መነሻ ገጽዜናወቅታዊ‹‹ስለ ሕዳሴ ግድብ ዝም አንልም›› የኪነጥበብ ባለሞያዎች!

‹‹ስለ ሕዳሴ ግድብ ዝም አንልም›› የኪነጥበብ ባለሞያዎች!

ስለአባይ ያልዘፈነ፣ ድምጽ ያላሰማና ያላዜመ፣ ያልጻፈ፣ ያልተናገረ፣ ያልሳለ፣ ያልገጠመ ወዘተ የኪነጥበብና ሥነ ጥበብ ባለሞያ የለም። ሁሉም ስለአባይ አንዳች ነገር ብለዋል። አሁንም የአባይ ዜማና ቅኝት ተቀይሮ፣ ከ‹አባይ ማደሪያ የለው› ወደ ‹ጭስ አልባው ነዳጅ› ሲለወጥ፣ ዜመኞችና ከያንያን አብረው በዚህ ዜማ ተቃኝተው ስለመተባበር አቤት እያሉ ይገኛሉ።

በቅድሚያ ወደኋላ መለስ እንበል። ስለ ጂጂ የ‹አባይ› ሙዚቃ። በእርግጥ ስለዚህ ስንኝና ዜማ ብዙ ቢባልም፣ ቢደጋገም የማይሰለች ነውና መለስ ብለን እንቃኘው። አዎን! አባይ ሲባል ብዙዎቻችንን ከእጅጋየው ሽባባው (ጂጂ) አባይ የተሰኘ ሙዚቃ ጋር በሐሳብ እንላተማለን። እንዲህ ስትል ስለአባይ ግርማ ሞገስና ውበት፣ ከኢትዮጵያ ስለሚወስደው ሀብትና ግብጾች ስለ አባይ ምን ያህል እንደሚቆረቆሩ በውብ ቃላት በተቀነበቡ ስንኞች እንዲህ ብላ ነበር፤

‹‹የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና
ከጥንት ከፅንሰ አዳም ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት
ግርማ ሞገስ!
የአገር ፀጋ የአገር ልብስ
ዓባይ!….የበረሀው ሲሳይ!
ቀጥላ ደግሞ የግብጾችን ስሜት እንዲህ ስትል ገለጸች፤
ብነካው ተነኩ አንቀጠቀጣቸው
መሆንህን ሳላውቅ ስጋና ደማቸው
የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ
ዓባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበረሀ
ዓባይ ወንዛወንዙ
ብዙ ነው መዘዙ
ወዲህ ደግሞ መለስ ብላ የመነሻውን የኢትዮጵያን ድምጽ አልሰማምና፣ ሳይሰማም ወደ ግብጽ ይነጉዳልና በወቀሳ መልክ እንዲህ ትለዋለች፤
ዓባይ የወንዝ ውሃ አትሆን እንደሰው
ተራብን ተጠማን ተቸገርን ብለው
አንተን ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ
ምን አስቀምጠሀል ከግብፆች ከተማ?
ዓባይ ዓባይ ዓባይ ዓባይ
ዓባይ ወንዛወንዙ ብዙ ነው መዘዙ

እርግጥም አባይ መዘዙ ቀላል አይደለም። ሆኖም ግን በሺሕ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ፣ ብዙ ድርድርና ክርክርን ካስተናገዱ መድረኮች፣ ከሽምግልና ጫፍ ደረሱ ከተባሉ ስምምነቶች በኋላ፣ አሁን 2012 ሲሆን ጉዳዩ ከወትሮው ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የተለየ ሆነ። ግብጽና ኢትዮጵያ ያደርጉ የነበሩት ድርድር ምንም እንኳ ‹ይሄ ነው!› የሚባል መፍትሄ ያስገኘ ባይሆንም፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃና ጫና ፈጥራ፣ በፍትሕ የአባይ ተጠቃሚነቷን ለዓለም አስረድታ ሥራዋን ቀጥላለች።

ይህ ብዙዎችን ደስ ያሰኘና ትውልድም የሚጠራበት አንድ አገልግሎት የሚሰጥ ሃውልት የማቆሙ ማሳያ ነው። ይህም ጉዳይ ደስ ካሰኛቸው ሰዎች መካል ደግሞ የጥበብ ሰዎች ይገኙበታል። የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ የሆኑ ድምጻውያን፣ ደራሲዎች፣ ገጣሚዎች፣ ሰዓሊዎች፣ ቀራጺዎች፣ ተዋንያን በድምሩ የኪነጥበብና የሥነጥበብ ሰዎች ይህን ጉዳይ አንስተው መክረዋል፣ ተነጋግረዋል።

የአገር ፍቅር መድረክ
አዲስ አበባ በአገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ሐምሌ 8/2012 አንድ መሰናዶ ተዘጋጅቶ ነበር። ጭር ብሎ የቆየው የአገር ፍቅር ቴአትር ቤት አዳራሽ ጥቂት በማይባሉና ተራርቀው ተቀምጠው አዳራሹን ግርማ ሞገስ በሰጡት አንጋፋና ወጣት የጥበብ ሰዎች ተመልቶ ነበር። ይህም የጥበብ ባለሞያዎች ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ‹ዝም አንልም› ያሉበት፣ ‹ይሄኔ ነው!› ሲሉም የጋራ ሐሳባቸውን ያንጸባረቁበት መድረክ ነው። አዲስ ማለዳ በዚህ መድረክ ላይ ለመታደም እድል ያገኘች ሲሆን፣ ከሞላ ጎደል ኹነቱን እንዲህ ልታካፍል ወደደች።

መድረኩን በማስተባበር በራድዮን ድራማ ድርሰት የሚታወቀው ኃይሉ ጸጋዬ ቀዳሚ ስፍራውን ሲይዝ፣ የፊልም ደራሲና አዘጋጅ ዳንኤል ወርቁም በዚሁ ተሳትፎው ከፍተኛ እንደነበር ተነስቷል። እነዚህ የጥበብ ሰዎች በዘርፉ ባለሞያ የሆኑ ባልደረቦቻቸውን ያሰባሰቡትም፣ ምን እንሥራ ከማለት ጎን ለጎን ግብጽና ኢትዮጵያ በቆዩበት ድርድር ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስከብራ ስለመቆየቷና ሥራዎች ስለመፋጠናቸው ድጋፍ እንዲሁም በዚሁ መንግሥት ጸንቶ እንዲቆይም በኪነጥበብ ሰዎች በኩል ያለውን አቋም ለማሳወቅ ነው። ለዚህም ፊርማቸውን ያኖሩበት አቋማቸውን አባሪ ያደረገ ሰነድም አሰናድተዋል።

መርሃ ግብሩ መክፈቻ ያደረገው የያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በግድቡና በድርድሩ ዙሪያ ባካፈሉት ሐሳብ ነው። በዚህም በግድቡ ቴክኒካዊና እንደ ጠቅላላ መረጃና እውቀት የሚቆጠሩ ሐሳቦችን ያካፈሉ ሲሆን፣ አያይዘውም ኢትዮጵያ በብዙ ፈተና ውስጥ ትገኛለችና ስለአባይ ብቻ ሳይሆን ለነገ የተሻለ አገር ለልጆች ለማስረከብ በሁሉም አገራዊ ጉዳይ ትብብር አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተዋል። ሌሎች በኢትዮጵያ የሚገኙ የውሃ አካላትንም እንደ አባይ ሁሉ በትኩረት መከታተል አስፈላጊነቱን አካፍለዋል።

መድረኩን በዚህ ሲመራ የነበረው ሙሉጌታ ጀዋሬ (ፕሮፌሰር) ‹የጥበብ ሰው ለእውነት ቅርብ ነው› ብሎ ሲጀምር፣ መድኃኒት ለታመመ እንደሚያስፈልግ ሁሉ፣ በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ጊዜ የጥበብ ሰዎች ሥራም ወሳኝና በገዛ አገሩ ላይ ድንጋይ እየወረወረ ለሚገኝ ወጣትም ማንቂያ ይሆናል ብሏል። በተለይም ሙያው ለሰው ልጅ ሁሉ ቅርብ እንደመሆኑ፣ ይህን ኃይልና አቅም መጠቀም ወሳኝ እንደሆነም አድምቆ ጠቅሷል።

ከመድረኩም የተለያዩ ሐሳቦች ሲነሱ ነበር። አብዛኞቹም ቁጭትን ያዘሉ ሲሆኑ፣ በተለይ ግብጽ በአገሯ ስለአባይ ወይም ናይል ብላ ስለምትጠራው ወንዝ በትውልድ ውስጥ ስላኖረችው ምስል በተደጋጋሚ ተነስቷል። እያንዳንዱ ዜጋ ጉዳዬ ብሎ እንዲከታተለው፣ አባይ ምግቡና መጠጡ፣ መጠለያና ሕይወቱ እንደሆነ እንዲያምንና እንደ ውድ ሀብት እንዲንከባከበው፣ ማንም ውሃውን ሊነካበት ቢሞክር ጠላቱ እንደሆነ ጭምር በየጊዜው ለሚፈጠር ትውልድ ሁሉ አስተምራለች። ይህም ሐሳብ በግብጻውያን ፍጹም ሰርጿል።

ሌሎችም የኪነጥበብ ባለሞያዎች በተመሳሳይ አስተያየታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አሁንም በመጪው ትውልድ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ነገረ ውሃን አካትቶ፣ ስለሕዳሴ ግድቡና በኢትዮጵያ ስላሉ የውሃ አካላት በሚገባ ማስተማር ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ትውልድ ቋሚና አንድ መሠረት ያለው እውቀትና መረጃ እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊነቱም ላይ ተነስቷል። ዛፍ የመትከልን ጥቅም ማስረጽ፣ አካባቢን መጠበቅና የውሃ አካላትን መንከባከብ የሚኖራቸውን ዋጋ ትውልድ እንዳይዘነጋም ጥበብ ልታገዝ ይገባል ሲሉ አውስተው አሳስበዋል።

ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) የተነሱ ሐሳቦች ተቅሚነታቸውን ገልጸው፣ በተግባር መሠራት ስላለባቸው ሥራዎች በተወሰነ ደረጃ አመላክተዋል። በተለይም በአባይና በግድቡ ዙሪያ የተጻፉ በርካታ መጻሕፍትን በአንድ ላይ ማቅረብና የዳበረ ሰነድ ማዘጋጀት ቢቻል ሲሉ ሐሳብ ሰጥተዋል። በተለያየ ጊዜ የታተሙና ለንባብ የበቁ መጻሕፍትን ጠቅሰው፣ ልጆችንና መጪ ትውልድን ስለ አባይና ስለ ግድቡ እንዲሁም በአባይ ዙሪያ ስለነበሩ ታሪኮች ለማሳወቅ መጀመሪያ ማወቅ ይቀድማልና፣ ለጥበብ ሰዎች ግብዓት ይሆንም ዘንድ መጻሕፍቱን እንዲመለከቱ የተወሰኑትን ጠቁመዋል።

አንዳንድ የጥበብ ባለሞያዎች በመድረኩ እንደተናገሩት ከሆነ፣ ይህ ገለጻ ዐይናቸውን የከፈተላቸው ነው። በወፍ በረር በእለታዊ እንዲሁም ወቅታዊ ዜና ላይ የሚሰሙት የአባይ ጉዳይ በዝርዝር ስለቀረበላቸውም ደስታቸውን አልሸሸጉም። ከዛም አልፎ የድርድር ሂደቶች፣ የግብጽ አቋም ከየት የመነጨ እንደሆነ፣ በታሪክ የነበሩ የድርድር ጉዳዮች፣ የሱዳን አቋም፣ የአሜሪካ በአደራዳሪ ሥም ገብቶ አቋም የመያዝ አዝማሚያ፣ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ኅብረት የመጣበት ሂደትና መሰል ኹነቶችም በያዕቆብ በዝርዝርና በግሩም አቀራረብ የተገለጹ ጉዳዮች ናቸው።

የፊልም ደራሲና አዘጋጅ ታምሩ ብርሃኑ ግድቡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ለተደረገ ርብርብና ለኪነጥበብ ማኅበረሰቡ ቅን አገልግሎት ሁሉ ምስጋና በማቅረብ ንግግሩን ጀመረ። ‹ይሄኔ ነው!› የሚል በኹለት ፊደላት የተቀነበበ ትልቅ ሐሳብንም አስተላለፈ። ይልቁንም ይህ ጊዜ አብሮ መቆሚያ፣ መተጋገዣና መተባበሪያ ነው ሲል ሐሳቡን አካፈለ። እንዳይረሳልኝ ሲል ያነሳው ጉዳይ ደግሞ እንዲህ የሚል ነው፣ ‹‹ምንም ቢመጣ ማን፣ ዛሬ ለቀጣይ ትውልድ እንሠራለን››

እንዳይረሳ ምን እንሥራ?
ደራሲ፣ ገጣሚና የተውኔት ጸሐፊ አያልነህ ሙላት በመድረኩ ከተገኙ አንጋፋ የጥበብ ሰዎች መካከል ነው። በግብጽ አንድ ጊዜ የነበራቸውን ቆይታ በማንሳት ግብጽ የአስዋን ግድብን ባጠናቀቀች ጊዜ ክፍት አድርጋው ስለነበረው ‹አይዳ› ስለተባለ ኦፔራ አንስቷል። ይህም በግብጽ አሁን ድረስ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ሲሆን፣ ግዙፉና ሥመ ጥርም ሆኖ ከርሟል። ታድያ ጋሽ አያልነህ ይህን ሐሳብ ሲያነሳ በቁጭት ነው።

በተለይም በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጀምሮ አሁን የደረሰበት ደረጃ እስኪደርስ በቆየው ዘጠኝ ዓመታት አንድ የማይረሳና ከግድቡ ጋር የሚታወስ የጥበብ ሥራ አለመኖሩ እንደሚያስከፋውም ጠቅሷል። በሥራና የሙያ ቆይታው አይረሴ የሆነውን ‹የሕዝብ ለሕዝብ› ጥበባዊ ክዋኔም በሰፊው አንስቷል።

- ይከተሉን -Social Media

ሕዝብ ለሕዝብ ኢትዮጵያ በችግሯ ሰዓት የደረሱ የዓለም አገራትን ለማመስገን ነበር የጥበብ ሰዎች፣ ድመጻውያን፣ ተወዛዋዢችና ከያንያን ወደተለያዩ የዓለም አገራት ጉዞ ያደረጉት። ይህ በምስጋና ዓላማ የተነሳ ጉዞም ዛሬ ድረስ የሚወሳና የሚነሳ፣ ምሳሌም ሆኖ የሚጠቀስ ጉዳይ ነው። ታድያ አሁንም በሕዳሱ ግድቡ ሂደት፣ መጠናነቅና የውሃ ሙሌት መጀመርን በሚመለከት አንዳች አይረሴ ሥራ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነና ምን እንሥራ የሚለው ላይ ሐሳብ እንዲቀርብ ጋሽ አያልነህ ጥሪውን ደጋግሞ አቅርቧል።

በዚህ ላይ ሐሳባቸውን ካካፈሉ መካከል ድምጻዊ አረጋኸኝ ወራሽ አንደኛው ነው። እንዲህ ያሉ አገራዊ ሥራዎችን በመሥራት ሂደት ውስጥ ለካሜራ እይታ ብቻ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተገቢ እንዳይደሉ አበክሮ ገልጿል። ለአገር ሲሠራ ለጊዜአዊ ጥቅም ሳይሆን በክብር እንደሚሰጥ አገልግሎት መቁጠር ተገቢ መሆኑንም ነው ከልምዱ በመነሳት ያካፈለው።

በተለይም የጥበብ ሰዎችን አንድነት ጠይቋል? መች ነው አንድ የምንሆነውና ያሰብነውን የምንሠራው ሲልም በጥበብ ሥራ ውስጥ የሚታዩ ፖለቲካ ቀመስ ጉዳዮችን ወቅሷል። በተለይም እንዲህ ባሉ አገራዊ ሐሳብ በሚነሳባቸው መድረኮች ጥሪ ሲደረግ የሚገኙ ብዙዎች አለመሆናቸውንና ሰው አይቶ፣ ‹እገሌ ስለጠራኝ› ብሎም ሰው መርጦ መገኘት አግባብ እንዳይደለ ከትዝብቱም በመነሳት አሳስቧል።

የጥበብ ሰዎች የእርስ በእርስ ትብብር አስፈላጊነትም ተደጋግሞ የተነሳ ሐሳብ ነው። ተዋናይ ይገረም ደጀኔ በበኩሉ፣ ለአገር ለመትረፍ ባለሞያዎች መጀመሪያ አንዳቸው ለሌላቸው ሊቆሙ ይገባል ብሏል። ለየግል ሥራ መሮጥና የራስን ኑሮ ለመሙላት የሚደረግ ሩጫ ትብብሩን እንዳዘገየና ይህ ባይሆንና በመረዳዳት እርስ በእርስ መደጋገፍ ቢቻል አገርን ማገልገል በትክክልና በውጤት ሊሠራ እንደሚችል ዕይታውን አካፍሏል።

በሌላ በኩል ሌሎች የኪነጥበብ ሰዎችም በጥበብ የታሰቡ ጉዳዮች በፖለቲካ የመጠለፋቸውን ነገር ኮንነዋል። ሐሳባቸውን ወደ መንግሥት ተቋማት ለትግበራ ሲወስዱና በነጻ ለማገልገል አለን ሲሉ፣ ተቋማቱ ሐሳቡን በቁንጽል ወስደው ‹ይህን ሠራን› ብለው እንደሚያቀርቡና በዛም የሚገኘውን የገንዘብ ጥቅም እንደሚወስዱ ያነሱም አሉ።
በቅርቡ በተከሰተው ወረርሽኝ መነሻነት በበጎ ፈቃድ በነጻ እናገለግላለን ያሉና የጥበብ ቡድናቸውን ይዘው ተቋማት ጋር የሄዱም፣ ክፍያ ባለመጠየቃቸው፣ ‹ነገ ተመለሱ!› በሚል ቀጠሮ ተሰላችተው እንደቀሩ ጭምር ያወሱም አሉ።

ምንም እንኳ እንዲህ ያሉ እንቅፋቶች ቢኖሩም፣ የኪነጥበብና ሥነጥበብ ባለሞያዎች ለአገር ይጠቅማል ያሉትን ሥራ ዝም ብለው ማንንም ሳይመለከቱ እንዲሠሩና በአእምሯቸው ያለውን ሐሳብ ማንም ሊጠልፍም ሆነ ሊሰርቀው ስለማይችል በሚችሉት እንዲያገለግሉ የሚል ሐሳብም ተነስቷል።

ይህን ሐሳብ ያንጸባረቀው ኃይሉ ፀጋዬ፣ ሌላው ቢቀር በግሉ አባይን በሚመለከት የራድዮን ድራማ እንደሚያዘጋጅ፣ ተዋንያንም በፍላጎትና በፈቃድ እንደሚሠሩና እንደሚያገለግሉ፣ ይህም አንድ የሚመስል ሥራ ብዙ ትሩፋት እንደሚኖረው አያይዞ አንስቷል።

የኪነጥበብ ባለሞያዎች ይህን ሁሉ ሐሳብ ዛሬ እንዲያነሱና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሰው በየቤቱ እንዲቀመጥ ግድ ባለበት ጊዜ ከየቤታው ወጥተው እንዲሰባሰቡ ያደረጋቸው፣ አንድም ድርድሩ የደረሰበት ቢደርስም ኢትዮጵያ በአቋሟ ጸንታ ሥራዋን መቀጠሏ ነው። እርግጥም ሥራዎች ቀጥለዋል። ለምልሰት እንዲረዳ የድርድሩን ነገር በመጨረሻ እናውሳ።

- ይከተሉን -Social Media

የድርድሩ ነገር – ለምልሰት
የሕዳሴው ግድብ ከመነሻውም ጀምሮ ሳንካ የበዛበት አገራዊ ጉዳይ ለመሆኑ ኹላችንንም በአንድ ድምጽ የሚያግባባን ነገር ነው። በተለይም ደግሞ ከተፋሰስ አገራት የሚቀርብበት ጉዳይ የተግዳሮቶች ሁሉ አናት ሆኖ ሲሰማ እና መወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖም ከከረመ እነሆ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ዘመን ብቻ ዘጠነኛ ዓመቱን ይዟል። ሦስቱ ተፋሰስ አገራት ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን ታዲያ በርካታ ድርድሮችን ከጅማሬው ጀምረው ሲያደርሱ እና ግማሹ በመግባባት ሲደመደም ገሚሱ ደግሞ ፍርስርሱ ወጥቶ ሲበተን ድርድሩን ጉዞ አድካሚ እና እልህ አስጨራሽ አድርጎት ቆይቷል።
የግድቡ የውጥረት ምንጭ እና መካረር በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ደግሞ እጅጉን የባሰ ጉዳይ ነው። በዚህም ረገድ ከአሜሪካ መንግሥት እና ከዓለም ባንክ ወዲህ ወደ አፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነትም ውይይት ሲካሔድም ነበር። በዚህም ረገድ ሠኔ 19/2012 በተደረገው ውይይት የአፍሪካ ኅብረትን ዋቢ አድርጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ አውጥቷል።

በተባለው ዕለት በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ ስብሰባ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት እና ውሃ አለቃቀቅ ደንብ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ ምክክር የተካሔደ ሲሆን፤ ስብሰባው የተጠራው የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ፕሬዝዳንት በሆኑት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ነው።

የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ እንዲሁም የጉባኤው አባል የሆኑት ኬንያ፣ ማሊ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪዎችም ተሳትፈዋል። መሪዎቹ የናይል እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ ከአፍሪካ የሚመነጭ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው አስምረበውበታል። በዚህ ረገድ ድርድሩ ስላለበት ሂደት ከኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መግለጫዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በቀጣይ ስለሚኖረው ሂደት አቅጣጫ ተቀምጧል። በዚህ መሰረት በግድቡ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥሉት ኹለት ሳምንታት እንዲጠናቀቅ መስማማት ላይ መድረሳቸውም ይታወሳል።

በወቅቱም ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ኹለት ሳምንታት የግድቡን ቀሪ የግንባታ ሥራዎች በማጠናቀቅ ሙሌት ትጀምራለች በማለት ተገልጿል። በእነዚህ ኹለት ሳምንታትም አገራቱ ከስምምነት ለመድረስ ወስነው የተለያዩ ቢሆንም፣ ከኹለት ሳምንታት በኋላም ስምምነት ላይ ሳይደርሱ መለያየታቸውን አዲስ ማለዳ ከውጭ ጉዳይ ምንጮች ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን መመልከት መጀመሩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት እንዲገለጥ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ አባላት ድርድሩን እንዲደግፉ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ከቃላት መካረር እና አላስፈላጊ መግለጫዎች እንዲቆጠቡ አቅጣጫ ተቀምጦ ልዩ የመሪዎች ስብሰባው መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

ከዚህ ባለፈም ግብጽ በግድቡ የውሃ ሙሌት ለሚዘጋጀው የምንጣሮ ሂደት ላይም የሚቆረጡት ዛፎች ከስራቸው ማይነቀሉ ከሆነ ለዓለም አቀቀፍ የዓየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛውን የጎጂ ኬሚካል ልቀትን የሚያከናውኑ ናቸው ስትልም ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ክስ በማቅረብ ላይ ትገኛለች። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ ወገን የምንጣሮውን ሂደት በተያዘለት ቀነ ገደብ እንዳይካሔድና ተጨማሪ የሙሌቱን ጊዜ ማራዘሚያ ተደርጎ እንደሚቆጠርም ማረጋገጫ አያሻውም።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች