መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየገነት ቁራጭ በምድር!

የገነት ቁራጭ በምድር!

በጥቂት መቶ ኪሎሜትሮች ልዩነት የተለያየ ባህል፣ ማንነት፣ የአየር ጻባይና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የሚገኝባት ናት፤ ኢትዮጵያ። የገዛ አገርን የመጎብኘትና የመመልከት ባህል ብዙ ባይለመድባትም፣ እድለኛ የሆኑ ብዙዎች ከቃል በዘለለ ይህን በልዩነት ውስጥ ያለ ውበቷን በዐይናቸው ቃኝተዋል፤ በመንፈሳቸው ተረድተዋል፣ በአካላቸው ደርሰዋል። ጋዜጠኞች ደግሞ የሥራቸው ጠባይ ይህን እድል በሚገባ ያስገኛቸው ይመስላል።

የአዲስ ማለዳው ኤርምያስ ሙሉጌታ እርሱ በአካል ደርሶ ከቃኛት ከፍሎ በዐይነ ሕሊና ወደ ሚዛን አማን ከተማ ቤንች ማጂ ዞን ይወስደናል። የቤንች ማጂ ዞን ቡና አምራች ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒዬን መነሻ ምክንያት በሆነው በዚህ ጉዞም፣ በመመልከት መረዳት ከሚቻሉ ኹነቶች ጀምሮ እግረ መንገድ ባሉ አካባቢዎች ስላለው ነባራዊ እውነታ እንዲሁም ስለየማኅበረሰቡ የልቦና ውቅር ቅንጣት መረዳት የሚያደርስ ዳሰሳንም አድርጓል። ጉዞውንና ቅኝቱን፣ የጉዞውንም ማስታወሻ እንደሚከተለው የአዲስ ማለዳ የሐተታዋ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የገነት ቁራጭ በምድር!

ቅዳሜ ማለዳ መስከረም 9/2013 ከአዲስ አበባ የተሰባሰበው የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለመጓዝ መሰናዶውን አጠናቋል። አዲስ ማለዳ በዕለቱ የጉዞው ርዝመት እና የመዳረሻው ርቀት ገና ሲያስቡት ጉልበትን የሚያዝል በመሆኑ ማልዶ ለመነሳት የተቀመጠውን የሰዓት ገደብ ለመጠበቅ ሞክራለች። ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጉዞውን ለመጀመር ታቅዶ ነበርና አጥንት ድረስ ዘልቆ በሚቀዘቅዘው የሌሊት ቁር ጋር ታግላ በስፍራው ለመገኘት ችላለች።

የሰዓት ነገር አሁንም መከበር የተለመደ አይመስልም። በተለይም ደግሞ በጋዜጠኞች የባሰ በሚመስል እና የሰዓትን ጥቅም ከጋዜጠኛ በላይ ሊገነዘበው የሚችል የለም በሚባልበት ሙያ ዘርፍ ለተሰማራነው የሰዓት አከባበራችን እጅግ የተዛባ ነው። 11 ሰዓት የተባለው ይኸው የመነሻ ሰዓት በተጓዥ ጋዜጠኞች በሰዓት አለመድረስ ምክንያት እስከ 12 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ድረስ አዲስ አበባ ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀነሲ ዋና መሥሪያ ቤት ደጅ ላይ መቆም ግዴታ ሆኖብናል።
ሰባት ጋዜጠኞችን እና የካሜራ ባለሙያዎችን ያቀፈው የተጓዦች ቡድን አሁን ተሟልቷል። ጉዞ ወደ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሚዛን አማን ከተማ ለማድረግ ልጅ እግሩ አሽከርካሪያችን የመኪናዋን ሞተር ኮልኩሎ አስነስቷታል። ጃፓን ሥሪቷ ኒሳን አርቫን ሚኒባስ ስምንት ተሳፋሪዎችን ይዛ በአዲስ አበባ ጀሞ በምእራብ አቅጣጫ መንጎድ ጀምራለች።

አሽከርካሪያችን አነዳዱ ከዚህ ቀደም ካየኋቸው እና በተለያዩ የጉዞ መርሃ ግብሮች ላይ ካጋጠሙኝ አሽከርካሪዎች በእጅጉ የተለየ ነው። ከመኪናው ቅንጡነት እና ጉልበታምነት ጋር ተዳምሮ የአነዳድ ፍጥነቱ በእጅጉ ነብስ እና ስጋን የሚያላቅቅ ነበር። መኪናዋን በፍጥነት ይነዳል ሳይሆን ያከንፋታል ቢባል ማጋነን አይሆንም። መኪናዋም ከአሽከርካሪዋ በሚሰጣት ነዳጅ ስምንት ተጓዦችን ከነጓዛችን በሆዷ ሸክፋ ትሰግራላች።

በዚህም መሰረት በቅጽበት ነበር የአዲስ አበባን ክልል ጨርሰን ኦሮሚያ ክልል መግባት የቻልነው። መውጣት ከነበረብን ሰዓት ወደ ኹለት ሰዓታት ማርፈዳችን ያበሳጨው አሽከርካሪያችን የባከኑትን ሰዓታት ለማካካስ በሚመስል አኳኋን በኃይለኛ ፍጥነት እየተጓዘ ከቤቱ ማንም አሽከርካሪ እንዲቀድመኝ አያስፈልግም በሚል ለራሱ ቃል ገብቶ የወጣ እስኪመስል ስንከንፍ እኛም በግማሽ ልብ ከጉዞ አጋሮቻችን ጋር ጨዋታ ጀምረናል።

ካለፉት ክረምት ወራት የጎርፍ እና የውሃ ሙላት ጋር በተያያዘ መንገዶች ሰፋፊ የገበጣ መጫወቻ በሚመስሉ ሁኔታ ተቆፋፍረው ጉድጓዶቻቸው ቢበዙም አሽከርካሪያችን ከቁብ የቆጠራቸው አይመስልም። ጉድጓዶች ላይ ገብቶ በወጣ ቁጥር መኪናዋ ሽቅብ እየወረወረችን ስትቀልበን ነበር ጉዟችን የቀጠለው።
የተገባደደው የክረምት ወራት በአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ምናልባትም ከ100 ኪሎሜትር ባነሰ ርቀት ላይ በምትገኝ የገጠር ከተማ ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድመት ማድረሱን ለማየት ችያለሁ። ቤቶች በውሃ ተጥለቅልቀው ወገባቸው ድረስ በውሃ ተይዘው ስመለከት ድንጋጤ እና ሀዘን በጥምረት ነበር ልቤን የመቱኝ። እርሻ ስፍራዎች በውሃ ተሸፍነው ዐይን ማየት እስከሚችለው ቢያማትሩ ደረቅ ስፍራን ማየት እጅግ ከባዱ ጉዳይ ሳይሆን አይቀርም።

እጅግ ምርታማ ነው የሚባልለት ይኸው አካባቢ አገር ውስጥ ሰምጦ ሱማሌ አሸዋማ መሬቶች ላይ ሰርጎ የሚቀረው የአዋሽ ወንዝ ሙላት ውጤት እንደሆነ ተነግሮኛል። እስከ አድማስ ድረስ ሰማይና ምድር የተጋጠሙበት እስከሚመስለው ስፍራ ድረስ በውሃ የተሸፈነው እርሻ መሬት ምን ያህል ምርት እንደወደመ ግምቱን ማስቀመጥ ከባድ ይሆናል። እዚህ አካባቢ ‹የኖህ ዘመን ተደግሞ ነበር እንዴ!› በሚያስብል ሁኔታ የተጥለቀለቀው አካባቢ ዋና መኪና መንገዱም ከፍ ተደርጎ ባይሠራ ኖሮ ተውጦ የቀድሞውን የመተሐራ በሰቃ መንገድ ዕጣ እንደሚደርሰው እሙን ነበር። ከእርሻ ስፍራዎች በውሃ መጥለቅለቅ ባለፈም ቀንድ እና ጋማ ከብቶች በውሃ ተወስደው እና ሞተው መመልከትም እጅግ ልብ የሚሰብር ጉዳይ ነበር።

ጉዟችን በዚህ ሁኔታ መጀመሩ ደስ ባያሰኝና ድብርትን የሚፈጥር ቢሆንም በቅጽበት በርካታ ስፍራዎችን ተወንጭፋ የምታልፈው መኪናችን በአንዱ አዝነን ሳንጨርስ በሌላ አስገራሚ ነገር እንድንደመም የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በሚቀያየሩበት ፍጥነት ነበር ስሜታችን ሲቀያየር የነበረው። ሰበታ፣ ሙግሌ፣ አዋሽ፣ ቱሉ ቦሎ እያልን እየተጓዝን ነው። በእርግጥ የተጓዝንበት የክረምት ወራት ከቅርብ ቀናት በፊት የተጠናቀቁ ቢሆንም፣ የጥቅምት ንፋስ እስኪያከስማቸው ድረስ የፈኩ እና መስኩን የእንቁላል አስኳል የፈሰሰበት ያስመሰሉት የአደይ አበባ መመልከት ነብስን በሀሴት ይሞላል። ልብንም ስልብ የሚያደርግ ስሜት አለው።

በነገራችን ላይ በምናልፍባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚታየው መልክኣ ምድር ከውበቱ የተነሳ በእርግጥ ለመናገር እና ለማስረዳት በሚከብድ ደረጃ ነው የተቀመጠው። እንደ አንዳንድ ጸሐፍት በእውቅ ቀራጺ ወይም ሰዓሊ የተሳለ ግሩም ብሩሽ ውጤት ይመስላል ብዬ ትልቁን የሰማይ የምድር ፈጣሪን ሥራ ልመስል አልፈልግም። ሥራህ ግሩም እና ድንቅ ነው ብዬ ከፈጣሪ ጋር በልቦናየ ከማውራት የዘለለ አድናቆቴን መግለጽ የቻልኩበት ነገር ማግኘት አልቻልኩም።

ጉዞው እንደቀጠለ ነው። አሁን ከአዲስ አበባ 150 ኪሎሜትር በምትርቀው የጠንካራ ሥራ ሰዎች መገኛ በሆነችው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ስር በምትገኘው የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ ደርሰናል። ማልደን ባይሆንም የተነሳነው ከሹፌራችን ዝግታ የሌለው አነዳድ የተነሳ ለቁርስ ወልቂጤ ላይ ቆመናል። እዚህ ሌላ ዓለም ነው። ድሮም ጉራጌ ባለበት ሥራ አለ፤ ወይም ሥራ ባለበት ጉራጌ አለ ነው እና ቀመሩ፤ ወልቂጤ እጅግ የሞቀች ከተማ ናት።
ማልዳ የሞቀች በማለዳ ወደ ባተሌነቷ የምትገባ ድንቅ የሥራ ወዳዶች እና ሰላማዊ ሰዎች መገኛ ናት። መስተንግዶ አዋቂዎች፣ ትዕዛዝን ሲቀበሉ ከወገባቸው ጎንበስ ከፊታቸው ፈገግ ብለው ገና ከትዕዛዙ ጀምሮ ምግብ አምሮትን የሚንጥ ነው። ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› ያሉት አበው ለካ ዝም ብለው እንዳልነበር የሚገባችሁ የጉራጌዎችን የትዕዛዝ አቀባበል ትህትና ካያችሁ እና የፊታቸውን ጸዳል ካስተዋላችሁ በኋላ ነው።

በፍስክ ቀን ነበርና ጉዞው የአዲስ ማለዳው የግራፊክስ ዲዛይን ባለሙያው እና በፎቶ ችሎታ ረቂቅ ጥበብን የታደለው ጨዋታ አዋቂው አሸናፊ ጸጋዬ የጉዞ አጋሬ ነበርና ቁርስ ለመመገብ ከሚኒባሳችን ወርደን በአንድ ስጋ ቤት ተገኝተናል። ያዘዝነው ምግብ ሲከተፍ እና ሲመዘን በፊት ለፊታችን እየተመለከትን በረንዳ ላይ ነበርን። እናም የሰውን እንቅስቃሴ ስንታዘብ ቆየን።

በዚህም ወቅት ቀልባችንን ኹለት ነገሮች ይዘውናል። አንደኛው ዳቦ በፌስታል እና በቅርጫት ሆኖ በመንገድ ዳር ላይ መሸጡ ነው። ይህ ጉዳይ እጅግ ቀልብን የሚገዛ እና ለነዋሪው ደግሞ የተለመደ አንዱ ንግድ ዘርፍ እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንደሆነ ለመታዘብ ችለናል። ወልቂጤን አልፈው ወደ ቀጣይ ከተሞች የሚጓዙ መንገደኞች ዳቦ ይገዛሉ ሲያሻቸው በፌስታል የታሰረላቸውን በቁጥር አምስት የሆነ ዳቦ ወይም ደግሞ በቅርጫት ከተቀመጠላቸው የዳቦ መና ያሻቸውን ያህል አስቋጥረው መግዛት መቻላቸው ነው።

ሌላው ጉዳይ ግን እጅግ አሳሳቢ የሆነው በወልቂጤ ከተማ በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ በሚመለከት ወረርሽኙን ለመመከት በሚደረገው ርብርብ እንድንከተላቸው ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች አንዱ የሆነውን የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ነው። ይሁን እንጂ ይህን መሸፈኛ ያደረገ በወልቂጤ ከተማ ማግኘት እጅጉ ከባዱ ሥራ ነው። ጉራጌ ጋር ሔዶ ምን ጠፍቶ ቢባልም ተረቱ የፊት መሸፈኛ ያደረገ ማግኘት ግን የለምን የምትሰሙበት ብቸኛው ጥያቄያችሁ ነው የሚሆነው።
ከዚህም ባለፈ ርቀትን የመጠበቅ እና የዕጅ ንጽህናን መጠበቅ ጭራሹኑ የሚያስታውሱት ጉዳይ አይመስልም። ሰው ከዚህ ቀደም እንደነበረው የቀጠለ ነው። በማራኪ የአማርኛ ለዛቸው ተቃቅፈው ያወራሉ፣ ተደጋግፈው አንድ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ምስል ይመለከታሉ፣ ዕጅ ለዕጅ ተያይዘው ዋና መንገድ ያቋርጣሉ። ብቻ ወልቂጤ ላይ ኮቪድ 19 መረጃው ያላቸው አይመስሉም።

ቁርሳችንን ከተቋደስን በኋላ በታዋቂው የጉራጌ ጀበና የተፈላ ግሩም ቡናችንን ጠጥተን ጉዟችንን ለመጀመር ወደ አቦ ሸማኔዋ መኪናችን ገብተናል። ‹‹ማትደክሙ፣ ማትታክቱ እናንተ የሥራ ሰዎች ሆይ ተመልሰን በዐይነ ስጋ እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን። የምታመልኩት አምላክ ሥራችሁን ባርኮ ጤናችሁን ይስጣችሁ›› ነበር ምርቃታችን። በባዶ ሆድ የተጀመረው ጉዞ ከቁርስ በኋላ ጨዋታው ደርቷል።

- ይከተሉን -Social Media

ከዚህ በፊት በሌሎች መርሃ ግብሮች ላይ በርቀትም በቅርበትም እንተዋወቃለን እና በመኪናው ውስጥ ባይተዋር ተጓዥ አልነበረም። ቢኖርስ ማን ባይተዋር ያደርገዋል፤ ሲጀመር ጋዜጠኛ ባይተዋርነትን የት ያውቀዋል? ቶሎ ተላምዶ ቤተሰብ መሆን ያውቅበታል፤ ሲቀጥል ደግሞ የጉዞው ርዝመት ለብቻ የሚገፉት አይደለም። ስድስት መቶ ኪሎሜትርን ለብቻ ከቅጣትም በላይ ቅጣት ነው።

ከወልቂጤ ተነስተን ወልቂጤን ለኹለት ከፍሎ የሚያልፈውን አስፓልት ረግጠን በተለመደው ነብስን ከስጋ በሚነጥል ፍጥነት ክንፍ ማብቀል የቀራት ሚኒባስ ወደ ጊቤ አቅጣጫ እየከነፈች ነው። ግራ እና ቀኝ ያልተዘመረላቸው ግን ደግሞ ቢወራላቸው የማያልቁ ገና ከርቀት ሲታዩ ቀልብን የሚስቡ የጎጆ ቤቶችን እየተመለከትን አድናቆታችንን እየለገስን እያለፍን ነው።

የእንሰት ተክል የሰው ልጅን ያህል ክብር የተሰጠው የጓሮ አትክልት ነው፤ በጉራጌዎች ዘንድ። እንሰት በጓሮው ያልተከለ ክስ እንደሚጣልበት አዋጅ የተላለፈ በሚመስል ደረጃ እያንዳንዱ ቤት ጀርባ ቤቶችን ከብቦ የበቀለው እንሰት ከርቀት ሲታይ ጎጆዎችን የሚጠብቅ ሚሳኤል አረር እንጂ በእርግጥም ለምግብነት የሚውል እና አካባቢውን ሥነ ምህዳር የሚጠብቅ ተክል ለመሆኑ ያጠራጥራል። ዐይነ ግቡው እንሰት ታዲያ መዳረሻችን ወደ ሆነችው ሚዛን አማን ድረስ የተከተለን ታዋቂ እና በስፋትም የተሰራጨ ተክል መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል። ጉዞው ወደ ፊት በሔደ ቁጥር ልምላሜው እየጨመረ እና ሙቀቱም በዛው ልክ እያየለ ነው።

ወደ ምድር ልብ ተምዘግዝገን ወርደን ወደ ሰማየ ሰማያት ስንከንፍ የምንመለከተው ልምላሜ እና ሙቀት እጅግ ለማስታረቅ የሚከብድ ጉዳይ ሆኖብኛል። ያቋረጥናቸው ገጠር ከተሞች ላይ የሚታየው ልምላሜ ቀልብን ስቦ የሚያስቀር እና ‹መኖርማ እዚህ ነው እንጂ!› የሚያስብል ጉደኛ መልክአ ምድር ነው።

አሁን ወደ የጊቤ በረሃ እየተቃረብን ነው። እግረ መንገድም ሙቀቱ ጨርቃችን ሊያስጥለን እየታገለን ነው። ኢትዮጵያዊያን ስለ መብራት ሲነሳ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ ኃይል ማመንጫ መንገዳችን ላይ ይገኛል። ከልምላሜው ባሻገር እግረ መንገዴን ኢትዮጵያ የተዋቀረችበትን ፌዴራሊዝም ስርዓት እና ክልሎችንም አከላለል እያሰላሰልኩ እጅጉን ሲገርመኝ ነበር።

በጅረት እና በድልድይ የሚከፋፈሉት ክልሎች ቋንቋን መሰረት አድርገው ነውና የተካለሉት በወግ በልማድ፣ በእሴት፣ በባህል ከሚራራቀው ጋር አንድ ክልል ነህ ተብሎ ሲኖር እንደመመልከት የሚገርም ጉዳይ ከየትም አይመጣም። ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ድንበር ጀምሮ ወልቂጤ ልንገባ ጥቂት ሲቀረን ድረስ ነበር። ቀጥሎም ደቡብ ክልላዊ መንግሥት ተቀብሎ ሲያስጉዘን እና ሲያቀማጥለን ቆይቶ ድጋሚ ኦሮሚያ ክልልን አግኝተን በግልገል ጊቤን አልፈን ወደ ጊቤ ወንዝ ለመድረስ በመጣንበት ፍጥነት ተወንጭፈን አልፈናል። የሰው ልጅ ብርቱ እንደሆነ ማሳያው ግልገል ጊቤ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ረጅም መንገድ አብሮን ተጉዞ ለጊቤ ወንዝ አደራ ሰጥቶን ከኋላ ቀርቷል።

የመልከዓ ምድሩ አቀማመጥ መንገዱን ጠመዝማዛ ቢያደርገውም የልምላሜው ጉዳይ ልባችንን አጥፍቶት ጠመዝማዛነቱን ወደነዋል። መኪናችን በሰዓት ቀላል የማይባል ኪሎሜትሮችን ስትከንፍ መጀመሪያ ላይ የፈራነውን ያህል አሁን እንኳን ለምደነዋል። ለዚህ አካባቢ የመጀመሪያ ተጓዥ ከሆናችሁ ማወቅ ያለባችሁ ጊቤ በረሀ ሲባል ጭልጥ ያለ በረሃ ነው የሚል ግምት ካላችሁ ስህተት ነው። ጊቤ በረሃ ከሚወብቀው የአየር ንብረቱ ባለፈ እጅግ ሲበዛ ጥቅጥቅ ያለ ደን ያለበት እና ዐይን ማየት እስከሚችለው ድረስ ብታማትሩ ከልምላሜ ውጪ ምንም የማታገኙበት እጅግ ውብ ስፍራ ነው።

የብር ቅየራው ጥያቄ
ጊቤ ወንዝን ከረጅም ርቀት በአረንጓዴ ተራሮች እና በስፋት ከሚበቅለው በቆሎ ምርት ጋር ደምረን እያየን አንድ በርሃ ውስጥ ጠመዝማዛውን መንገድ ተንተርሳ ከተሠራች ቤት ለሻይ ቆመናል። ያው እንዲያው አመል ሆኖብን ሻይ እንላለን እንጂ ወደዚህ ስፍራ መጥተውማ ቡና እና ሻይ መሳ ለመሳ ቀርበው ግን የቡናው ተጠቃሚ እንደሚልቅ የማያወላዳ ነው። የጅማ ቡናን ገና ከወዲሁ እንልመደው በሚል ጊቤ ወንዝ አፋፍ ላይ ያለችው ስፍራ ላይ በሚገርም እንክብካቤ እና እንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ተነስተው ሲያስተናግዱን እና በቂ መቀመጫ ቢኖርም የራሳቸውን ወንበር ይዘው በመምጣት እንድንቀመጥ ሲጋብዙን ኢትዮጵያዊነት ለካ ጋራ ሸንተረር የማይገድበው፣ ፖለቲከኛ እና አክቲቪስት የማይበርዘው እንደሆነ ተረዳሁ።

- ይከተሉን -Social Media

ትህትናቸው ቀልብን ይገዛል፣ ቋንቋ ሳንግባባ በፍቅር ተመራርቀን እና ግሩም ቡና ጠጥተን ስንለያይ በስፍራው ገብተን እስክንወጣ ድረስ ቤቷ ውጭ የተቀመጥነው እኛ ድረስ በሚገባ በሚሰማ ድምጽ በትግረኛ ሙዚቃ ስትናጥ ነበር። በሺሕ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከመቐለ ርቃ ለምትገኘው ለዚህች ስፍራ ዋናው ሙዚቃ ሲቀጥል ደግሞ አገርኛ ቋንቋ መሆኑ እንጂ ሌላ አያሳስባትም።

መስተንግዷችንን ጨርሰን የሚከፈለው ተከፍሎ ጉዞ ጀምረን ትንሽ እንደተጓዝን ኹለት ባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪዎች (ባጃጆች) በወጣቶች ተሞልተው በጩኸት መኪናውን እንድናቆመው ነገሩን። ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፍራዎች የሚፈጠረውን ደቦ ጥቃት መሰረት ያደረጉ ዘገባዎችን ለሠራነው እና ያለውን ውጥንቅጥ በቅርበት ለምንታዘበው እንዲሁም ወደ ሕዝብ እና ወደ መንግሥት በማቅረብ እንጀራችን ለሆነው ለእንደኛ አይነቱ ጋዜጠኛ ኹነቱ እጅግ አስደንጋጭ ነበር።
ኦሮምኛ ተናጋሪው አሽከርካሪያችን ጉዳዩን ረጋ ባለ መልኩ ጠየቃቸው። በዚህ ወቅት ታዲያ እኛ እንዳሰብነው ሳይሆን ቡና ስንጠጣ የተቀየረውን አዲሱን ገንዘብ ስናወጣ አይተውን ኖሮ በድሮ አስር ብር እንድንቀይራቸው ነበር አመጣጣቸው።

የጩኸታቸው ምስጢርም ርቀን ሔደን ስለነበር እና በባጃጅ አቅም ሊደርሱብንም ሆነ ሊይዙን ባለመቻላቸው እንጂ የኹከት ወይም የጠብ አጫሪነት ተግባር እንዳልነበር ስንረዳ አፍታ አልቆየብንም። የሚገርመው ነገር ልንቀይርላቸው የምንችለው ገንዘብ አልነበረንም። በወቅቱም የአንድ መቶ ብር አዲስ የገንዘብ ኖት ነበር ከስምንታችን ውስጥ በአንዳችን ኪስ ውስጥ የተገኘው። ስለሆነም እንደማይሆን ሲያውቁ በሰላም ግቡ ብለው መርቀውን ተለያየን።

‹‹ጅማ ልውረድ ልደር ወይ፤ ሳይመሽ ቀኑ ልግባ ወይ›› እንዳለው ድምጻዊው የአባ ጅፋርን አገር የቆንጆዎች መፍለቂያዋን የባለ ሦስት እግር መቀመጫ (በርጩማ) ምድር ጅማን አሻግረን እየናፈቅን የጫካ ውስጥ ጉዟችንን ተያይዘነዋል። ሽንጠ ረጅሙ ጊቤ በኩራት አላፊ አግዳሚውን እየተመለከተ የአገሩ አድባር ነው እና በማን አለብኝነት ‹‹ባጋ ነጋ ዱፍተኒ›› (እንኳን ደህና መጣችሁ) በሚል አኳኋን ሲገማሸር ልብን ይሞላል።

በግራ እና በቀኝ የመኪናችንን የኋላ መመልከቻ መስታወት እየጨረፉ የሚያልፉት የዛፍ ቅርንጫፎች በአካባቢው የደን ሽፋን እና እጽዋቶች አበቃቀል ምን ያህል ከዋና መንገድ ጋር ያለውን ቅርበት እና ጥቅጥቅ ደን መሆኑን ያሳያል። ወደ ጊቤ ወንዝ የወረድነውን ጠመዝማዛ መንገድ የጊቤን ድልድይ እንደተሻገርን ሽቅብ ልንወጣው ግድ ሆኖብናል።

ከልምላሜ ወደ ላቀ ልምላሜ እየነጎድን ጅማ ከተማ ደረስን። ለምሳ ለመቆም የተወሰነው በጅማ ከተማ ነው እና እንደ ጉድ ስትሰግር የነበረችው መኪናችን ልጓም ተበጅቶላት አንድ ምግብ ቤት ደጅ ላይ ቆመናል። ለቁርስ ተለያይተን የተመገብነው አሁን ቢያንስ አንድ ምግብ ቤት ላይ ተሰይመን ምግብ ለመቅመስ ታድመናል። ጅማ የምትወደድ፣ አየሯ ተስማሚ እጅግ ሰው አክባሪ ሕዝብ ያለባት ከተማ ናት።

‹‹እንኳን ሰው እንስሳት የፍቅር ነው ሰራዊቱ፤ ዱር አራዊቱ›› እንዳለ ብላቴናው፤ ጅማ ፍየል እና ውሻ በፍቅር እና በወዳጅነት መንፈስ ሲላፉ እና ፍቅራቸውን ሲገልጹ መመልከት ቀልብን የሚገዛ ጉዳይ ነው። የእውነት ጅማ ልዩ ከተማ ናት። የጀበና ቡና ለመጠጣት ጅማ ውስጥ ጉልበት አባክኖ መጓዝ አይጠበቅብም። በተቀመጡበት በረንዳ ላይ ሆነው ወደ ቀኝ አልያም ደግሞ ወደ ግራ ማማተር ነው። በቃ! እዛው እግርዎ ስር አንዲት ቆንጅዬ የጅማ ልጅ ረከቦቷን በስኒ ሞልታ ‹‹ኮቱ ቡና ዱጋ›› (ኑ ቡና ጠጡ) ልትልዎት ትችላለች። ጅማ ውብ ከተማ ናት!

ምሳ ተበልቶ ቆንጆ ቡና ከቆንጆ የቡና ስነ ስርዓት ጋር ተቋድሰን ጉዟችንን ቀጥለናል። መጀመሪያ አካባቢ እጅግ አኩርፎ እና ተቆጥቶ የነበረው አሽከርካሪያችን ወደ ዋና ጸባዩ ተመልሶ ሲበዛ ተጫዋች እና ተግባቢነቱን መስክረንለታል። አሁን ለመዳረሻችን ከ200 ኪሎሜትር በላይ ይቀረናል። ከጅማ ቦንጋ ሚዛን አማን ድረስ የሚያዘልቀንን መንገድ ይዘን መክነፍ ጀምረን 113 ኪሎሜትር ወደምትርቀው የቦንጋ ከተማ ደርሰን በብርሃን ፍጥነት አልፈናል።

- ይከተሉን -Social Media

የመንገዱ ጠመዝማዛነት እና የልምላሜው ጉዳይ እየጨመረ መጥቷል። መንገዱ በሚገርም መተጣጠፍ ሊያደክመን ቢፈልግም የአካባቢው ደን እና ልምላሜ ከአንደኛው የመንገድ ዕጥፋት በኋላ ሊኖር የሚችለውን ሌላ ልምላሜ በናፍቆት እየጠበቅን ስለምንጓዝ ተጨማሪ ጉልበት ሆኖልናል።

አሁን ጀንበር አብራን እንዳልነበረች ‹‹ሳያችሁ እናንተ የምትደርሱ አልሆናችሁም›› በሚል ይመስላል ጥላን ለሚጠብቋት ብርሀኗን ልትለግስ እና ለእኛ ደግሞ ነገ የሚባለውን ንጋት ልታበስረን ፍም መስላ ልትሰናበተን ነው። እጅግ የሚገርም ውበት በቅጠል የተያዘ የእሳተ ጎመራ ፍልቃቂ የምትመስል ጀምበር፣ ሆድ የሚያባባ ስንብት፣ ልብ የሚያሸፍት ‹‹ደኅና እደሩ›› ነበር።

ታታሪው እና ፈጣኑ የካሜራው ጠበብት አሸናፊ (አሹ) በምትሃታዊ ችሎታ የጀምበርን ስንብት ከመኪናው ፍጥነት እና መንገጫገጭ ጋር እየታገለ በካሜራ ለማስቀረት ጥረት ሲያደርግ ማየት የሰው ልጅ ከጊዜ ጋር እና የጊዜን ኹነት ለማስቀረት የሚያደርገውን ውጣ ውረድ ማሳያ ይመስላል።

ጀምበር ጋር ውድድር የያዘ የሚመስለው አሽከርካሪያችን ኦሮሚያን እና ደቡብ ክልልን የሚለየውን የጎጀብ ወንዝን ተሻግሮ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል አዝልቆናል። ‹‹ጃሽቴ›› ይላሉ ሸኮዎች እንግዶቻቸውን ሲቀበሉ፤ ያኔም ብቻ ሳይሆን ቤት የነበረ ሰው ለጉዳይ ወጥቶ ወደ ቤት ሲመለስም ያንኑ ይላሉ። ‹‹እንኳን ደህና መጡ፣ እንዴት ናችሁ?›› አይነት መልዕክት ያለው ሰላምታ ነው።

ከመነሻችን ጀምሮ ኹለቱ ብሔራዊ ክልሎች እየተፈራረቁ ሲቀበሉን እና እኔም በፌዴራሊዝሙ አወቃቀር እና አከለላለል ስደመም ብቆይም አውጥቼ አልተናገርኩትም። ቅሉ ከተጓዦች መሐል ግን ‹‹አሁን ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነን›› ሲባል እና ከቆይታ በኋላ ደግሞ ‹‹ደቡብ ገብተናል›› ሲሉ፤ ጨዋታ አዋቂው አሸናፊ ‹‹ኢትዮጵያስ መቼ ነው የምንገባው?›› ብሎ አስፈግጎናል።

ውሽውሽ
በኢትዮጵያ በኹሉም አቅጣጫ ይህን ሥም የማያውቀው የለም፤ ውሽውሽ። በሻይ ቅጠል ምርቷ የምትታወቀው ውሽውሽ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን የሻይ አምሮት የቆረጠች እና ስትቆርጥም ዘመናትን የተሻገረች የሻይ ቅጠል አምራች ምድረ ገነት ናት። ውሽውሽ ስንደርስ ቅድም የተሰናበትናት ጀምበር ተጨማሪ ዕድል የሰጠችን በሚመስል መልኩ ብርሀኗን ለግሳናለች። ከተማዋ ‹ቱ!ቱ! አድባር ትቀበላችሁ› እያለችን ይሆን እንዴ በሚያስብል ሁኔታ ከጀምበሯ ጋር የሚታገል ስስ ዝናብ እያርከፈከፈች ነበር የተቀበለችን።

ተሰናባቿ ጀምበር ታዲያ የሻይ ቅጠሉ ላይ አርፋ ልዩ ውበት ስትሰጠው እና ሌላኛው ተፈጥሮ ዝናብ ደግሞ ወዙን ሲያርከፈክፍበት በእኩል ቁመት ላይ የሚገኘው የሻይ ቅጠል ማሳ ከሩቅ ለሚመለከተው ዕውቅ ሸማኔ የሠራው ጥለት እንጂ በእርግጥ ሰው ተክሎት ተንከባክቦ ያበቀለው ምርት አይመስልም።

እዚህ ከተማ ግን አንድ አስደንጋጭ ነገር ተከስቶብን ነብሳችን ከስጋችን ልትላቀቅ ምንም አልቀራትም ነበር። መኪና ያከንፋል እንጂ ይነዳል የማይባልለት አሽከርካሪያችን ውሽውሽ ከተማ ውስጥም በመጣበት ፍጥነት ለማለፍ ሲሞክር አንድን ታዳጊ ከመግጨት ለጥቂት ተረፍን። ይህ ብቻ ሳይሆን ታዳጊው መንገድ ለመሻገር ሲሞክር መውደቁ እና እሱን ለማትረፍ መሪ ወደ ግራ በኃይል መጠቀሙ ከነበረው ፍጥነት ጋር ተዳምሮ ከመገልበጥ ለጥቂት ነበር የተረፍነው። ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገባነው ተጓዦች እና አሽከርካሪ እንደተኮራረፍን እና ጉዞው ምንም ስሜት ሳይሰጠን ጥቂት ተጉዘን መልሰን ረሳነው።

ዐይን አፋሩ ተክል እና እንስሳ
የደኑ ሽፋን እጅግ ሲበዛ ጥቅጥቅ ያለ ሲሆን ምናልባትም በውስጡ ከአንድ ሜትር በላይ መተያየት ሊቸግር እንደሚችል ያሳብቃል። በዚህ ስፍራ ታዲያ ለኑሮው የተመቸው እዩኝ እዩኝ የማያውቀው የኢትዮጵያ መገለጫ ዐይን አፋሩ ተክል (ቡና) በዚህ በስፋት ይገኛል። ቡና በተፈጥሮው በግላጭ የማይበቅል እና ሰውን ፊት ለፊት ለማየት የፈራ ራሱን ዝቅ አድርጎ የተገኘ ግን ደግሞ በዓለም መድረክ ላይ ከፍ ብሎ የሚጠራ ግሩም ተክል ነው። ከባድ የደን ሽፋን እና ከኩራቱ የተነሳም ጥላ የሚፈልገው ቡና ተክል እዚህ በሚገርም ስፋት እና ብዛት ጥራትን ታድሎ ይገኛል።

የመጣንበት መንገድ ሁሉ ቡና በየደረጃው የሚገኝ ተክል ቢሆንም የደን ሽፋኑ በጨመረ ቁጥር ደግሞ አብሮ ይጨምራል። በዋናነት የጉዟችን ምክንያት የሆነው የቤንች ማጂ ቡና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን 12ኛ ዓመት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ነው። እናም ቡና ትኩረታችንን ስቦታል። በዚህ አካባቢ አንድ አርሶ አደር ቡና ለመግዛት ወደ ሱቅ የሚያመራበት ምንም አይነት ዕድል የለውም። ከመኝታው መስኮት እጁን አሻግሮ ዘርግቶ የጓሮ ቡናውን ሸምጥጦ ማድረቅ እና መፈልፈል ለቡና ሱሱ ማስታገሻ ብቻ ሳይሆን ቀኑን የሚያበራበት ዕጽም ነው። ይህ የጓሮ ገጸ በረከት ታዲያ ለአርሶ አደሩ ተርፎ የውጭ ምንዛሪን ለማምጣትም አይሰንፍም፤ ዋናው በማኅበራት መደራጀት ነው።

ከቡና ባለፈ በዚህ ጉዞ ላይ የታዘብነው ደግሞ በሰንበት ቅጠል አይበጥስም የሚባልለት፣ ፊቱ የማይፈታው ‹‹መነኩሴው›› የሚል ሥያሜን ያገኘው ዝምተኛው እና በአርምሞ የተሞላው የዛፍ ላይ ንጉሡ ጉሬዛ ነው። ወደ ሰው ላለመቅረብ ሰማይ ጠቀስ ዛፎች ላይ ተቀምጦ ‹‹ምን ጉዶች ናቸው ደግሞ እነዚህ›› በሚል ጥያቄ በአንክሮ እየተመለከተ፣ ምንም ሳይደንቀው እና ሳይገርመው ሸኝቶናል። የሚገርም ጥምረት ሆኖብኛል፤ ዐይን አፋሩ ተክልን ከአናቱ እየተመለከተ ከፍ ብሎ ዛፍ ላይ የሚኖረው ዐይን አፋሩ እንስሳ መኖሩ።

አሁን የእውነት ጨልሟል። እኛም ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። በዚህ ድቅድቅ ጨለማ እና ጫካ ውስጥ ታዲያ የሚኖሩ ሰዎች የመንገዱን ዳር ዳር ውሃ በእንስራ እና እንጨት በጀርባቸው ተሸክመው ወደ ማደሪያቸው ሲነጉዱ ለመታዘብ ችያለሁ። ይህ ታዲያ ምን ይገርማል ለሚል አንባቢ አስገራሚው ነገር የአካባቢው ጥቅጥቅ ያለው ደን ከምሽቱ ጋር ተዳምሮ ሴቶች ብቻቸውን ውሃ ቀድተው በልበ ሙሉነት ወደ ማደሪያቸው ሲጓዙ መመልከት የአካባቢውን ጨዋነት እና ሰላማዊ አኗኗራቸውን የሚያሳይ ነው።

ሚዛን አማን ከተማ ነን። በደን ውስጥ ተደብቃ የተቆረቆረች እጅግ የምትደንቅ ሕብረ ብሔራዊ ስብጥር ያለባት በአማርኛ እና ትግርኛ ዘፈኖች ስታብድ የምታድር ውብ ከተማ።

ቤንች ማጂ ቡና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒዬን
በርካታ ዓመታትን በእንግልት ያሳለፈ የሕብረት ሥራ ዩኒዬን ነው። ወደቁ አበቁ ሲባሉ አፈር ልሰው ተነስተው የጥንካሬ መሰረት በመሆን እጅግ የተፋጠነ ለውጥ በማምጣት ከ7500 ብር መነሻ ገንዘብ በዓመታት ጉዞ 10 ሚሊዮን ማድረስ የቻሉ የጥንካሬ ተምሳሌቶች ናቸው። በኢትዮጵያ ካሉ በርካታ የቡና ላኪዎች እና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒዬን 462ኛ ደረጃ ላይ እንደነበሩ የሚናገሩት የዩኒዬኑ አመራሮች፣ አሁን 29ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ጭራሹኑ የገንዘብ እና ብድር እና ቁጠባ በማቋቋም ለአባላት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ለማድረግ የተጉ ነገን አሻግረው ተመልክተው ለተሻለ ነገ የኖሩ የብልህ ገበሬዎች ስብስብ ነው።

በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ አሁን ያቋቋሙትን የብድር እና ቁጠባ ማዕከልንም ወደ ባንክ የማሳደግ ቁርጠኛ አቋም ያላቸው ሲሆን፣ ይህን እንዳያደርጉ የሚያግዳቸው ምንም ነገር እንደሌለ በቁርጠኝነት ሲናገሩ ከመስማት የበለጠ ልብን የሚሞላ የለም። ለነገ የላቀ ደረጃ ከፍተኛ ስንቅ የሰነቁት እነዚህ ታታሪዎች በቡና ብቻም ሳይሆን በዞኑ ከፍተኛ ምርት ይገኝባቸዋል በሚባልባቸው የቅመማ ቅመም እና የማር ምርት ላይም አበክረው በመሥራት የዕድገታቸውን ፍጥነት በመጨመር ዛሬን ኖረው ነገንም ለማጣጣም የሚተጉ ዩኒዬን እንደሆኑ አስመዝግበዋል።

20 ሺሕ በላይ አባላትን ይዘው በቀጥታ ለዓለም የሚያቀርቡት የቡና ምርት በእጅጉ ተወዶላቸው ተፈላጊነታቸውም በዛው ልክ እየጨመረ የመጣ ህብረት ነው። በዓመት ከ20 እስከ 25 ሺሕ ቶን ድረስ ለዓለም ዐቀፍ ገበያ ያቀርባሉ። በአስተናባሪያችን ትጉሁ እና ድካምን አሽቀንጥሮ የጣለ በሚመስል ለጋ ወጣት ሳሙኤል አለማየሁ ታግዘን ጉብኝታችንን በምድረ ገነት የቡና ምድር አድርገናል።

የምርት አቅሙ ግሩም የአመራረት ጥበብም እጅግ ረቂቅ ነው። ለበርካቶች አርአያ የሚሆነው ይኸው ዩኒዬን በሚገርም ፍጥነት ዘርፈ ብዙ ዕድገት እያስመዘገበ ግስጋሴውን ተያይዞታል። ‹‹ዘርፈ ብዙ ምርት ለሁሉን ዐቀፍ ዕድገት›› በሚል መሪ ቃል የተካሔደው 12ኛው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ታዲያ በእርግጥም ያሉበትን ሁኔታ የሚያሳይ የትጉሀን ስብስብ ነው። በቡና የጀመረው ሥራቸው ወደ ቅመም እና ማር ማደጉ ዘርፈ ብዙነታቸውን የሚያሳይ ነው።

ይህ የትጉሃን ስብስብ የሆነው ዩኒዬን ታዲያ አንድ ተግዳሮት አለው፤ እርሱም ጸጥታ ነው። አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ ከአርሶ አደሮች እንደሰማችው በርካታ ሔክታር መሬት ቡና ተቃጥሏል። ቀሪው ደግሞ በአካባቢው አለመረጋጋት የተነሳ ሰዎች ስለተፈናቀሉ አሁንም የሚሰበስበው አጥቶ ቡናው ጫካ ውስጥ ተበላሽቶ ቀርቷል።
ቆይታችንን በዚሁ ካልገደብነው ዘመናችንን ስንጽፍ መኖራችን ነው። እያንዳንዱ ክስተት ስንክሳር የሚያስጽፍ ግሩም ቀልብን የሚገዛ ጉዳይ ነው። ለዛሬ ግን በዚህ ይብቃን።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች