መነሻ ገጽአምዶችማኅበረ ፖለቲካየቢዝነስ ዘገባዎቻችን የምንፈልገውን ጉዳይ እየነገሩን ይሆን?

የቢዝነስ ዘገባዎቻችን የምንፈልገውን ጉዳይ እየነገሩን ይሆን?

ጋዜጠኝነት ብዙ መልክና ቀለም ያለው ሙያ ነው። በሁሉም አቅጣጫ ግን ሁሉም ሊስማማበት የሚችል የወል ተግባር አለው፤ ይህም ሕዝብን ማገልገል የሚል ነው። በዚህ መሠረት ሙያው ሕዝብን የሚያገለግልበት አንዱ መንገድ የምጣኔ ሀብት ጉዳዮችን መዘገቡና ጉዳዮቹን የሚዘግብበት መንገድ ነው። አብርሐም ፀሐዬም ይህን ነጥብ በማንሳት የቢዝነስ ዘገባዎች ምን ያህል አጋዥና ዐይን ከፋች ሊሆኑ እንደሚገባና በተጓዳኝም ያለውን ነባራዊ እውነት ቃኝተዋል።

ከጋዜጠኝነት የሙያ ዘርፎች አንዱ የቢዝነስ ጋዜጠኝነት /Busibess Journalism/ ነው። ይህ ዘመን ገንዘብ የሚያሾረው የቢዝነስ ጊዜ ነው። ኃያላኑ የሚገዳደሩት በቁጥር ተሰልቶ በተቀመጠው የየአገራቸው የምርት መጠን ክምችት ነው። የምጣኔ ሀብት ቀመር የዓለማችን ትልቁ ሒሳብ ሆኗል። ‹‹መከበር በኪስ ነው›› የሚለው አዲስ ይትበሃል በእኛም አገር ተተክሏል። ይታመንበታልም። በዚህ ውስጥ ደግሞ የቢዝነስ ጋዜጠኝነቱ የየዕለቱን ውጣ ውረድ ለሕዝብ የሚያደርስ ከፍ ሲልም ለምንና እንዴት ባይ ዘርፍ ሆኖ ከዚህ የካፒታል ዘመን እኩል እየሮጠ ነው።

በኢንዱስትሪ የበለጸጉት አገራት፣ አሁንም ምጣኔ ሀብቱ ላይ አትኩረው ሠርተው ሕዝባቸውን በልቶ ከማደር አዘልለው በተድላ ወደማኖር የተሻገሩትም፣ ከባንካቸው ቀጥለው የብዙኀን መገናኛዎቻቸውን የቢዝነስ ዘገባ በአንክሮ ይከታተላሉ። የቢዝነስ ጋዜጠኝነት የአገራት የስርዓት ሚዛን እንዳይናጋ ደግፎ የሚይዝ ማገር ነው። ሙስና ይጠቆምበታል፣ እንደአየር ትንበያ የፖለቲካ አውሎ ነፋስ ከመነሳቱ በፊት የምጣኔ ሀብት ዘገባን በምልክትነት ያሳያል።

ቢዝነስ የመስኖ ውሃም፣ አደጋ ፈጣሪ ጎርፍም ነው። ምጣኔ ሀብት ሲናጋ ዕዳው ብዙ ነው። መንግሥታት የቢዝነስ ዘገባዎችን ቀድሞ የጥንቃቄ ዕርምጃ ለመውሰድ ይጠቀሙበታል። የንግድ አሻጥሮች አገርና ሕዝብን እንደብል ሰርስረው እንዳይጥሉ ከሚዘረጉት ስርዓት እኩል ብዙኀን መገናኛዎችን እንደመጠቆሚያ ማሽን ይገለገሉበታል።

ምንጊዜም ቢሆን በየዘመኑ ጎልተው የሚወጡ ርዕዮተ ዓለማት አሉ። የግብርና ዘመን፣ የውትድርና ዘመን፣ የፖለቲካ፣ የፍልስፍና፣ የኃይማኖት ወዘተ እየተባለ ዘመኑ የሚጋብዘውና ትኩረት ሰጥቶ የሚንከባከበው አለ። ይህ የኻያ አንደኛው ዘመን ሉላዊነት ከፈጠረው ቅርርቦሽ አንጻር የቢዝነስ ዘመን ሆኖ ብቅ ብሏል።
ዓለም ከኹለቱ ጦርነቶቿ ስታገግም ቀጣይ ጉዳይዋ ምጣኔ ሀብት ላይ ማተኮር ሆኖ ዓለም በዚህ እየተዘወረች ነው። የአሁኑ ትልቅ ጦርነቱ ራሱ የንግድ ጦርነት ነው። ሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም ካደረጉት ቀዝቃዛው ጦርነት ቀጥሎ የተካሄደው ግዙፉ ጦርነት የኃያላኑ የንግድ ጦርነት /Trade War/ ነው።

አገራት ቋንቋቸው ገንዘብ ሆኗል። ቁጣቸው፣ ኩርፊያቸው፣ ጦር መሣሪያቸው፣ ፍቅራቸው በገንዘብ ስሌት ነው። ዓለም አንደኛ፣ ኹለተኛና ሦስተኛ ተብላ የተከፈለችው በዚያ ነው። ገንዘብ ላይ መሥራት ግድ ሆኗል። መንግሥት ይህንን የገንዘብ ፍላጎት በተሻለ ንግድ ሥራ ምጣኔ ሀብቱን የተዋጣለት በማድረግ አሳክቶና ማኅበረሰቡም ተሳክቶለት በዚያ ከተጠቀመ ሕዝቡ ትልቅነቱን ያውጃል፤ ዝቅ ሲል መካከለኛነቱን፣ ካልሆነ ደሞ ዝቅተኝነት ላይ ይቀመጣል።

ምጣኔ ሀብት ካልተሳካ መዘዙ ብዙ ነው። ቀውሱ በቀላሉ አይለቅም። የፖለቲካው መቀመጫ ምጣኔ ሀብት ነው። በአጠቃላይ ምጣኔ ሀብት ህልውና ሆኗል። መዘወሪያው ደግሞ ገንዘብ!

እንደድሮ ከዛፍ ሸምጥጦ፣ አፈር ምሶ በልቶ ማደር የለም። በመሸበት ‹የእግዜር እንግዳ ነኝ› ብሎ ቀምሶ ማደሩ አስቸጋሪ ሆኗል። አገራት በጦርነት ወረራ አድርገው አይዘርፉም። ሁሉም በንግድ ስርዓት ማዕቀፍ ወስጥ ሆኖ በገንዘብ ልውውጥ የሚከወን ነው። ስለሆነም ከአገርና ሕዝብ ወርዶ ስርዓት በተበጀለት ምጣኔ ሀብታዊ ቀመር የማለፍ ጉዳይ የእያንዳንዱ ሰው ግዴታ ጭምር ሆኗል።

ደሞዝ፣ ግብር፣ ግዢ፣ ሽያጭ፣ ትርፍ፣ ኪሳራ መደበኛ ቋንቋዎቻችን ናቸው። ንግድ ከመኖር አለመኖር ጋር የሚያያዝ ነው። ለዚህም ነው የቢዝነስ ጋዜጠኝነት በዓለማችን ከተፈጠረበት የአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከምንጊዜውም በላይ ደግሞ አሁን ላይ ከተራው ሕዝብ እስከ መንግሥታት ጭምር ሳይሰሙ ውለው የማያድሩት። ለመሆኑ ጋዜጠኝነቱ ያለው ተጽዕኖ ምንድነው? ምንስ መሆን አለበት?

የቢዝነስ ጋዜጠኝነት ምንነትና ተግባራቱ
የቢዝነስ ጋዜጠኝነት ንግድ፣ ገንዘብና ምጣኔ ሀብት ላይ ያተኮረ በብዙኃን መገናኝ የሚሰራጭ ዘገባ ነው። ይህም ሲባል ገንዘብን ወይም የንግድና ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ሲነሱ በውስጡ ሰው አለ። ጋዜጠኝነት ምንም ነገሩ ከሰውኛ ጉዳይ ጋር እየተያያዘ የሚሠራ ነው። ሰው ምን ሆነ? ምን ተጠቀመ? ምን ተጎዳ? ምን ቀረበለት? ምን አጣ? ምን ሊሻሻልለት ነው? ምን የአኗኗር ተጽእኖዎች አሉበት ወይም ምን ተከስተውበት ነበር? ዛሬስ ምን እተካሄደ ነው? ነገ ምን ሊሆን ነው? እየተባለ ከሰው ልጅ የዕለት ከዕለት ሕይወት ዘዬው ጋር ያሉ ቁስና አገልግሎቶች በአግባቡ ይፈተሹበታል። በምጣኔ ሀብታዊ መንገድ ይሰላሉ።

ሰው ሲባል ማኅበረሰብ ነው። እያደገ መጥቶ አገር እና ዓለም የሚሆን የሕዝብ ስር መሠረት ነው። የቢዝነስ ጋዜጠኝነት የንግድ መመሪያው፣ ልውውጡና አተገባበሩ እየፈጠረ ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽእኖው በመዘገብ ሰው ወይም ማኅበረሰቡ ሊረዳበት በሚችለው የዕለት ከዕለት ቋንቋው እየነገሩ ማንቂያ ደወል ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል።

ጋዜጠኝነት በቢዝነስ ጋዜጠኝነት ቁመና ላይ ተገኘ የሚባለው ሰዎች ወይም ተቋማት ከንግድ ወይም ምጣኔ ሀብት ጋር ተያይዞ የተዘገበውን ዘገባ ሰምተው ራሳቸውን ወይም ዙሪያቸውን ማየት ሲጀምሩ ነው። የተከታተሉትን መረጃ ሰምተው ሥራቸውን፣ ንግዳቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ በአጠቃላይ አኗኗራቸውን ይፈትሻሉ፣ ያቅዳሉ፣ ይከልሳሉ፣ ያስተካክላሉ ማለት ሲቻል ነው።

ይህ ከላይ የተጠቀሰውን ለማድረግ ገፊ ምክንያት ሲሆናቸው ጋዜጠኝነቱ በትክክልም የቢዝነስ ጋዜጠኝነት ሆነ ማለት ነው። ዘርፉ መንግሥትም በትኩረት እንዲሠራ መቀስቀሻ፣ ማስጠንቀቂያና መጠቆሚያም በመሆኑ የዓለም ኃይል እዚህ ዘርፍ ላይ ያተኩራል።

የቢዝነስ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ
በአገራችን የቢዝነስ ጋዜጠኝነት እንዴት እየተሠራ ነው ካልን፣ እንደሌላው ሙያ ሁሉ እዚህም ላይ ገና ብዙ ይቀራል። በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ተቀብሎ ቀጥተኛ ዜና አድርጎ ከማቅረብ በዘለለ በትኩረት ሲሠራበት አይታይም።

ወደዘገባዎቹ ስንመጣ ለምሳሌ የሽንኩርት መወደድ ላይ ዘገባ ሲሠራ፣ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ ከትላንት እስከ ዛሬና ቀጥሎስ ምን ተጽእኖ ያመጣል እስከሚለው ደረጃ ድረስ ተጉዞ ማየት ይገባል። የሽንኩርት ዋጋ መጋሸብ የምግብ ዋጋ መወደድ ላይ ተጽእኖ ካመጣ፣ የአምራቾች ገቢ ሁኔታ ላይ ምን ለውጥ እንዳስከተለ፣ የተጠቃሚዎች ጉዳት፤ ወደፊትስ ምን ሊሆን እንደሚችል ስጋትና መልካም አጋጣሚውን በማየት ያለውን እውነታ ከቀጥተኛ ተዋናዮች፣ ከባለሙያና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በማያያዝና መጨረሻ ላይ ምጣኔ ሀብቱን ከሰዎች ሕይወት ጋር በማሰናሰል የሚሠራበት ዘርፍ ነው።

የቢዝነስ ጋዜጠኝነቱ ‹የሽንኩርት መወደድ ምናልባት በራሱ በገበያው ነው? ወይስ ሆን ተብሎ በሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት የተፈጠረ?› የሚለው እውነታ ላይ ሊደረስ ስለሚችል መጠቆሚያ አላርም የሚሆን ጠቃሚ ዘርፍ ነው። ሽንኩርት በመወደዱ የተነሳ አማራጭ መንገዶች እንዲታሰቡ ምክንያት መሆን በሚያስችል መልኩ ዘገባው ጠለቅ ሊልበት ይገባል።

- ይከተሉን -Social Media

በዚህ ደረጃ እስካልተሠራ ድረስ ግን ማኅበረሰቡ ይህንን ዘገባ ትኩረት ሰጥቶ ሊከታተለው አይችልም። ብዙኀን መገናኛውም የአየር ሰዓቱን እያባከነው ስለመሆኑ አይጠረጠርም። ከዚህ ባሻገርም አንድ የተከሰተን የንግድና ምጣኔ ሀብት ጉዳይ ከጅምሩ እስከ መጨረሻው የመከታተል አሰራር ሊኖር ይገባል። ከሰዎች የዕለት ከዕለት ጉዳይ ጋር የተያያዘን ዜና የሰሞነኛ ወሬ አድርጎ ማለፉ የቢዝነስ ጋዜጠኝነት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የጋዜጠኝነት ሙያ የሚደግፈው አይደለም።

አብዛኛዎቹ የእኛ አገር ብዙኀን መገናኛዎች ለቢዝነስ ጋዜጠኝነት ዘገባ ብለው ለብቻው በተዋቀረ ቡድን ወይም በክፍል ደረጃ የተደራጀ አሰራር የላቸውም። በዜና ክፍል ውስጥ በንዑስ ዘርፍነት በማካተት እየተሠራ ያለና ከማንኛውም ዓይነት መደበኛ ዜና አሰራር ብዙም ያልራቀ ነው። በዚሁ አጋጣሚ ከብዙኀን መገናኛዎቻችን መካከል የኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው መጽሔት፣ እንዲሁም የፎርቹንና የካፒታል ሳምንታዊ የእንግሊዘኛ ጋዜጦች እንደ ጥሩ የቢዝነስና ምጣኔ ሀብት ዘጋቢ በምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው ማለት ይቻላል።

በአጠቃላይ ቢዝነስ ጋዜጠኝነት ሆነ፣ ተደረገ፣ ታቀደ፣ ተመረቀ፣ ተተከለ፣ አደገ፣ ቀነሰ ከሚለው ቀጥተኛ ዜና የዘለለ በተለይም የገንዘብ ወይም የንግድ ቁጥሮችን ትርጉም ባለው መልኩ ወደ ቋንቋ ቀይሮ ለብዙኀኑ የሚነገርበት ዘርፍ ነው። እየተከወኑ ያሉ የንግድና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች ትልቁን ጥቅል ጉዳይ ከያዘው ምጣኔ ሀብት ጋር በማስተያየት መዘገብ ላይ የሚሠራ ሙያ ነው።

የቢዝነስ ጋዜጠኝነቱ እንዴት ይሠራ?
የኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ ቻርልስ ዊትከር ስለቢዝነስ ጋዜጠኝነት አሠራር ሲገልጹ ‹‹የቢዝነስ ጋዜጠኝነት ሉላዊነትና ዲጂታል ዘመን በሰው ልጅ አኗኗር ላይ እያመጡት ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈትሽ ይገባል›› ብለዋል። በመሆኑም ‹‹የቢዝነስ ጋዜጠኝነት በሳል የቢዝነስ ሰው ሊመደብለት የሚገባ ትልቅ ሙያ ነው›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ሉላዊነትና ዲጂታል ቴክኖሎጂው በሕዝቦችና በአገራት ላይ እየተፈጠሩ ያሉ የምጣኔ ሀብት ክስተቶችን ቀድሞ በማነፍነፍ ማሳወቅ ይኖርበታል።›› ብለዋል።

ሌላኛው ምሁር የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኮምዩኒኬሽን እና ጋዜጠኝነት ፕሮፌሰሩ ጀምስ ቲ. ሃሚልተን ናቸው። እኚህ ምሁር ‹‹የቢዝነስ ጋዜጠኝነት ማለት ንግድና ምጣኔ ሀብት ላይ በቁጥር ያሉትን ጥሬ ሐቆች ከንግግራዊ ወይም ከዝርው ጽሑፍ ጋር አስማምቶ ከጉዳዩ ባለቤቶች ባለፈ ለማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል የምናደርስበት ጥሩ መንገድ ነው።›› ይሉታል።

የቢዝነስ ጋዜጠኝነት ሙያ የሚከወኑ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን ወደ ሰውኛ በማቅረብ ያለውን ንክኪ የማስረዳት ጥበብ መሆኑን ይገልጻሉ።
ወደ እኛ አገር ስንመጣ ለብዙኀን መገናኛዎቻችን በዚህ ዘርፍ ብቻ መታወቅ ራሱ እንደመልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው። ብዙ የማኅበረሰብ ክፍል ከኑሮ ጋር የሚታገል እንደመሆኑ ራስን ለመቻል በሚደረጉ ጥረት ውስጥ ማገዝ መቻል ትልቅ አስተዋጽኦ ከመሆኑም ባሻገር አምራቾች፣ አከፋፋዮችና ሻጮች እንዲሁም ገዢዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚያምኑበት የመረጃ ምንጭ በመሆን ተደማጭነትና ተነባቢነትን ማትረፍ የሚቻልበት ነው። የብዙኀን መገናኛ አንዱ ዓላማም ይህ በመሆኑ ጠቅሞ መጠቀም ብልህነትና ዘመኑ የሚፈልገው አካሄድ መሆኑን መረዳት ተገቢ ይሆናል።
አብርሐም ፀሐዬ ጋዜጠኛና የቢዝነስ አማካሪ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው geraramc@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች