‹‹የመድኃኒት እጥረት ለሕክምና አገልግሎት ማነቆ ሆኖብናል›› የጤና ተቋማት

0
625

የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች አቅርቦት እጥረት በሕክምና አገልግሎት ላይ ማነቆ መሆኑን የጤና ተቋማት ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የመድኃኒቶች፣ የሕክምና መገልገያዎችና የላብራቶሪ ሪኤጀንቶችን እንዲገዛላቸው በጠይቁት መጠን እያቀረበላቸው አለመሆኑን የጤና ተቋማት ጠቅሰዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የሕክምና ግብአቶችን የሚያቀርበው ኤጀንሲ አሰራር ስርአቱ ቀልጣፋ ባለመሆኑ የጤና ተቋማት አገልግሎትን በማስተጓጎሉ መንግስት አማራጮችን ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኤጀንሲው የሕክምና ግብአት አቅርቦት ስራቸው ላይ ፈተና መሆኑን ከተናገሩ የጤና ተቋማት መካከል የአበበ ቢቂላ ጤና ጣቢያ አንዱ ነው፡፡ የጤና ጣቢያው ሀላፊ ብርሃኑ በዳዳ እንዳሉት በኤጀንሲው በኩል እንዲቀርብላቸው ከሚጠይቁት የመድኃኒት፣ የሕክምና መገልገያዎችና የላብራቶሪ ሪኤጀንቶች መካከል እየቀረበ ያለው መጠን አነስተኛ ነው።

በጤና ተቋሙ መጥፋት የሌለባቸው መድኃኒቶችና የሕክምና ግብአት ጭምር እጥረት በመኖሩ ከሌሎች ተቋማት ለመዋስ የሚገደዱባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። በአብነትም በቅርቡ ኤጀንሲው እንዲገዛላቸው ከተጠየቁት 210 የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች 35 አይነትን ብቻ ማቅረቡን ተናግረዋል።

ይህም ጤና ጣቢያው ለህብረተሰቡ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ኃላፊው ገልጸዋል። በቅርቡ ጤና ጣቢያው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የተጀመረ በመሆኑ በበቂ መጠን ከኤጀንሲው መድኃኒት ማግኘት ካልተቻለ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ቅሬታ ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል።

ከኤጀንሲው መድኃኒቶች በማይገኝበት ወቅት በጨረታ ለመግዛት ጊዜ ይፈጃል የሚሉት ብርሃኑ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ሌሎች አማራጮች እንዲፈልግ ጠይቀዋል፡፡
የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፋርማሲ ዳይሬክተር አሸናፊ ሂርኮ በበኩላቸው የኤጀንሲው አቅርቦት ላይ መሻሻል የነበረ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን የአቅርቦት እጥረት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ይናገራሉ። በኤጀንሲው እየቀረበ ያለው የመድኃኒቶች፣ የሕክምና መገልገያዎችና የላብራቶሪ ሪኤጀንቶች መጠን አነስተኛ መሆኑን ነው የገለጹት ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here