አራት የውጭ አገራት ዜጎች ከሕገ ወጥ ገንዘቦች ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ

0
487

የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኢንተለጀንስ ክፍል ጋር በቅንጅት ባደረገው ጥናት አራት ውጭ አገራት ዜጎችን ከሕገ ወጥ ገንዘቦች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

በክፍለ ከተማው በርካታ የውጭ አገራት ዜጎች ለመኖሪያነትና ለንግድ እንቅስቃሴ የሚመርጡት እንደመሆኑ መጠን በአካባቢው በርካታ ውጭ ሀገራት ገንዘቦች ልውውጥ ይደረጋል ያለው ፖሊስ መምሪያው ከኅብረተሰቡ ባገኘው ጥቆማ ባደረገው አሰሳ 163,900 ዶላር በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

ፖሊስ በክፍለ ከተማው ወንጀልን ቀድሞ ለመከላከል ወንጀል አካሄዶችን ከኮሚሽኑ የኢንተለጀንስ ክፍል ጋር በቅንጅት ጥናት በማድረግ ሠላማዊ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እንዲኖር ሲያደርግ ቆይቷል፤ በዚህም ከህብረተሰቡ የመጣለትን መረጃ መሰረት በማድረግ ባደረገው ክትትል በወንጀሉ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት አራት የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሲሆኑ ወደ አዲስ አበባ የገቡት ከአንድ ወር በፊት መሆኑን የገለፁት የክፍለ ከተማው ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ያሬድ ታረቀኝ ተጠርጣሪዎቹ ከአንድ በላይ ቤቶችን ሲቀያይሩም እንደነበር ተናግረዋል፡፡

መጋቢት 25/ 2012 ተጠርጣሪዎቹ ይኖሩበታል ወደ ተባለው የእንግዳ ማረፊያ የምርመራ ቡድኑ ባደረገው ክትትልና ማጣራት ተጠርጣሪዎቹ ሀሰተኛ ገንዘብ ለማተም ከሚያስችሉ ተጨማሪ ኬሚካሎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ፖሊስ የገንዘቡን ትክክለኛነት ከብሔራዊ ባንክ ባረጋገጠው መሰረት ገንዘቦቹ የሀሰት ያለመሆኑን ቢያረጋግጥም አንድ የውጭ አገርም ይሁን የአገር ውስጥ ዜጋ ከ3ሺህ ዶላር በላይ ወደ አገር ውስጥ በሚያስገባበት ወቅት የጉምሩክ ኮሚሽን ማረጋገጫ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ተከሳሾችም ይህን እንደፈተላለፉ ገልፀዋል፡፡
ህብረተሰቡ ከዚህ በፊት እንደሚያደርገውም በክፍለ ከተማው ያሉ ውጭ ሀገርም ይሁን ሌሎች ነዋሪዎችን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ በመቃኘት አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥም ለፖሊስ መጠቆም አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here