ ሕሳብ ደግሞ መንግሥት ሩቅ አላሚ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንድኛው ነው።

- ይከተሉን -Social Media

መንግሥት የሚያወጣው ወጪ ከሚሰበስበው ገቢ ከበለጠ የዋጋ ግሽበት ይከሰታል- ኑሮ ይወደዳል። እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ባሉ አገራት ይሄ የወጋ ግሽበት ከኹለት በመቶ ከበለጠ፤ የኢኮኖሚ ሹማምንቶቻቸውን ያስደነግጣል። መንግሥት የሚጠቀመውን ገንዘብ እንዲቀንስ ይታዘዛል። ይህ ቅነሳ ለዜጎች ማኅበራዊ፤ የጤና እና የትምህርት አገልግሎት ድጋፍ የሚውለውን ገንዘብ እስከመቀነስም ይደርሳል። ገበያ ውስጥ ገንዘብ ስለበዛ ይሰብሰብ ይባላል። መንግሥት የቦንድ ሰነድ መሸጥ ይጀምራል፤ አሊያም በባንክ ገንዘባቸውን ማስቀመጥ ለሚሹ ዜጎች የሚከፈለውን ወለድ ይጨምራል።

በዚህ ምንያት መንግሥት ለዜጎቹ የሚያልመውን ሁሉ ማስፈጸም አይችልም። ዜጎች የትኛውንም ያክል ሥራ አጥተው ቢንገላቱ፤ በመሰረተ ልማት እጦት ራሳቸውን እንዳይደግፉ እንኳን ሆነው ቢሰቃዩ፤ መንግሥት ምንም ማድረግ አልችልም ይላል። ጠቅላላ ምርቱ ጨምሮ የምሰበስበው ገቢ እስኪጨምር፤ አሊያም አሁን ያለብኝን ብድር ትንሽ ቀንሼ ሌላ እስክበደር (ጠቅላዩ ወደሥልጣን እንደመጡ እንዳደረጉት) ታገሱ ይላል። ዜጎች የሚታገሱትን ችግር ይታገሱታል፤ የማይታገሱትን ይለማመዱታል- ኢትዮጲያውያን ሥራ አጥነትን፤ ድህነትን እንደተለማመዱት፤ ጽድቅ እንዳረጉት።

መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ያሻውን ያክል እየተበደረ ለዜጎች ችግር በፍጥነት መድረስ ቢችልስ?
በዘመነ ኮሮና አትኩሮትን ካገኙ ጽንሰ ሐሳቦች አንድኛው የዘመናዊ የገንዘብ ስርዓት ጽንሰ ሐሳብ ግንባር ቀደሙ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በኮሮና ምክንያት በቤታቸው እንዲቀመጡ የተገደዱ ዜጎቻቸውን በመደገፍ ብድር የተደቆሱ አገራት፤ የዘመናዊ የገንዘብ ስርዓት ጽንሰ ሐሳብ እውነት ይሠራ ይሆን? በሚል በጉግል ላይ ፍላጋቸውን ሲያጧጡፉት እንደከረሙ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ።

የዘመናዊ የገንዘብ ስርዓት ጽንሰ ሐሳብ ምንድነው?
“መንግሥት ወጪውን ግዴታ ከገቢው ጋር ማመጣጠን አለበት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የማይረዱትን ነገር ሁሉ ትክክል አይደለም ከሚሉ ግለሰቦች የተዘሰነዘረ ስድብ ነው የሚመስለኝ”።

ትላለች ስቴፋኒ ኬልተን። ስቴፋኒ ለዓመታት የዘመናዊ የገንዘብ አስተዳደር ጽንሰ ሐሳብን ስትሰብክ የኖረች ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የተሳካላትም ይመስላል። ስቴፋኒ በ2016 እ.ኤ.አ.የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምራጫ ተወዳዳሪ የነበሩት በርኒ ሳንደርስ እና በ2020 እ.ኤ.አ. ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን እንዳሸነፉ የተነገረላቸው ጆ ባይደን የኢኮኖሚ አማካሪነትንም ሚና እንዲኖራት ከተመረጡ የኢኮኖሚክስ ምሁራን መካከል አንዷ ናት።

የብድር ችግር የለብንም፤ የበጀት እጥረት ችግር የለብንም፤ ያለብን የቋንቋ ችግር ነው። “ብድር” “የባጀት እጥረት” እና “የገቢና ወጪ አለመመጣጠን” የሚሉት ቃላቶች እራሳቸው ናቸው ችግሮቹ።

ትላለች ስቴፋኒ ጽንሰ ሐሳቡ ወደብርሃን እየወጣ መሆኑን ተከትሎ ከፋይናንሺያል ታይምስ የኢኮኖሚክስ አዘጋጅ ብሬንደን ግሪሌይ ጋር ባደረገችው ውይይት።
መንግሥታት ገንዘብን መበደር ይችላሉ፤ አሊያም በግብር መልክ ሊሰበስቡት ይችላሉ። ከዚያ በዘለለ ግን የራሳቸውን ወጪ ለመሸፈን ሊያሳትሙት አይችሉም የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ጊዜው ሊያልፍበት ይገባል- እንደ ስቴፋኒ።

መንግሥት ከሚሰበስበው ገቢ በላይ እንዳሻው ቢያወጣ ሃጢያት እየሠራ አይደለም፤ ክፍተቶችን እየደፈነ ነው።
ትላለች ስቴፋን መንግሥት ሥራን ለመፍጠር፤ ጤናን፤ ትምህርትን ለማሻሻል እንዲሁም የኪስ ገንዘብ ለዜጎቹ ለመክፈል ከሚሰበስበው ገቢ በላይ የቱንም ያክል ቢያወጣ ምንም ችግር እንደማያመጣ ስታብራራ።

- ይከተሉን -Social Media

ከሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ፤ የአለም አገራት ብሔራዊ ባንኮቻቸው ማሳተም የሚችሉት የገንዘብ መጠን ከወርቅ ምርት እና ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ መሆን ይገባዋል የሚለውን አሠራር እርግፍ አድርገው ትተውታል። ገንዘብ ይታተም ወይ? መቼ ይታተም? ምን ያክልስ ይታተም? የሚለው ጉዳይ የብሔራዊ ባንኮች እና የመንግሥታት ስምምነትን ብቻ የሚጠይቅ እንዲሆን ከተደረገ ውሎ አድሯል። እነዚህ የገንዘብ አስተዳደራቸውን በመንግሥታቸው ቁጥጥር ውስጥ እንዲሆን ያደረጉ አገራት፤ ገንዘብን ለማሳተም እንደወትሮው መሳቀቃቸው አግባብ አይደለም ይላል- ይህ የክርክር ሐሳብ።

በላንሴስተር ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህር በሆነው ጆን ዊታከር ተጽፎ በ ዘ ኮንቨርሴሽን ድህረ ገጽ ላይ በነሃሴ 2020 እ.ኤ.አ. የታተመ ጽሑፍ ይህንን ያጠናክራል። እንደ ጆን ከሆነ መንግሥታት ላሻቸው አላማ፡- ከድህነት ቅነሳ እስከ ሥራ አጥ ቅነሳ፤ አሊያም የጤና መሰረተ ልማቶችን ለማሻሻል፤ አሊያም ለተሻለ የትምህርት ጥራት ኢንቨስትመንት ገንዘብ ቢያስፈልጋቸው ያሻቸውን ያክል በብሔራዊ ባንካቸው አማካኝነት በሚታተም ገንዘብ መሸፈን ይችላሉ። የዋጋ ግሽበት ምልክቶችን ሲያዩ፤ ግብር ጨምረው ማስተካከል ይችላሉ ይላል ጆን።

የግብር አላማው የመንግሥትን ወጪ መሸፈን መሆን የለበትም፤ እንዲያውም ዜጎች ገንዘብን የሚጠቀሙበትን ምንያት መፍጠር እንጂ ሲል ይከራከራል ሐሳቡ። የሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የሚወሰዱት ውሳኔዎች ደግሞ ጽንሰ ሐሳቡ ብዙም ከተለመደው አሰራር የራቀ መሰረት እንደሌለው ያሳያል። ሥራ አጥ ሲበዛ፤ የባንክ ወለድ ይቀንሳል። ዜጎች ገንዘባቸውን በብዛት እንዲጠቀሙ እና ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቁ፤ የተነቃቃው ኢኮኖሚም ሥራን እንዲፈጥር ይደረጋል። ዜጎች ገንዘባቸውን በብዛት ሲጠቀሙ፤ ኢኮኖሚው ተነቃቅቶ ሥራ አጥነትን የሚቀንስ ከሆነ፤ ተጨማሪ ገንዘብ ሁል ጊዜ የዋጋ ግሽበት ተጽዕኖ እንጂ ሌላ ጥቅም የለውም የሚለው ሐሳብ ውሃ ያነሳል ወይ? ሲሉ ይሞግታሉ- የጽንሰ ሐሳቡ ደጋፊዎች።

ከ2009 እ.ኤ.አ. ጀምሮ መንግሥታት ብድር ፍለጋ ቦንድ እየሸጡ ሳይሆን እንዲያውም ከግል ባለሀብቶች ቦንዶችን እየገዙ ነው- ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት። የነዚህ የቦንድ ግዢዎች በቀጥታ በብሔራዊ ባንኮቻቸው በታተመ ገንዘብ የተሸፈነ ነው። ከኮሮና መምጣት በፊት እንኳን፤ በዩናይትድ ኪንግደም፤ ከ300 ቢሊዮን ዩሮ ወይም ከጠቅላላ ምርቷ 30 በመቶ በላይ የመንግሥት ብድር በተመሳሳይ መልኩ የተሸፈነ ነው። ይህ ሁሉ ገንዘብ በዩናይትድ ኪንግደም፤ በአሜሪካ የአውሮፓ ኅብረት ቀጠና እና በጃፓን በመሳሰሉ አገራት ወደ ኢኮኖሚው ሲገባ፤ ምንም የዋጋ ግሽበት ምልክት አልታየም። የጃፓን መንግሥት በዚህ መንገድ ወጪውን ከሦስት አስርተ አመታት በላይ እየሸፈነ ቢቆይም፤ የዋጋ ግሽበት መጠኑን እንዲያውም ከዜሮ በላይ ለማምጣት ሲቸገር ተስተውሏል ይላል ጆን።

በርግጥ የመንግሥትን ወጪ በቀጥታ በብሔራዊ ባንክ በሚታተም ገንዘብ መሸፈን የዋጋ ግሽበት ያስከተለባቸው አገራት አሉ። አርጀንቲና፤ የሶቪየት ህብረት በተበታተነችበት ወቅት፤ ዚምባብዌ፤ እና ቬንዚዌላን የመሳሰሉ አገራት ለዚህ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላለሉ። ሆኖም እነዚህ አገራት አንድም ሥር የሰደደ ሙስና፤ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የተበደረውን ገንዘብ ያለመመለስ ችግር፤ አሊያም አገራቱ በገዛ የገንዘብ ኖቶቻቸው መበደር የማይችሉ በመሆናቸው የተፈጠረ እንጂ መንግሥት በቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ተበድሮ ወጪውን በመሸፈኑ የተፈጠረ አይደለም ይላሉ የጽንሰ ሐሳቡ አቀንቃኞች።

የኮሮና ቫይረስ መምጣትን ተከትሎ ደግሞ ሐሳቡ ጥንካሬን ያገኘ ይመስላል። የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ወጪ በቫይረሱ ዘመን እጅጉን ጨምሯል። ወጪውን ደግሞ እየሸፈነ ያለው የኢንግላንድ ብሔራዊ ባንክ ነው። በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ብድር ከኹለት ትሪሊዮን ዩሮ በላይ ተሻግሯል፤ ይህም የአጠቃላይ ምርቱ መቶ በመቶ እንዲሆን አድርጎታል። የዋጋ ግሽበት ምልክት ግን እስካሁን አልታየም።

ከባድ የሆነ የብሔራዊ ባንክ እዳ ይኖባቸዋል፤ ግን ምንም ችግር የለውም፤ እንዲያውም ጥሩ ነው።
ትላለች ስቴፋኒ ስለዩናይትድ ኪንግደም የብድር እድገት ስታወራ።
የዘመናዊ የገንዘብ አስተዳደር ጽንሰ ሐሳብ መቀንቀን የጀመረው በ1970ዎቹ እ.ኤ.አ. ዋረን ሞዝለር በተባለ ግለሰብ ነበር። ሞዝለር በአለም ግንባር ቀደሙ የባለቤትነት ድርሻ ንግድ በሚሳለጥበት የዎል ስትሪት ገበያ ደላላ በነበረበት ወቅት ሐሳቡን እየተጠቀመ ያተርፍበት የነበረ ግለሰብ ነው። የግሪክ መንግሥት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበት መፍትሄው ቁጥብነት ነው፤ መንግሥት ወጪ የሚያደርግባቸውን ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶችንም መቀነስ አለበት በሚባልበት ወቅት፤ ሞዝለር የግሪክ የቦንድ ሰነዶችን በድፍረት እየገዛ ያተርፍባቸው ነበር። የሞዝለር መከራከሪያ፡- ግሪክ የትኛውንም ያክል ብትከስር የግሪክ ኢኮኖሚ ውስጥ ተጨማሪ ገንዘብ መጨመር እንጂ ያለውንም መንጠቅ መፍትሄ አይሆንም የሚል ነበር።

በኢትዮጲያ በመንግሥት ታቅደው፤ በመንግሥት አስተዳዳሪነት እና በመንግሥት ቀጥተኛ የገንዘብ ፈሰስ የሚደረግላቸው ፕሮግራሞች፤ ፕሮጀክቶች እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ዋንኛ የሥራ እና የገቢ ምንጭ መሆን ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። የመንግሥት መዋቅሩ በቀጥታ ከ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎች በላይ ቀጥሮ ያስተዳድራል። የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን በ2012 እ.ኢ.አ.በዋናነት በመንግሥት የቁጥጥር ማዕቀፍ ውስጥ የሚንቀሰቃሱ ከኹለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ሥራዎችን ለዜጎች ፈጥሪያለው ብሏል። በ2025 እ.ኤ.አ.ደግሞ የንግድ ነባራዊ ሁኔታውን በማነቃቃት የሚፈጠሩትን ጨምሮ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሥራዎችን ለዜጎች እንደሚፈጥር ቃል ገብቷል። መንግሥት ከገቢው በላይ ማውጣት ቢችል ከዚህም በላይ መሄድ ይቻል ነበር ማለት ነው?

- ይከተሉን -Social Media

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይሻ ሞሃመድ በጥቅምት 2013 እ.ኢ.አ. የዘርፉን የ10 ዓመት የልማት እቅድ አስተዋውቀዋል። በዋንኛነት በመንግሥት የገንዘብ ፈሰስ በሚደረግበት በዚህ ዘርፍ፤ ከ11 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደታቀደ ጠቅሰዋል። ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ቀጥተኛ የሆነና ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል ይፈጥራል የተባለለት እቅድ ይፋ ሲሆን፤ ሚኒስትሯ ግቡ እንዲሳካ ዘርፉ የተተበተበበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታት እንደሚያስፈልግ አልሸሸጉም።

ግልጽነት፤ ሙስና፤ የመንግሥት ተጠያቂነት፤ ያልተራጋጋ ፖለቲካ እና መሰል ችግሮች የተበተቡት የወ/ሮ አይሻን ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የኢኮኖሚው ዘርፎች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። መንግሥት ለዜጎች ሥራ ለመፍጠር የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ቢነድፍ፤ አሊያም የግል ዘርፉን ለማነቃቃት ያሻውን ገንዘብ ከብሔራዊ ባንክ እየተበደረ ማስፈጸም ይችላል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በአለም ላይ አሸንፎ የሚወጣበት ጊዜ ቢመጣ እንኳን እነዚህን ችግሮቿን ያልፈታች አገር ትጠቀምበታለች የሚል ግምት ከቀበጦች ተስፋ የዘለለ አይሆንም።

አሁን ባለው ሁኔታ፤ የመንግሥትን ፕሮጀክቶች ወጪ የሚሸፍኑትን የግብር ገቢ እና በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ ከሚሸጡ የቦንድ ሰነድ ሽያጮች የሚገኙ ብድሮች፤ የቀጥታ የልማት ድጋፎችም ሆኑ ቀጥተኛ ብድሮች ማስተማመኛ በማጣት እንዳይሸሹ ያሰጋል። ስጋቱ እራሱ እስኪሸሽ፤ ዜጎች ችግራቸውን ይታገሳሉ፤ የማይታገሱትን ይለማመዱታል፡- ኢትዮጲያውያን ሥራ አጥነትን እንደተለማመዱት፤ ድህነትን ጽድቅ እንዳረጉት።
E. addisuderesse@gmail.com
M. +251 912 032 439/ +251 932 199 677
facebook.com/Addisu Deresse
@addis_elf

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች