መነሻ ገጽአምዶችበታሪክ ዕይታሚያዝያ 27 በታሪክና በ‹ውዝግብ› ውስጥ

ሚያዝያ 27 በታሪክና በ‹ውዝግብ› ውስጥ

ጣልያን ያልጠበቀችውን ዓለምም አየዋለሁ ብላ ያላሰበችውን ድል ኢትዮጵያ በአድዋ ተራሮች መካከል ተቀብላለች። ይህንንም ተከትሎ ሽንፈቷ የቆጫት የምትመስለው ጣልያን ቂም ይዛ ኖራ፣ ለበቀል ከ40 ዓመታት በኋላ በ1928 ዳግም ኢትዮጵያን ወርራለች። ይህንንም በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ተደራጅታ ያደረገችው በመሆኑ፣ በአድዋ ከነበራት ትጥቅ ያልተሻለ አቋም ላይ ለነበረችው ኢትዮጵያ እጅግ ከባድ ሆኖ ነበር። ቢሆንም አርበኞቿ በጽናት ከመዋገት አልተቆጠቡም።

በዲፕሎማሲው የተደረገው ጥረት ሁሉ ግን የተሳካ አልነበረም። ኢንግሊዝና ፈረንሳይ ለጣልያን ተደርበው ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ እንዳታገኝ አድርገዋል። ጣልያንም በጭካኔ የኢትዮጵያን ሠራዊት በመርዝ ጋዝና በአውሮፕላን ቦንብ በማጥቃት ኢትዮጵያን አቅም አሳጥታለች። ይህም ጣልያን በድል አድራጊነት በተለያዩ ከተሞች ባንዲራዋን ሰቅላ እንድትቀመጥ አድርጓል። ሆኖም ግን አርበኞችንም ወልዷል። አገሬን አላስነካም ያለውም የሽምቅ ውጊያን ጀምሮ ነበር።

ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አቤቱታቸውን ለሊግ ኦፍ ኔሽን ቢያቀርቡም ሰሚ አልነበረም። ሚያዝያ 27 ቀን 1928 የፋሺስትን ጦር ድል ለማብሰር የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ፣ የጣልያንን ባንዲራ ሰቀለ።

የኹለተኛው የዓለም ጦርነት ለኢትዮጵያ በጎ አጋጣሚን አነሳላት። ቀድሞ ለጣልያን ወግነው የነበሩት መልሰው ሲለያዩ፣ ‹የጠላቴ ጠላት› ብለው ኢትዮጵያን ለመደገፍ አቤት አሉ። ይህም የሆነው በኹለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ጣልያን ከናዚ ጀርመን አጋር በመሆኗ ነው። እናም በተለይ ኢንግሊዝ ለኢትዮጵያ በሰጠችው ወታደራዊ ድጋፍ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ወደ አገራቸው ሊገቡ ችለዋል።

ውዝግቡ?
የ1928 የድል በዓል በንጉሡ ዘመን ሚያዝያ 27 ቀን በየዓመቱ ይከበር ነበር። ደርግ ወደሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ ግን ‹ኢትዮጵያ ከጣሊያን ወረራ ነፃ የወጣችበትን ቀን ነው የማከብረው› በማለት ደርግ በዓሉን ወደ መጋቢት 28 ቀይሮታል። ኢሕአዴግ ደግሞ ‹‹ንጉሡ በግዞት ላይም ሆነው የዲፕሎማሲ ተጋድሏቸውን አላቋረጡም ነበር›› በማለት በዓሉ ሚያዝያ 27 ቀን በየዓመቱ እንዲከበር አድርጓል::

ይህ ውዝግብ ለምን ተነሳ? የታሪክ መምህር ሰሎሞን ተሰማ ጂ. ‹ሚያዝያ 27 – የኢትዮጵያ ትንሣኤ› በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሑፍ ይህን ሐሳብ አንስተዋል። በዛም እንደጠቀሱት ደርግ ከ34ተኛው የድል በዓል ጀምሮ በዓሉን ወደ መጋቢት 28 ያዞረበትን ምክንያት ሲያስረዳ ‹‹እንደቀድሞው የንጉሡን ታሪክ ለማሞካሸት ሳይሆን፣ የድሉ ባለታሪክ የሆነውን ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ፣ እውነተኛው የታሪክ ቀን ስፍራውን እንዲያዝና ሕዝቡም በራሱ ደም የገነባውን ታሪክ በእጁ መልሶ እንዲጨብጥ ለማድረግ ነው›› እንዳለ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመጋቢት 28/1967 እትምን ጠቅሰው አስቀምጠዋል።

መጋቢት 28 ምን ተፈጠረ ብለን ስንጠይቅ፣ መጋቢት 28 ቀን 1933 ሜጀር ጄኔራል ካኒንግሃምና ጦሩ አዲስ አበባን የተቆጣጠሩበት እለት ነው። ደርግም ይህን ነው ማክበር ያለብን በሚል እንደተጠቀሰው ከ34ተኛው የድል በዓል አንስቶ እስከ 55ተኛው የድል በዓል ድረስ፣ ለሃያ ዓመታትም ያህል መጋቢት 28 የድል በዓል መከበሪያ እለት ሆኖ እንደነበር ሰለሞን ያወሳሉ።

እንዲህ ነው፣ ኢንግሊዝ ኢትዮጵያን ልትደግፍ ስትነሳ፣ የጦር ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያ ያስገባችው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ነበር። ከዛም መካከል በጄኔራል ካኒንግሃም የሚመራው ኢንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ በደቡብ አቅጣጫ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ሲያቀና፣ በጄኔራል ፕላት የሚመራ ሌላ ጦር ደግሞ ከሱዳን ተነስቶ ወደ አስመራ፣ ከዚያም ወደ መሃል ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ አደረገ።

በንጉሠ ነገሥቱ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ‹ጌዲዮን› ተብሎ የተሰየመው ጦር ደግሞ ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጎጃም በኩል ወደ መሃል ኢትዮጵያ ጉዞ ላይ ነበር። ዘመቻው ኹለት ወር ሳይሞላው ጣልያኖች አዲስ አበባን ለቀው ሲወጡ፣ መጋቢት 28/1933 የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፣ በከተማዋም የኢትዮጵያን ባንዲራ ሰቀለ።

ይህ ሲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ቤተመንግሥት አልተመለሱም ነበር። በኋላ ነው በሚያዝያ ወር በ27ኛው ቀን ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ ገብተው በቤተመንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሰቀሉት።

ታድያ ይህን ቀን ነው አሁን ኢትዮጵያ የነጻነት ቀን ብላ የምታከብረው። የታሪክ ምሁራን የትኛው ነው መከበር ያለበት በሚለው ዙሪያ ሚያዝያ 27 ለመሆኑ ምክንያቶችን የሚሰጡ ሲሆን፣ ይልቁንም ንጉሡ በተመለሱበት ጊዜ በመሆኑ ነው መከበር ያለበት በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ። አልፎም ኢትዮጵያ በኢንግሊዝ እጅ የዋለችበትን ሳይሆን ንጉሡ ወደወንበራቸው የተመለሱበትንና በክብር ሰንደቅ የሰቀሉበት ቀን ነው ወሳኙ ሲሉም ይሞግታሉ።

ሰለሞንም ይህን ጉዳይ እንዲህ ገልጸውታል፤ ‹‹ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ-መንግሥት ሰቀሉ። የሚያዝያ 27 የንጉሠ ነገስቱ አዲስ አበባ ገብቶ ሰንደቅ ዓለማ መስቀል ታሪካዊ ምፀትም ነበረው። ከዚያን ጊዜ 5 ዓመታት አስቀድሞ ሚያዝያ 27/1928 በዚያው ቀን ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ አዲስ አበባ ገብቶ በታላቁ ቤተ-መንግሥት የጣሊያንን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን ነበር።››

ዘውዴ ረታ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ታሪክ በሚል በ2005 ባሳተሙት መጽሐፍም በጊዜው የነበረውን ድባብ እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፤ ‹‹ልክ በአምስት ዓመቱ፣ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ከታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተመንግሥት አደባባይ ላይ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀዩን ሰንደቅ ዓላማችንን መልሰው ሰቀሉት። የክብር ዘብ ተሰልፎ፣ በራስ አበበ አረጋይ የሚመራው ዐስር ሺሕ አርበኞች ያሉት ጦር ዙሪያውን በአገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት እንደቆፈጠነ፣ በሱዳን በኩል የመጣውና በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው የጌዲዮን ጦርም ተሰልፎ፣ መድፍ ተደጋግሞ እየተተኮሰ ሰንደቃችን በክብር ከፍ አለ።››

እዚህ ላይ አንድ ሳይነሳ የማይዘነጋ ታሪክም አለ። ይህም በዓሉ የሚከበርበትን ስፍራ የሚመለከት ነው። የደርጉ መንግሥት የበዓሉን ማክበሪያ ቦታ ሦስት ጊዜ እንደቀያየረው ሰለሞን ጠቅሰዋል። የ1967ቱ የድል በዓል የተከበረው በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ (ጊዮርጊስ አጠገብ) ነበር ያሉ ሲሆን፣ ከ35ተኛው የድል በዓልም አንስቶ እስከ 50ኛው የድል በዓል ድረስ ያከብር የነበረው በአብዮት አደባባይ ነበር።

በእርግጥ በጎ ተብሎ ሊነሳ የሚችል ነጥብ ነበር ይላሉ። በተለይም ከደርግ ዘመን የድል በዓል አከባበር ስነ-ሥርዓት ውስጥ ከ1968 ጀምሮ በዋና ዋና ከተሞች ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የድል በዓልን (መጋቢት 28 ቀን) እንዲያከብር ማድረጉ ተጠቃሽ ነው ባይ ናቸው።

አሁን ላይ ታድያ ድሉን ታሳቢ አድርጎ በተገነባው የድል ሃውልት ዙሪያ እናትና አባት አርበኞች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ብዙ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ነው በዓሉ የሚከበረው።

- ይከተሉን -Social Media

ሚያዝያ 27`ዎች – በታሪክ ማኅደር
አሁንም ከታሪክ መምህሩ ከሰለሞን ጦማር ላይ እናንሳ። ሚያዝያ 27 በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ክስተቶች የተጻፉበት ስለመሆኑ አንስተዋል። አንደኛው የ1928ቱ ሚያዝያ ሲሆን ይህም ጣልያን ኢትዮጵያን የያዘችበት ሆኖ ሲመዘገብ፣ ልክ ከአምስት ዓመት በኋላ የመጣው ሚያዝያ 27/1933 ደግሞ የኢትዮጵያ ዳግም ድል የተመዘገበበት እለት ነው።

ሌላው ያነሱት ሚያዝያ 27/1935 እና ሚያዝያ 27/1936ን ነው። አራት ኪሎ የሚገኘው የድል ሃውልት በሚያዝያ 27/1935 የመሠረት ድንጋዩ ተቀምጦ በሚያዝያ 27 ቀን 1936 ነው የተመረቀው። ሌላው ሚያዝያ 27/1947 ሲሆን በሰለሞን ገለጻ ይህ ደግሞ እንዲህ ነው፣ ‹‹ከ10 ቀናት በፊት በሚያዝያ 17/1947 ትልቁን ፀሐፌ ትዕዛዛቸውን (ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስን) የአርሲ አገረ ገዢ አድርገው ከሸኙ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ መጋረጃቸውን ሙሉ ለሙሉ ገልጠው፣ “ከሥልጣን አራስ ቤት” ያለምንም ተቀናቃኝ በድል አድራጊነት የወጡበት ዘመን ነው።››

በተመሳሳይ የድል በዓል አከባበሮችም አስገራሚና አስጨናቂ ድባብ ተላብሰው የነበሩበትን ጊዜ ጠቅሰዋል። በዚህም ኃይለሥላሴ አስራ አምስት ሚኒስትሮቻቸውን፣ አገረ ገዢዎችንና ባለሟሎቻቸውን ካጡ በኋላ በ53ቱ መፈንቅለ መንግሥት ያከበሩት የሚያዝያ 27/1953ቱ የድል በዓል ጠቅሰዋል። እንዲሁም ሚያዝያ 27/1966 የተከበረው የድል በዓል እጅግ አሳዛኙም አስገራሚውም ነበር ሲሉ እንዲህ አስፍረውታል፣

‹‹አሳዛኝነቱ ንጉሠ ነገሥቱ የመጨረሻ የድል በዓልን ያከበሩበት እለት በመሆኑ ነው። አስገራሚነቱ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ በዚያች ቀውጢም ሰዓት ለ30 ዓመታት ሲያደርጉት የነበረውን የሚያዝያ 27 ቀን ፕሮግራም ያለማዛነፍ ማድረጋቸው ነበር። ይባስ ብለው አበባ እያስነሰነሱ ክብረ በዓሉን በተለመደው መርሀ-ግብር መሠረት አከናወኑት።››

ዘንድሮ የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል ለ79ኛ ጊዜ ሲከበር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አከባበሩ እንደቀደመው ጊዜ የደመቀ አልነበረም። ይህም በታሪክ መዝገብ የሚጻፍ ሌላ ክስተት ሆኗል።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች