መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናታክሲዎች በሙሉ ወንበር እንዲጭኑ ጥያቄ ቀረበ

ታክሲዎች በሙሉ ወንበር እንዲጭኑ ጥያቄ ቀረበ

ጥያቄው የከተማ ባቡር፣ አውቶቡስና ድጋፍ ሰጪ ሚኒባሶችንም ይጨምራል

በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ሕግ እንዲያሻሻል ጥያቄ ማቅረቡን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን አስታወቀ።

ትራንስፖርት ባለሥልጣኑ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ባቀረበው ጥያቄ ታክሲዎች እና ሌሎች የሕዝብ የትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ከመጫን አቅማቸው በታች በግማሽ ቀንሰው መጫናቸው እንዲሻሻል እና በሙሉ ጭነው ታሪፉ ወደነበረበት እንዲመለስ የሚጠይቅ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
እንደ ባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ ገለፃ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው በግማሽ እንዲቀንስ እና በዛው መጠን ደግሞ ታሪፉ በዕጥፍ ከፍ እንዲል አስፈልጎ የነበረበት ምክንያት፣ ኅብረተሰቡ ከቤት መውጣት እንዲቀንስ፣ አካላዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ ለማድረግ እና በየቤቱ ሆኖ የመሥራት ሁኔታው እንዲጨምር ታስቦ እንደነበር ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ አሁን በመላ ከተማው የሚስተዋለው ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ የመመለሱ ነገር መሆኑን እና ውሳኔው ላይ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በድሉ ሌሊሳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በድሉ አያይዘው እንዳስታወቁት፣ ውሳኔው ላይ ማሻሻያ ካልተደረገ እና ኅብረተሰቡም ወደ ዋናው እንቅስቃሴው ከመመለሱ ጋር ተያይዞ ለመጥቀም የታሰበውን ኅብረተሰብ ከመጥቀም ይልቅ በትራንስፖርት ዕጥረት መጉዳቱ እንደሚያመዝን ጠቅሰዋል። በዚህም ተደጋጋሚ ቅሬታ ከኅብረተሰቡ እንደሚመጣላቸው አውስተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ በሠራው ዳሰሳ እና በታዘበው መሠርት የዋና ዋና ትራንስፖርት ስምሪት ኬላዎች ላይ የሕዝብ ሰልፍ መብዛት፤ ሰልፉ ደግሞ እንደ ከዚህ ቀደሙ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ሳይሆን ዘለግ ላለ ጊዜ የሚቆይ መሆኑ መታየቱን አንስተዋል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ይሄ ችግር በማይበዛባቸው ቦታዎች ላይ እየተስተዋለ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የትራስፖርት አገልግሎቱ ማለትም አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የመጫን አቅማቸው በግማሽ እንዲቀንስ መሆኑን እና ከተማዋ ደግሞ ወደ ዋና እንቅስቃሴዋ መመለሷ መሆኑን ነው ያነሱት።

ይሄንን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ጉዞ እና ለመንግሥት ሠራተኛ አገልግሎት የሚሰጡ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ተሽከርካሪዎች እገዛ እያደረጉ ለማስተካከል ቢሞከርም ቀላል አልሆነም ብለዋል።

አሁን በመሥራት ላይ ያሉ አገልግሎት የሚሰጡ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በቁጥር፣ ታክሲዎች 10 ሺሕ፣ ኮድ 3 ደግሞ ከ16 ሺሕ በላይ በሥራ ላይ ያሉ ተብለው ቢመዘገቡም፣ ባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ ባደረገው ክትትል በጥቅሉ 10 ሺሕ 200 ተሽከርካሪዎች በሥራ ላይ እንዳሉ ነው የሚታወቀው።
አውቶብስ አንድ ሺሕ አምበሳ አውቶብስ እና ሸገርን ጨምሮ አሉ። በእነዚህ ሙሉ በሙሉ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት ኮቪድ ሲገባ አሰራራቸው እንዲስተካከል በግማሽ እንዲጭኑ መደረጉም ይታወሳል።

በተጨማሪም በተደረጉት ማሻሻያዎች ለሥራው እገዛ እንዲሰጡ በማሰብ ለመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ‹ፐብሊክ ሰርቪሶች› የሠራተኞችን ሰርቪስ ከሰጡ በኋላ ለከተማው አገልግሎት በመስጠት እንዲረዳ የማድረግ ነው።

ይሄ እንዲሆን ከፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት ጋር ስምምነት አድርገናል የሚለው ባለሥልጣኑ፤ ትራንስፖርቱ ተጠሪነቱ ለሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ሲሆን፣ በየቀኑ የሚታወቅ ቁጥር ያለው ፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት አይደለም። ነገር ግን በተጠና ጥናት መሠረት ፐብሊክ ሰርቪስ 240 አውቶብሶችን እንደሚያሰማራ ቢገልፅም 150 የሚሆነው ስምሪቱን እንደሚሠራ ነው እኛ በግምገማችን ያገኘነው ብለዋል።

ፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርትን ማዘዝ አንችልም ያሉት በድሉ፣ ነገር ግን ስምሪቱ በእገዛ መልክ እና በዋናነት በብዛት የትራንስፖርት እጥረት እንዲሁም የሰዎች ብዛት በሚታይባቸው አካባቢዎች እንደ መገናኛ፣ ሜክሲኮ እና ፒያሳ እርዳታ እንዲያደርጉ በመነጋገር እንደሚሠሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በዋነኛነት የሕዝብ እና ጭነት ትራንስፖርት ስምሪት እና ቁጥጥሩን በበላይነት ይመራል። የትራንስፖርት መሰረት ልማቶቹን የማልማት እና ማስተዳደር፤ የትኛውም ከባቡር ትራንስፖርት ውጪ ያሉትን የሕዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ስምሪት መስጠት፤ የመንቀሳቀሻ ታሪፍ፤ በተሰጣቸው ስምሪት እና በወጣላቸው ታሪፍ መሰረት መሥራታቸውን እና እለት ከእለት ገብተው መሥራታቸውን መከታተል የመሥሪያ ቤቱ ዋና ኃላፊነት መሆኑም ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች