ዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት የራስዋን አሸናፊዎች ትፈጥራለች፡፡ በኢኮኖሚያዊ አቅም ግንባታ እና በንግዱ ዓለም ሰብረው መውጣት ከቻሉ መሀከል ዋረን በፌት አንዱ ነው፡፡ ዋረን በፌት የንግዱን ዓለም በአሸናፊነት ለመወጣት የሄዱባቸው ውጣ ውረዶች ወደ እውቀት በመቀየር በርካታ አዳዲስ ሀብታሞችን ለማፍት ችለዋል፡፡አብርሐም ፀሐዬ ከዚሁ ታላቅ የንግዱ ዓለም ጀግና ጥቂት የሥራ መርሆችን እነሆ ብሏል፡፡
የባለጸጋው ዋረን በፌት የቢዝነስ ምክሮች እነቢልጌትስን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥትና የግል ግዙፍ ተቋማትና ባለሃብቶች ትኩረት ሰጥተው የሚከታተሉት ነው። የቢዝነስ ድርጅቶች በተደራጀ ቁመና ላይ መቆም የሚችሉት ራዕያቸው ገንዘብ በማትረፍ ላይ ብቻ ሳይሆን ወጥ በሆነ አጠቃላይ ዕድገት ውስጥ መገኘት መቻላቸውን ሲያረጋግጡ ነው። የተቋቋመው ድርጅት ከአስርና ሃያ ዓመታት በኋላም በተጠናከረ ቁመና ላይ መጓዝ መቻሉን ለማረጋገጥ አሁን ላይ ያለውን አመራር መፈተሽና ትኩረት መስጠት ያሻል። ይህንን የሚሉት ዋረን በፌት ናቸው። ባለጸጋው በይበልጥ የቢዝነስ አመራሮች ላይ ምን መደረግ እንዳለበት በየጊዜው በተጋበዙበት መድረክ ላይ ሐሳብ ይሰጣሉ።
እኚህ የዘጠና ዓመት ልደት በዓላቸውን እያሳለፉ የሚገኙት አዛውንቱ ዋረን ባፌት ለዚህ ዓይነት የራዕይ መሳካትና የጠንካራ የድርጅት ግንባታ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው የቢዝነስ ምክር አጋርተዋል። በአመራር ደረጃ ላይ ምን አይነት መሪ ወደ አንድ ትልቅ ተቋም ገብቶ መሥራት ይኖርበታል በሚለው ሐሳብ ላይ ሰውየው ያስቀመጧቸውን ምክረ ሐሳቦች እናነሳለን። ከዚያ በፊት ግን ስለበፌት ባህሪ ጨረፍ አድርገን እንለፍ።
ዋረን በፌት ለታዳጊዎች
እንደሚታወቀው ዋረን በፌት በንባብ ልምዳቸው ጥሩ አርዓያ ናቸው። በተለይ ገንዘብ ለመቁጠር እንጂ ገጽ ለመግለጥ ጊዜ የለኝም ለሚሉ ገንዘብ ቆጣሪዎች እሳቸው በቀን ስድስት ሰዓት እያነበቡ ቢሊየኖችን ለመቁጠርም ጊዜ እንደሚተርፋቸው መንገር ያስፈልጋል። ዋረን በፌት ካነበቡትና በሥራ ካለፉት ላይ መረዳታቸውን ለሌሎች በማጋራት ይታወቃሉ። በዚህ ቀና ባህሪያቸው የሚመሰገኑ ባለጸጋ ናቸው። ሌሎች አቻ ባለጸጋዎችን ብቻ ሳይሆን ታዳጊዎች ባሉበት ቦታ ጭምር እየተገኙ ሐሳባቸውን ያካፍላሉ። ከንግድ ሥራ ጎን ለጎን ስለሕይወት ዘዬ ጭምር መናገር የሚችሉ ጥልቅ አንባቢና ዘርፈ ብዙ አስተውሎት ያላቸው ናቸው።
ከሶስት ዓመታት በፊት ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ በተጋበዙበት ወቅት ለታዳጊ ተማሪዎች ሲገልጹ የወጣቶች ዋንኛ ተጽእኖ አድራጊና አቅጣጫቸውን የሚወስነው ጉዳይ
የጓደኝነት ግንኙነታቸው እንደሆነ በማብራራት
“ውሏችሁን በተገቢው ቦታ አድርጉ፤ ጓደኞቻችሁንም ስትመርጡ ጥንቃቄ አድርጉ። የምትቀርቡት ጓደኛችሁ የሕይወት መንገዳችሁ ላይ ከባድ ተጽእኖ ስለሚያደርግ የወዳጅ ምርጫችሁን በቀላሉ እንዳትመለከቱት… “ ሲሉ ተናግረዋል። የወጣትነት መንገድ አቅጣጫ ተቀያያሪና ፈጣን በመሆኑ ከስር ጀምሮ ያልተገራ ከሆነ መንገድ የመሳት ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነም አስገንዘበዋል።
የዋረን በፌት ዘመን አይሽሬ ምክሮች የሰላሳ ዓመት ወዳጃቸው በሆኑት ቢልጌትስ ጭምር የሚመሰከር ነው። ቢልጌትስ ዋረን በፌት ያሉትን አስታውሰው ተናግረዋል “የጓደኛን ምርጫ በማስተካከል እስከሕይወት ዘመን ፍጻሜህ ድረስ በተሻለ መንገድ አብረህ መጓዝ ትችላለህ፤ ከነገ ሥራህ ጋር ተቃርኖ ውስጥ የማይገቡ፣ ለራዕይህ እንቅፋት የማይሆኑ ሰዎችን በወዳጅነት ብትይዝ መልካም ነው… በተለይ የምታደንቃቸውንና አርዓያህ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ጭምር የምትከተልና የምትቀርብ ወዳጅ ማድረግ ትርፉ ብዙ ነው…።
ይህ የዋረን ባፌት ምክር ከፍ ባለው የቢዝነሱ ዓለምም የሚታይ ነው።
የቢዝነስ አመራር ላይ መቀመጥ ያለባቸው ሰዎች
ዋረን በፌት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት ሥራውንና ሠራተኛውን ለሚመሩት የሥራ መሪዎች ነው። አንድን ድርጅት ለአንድ የታቀደ ስኬት ማብቃት ብቻ ሳይሆን ያንን ስኬት ማስቀጠል መቻል ትልቁ የአመራር ጥበብ እንደሆነ ይታመናል። በዚህም በአመራር ደረጃ የሚቀጠሩት ሰራተኞች ወይም መሪዎች ላይ የተለየ የአቀጣጠር መስፈርት መከተል ግድ እንደሚልና ለዚህም የድርጅት ባለቤቶች ለቃለ ምልልስ ጥያቄዎችና መልሶች የላቀ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ዋረን በፌት ይናገራሉ። ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገውም ሲያብራሩ የሚቀጠሩ ሠራተኞች በቃለምልልስ ወቅት አደገኛ ተናጋሪ የሚሆኑ አሉ፤ የተሳሳተ መረጃ የሚያቀርቡ እንዳሉ ሁሉ ተገቢው የሥራ ልምድ፣ ሰርተፊኬት፣ የምስጋና ደብዳቤ ኖሯቸው ነገር ግን የሚፈለጉበት ሥራ ላይ ሲመደቡ ብቃት የማይኖራቸው ባለሙያዎች እንደሚኖሩ መረዳት ያስፈልጋል።
ሌላው ከአመራሮች የሚጠበቁ ሦስት ወሳኝ ነገሮች ማለትም የዳበረ ሙያዊ ዕውቀት፣ ተነሳሽነትና የተነሳበትን ነገር ከዳር ሳያደርስ የማይተኛ ጽናትና ቁርጠኝነትን የተላበሰ መሪ ያስፈልጋል፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ተናቦ በአንድነትና በመግባባት የሚሰራ መሪ ትክክለኛው የአመራር ቁመና ላይ እንደሚገኝ ዋረን በፌት ያሰምሩበታል። ከነዚህ ከሶስቱ አንዱ ቢጎል እንኳን የሚመራው ድርጅት አንድ ሶስተኛ ክፍሉ እንደሚጎዳ ማወቅ ያስፈልጋል በማለት አጠናክረውታል።
የሥራ መሪዎችን ለመቅጠር ሊደረጉ የሚገባቸው ወሳኝ ቃለ ምልልሶች
ከላይ የተጠቀሱት ወሳኝ ብቃቶችን የያዘ የሥራ መሪ አግኝቶ ለመቅጠር የሚከተሉት ጥያቄዎችን በማቅረብ መገምገም ይገባል።
1. ሥራ ላይ ምን ፈታኝ ችግር አጋጥሞህ ያውቃል?
በምን ያህል የጊዜ ገደብ ውስጥ መፍትሄ በመስጠት ፈተኸው ታውቃለህ?
ይህ ጥያቄ ተቀጣሪው የሥራ መሪ በአንድ ድርጅት ላይ ችግር ብሎ የሚያስበው ምን ዓይነት ጉዳዮች ሲገጥሙት ነው የሚለውን ለማወቅ ይጠቅማል። በተጨማሪም ከጊዜ ጋር አያይዞ ተገቢ የመፍትሄ አሰጣጥ፣ ፍጥነቱንና ክህሎቱን ለመገንዘብ የሚጠቅም ይሆናል።
2. ውሳኔ ለመስጠት ሲባል በድርጅቱ የተቀመጡ ሕገ ደንቦችን የጣስክበት ጊዜ ካለ ንገረን። ለምንና እንዴት?
ይህ ጥያቄ በሕገ ደንብ ላይ ተጣብቀው የሚቀመጡና ከትዕዛዝ ጠባቂነት ያልወጡ መሪዎች የሚለዩበት ጥያቄ ነው። በመሆኑም መሠረታዊ የሚባሉ አይነኬ ሕጎች እንዳሉ ሁሉ እንደጊዜውና እንደሁኔታው መስተካከል ወይም መሻሻል ያለባቸው የሥራ ሕጎችን በማየት ምን ያህል የውሳኔ ሰጪነት ብቃት እንዳለው ለመረዳት ይጠቅማል።
3. አንድ ሰራተኛ ጎላ ባለ መልኩ ተገቢ ያልሆነ ሥራ ሰርቶ አጋጥሞህ ከሆነና የወሰድከው ዕርምጃ ምን እንደነበር ብትገልጽ?
ይህ ጥያቄ አግባብ ያለው የመፍትሄ አሰጣጥ ብቃትን ይመለከታል። እንዲሁም የሠራተኞች የጥፋት ደረጃ የድርጅቱን ህልውና ምን ያህል እንደሚነካው የሥራ መሪው የተረዳበትን መንገድ ለማወቅ ያስችላል። ተከሰተ የሚባለው ጥፋትም በሥራ መሪው ላይ የነበረን ክፍተት ያመላክታል።
4. ከሥራ ባልደረቦችህ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? በምን ጉዳይ ላይ ቅርበት አለህ?
የሥራ መሪዎች በአለቅነት መንፈስ በተለምዶ ፊት በማኮሳተር ወይም ደግሞ በተቃራኒው አብሮ ቆሞ በማውራትና በየቢሮው በመዞር የሚሉት ዓይነት አቀራረብ አደጋ ፈጣሪ ነው። የሥራ መሪው በጣም በመሸሽ ከመረጃ እንዳይርቅም ወይም ደግሞ በራስ የፈጠራና የውሳኔ ሰጪነት ከመመካት ይልቅ ከሰራተኛው በሚመጣ ግብረ መልስ ብቻ ሁኔታዎች ላይ የሚወስን ጥገኛ መሆኑን ለመለየት ያግዛል። የተግባቦት ችሎታ መለኪያ የሚባሉት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚመካከር፣ ለሐሳብ ዋጋ የሚሰጥ ለድርጅቱ ራዕይ መሳካት ሰራተኞችን ማስተባበር የሚችል መሆን መቻል አለበት።
5. በአብሮ መሥራት ውስጥ ምን ዓይነት እሴት ወይም ባህሪ ይመችሃል?
ከሥራ መሪዎች ብቃት ላይ በዋነኝነት ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል የሥራ ክፍሎችንና ባለሙያዎችን ወይም ሠራተኞችን ማስተባበርና ለአንድ ዓላማ ማነሳሳት መቻል ነው። ይህ ጥያቄ እንደግልጽነት፣ ታማኝነት፣ መከባበር፣ መተጋገዝ፣ አገልጋይነት የሚሉ እሴቶችን በድርጅቱ ውስጥ ለማስፈን ያለውን አመለካከት ለመረዳት ይጠቅማል።
6. ከደንበኞች ጋር በሚኖር ግንኙነት ድርጅትህን የሚጠቅም ሆነህ ካገኘህ ልትዋሽ ትችላለህ?
ይህ የሚጠቅመው የራሱ የተቀጣሪውን የሥራ መሪ እሴት ወይም ማንነት ለመለካት ነው። ደንበኞች የድርጅት ህልውና እንደመሆናቸው እውነተኛ አገልግሎትን ይሻሉ። አንዳንድ ተቋማት ግን በማስመሰል ላይ የተመሠረተ አገልግሎት በመስጠት በስተመጨረሻ ድርጅቱን ለአደጋ ያጋልጣሉ። የድርጅት ምስጢር መጠበቅ የሚለው መርህ እንዳለ ሆኖ ከደንበኞች ጋር በሚደረግ ግንኙነት ውስጥ ግን በምንም ዓይነት መንገድ የሽንገላ አሰራር መወገድ እንደሚኖርበት ይታወቃል። ይህ ጥያቄ የሥራ መሪው ለዚህ መርህ ያለውን ተገዢነት ለማወቅ ይጠቅማል።
7. ትሠራበት ከነበረበት መሥሪያ ቤትም ይሁን ከሌላ የበላይ አካልና ሠራተኝች ወይም ከድርጅቱ ባለቤት ምን ዓይነት የሥራ ምክርና ሐሳብ ሰምተህ ታውቃለህ? እንደሚያውቅ መጠየቅ።
ይህ ጥያቄ የሥራ መሪው ከላይ ወደታች ወይም ከታች ወደላይና የጎንዮሽ በሚኖር የሥራ ውይይትና የሐሳብ ልውውጥ ያለውን ተነሳሽነት ያመለክታል። ጥሩ ሐሳብ ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን በማየት ያለውን የአስተሳሰብ ደረጃ ከዘመናዊው ዓለም አቀፍ የንግድ አመለካከት አንጻር መለካት የሚቻልበት ጥያቄ ነው።
ቸር እንሰንብት
አብርሐም ፀሐዬ
(Email: geraramc@gmail.com)