የድርድር ጥያቄዎችን በጥበብ መመለስ ብልህነት ነው!!

0
1299

የጦርነት ታሪክ ሁሌም የሚቋጨው በሰው ክቡር ሕይወት እና ንብረት ውድመት ላይ አስከፊ ገጽታውን ካስቀመጠ በኋላ ነው፡፡ ይህ ክስተት መቼም ቢሆን ተግባር ላይ የሚውለው አሉ የተባሉ አማራጮች ሁሉ ሚዛን የማይደፉ ሆነው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በሐሳብ አለመግባባት በልዩነት ጎራ ውስጥ የገቡ አካላት የግል ፍላጎታቸውን ወደጎን በመተው ለአገር እና ለወገን በሚበጀው ጉዳይ ላይ ጊዜ ወስደው በሽምግልና መደራደሩ ትልቅ የሥልጣኔ ምልክት ተደርጎሊወሰድ የሚገባው ነገር ነው፡፡ ከሰሞኑ በአገራችን ለተከሰተው የሕውሓት እና የፌደራል መንግሥት ጉዳይ ያለ ደም መፋሰስ የሚቋጭ ባይሆንኳ በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ኪሳራ ለመቋጨት የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ የዘውትር ጸሓፊያችን ግዛቸው አበበ “ድረድር ጥያቄዎች በጥበብ ከተመለሰበት ከሁሉም የላቀ አዋጭ መንገድ ነው” ይለናል።

በወርሐ ግንቦት 1983 የደርግ፣ የሕወሐት እና የኤርትራው ሕዝባዊ ግንባር ባለሥልጣናት ለንደን ከተማ ውስጥ ነበሩ። ባለሥልጣናቱ በቦታው የተገኙት ለድርድር ነው። በዚህ ጊዜ በተለይም በመጨረሻው ዙር ድርድሮች ወቅት። ሕወሐት አዲስ አበባን ከበባ ውስጥ አስገብቶ፣ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተኩስ ርቀት ውስጥ አስገብቶ፣ ያለ ሕወሐት ፈቃድ አውሮፕላን እንዳያርፍና እንዳይነሳ አስጠንቆም ጭምር ነበረ ከደርግ ጋር ለድርድር የተቀመጡት። ድርድሩ እየተካሄደ በነበረበት ጊዜ ሕወሐት በአዲስ አበባ ዙሪያ መሽጎ፣ ብዙ ኤምባሲወች ወደሚገኙባት ወደ አዲስ ከመተኮስ ታቅቦ ጸጥ ብሎ የተቀመጠ ይምሰል እንጅ በቁጥጥሩ ስር ያልገቡ በደቡብ፣ በምስራቅና በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ክፍለ ሀገሮችን እና ከተሞቻቸውን እየከበበ፣ እየተቆጣጠረና ከፊቱ ሊቆም በሞከረ ላይ ሁሉ እየተኮሰ ሥራውን ሳያቋርጥ በመስራት ላይ እያለ ነው አቶ መለስና አቶ ኢሳያስ ሱፍና ከረባታቸውን አድርገው ለድርድር የተቀመጡት።

ይህ የመጨረሻ ሰዓት ድርድር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ጥቅም የማያመጣ፣ የሕወሐትን እና የሕዝባዊ ግንባርን ግስጋሴወችን በስንዝር የማያዛንፍ መሆኑን ማንም ያውቃል። ነገር ግን ሕወሐት እና ሕዝባዊ ግንባር ገጽታቸውን አሳምረውበታል፣ ድል ጨብጠውም ሰላምን በጠረጴዛ ዙሪያ ለማግኘት የሚገፋፋ ታላቅ ትዕግስትና ማስተዋልን የተካኑ ወጣቶች ተብለው ተወድሰውበታል። መለስ ዜናዊና ኢሳያስ አፈወርቂ እንደ እነሱ በሽምቅ ውጊያ ለሥልጣን ከበቁት ከፖል ካጋሚ ጋር የአፍሪካን ብሩህ ተስፋ የፈነጠቁ ወጣት መሪወች ተብለው ተደንቀውበታል። ብዙም ተስፋ ተጥሎባቸው ነበረ። ይህ ድርድር የአቶ መለስ ዜናዊን ገጽታ ከማሰር የተለየ ጥቅም ነበረው ከተባለ የተወሰኑ የደርግ አባላትን በድርድር ስም ከኢትዮጵያ ወጥተው በዚያው መጠጊያቸውን እንዲያፈላልጉ መርዳቱ ነው።

ማንም ይሁን ምን የዘራውን ያጭዳልና፣ አሁን ድርድር እናድርግ ብሎ የመጠየቅ ተራው የሕወሐት ሆኗል። ይሕ የሕወሐት ድርድር ጠያቂ መሆን በጠቅላይ ሚ/ሩም ጭምር የሕወሐትን ሽንፈትን መቀበል፣ እባካችሁ ማሩን ብሎ እንደ መለመን ተቆጥሯ። ድል ያሰከራው ብዙዎች በመገናኛ ብዙሐን ላይ እና በማኅበራዊ ሚዲዎች ላይ ብቅ እያሉ ያ ምህረት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ብዙ ከባድ ነገሮችን በመናገር ላይ ናቸው። ኢሳት ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ የሊቢያውን ሙአመር ጋዳፊ፣ የላይቤሪያውን ሳሙኤል ዶ እና የመሳሰሉ የመጨረሻ ሰዓታት ቪዲዮዎች እየጋበዘ ሕዝብ ለብቀላ እንዲነሳሳ በይፋ እየቀሰቀሰ ነው።

ኢሳት በዘመነ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመን አሜሪካ እና እንግሊዝን በሶርያ እና በሊቢያ ላይ እንዳደረጉት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሳይከፍቱ ቀሩ ብሎ መቆጨቱን የገለጸ ሚዲያ ነውና አንዳንዴ ቆም ብሎ ማሰብ ይቸግረዋል። ኢሳት 90 ሚሊዮን ሕዝብ ከ5 ሚሊዮን ሕዝብ ጋር ግብግብ እንደገጠመ አድርጎ በመቁጠር የሕዝብ ለሕዝብ ግጭትም እንዲነሳ የቀሰቀሰ ሚዲያ ነው እና የአሁኑ የኢሳት አካሄድ በለው፣ ቁረጠው፣ ፍለጠው ከሚለው የመደበኛና የማኅበራዊ ሚዲያወች መጯጯህ ጋር ተደማምሮ ሰቆቃና ጭፍጨፋ እንዳስከትል ብልጽግናወች ሊያርሙት ይገባል። ማንኛውም ወንጀለኛ ለፍርድ ቀርቦ የሥራውን የሚያገኝበት አሰራር በየግለሰቡ መገፋትና እርምጃዎች በየግለሰቡ መወሰድ አይገባቸውም።

በኦሮሚያ ጭፍጨፋዎች ሲካሄዱ ነገሩን ለማስተባል የሚጣደፉ የኦሕዴድ ብልጽግና ካድሬዎች ፎቶዎችን በመለጣጠፍ ሕወሐት አማራዎችን ጨፈጨፈ እያሉ አዛኝ ቅቤ አንጓችነታቸውን እያሳዩ ነው። የኦሕዴድ ብልጽግናዎች፣ የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት አባላት ሲጨፈጨፉ የኦነግን ባንዴራ ይዘው ከሕወሐት ታጣቂዎች ጋር ተባብረው ሰራዊቱን ያጠቁት ኦሮሞዎች ከየት እንደመጡ እና እነ ማን እንደሆኑም ጭምር ሊነግሩን ይገባል። ይህን መሰሉ ነገር የኢትዮጵያን ጦር መፈተሸ እንደሚገባም የሚያሳይ ይመስላል።

በብልጽግናዎች ዘንድ ስለ ሕወሐት ሽንፈት ሲታሰብ፣ ኦሕዴድ/ብልጽግና ከጎኑ ያሰለፈውና የማይከዳው የኦሮሞ ሕዝብ አለ እንደሚባው ሁሉ ሕወሐትም ከጎኑ የተሰለፈለትና የሚያምንበት ሕዝብም እንዳለ በመረዳት አካሄድን ማስተካከል ይገባቸዋል። ሕወሐት ቢሸነፍ እንኳ የማይሸነፍና መኖሩን የሚቀጥል ሕዝብ አለ። ይህ ሕዝብ በሽዎች ወይም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሊሆን ይችላል። ሕወሐትን አሸንፎ ትግራይን የሚገዛ ቡድን ካለም ይሕን ሕዝብም ጭምር ነው ሚገዛው፣ በዚህ ሕዝብ መካል ሆኖ ነው የሚገዛው። ስለዚህ አሸናፊ ነን በሚል መንፈስ ድርድር ማድረግ ባይፈለግ እንኳ ስለ ድርድር በተወሳ ቁጥር መልስ ሲሰጥ ይህን ሕዝብ፣ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብና እናደራድር የሚሉ ወገኖችን ግምት ውስጥ በማስገባት በቅጡ የታሰበበት ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው።

በዕብሪት ‘የመጨረሻው ጁንታ እስኪሞት ወይም እጁን እስኪሰጥ እተኩሳለሁ፣ በጀት ትግራይን እደበድባለሁ፣ የትግራይ ሕዝብ የምጥለው ቦምብ ጭዳ እንዳደርግህ ጥግህን ያዝ’ እያሉ ለፈራጅ ለገናዥ አስቸጋሪ መሆን ተገቢ አይደለም። በበሳል ፖለቲካዊ አካሄድ ይህን ሕዝብ ከሕወሐት መነጠል ጥበብ ነው፣ ከልብ በመነጨ አስተዋይነት ከሕወሐት ኈች ውስጥ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ የቆሙትንና ለሕዝብና ለአገር ሚያስቡትን ተለያይተው የሚቆሙበትን ስንጥቅ ለመፍጠር መስራትም በጦር ሜዳ ጀብድ ከመስራት ያልተናነሰ ወይም የተሻለ የጀግንነትና የጥበብ ሥራ ነው።

በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት በሚመለከት በወንድማማቾች መካከል የሚካሄድ ጦርነት ነው የሚሉ ወገኖች ብዙ ወቀሳና ትችት እየደረሰባቸው ነው። የድርድር ሐሳብ የሚያቀርቡ ወገኖችማ ‘የወያኔ ቡችሎች’ ተብለው ይዘለፋሉ። እነ ታዬ ደንደአን ጨምሮ ብዙ የኦሕዴድ/ልጽግና፣ የብአዴን/ብልጽግና እና የሌሎች ብልጽግና ካድሬዎች ጠቅላይ ሚ/ሩ ‘ጁንታ’ ብለው ፈርጀው የፎከሩበት የትግራይን ሕዝብ በሙሉ ሆኖ እየታያቸው እንዳይሆን መስጋት ተገቢ ነው። በዚህ ሰዓት የትግራይ ሕዝብ ወገን መሆኑን ከመናገር ይልቅ የትግራይን ሕዝብ ስለ መምታትና ስለ መቅጣት፣ ስለ መዝረፍና ማባረር መናገር እንደ ጀግንነትና አገር ወዳድነት እየተቆጠረ ነው።

በማኅበራዊ ሚዲዎች ላይ ያለ ገደብና ያለ ጥንቃቄ እየተለቀቀ ያለው የጥላቻ መልዕክት በየክልሉ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን በማጥቃትና በመዝረፍ ተግባራዊ እንዳይደረግ መጠንቅና ማስጠንቀቅ የመንግስት ፋንታ ነው። ወያኔወች በኤርትራውያ ላይ ያረጉትን በትግሬወች ላይ መፈጸም አለብን ባዮችም እየተነሱ ነው።

መዝረፍን፣ ሃብትና ንብረትን መውረስን እና ትግርኛ ተናጋሪወችን ከየክልሉና ከየከተማው ማባረርን እየሰበኩ ነው። ይህንን ቅስቀሳ ማስቆምም የመንግስት ፋንታ ነው።
ጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ ሱዳኖችን አደራድረው አስታርቀዋል፤ ለኖቤል ሽልማቱ ተገቢነት እንደ ማስረጃ ተደርገው ከተጠቀሱት ተግባራት መካከል ይህ የሱዳኑ የአስታራቂነት ተግባራቸው አንዱ ሆኖ መጠቀሱ የሚረሳ አይደለም። የሱዳኑ ጠቅላይ ሚ/ር አብደላ ሃምዱክ ለጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ በአራት የተለያዩ ጊዜያት ድርድርን በሚመለከት ስልክ ደውለው እንደነበረ አል-አይንና ሱዳን ትሪብዩን የተባሉ ሚዲያዎች ዘግበዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የኢጋድ፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የብሪታኒያ እና የአሜሪካ ባለሥልጣናትም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ወይም ሐሳቦችን ሰንዝረዋል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ጉዳዩ ዓለም አቀፋዊ መልክ ሊይዝ አይገባውም በማለት ሁሉንም ጥያቄዎች ውድቅ አድርገዋል።

ጠቅላዩ የሕወሐት መሪዎችን ይዘው ለፍርድ ሳያቃርቡ ጦርነቱ እንደማይገታና ድርድር አስፈላጊ አለመሆኑን ለዚህም ለዚያም ተናግረዋል። የአገራት መሪዎች በሚነጋሩበት በትዊተር ላይ ይህን ጸረ-ድርድር አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚ/ሩ ከዚሁ ድርድር ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽ ውስጥ በዚህ ጦርነትም ሆነ ከጦርነቱ በሚወለዱ ሌሎች ሁኔታወች ኢትዮጵያ ወደ ትርምስ ውስጥ ትገባለች የሚሉ ወገኖች ኢትዮጵያን የማያውቁ ናቸው ብለዋል፤ ከጠቅላላው አነጋገራቸው ጠቅላዩ ድርድሩን ወንጀለኞችን ለመደበቅና ለማዳን የታቀደ ዘዴ አድርገው እንደቆጠሩት መረዳቱ አያዳግትም።

እንደ አንድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ የድሃ አገር መሪና ፖለቲከኛ የድርድር ጥያቄ ሲቀርብ የመደራደሪያ አጀንዳዎችን በጦርነቱ ሊገኝ የተፈለገውን ግብ በሚያሳካ መንገድ ቀርጾ ቅድመ ድርድር በማድረግ የበላይነትን ለማሳየት የመሞከር ብልጠትን መጠቀም ተገቢ የነበረ ቢሆንም ጠቅላይ ሚ/ሩ ጦርነቱን ብቸኛ አማራጭ ነው ብለው በይፋ ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ተናግረዋል።

ድርድርን ከመግፋት ይልቅ የመደራደሪያ አጀንዳን ለፍርድ የሚቀርቡ የሕወሐት አውዎችን ስም የያዘ ዝርዝር በማዘጋጀት እነሱን አሳልፎ በመስጠት ድርድሩን መጀመር እንደሚቻል ሐሳብ ማቅረብ ይቻል ነበረ። የስም ዝርዝሩ ዐስርም ይሁን ዐስር ሺህ ስሞችን ያካተተ ሊሆን ይችላል። ይህ ሲሆን ደግሞ ራሱ ሕወሐት ድርድሩን ውድቅ በማድረግ ፖለቲካዊ ማኖ ይነካል። በዕብሪተኛነት የሚፈረጀው ጥፋተኛም እሱ ይሆናል። ይህን መሰል ፋዎል (ጥፋት) በሕወሐት ከተሰራ የሕወሐት አውራዎችን ከሕዝብ የሚነጥል ብቻ ሳይሆን በነባርና በአዳዲስ የሕወሐት አውራወች መካከል ስንጠቅ የመፍጠር አጋጣሚም ሊፈጠር ይችላል።

ይህን መሰሉ አጋጣሚ ያለ ተጨማሪ የሕይወት ኪሳራ ብዙ ድሎችን ለማግኘት የሚያስችል ሊሆን ይችላል። መደራደሪያ አጀንዳ ከማስያዙ ጎን ለጎን፣ ነገር ግን ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ከትግራይ ወጥተው ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል መጓዝ የሚፈልጉ፣ በከበባ ውስጥ ያሉም ሆነ በምሽግ ውስጥ የተቀመጡ የሰሜን ዕዝ መሪዎች እና ወታደሮች፣ የፌደራል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት እንዲሁም ሌሎች ሰዎች በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ጣልቃ ገብነት እና አጃቢነት ከትግራይና ከከበባ ወይም ለሕወሐት ያደሩ መስለው አንገታቸውን ከደፉበት ሁኔታና ቦታ የማውጣቱ ጉዳይ የድርድር ቅድመ ሁኔታ ማድረግም ተገቢ ነበረ።

ጠቅላይ ሚ/ሩ ጦርነቱን እንደሚያሸንፉ ሙሉ እምነት አሳድረው፣ ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦችስ አሸናፊ ይሆናሉን የሚለውን ጥያቄ ችላ ብለው ድርድሩን እያጣጣሉት እንዳይሆን መስጋት ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ አሸነፈች የምትባለው አንድነቷ ተከብሮ ስትኖርና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰላም አግኝቶ መኖር ሲችል መሆኑ መረሳት የለበትም። ሕወሐት በጠላትነት የፈረጀውን አራማን ወዳጅ ብሎ ትግራዋይን በጅምላ ተረኛ ጠላት የማድረግ አካሄድ ከተፈጠረ ለኢትዮጵ ለኢትዮጵያውያን ሽንፈት ነው።

ይህን መሰል ነገር ከፈጠረ አሸናፊው የዘረኛነት መሐንዲሱ ሕወሐት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ኢትዮጵያ አሸነፈች፣ ለውጡም ተሳካ ማለት የሚቻለው ይህ ሁሉ ነገር ታልፎ ኢትዮጵያውያን በመረጡት መሪ መመራት ሲጀምሩ ነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ የሚገኘው ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ መሆን አለበት። በተረኛት ፖለቲካ ዲሞክራሲን ማስፈን አይቻልም። በተረኛነት ፖለቲካ ገዥ መሆን ጊዜን ጠብቆ ሕወሐት ያጣጣማትን ተረኛ ተሸናፊነት ከመከናነብ ያለፈ ውጤት አይኖረውም።

የአንድ ቀን ይሁን የመቶ ቀን ጦርነት ፍጻሜው ከዚህ የተለየ አይደለም። በጦርነቶቹ ውስጥ ደግሞ የክላሽና የመትረየስ ጥይቶች ብቻ ሳይሆኑ ቦምብ፣ የመድፍ አረር፣ ሮኬቶች፣ ሞርታሮች፣ ላውንቸሮችና የመሳሰሉ ከፍተኛ የውድመት መሣሪያዎችም ጭምር ናቸው ጥቅም ላይ የሚውሉት። ስለዚህ ድርድርን መግፋት ተገቢ የማይሆነውና ድርድርን በጦር ሜዳ ሊገኝ የሚፈለገውን ድል ያለ ሕይወትና አካል ኪሳራ ለማግኘት በሚያስችል መልኩ ማካሄድ ፈሪነት ሳይሆን ብልህነት ነው የሚባለው ለዚህ ነው።

አንዳንድ ወገኖች ይህ ጦርነት አገሪቱን እንዳያፈራርስና እንዳያተራምስ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። ጠቅላይ ሚ/ሩ ደግሞ ኢትዮጵያን የማያውቁ ብለው አፊዘውባቸዋል። ኢትዮጵያ በአንዱ ክልሏ ላይ ይህን የመሰለ ከባድ ጦርነት ለማካሄድ የበቃቸው በጠቅላይ ሚ/ሩ የአመራር ብቃት ማነስ፣ በመንግሥታቸው ማስተዋል መጉደል መሆኑን መካድ ተገቢ አይደለም። ለመሆኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ከዛላንበሳና ከአካባው ሊወጣ ሲል ሕወሐት በላካቸው ወጣቶች ክልከላ ደርሶበት ወደ ኋላ ሲመለስ ምን እርምጃ ተወሰደ? በባድመና በአካበባው የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ሸሬ አካባቢ መንገድ ሲዘጋበትና ንብረቱን በሙሉ መንገድ ላይ ትቶ በሽሬ ስቴዲዮም እንደ እስረኛ ሲታጎርስ ምን እርምጃ ተወሰደ? ለመሆኑ ይህ ክስተተ የከፋ ነገር እንደሚመጣ ጠቋሚ ተገርጎ ያልታየው ለምንድን ነው?

በሰሜን ዕዝ ጦር አመራሮች እና ወታደሮች ላይ ለደረሰው ሰቆቃ የመንግሥት ችላ ባይነት ሰአስተዋጽኦ አላደረገምን? ለበርካታ ከባድና ቀላል የጦር መሣሪያወች በሕወሐት መወረስስ መንግሥት ተጠያቂ አይሆንምን? እንዲህ ወደ ኤርትራ ምድር መግባት ካልቀረ ቀድሞውንስ ቢሆን ጦሩና መሳሪያው ወደ ኤርትራ ምድር ገብቶ በአሰብ በኩል ወይም በሱዳን በኩል ወደ ታሰበለት ቦታ እንዲጓጓዝ ያልተደረገው ወይም ሌላ መፍትሔ ያልተፈለገለት ለምንድን ነው? ይህን ችግር የሚቀርፍ መፍትሔ ሳይሰጥ ወደ ኹለት ዓመት በመቆጠሩ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት አባላት በግፍ ተገድለዋል። ጠቅላይ ሚ/ሩ እና የብልጽግና ጓዶቻቸው በታሪክ ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ቸልተኝነት የፈጸሙ መሆኑንም መካድ አይቻልም።

ሕወሐት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሰበብ ብቻ ሳይሆን ከ1997 ምርጫ ማግስት ጀምሮ በልዩ ዘመቻ የጦር መሣሪያዎችን ወደ ትግራይ በገፍ ማጋዙ እየታወቀ፣ ሕወሐት በ2010 ወደ መቀሌ መጓዙን ተከትሎ በተከታታይ ልዩ ኃይልና ኮማንዶ እያሰለጠነ ወታደራዊ ጡንቻውን ሲፈረጥምስ ምን ተመጣጣኝ ዝግጅት ተደረገ?
አሁንም ቢሆን የጠቅላይ ሚ/ሩ ኢትዮጵያ አትተራመስም የሚል አመለካከት በጥልቀት ሊታሰብበት ይገባል። የኢትዮጵያችንን ሰላምና መረጋጋት፣ እንጦጦ መናፈሻንና አንድነት ፓርክን እየጎበኙ “ይህን የመሰለ መዝናኛና መናፈሸ የሚሰራልንን መሪ የሰጠን ጌታ ይመስገን!” በሚሉ ሰዎች አስተሳብ መለካት ተገቢ አይደለም። ኢትዮጵያ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአፋር እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝና አነታራኪ ቦታወች ወዘተ…. መጤ እየተባሉ ሕይወታውን ለሚገፉ ሰዎችና እንጦጦ ፓርክን ለሚጎበኙና ሰላሟን በፓርኩ ውበት ለሚመኩ ሰዎች አንድ ዓይነት አገር አይደችም።

መጤ እየተባሉ የመከራ ሕይወት ለሚገፉ ምስኪኖች ኢትዮጵያ ከመተራመስ በላይ የመከራ ምድር ናት። ከክልላቸው ውጭ ለሚኖሩ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች በተለይም ለአማራ ተወላጆች ሕይወት ምስቅልቅል ሆኖባቸዋል። ኑሯቸው ከመተራመስ በላይ ነው። የመከላከያ ኃይል ከቦታው ሲነሳ (ሲወጣ) አድፍጠው ሲጠባበቁ የነበሩ ገዳዮችና ጨፍጫፊወች ሰተት ብለው ገብተው መከራ የሚያዘንቡባው አካባቢወች በጣም እየብዙ ነው። ይህን መሰሉ አካሄድ ለእርስ በርስ ግጭትና ለሌላ ሰፋ ያለ ትርምስ የሚገፋፋ መሆኑን መካድ አይቻልም።

ኢትዮጵያ ውስጥ በመታየት ላይ ያለው ችግር መጤ በተባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃትና ጭፍጨፋ መካሄዱ ብቻ አይደለም። የታጣቂዎች ግጭትም አለበት። በኦሮሚያ ታጣቂዎች ከመንግሥት ሃይሎች ጋር ይጋጫሉ፣ ይታኮሳሉ። ታጣቂዎች ፖሊሶችን ወይም ባለሥልጣናትን ገድለውም ይሰወራሉ፣ አንዳንዴም የመንግሥት ታጣቂዎች እርምጃዎችን ይወስዳሉ። ተመሳሳይ የታጣቂወች ግጭቶች በቤኒሻንጉል ክልልም እየተከሰቱ ነው። በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ከተራዘመ ወይም ጦርነቱ ቆሞ ትግራይ ክልል ውስጥ በኦሮሚያ የሚታየውን የመሰለ ግጭት፣ ትርምስና ሰዎችን በአንዳች መመዘኛ ለይቶ የማጥቃት ሴራው ከቀጠለ፣ ኦሮሚያን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ ያልተሳካለት ብልጽግና ይህን ዝርክርክ አመራሩን በትግራይም ከደገመው ቀጣዩን ችግር ‘ትርምስ’ የሚለው ቃል የሚገልጸው ላይሆን ይችላል።

በመጨረሻም በሌሎች መንግሥታት ዘንድ ጭምር አነጋጋሪ እየሆነ የመጣው የኤርትራ መንግሥት ሚና መስመር የተበጀለትና የተገደበ መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ሕወሐትን እንደ ኢትዮጵያዊ ማየቱ ቢከብድ የትግራዋይ ኢትዮጵያዊነት ሊዘነጋ አይገባውም። ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ከአዲስ አበባ ጉብኝቶቻቸው ከአንደኛው መልስ ከኤሪ-ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሕወሐት እንዳከተመለት፣ ከጨዋታ ውጭ መሆኑን የገለጹት በእንግሊዝኛ ‘Woyene Game Over!’ በማለት ነበረ። አሁን ደግሞ የኤርትራ መንግሥት በጦርነቱ ጣልቃ ገብቷል የሚል ውንጀላ ከሕወሐት ዘንድ እየተሰማ ነው። በሑመራ በኩል የኤርትራ ጦር በተዋጊወቼ ላይ የከባድ መሣሪያ ድብደባ አካሂዷል የሚል ውንጀላ በሕወሐት በኩል ተሰንዝሯል።

እዚህ ላይ ሕወሐቶች እያሳዘኑንም እያሳፈሩንም መሆኑን የተረዱት አይመስሉም። ሕወሐቶች ብዙውን ሕዝብ በአስተሳሰብና በአመለካት አጣቂኝ ውስጥ እንደጨመሩትን ረስተዋል። የሕወሐትና የትግራይ ክልል መሪ የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከሳምንት በፊት በትግራይ ምድር የሚገኙ ከባድ መሳሪያወችን ሁሉ ሕወሐት እንደወረሰ መናገራቸው አልበቃ ብሎ የኢትዮጵ መከላከያ ሠራዊት ከታጠቀው ከባድ መሳሪያ ይልቅ የሕወሐት ታጣቂወች የወረሱት ከባድ መሣሪያወች በብዙ እጅ ብልጫ እንዳለው በይፋ ተናግረዋል። ይህ የደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) አነጋገር ‘መከላከያ ጦርህን መዝብሬዋለሁ፣ መከላከያህን ባዶ እጁን አስቀርቸዋለሁ’ ብለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ መርዶ እንዳረዱና ግብጽን ጨምሮ ለሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ሁሉ የምስራች እንደተናገሩ አይቆጠርምን?

ስለዚህ “የኤርትራ ጦር የሕወሐትን ምሽግ በከባድ መሣሪያ አጠቃ” ያሉትን ደብጽዮን ገብረሚካኤልን እንደ ምስራች ነጋሪ ነው ወይስ እንደ መርዶ አርጅ ልንመለከታው የሚገባን?

ብዙ ብልህና አስተዋይ አባቶችና አያቶች የገነቧት ኢትዮጵችን፣ በሥልጣኔም ሆነ በኋላቀርነት ዘመኗ በክብሯ ተደራድረው የማያውቁ ኩሩ ሐበሾች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ያቆዩልን አቢሲንያችን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ እየተጣላን ሌላ ጠላት የምንጠራላት አገር መሆኗ ያሳፍራል፣ ያሳዝናልም።
ግዛቸው አበበ / gizachewabe።gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here