‹‹ግድብ ስለገነባን አባይን አሳልፈን አንሰጥም›› ኢትዮጵያ

0
766

ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ስታነሳ የቆየችውን የተፈጥሯዊ ፍሰት ጥያቄ ኢትዮጵያ በሱዳን ካርቱም በተካሄደው ጉባኤ ላይ ውድቅ ብታደርግም፣ ግብጽ ግን ጥያቄውን ወደ አዲስ አበባ ጉባኤ መልሳ አምጥታለች። ይህ አግባብ አይደለም ያለችው ኢትዮጵያ፣ የታላቁን ህዳሴ ግድብ በመገንባቴ በወንዙ ላይ ያለኝን መብት እንድተው የቀረበ ጥያቄ በመሆኑ አልቀበለውም አለች።

የግብጽ ተደራዳሪዎች በንግግሮች መካከል የተፈጥሮ ፍሰት የመጠበቅ ጉዳይ ሲዘረዘር የኢትዮጵያን የወደፊት አጠቃቀም አንነካም ቢሉም፣ በጽሑፍ ግን ይህንን የአባይ ወንዝ ተፈጥሮአዊ ፍሰት ይጠበቅ የሚል ሐሳብ ይዘው እንደሚመጡ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ተናግረዋል። ይህንን መቀበል ተፈጥሮ የሰጠንን መብት አሳልፈን መስጠት ማለት ነው የሚሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታ ያለ አግባብ መወሰን በመሆኑ ኢትዮጵያ አትቀበለውም ብለዋል።

በሃይድሮሎጂ የሚታወቀው የተፈጥሮ ፍሰት ትርጉም ከግድቡ በላይ ያለውን የወንዙን መጠን እና ፍሰት የሚያስተጓጉል መሰረተ ልማት ያለመገንባት ማለት በመሆኑ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ እና ተቀባይነት የሌለው ጥያቄ መሆኑን ኢትዮጵያ ገልፃለች።

ስድስት የድርድር ነጥቦችን የያዘው እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በሩሲያዋ ሶቼ ከተማ በህዳሴ ግድቡ ላይ ተጨማሪ ድርድር ለማድረግ በተስማሙት መሰረት ሲደረግ የነበረው የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ የመጨረሻ ጉባኤ፣ ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ተካሂዷል። ስብሰባው ላይም የግብፁ ፕሬዘዳንት ለአሜሪካው አቻቸው ያቀረቡትን የአደራድሩን ጥያቄ ተከትሎ፣ ታዛቢ የነበሩት የአሜሪካ እና የዓለም ባንክ ታዛቢዎችም የተከታተሉት እና የመዘገበት ድርድር ነበር።

በአዲስ አበባ ተጀምሮ በአዲስ አበባ የተጠናቀቀው ይህ ድርድር የያዛቸው ነጥቦችም የመጀመሪያው የድርድሩ መሰረቶች ሲሆኑ፣ የድርድር መርሆዎች፣ የሙሌት እቅድ፣ የግድቡ የውሃ አለቃቀቅ እና ኃይል ማምረት፣ የማስተባበር እንዲሁም የመረጃ መለዋወጥ እና የመተግበሪያ ስልቶች ናቸው።

ባለፉት ድርድሮች ላይ በሰፊው ውይይት የተደረገበት የግድቡ ሙሌት አንዱ ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት አጀንዳ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን በኩል ስምምነት ላይ ቢደርስም ግብፅ ግን የተለያየ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጧ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቀርቷል። በሦስቱ ስብሰባዎች ላይ ያልታየ የሙሌት ሰንጠረዥ ይዛ የመጣችው ግብፅ፣ የግድቡ ሙሌት ከ 12 እስከ 21 ዓመት ድረስ እንዲካሄድ ሐሳብ አቅርባለች። ይህን ተከትሎም ስለሺ ‹‹ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው›› በሚል ገልፀውታል።

ኢትዮጵያ የግድቡ ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ባለው ይሁን የሚል ሰንጠረዥ ስታቀርብ የቆየች ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የግብፅ ተደራዳሪዎች በአምስት እርከን ይሞላ የሚል እና ከኢትዮጵያ እንብዛም የማይለይ ሰንጠረዥ ስታቀርበ ቆይታ ነበር። በኢትዮጵያ ወገን በተለይም ግድቡ መሞላት ከጀመረ ጀምሮ ባሉ የመጀመሪያው እና የኹለተኛ ዓመት የማመንጨት መጠን ላይ መድረስ ይገባዋል የሚል ሐሳብ ፀንቶ ቢቆይም፣ ግብፅ ግን የተለየ ሰንጠረዥ አምጥታለች።
ግብፅ አዲስ ውሃ አሞላልን እና አለቃቀቅን በተመለከተ ያመጣቸው የስሌት ሰንጠረዥ አግባብ ያልሆነ ነው ያሉት የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴሩ ስለሺ፣ አንዴ ግድቡ የሚፈለገው ያህል ከደረሰ ወደ ግድቡ የገባ ውሃ በሙሉ ይወጣል። ስለዚህም አዲስ ያመጡት ሰንጠረዥ አስፈላጊ አልነበረም ብለዋል።

ሌላኛው በድርቅ ወቅት እንዴት እናቻችለዋለን በሚል በተደረገው ድርድር ላይ በ1913 ተከስቶ እንደነበረው ድርቅ ዓይነት ቢከሰት በሚል የአባይ ወንዝ መጠን 20 ቢሊዮን በሚል እጅግ ያነስ የሚባለውን የውሃ መጠን በመያዝ ድርድር ተደርጓል። ‹‹የግድቡ ሙሌት መሃል ድርቅ ቢያጋጥም ታችኛው ተፋሰስ አገር የሆነችው ግብፅ እንዴት ትሆናለች?›› የሚል ጥያቄም በመኖሩ፣ በድርድሩ ወቅት ‹ድርቅ› የሚለውን ቃል የመተርጎም ሙግት በአራቱም ጉባኤ ተካሒዷል።

በኢትዮጵያ ዘንድ ድርቅ መባል ያለበት የውሃ ፍሰቱ ከ 35 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በታች ከሆነ ነው የሚል አቋም የተያዘ ሲሆን፣ ይህም የተሰላው በሃይድሮሎጂ ሳይንስ መሰረት መሆኑን ስለሺ ይናገራሉ።

ግብፅ በበኩሏ የውሃ ፍሰቱ ከ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በታች ከሆነ ይህ ድርቅ ሊባል ይገባል በማለት ስትሞግት ቆይታለች። ኢትዮጵያ ድርቅ ቢከሰት በየ ዓመቱ 13 ነጥብ አራት ቢሊዮን ለመልቀቅ ሐሳብ ብታቀርብም፣ ግብፅ ግን 14 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ይሁን ብላ ተከራክራለች። ኢትዮጵያም የኹለቱ ሐቦችን ቅርበት በመውሰድ፣ አማካኝ የማውጣት ወይም የግብፅን ጥያቄም መቀበል ኢትዮጵያ ኃይል አመንጭታ የምትለቀው ውሃ በመሆኑ እንደማይጎዳት ገልጻለች። ይሁንና በዚህ ጉዳይ ላም ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቀርቷል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የአባይ ወንዝ አማካኝ የውሃ ፍሰት 38 እስከ 52 ያለ በመሆኑ ከዛ በላይ ያለው ከፍተኛ ጎርፍ ያለበት፤ ከዛ በታች ያለው ደግሞ ድርቅ ሆኖ እንዲወሰድ ስትከራከር ሰንብታለች። ግድቡ ውስጥ ያለው የውሃ አስተዳደር በድርቅ ሰዓት ለታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚለቀው የውሃ መጠን እና የመሳሰለው ጉዳይ የሚወሰነው የአጠቃላይ የአባይ ዓመታዊ የውሃ ፍሰት ከ 35 ቢሊዮን ሜትሪክ ኩብ በታች ከሆነ ብቻ ነው የሚል አቋምም ተይዟል።

የህዳሴው ግድብ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ካለ እና የድርቅ ወቅት ከመጣ ምን እናድርግ የሚለውን ሐሳብ ተከትሎም፣ ኢትዮጵያ ወደ ግድቡ የሚገባውን ውሃ ሙሉ በሙሉ ወደ ታች ለማፍሰስ እንዲሁም ግድቡ ካጠራቀመው ውሃ ላይም የተወሰነውን ለመለቀቅ ሐሳብ አቅርባለች። ኢትዮጵያ በአዲስ አበባው ጉባኤ ላይ የድርቅ ወቅት የውሃ አለቃቀቅ ሰነጠረዥ በማዘጋጀት ውሃ የምትለቅበትን ሐሳብ ብታቀርብም፣ ግብፅ ሳትስማማ ቀርታለች። ግብፅ ተመሳሳይ ሰንጠረዥ ይዛ መምጣቷን ተከትሎ ኢትዮጵያ ግብጾች ያመጡትን ሰንጠረዥ ለመቀበል ሐሳብ ብታመጣም፣ ግበጾች በራሳቸው ሰንጠረዥም ሳይስማማ ቀርተዋል።

‹‹ራሳቸው ያመጡት ሰንጠረዥ ግራ አጋብቷቸው ይሁን ወይም ሌላ አላውቅም። ነገር ግን በሱም ሳይስማሙ ሄደዋል›› ያሉት ስለሺ፣ እንመክርበታል የሚል ሐሳብ ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

‹‹ግብጾች አዲስ አበባ ሲመጡ ለመስማማት የመጡ አይመስለኝም። ያልተመነዘረ የቴክኒክ ችግር አልነበረም። ሁሉም ነገር ሳይንስን ተከትሎ በግልጽ የተካሄደ ሲሆን ችግሩን ተረድቶ ችግሩን የማስቀረት ሐሳብ ቢቀረብ እና ችግሮች ቢሻሻሉም መስማማት ሳይቻል ቀርቷል›› ሲሉ ስለሺ ተናግረዋል። ‹‹ምን አልባት እዚህ ስበሰባ ውስጥ ሌለሰ አካል እንዲገባ ተፈልጎ ካልሆነ ለስምምነት የሚከለክል ነገር አልነበረም›› ብለዋል።

ግድቡ እንደማያስፈልግ አድርጎ የማሰብ ወይም የመገመት እዝማሚያ ቢኖርም፣ በተገቢው የዓመታት ርቀት ውስጥ እንዳይሞላ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር በጥናት የተቀመጡት ቁጥሮች ተገቢ ነበሩ ሲሉም አክለው ተናግረዋል።
ድርድሩ ግን ሙሉ ለሙሉ የከሸፈ ሊባል እንዳማይቻል እና በብዙ ነጥቦች ዙሪያ መስማማት ላይ እንደተደረሰ ስለሺ ተናግረዋል። ከእነዚህ መካከልም ግብጽ ቀድማ ስታነሳው የነበረውን የህዳሴ ግድቡን ከአስዋን ጋር በማጣመር የቀረበው ሐሳብ መቅረቱን ተናግረዋል። የህዳሴው ግድብ የአስዋን ግድብን የተወሰነ ከፍታ እንዳይጎድል በዚህ ስምምነት ሊታሰር ይገባል የተባለውን ሐሳብ በኢትዮጵያ ውድቅ እንዲደረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

‹‹የህዳሴው ግድብ ምን በወጣው፣ ከአስዋን በላይ እኮ ሱዳን አለች። ኢትዮጵያም ያለማቻቸው ሌሎች ልማቶች አሉ። ስለዚህ በህዳሴው ምክንያት የአስዋን ከፍታ ላይ የምንገባው ቃል የለም›› ሲሉ ኢንጂነሩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዓመት 49 ቢሊዮን ሜትሪክ ኩብ ውሃ እንዲለቀቅ ማረጋገጫ ይሰጠኝ ስትል ግብጽ ያቀረበችው ጥያቄም፣ በአራቱ ድርድሮች ላይ መፍትሄ በመጨረሻ እንዲቀር መደረጉም የድርድሩ ውጤት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።

በአገራቱ መሪዎች ትዕዛዝ መሰረት አራት ስብሰባዎችን በማካሄድ ልዩነቶችን ለማጥበብ ለሚኒስትሮቹ የተሰጠው የቤት ሥራ በመጠናቀቁ በኢትዮጵያ በኩል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖረት እንደሚደረግ ስለሺ ተናግረው፣ በመጪው ሰኞ ጥር 04/2012 ወደ አሜሪካ በመሄድ በጋራ ሦስቱ አገራት ታዛቢ ለሆነቸው አሜሪካ የደረሱበትን ያስታውቃሉ። የሚያቀርቡት ሪፖርትም የተለየ ሳይሆን የኢትዮጵያን አቋም እና የድርድሮቹን ውጤት እንደሆነም ስለሺ ገልፀዋል።

ከዚህ በኋላ ችግሩ በቴክኒክ ይፈታል ወይስ በፖለቲካ ይፈታል የሚለው ቴክኒካዊ ሥራው በበቂ ሁኔታ ሳይንስን መሰረት ተደርጎ መሰራቱን እና ድርድሩም እነሱ ይዘውት የመጡትን ሰንጠረዥ እንኳን እንቀበል ለሚለው እንኳን ፍላጎት የሌለበት ስለሆነ እንጂ፣ የቴክኒክ ጉዳይ በአግባቡ የተፈታ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላም አንቀጽ አስርን ለመተግበር የሦስቱ አገራት ስምምነት ያስፈልጋል። ይህንንም ኢትዮጵያ ለመሪዋ የደረሰችበትን ካሳወቀች በኋላ፣ ከዛ ቀጥሎ የሚወሰን ወይም የሚታይ እንደሚሆን ተናግረዋል። ከአምስት ዓመት በፊት ሦስቱ አገራት ያጸደቁት የመርሆዎች መግለጫ (Declaration of Principles) አንቀፅ 10ን ወደ ሥራ ሊገባ ይችላል። አንቀፅ አስር፣ ሦሰት አማራጮችን የሚያቀርብ በአደራዳሪ፣ ማደራደር እና በአገር መሪዎች ቀርቦ ድርድር የሚደረግበት የሚሉ ይገኙበታል።

በግድቡ ላይ ከዚህ በፊት ኹለት ዓይነት ድርድሮች የተደረጉ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የባለሞያዎች ፓናል በሰጠው አስተያየት መሰረት በሦስቱ አገራት ለተቋቋሙ የቴክኒክ ቡድን በማቅረብ ለማፀቀው የተደረገው ሙከራ የመጀመሪያው ነው። የቴክኒክ ቡድኑም በዚህ መሰረት አማካሪ በመቅጠር ድርድሮቹ እንዲሳኩ ለማድረግ ቢሞከርም ሳይሳካ ቀርቷል።

ከዚህ በኋላም ሦስት በሦሰት በሚበል መርህ፣ ከሦስቱም አገራት ሦስት ሦሰት ሚኒስትሮች ተመርጠው ዘጠኝ ሚኒስትሮች ሲደራደሩበት የነበረው መንገድም ሳይሳካ ቀርቷል። ከየአገራቱ አምስት አምስት ሳይንቲስቶች ተመርጠው ይህንን ድርድር ቢቀላቀሉም መስማማት ሳይቻል ቀርተዋል።

ይህ በመሆኑም የኢትዮጵያ እና የግብፅ መሪዎች በተስማሙት መሰረት፣ ለውሃ ሚኒስትሮቻቸው በሰጡት ኃላፊነት መሰረትም ከአዲስ አበባ ጀምሮ አራት ጉባኤዎች ቢደረጉም አሁንም ባለመግባባት ተጠናቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here