መነሻ ገጽአንደበት‹‹ስለወጣቶች እያወራን እንጂ ወጣቶችን እያወራናቸው አይደለም››

‹‹ስለወጣቶች እያወራን እንጂ ወጣቶችን እያወራናቸው አይደለም››

‹‹ባልንጀራዬ›› ይሰኛል፤ በማኅበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ ‹‹ባልንጀራዬ /Balinjeraye›› በሚል ሥያሜ ይገኛል። ሌላውን እንደራስ የመውደድ እንቅስቃሴ ነው። በአሜሪካዊው አንድሪው ዴኮርት (ዶ/ር) የተመሠረተ እንቅስቃሴ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ፋካሊቲ የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ረዳት ፕሮፌሰር ተካልኝ ነጋ ምሥረታው ላይ አሉበት። ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ በፖለቲካ ሰበብ ማኅበራዊ የሆኑ የኢትዮጵያውያን እሴቶች እየደበዘዙ በመሰሉበት ጊዜ፣ አንድን ሰው ለሌላው፤ ሌላውንም ለአንዱ የባልንጀራ አምባሳደር አድርጎ ስለመሾም በባልንጀራዬ እንቅስቃሴ ተነስቷል። ኹለት ወር ገደማ ተግባራዊ ሥራዎችን መከወን የጀመረው እንቅስቃሴው፣ዝነኛና ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችን ይዞና ግዙፍ የሆነውን የባልንጀራነት ሐሳብ አንግሦ እየቀጠለ ነው።

የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ በእንቅስቃሴው ዓላማ፣ ተግባራትና የወደፊት ርዕይ ዙሪያ ከእንቅስቃሴው መሥራቾች አንዱ ከሆኑት የባልንጀራዬ ተባባሪ ዳይሬክተር ተካልኝ ነጋ (ዶ/ር) ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

‹ባልንጀራዬ›ን እንተዋወቅ፤ በቅድሚያ ግን ሴት ናት ወይስ ወንድ ነው? በምን አንቀጽ ነው የምትጣሩት?
ጾታ አላወጣንም፤ ባልንጀራዬ የእኔ የሚለውን ነገር ነው የሚያመለክተው። ስለዚህ ለወንድም ለሴትም በእኩል ነው የምናገለግለው፤ በፆታ እኩልነት ስላምናምንም ማለት ነው።

የባልንጀራዬ ምሥረታ እንዴት ነበር?
የባልንጀራዬ ምሥረታ በዋነኛነት ከኹለት ነገር አንጻር ሊታይ ይችላል። አንደኛ ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር ይያያዛል። የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት፣ ከበጎ ነገሮች ባሻገር መፍትሔና ትኩረት የሚፈልጉ ነገሮች እንዳሉ አየን። ያየናቸው ብዙ ቢሆኑም ሲጨመቁ አራት ነገሮች ናቸው። በመጀመሪያ ያየነው ከማንነት ግንዛቤ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ነው።

ይህን ስንል ሰው ከተካተተበት ቡድን አንጻር ራሱን የሚመለከትበት እይታ ነው። የፖለቲካ ፓርቲ ከመደገፍ ጋር፣ የሆነ ብሔር አባል ከመሆን ጋር ወይም ከእምነት ተቋም ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ከማንነት ጋር ባለው ግንዛቤ ውስጥ አግላይነት አየን። ይህም የቡድን አባል የሆነን ሰው የመውደድ፣ ያለምንም ጥያቄ የተናገረውን መቀበል፣ ከዛ ውጪ ያለ ሰው ደግሞ ምንም ነገር ቢናገር ያለማመን፤ በጥርጣሬ መመልከት፣ ሲብስ ደግሞ እንደ ጠላት ማየት።

እነዚህ ነገሮች በብዙ መንገድ ተገልጠው ጎጂ መሆናቸው ታይቷል። አንዳችን ሌላችንን የምናይበት መንገድ በጣም ችግር አለበት ብለን ወሰድን።

በኹለተኛ ደረጃ የእኛን አገር ሁኔታ ስንመለከት፣ በጣም ጥልቅ ድህነት የሚባለው ነው ያለው። መንገዶቻችን በምን ዓይነት ሰዎች እንደተሞሉ እናውቃለን፣ ልባችን ሳይሰበር ወደ ቤት የምንገባባቸው ቀናት የሉም ማለት ይቻላል። ካሉም እንኳ ላለማየት ስለወሰንን እንጂ ስለሌሉ አይደለም። እና ይህም ጉዳይ የእኛን ትኩረት ይፈልጋል አልን።
በሦስተኛ ደረጃ ያየነው የፍትህ ጉዳይ ነው። እርስ በእርስ ባለን ግንኙነቶች ውስጥ የፍትህ መጓደል አለ። ጥቅሞችን የምንጋራበት መንገድ ሁላችንንም በእኩልነት እያሳተፈ አይደለም። የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እየተካፈልን ያለንበት መንገድ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ስላልሆነ፣ ለወደፊት ቅሬታ በሚፈጥር ዓይነት መንገድ በመካከላችን ክፍተት እየፈጠረ ነው። እነዚህ ሊታረቁ የሚያስፈልጋቸው መዋቅራዊ አሠራሮች አሉት ማለት ነው።
በአራተኛ ደረጃ የተመለከትነው ከኢትዮጵያ ወጣነት ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ወጣቶች ሳይሆን ከኢትዮጵያ ወጣትነት ጋር ነው። ከ50 ዓመት በታች ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ63 በመቶ በላይ ናቸው። ስለዚህ ስለ ኢትዮጵያ ማውራት ማለት ስለ ወጣቶች ማውራት ነው።

ማኅበረሰቡ ወጣቱን እንደ ችግር የመቁጠር አዝማሚያ ታይቶበታል። ወጣቱ ግን በትክክል ከያዝነው፣ አቅሙን ካጎለበትን ችግር አይደለም። ከወጣትነት ጋር በተያያዘ ያየነው ትልቁ ችግር ትርጉም ከማጣት ጋር ይያያዛል። የሰው ሕይወት ትርጉም የሚያጣው ዓላማና ርዕይ ሳይኖረው ሲቀር፣ ሌላውን በማገልገል ውሰጥ ያለውን እርካታ መገንዘብ ሳይችል ነው። እነዚህ አራት ነገሮች ሁላችን አቅም አሰባስበን ካልተረባረብን በቀር ዛሬ ላይ አሉን የምንላቸውን በርካታና ጥሩ እሴቶቻችንን የሚያጠፉ ናቸው።

በኹለተኛ ደረጃ አካባቢያችንን ከመገንዘብ ባሻገር ነው። ባልንጀራዬ የሚለው ሐሳብ እኛ የወለድነው አይደለም። በርካታ ሐይማኖቶች ሲያስተምሩት የነበረ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ የአማኞች አገር ናት። እንደውም 2015 የተደረገ ጥናት እንዳሳየው፤ ከ100 ሰዎች መካከል 98ቱ ሐይማኖት ለእኔ ትልቅ ቦታ አለው የሚሉ ናቸው።
ቀደምት የሚባሉት ሐይማኖቶች ከይሁዲነት ብንጀምር በብሉይ ኪዳን ባልንጀራን መውደድን ሙሴ አስተምሯል። አዲስ ኪዳን ላይ ስንመጣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምረው እናያለን። በእስልምናም በቅርብና ሩቅ ያሉ ባልንጀሮቻችሁን ውደዱ የሚል ትምህርት አለ። እነዚህ ሦስት ሐይማኖቶች በዋነኛነት የእኛነታችን መገለጫዎች ናቸው፤ የሚስማሙበት ነጥብም ነው።

በመቀጠል እየተከተልን ያለነው የዴሞክራሲ ስርዓት በራሱ ይሄን በባልንጀርነት ውስጥ ሊታዩ ያስፈልጋሉ የምንለውን እሴት የሚደግፍ ነው። ከሰዎች መብት ጋር የተያያዙ የነጻነት እንቅስቃሴዎች ይገኛሉ። ስለዚህ እኛ ዱላ ተቀብሎ ሒያጅ ነን፣ የተረሳውን ነገር አስታዋሽ ነን። እንጂ የዚህ ነገር ፈጣሪ ነን አንልንም።

ባልንጀራዬ በምን መንገድ እነዚህን የተነሱ ነጥቦችን ሊያስተናግድ የሚችለው?
ከመጀመሪያው ስጀምር አንዳችን ሌላችንን የምናይበትን የእይታ ዓይነት እንለውጠው ነው። የባልንጀራዬ መልዕክቱ ግልጽ ነው። ሰው ሁሉ ፍቅርና ፍትህ የተገባው ለፍሬያማነት የተጠራ ነው የሚል ነው። የእኛም ግብ ለሁሉም ጎረቤቶቻችን ወይም ባልንጀሮቻችን ፍቅርና ፍሬያማት ያስፈልጋል፤ ለዚህም ሰዎች መነሳሳት አለባቸው ብለን ነው የምናስበው።

አንዳችን ሌላችንን ስንመለከት እኩዮች እንደሆን፣ በመደጋገፍ አብረን የምናድግ ሰዎች እንደሆንን ከተመለከትን፣ ዛሬ ላይ እያየን ያለውን ሌላውን ሰው የማጠልሸትና የማሰይጠን፤ ከሰውነት ተራ የማውረድ፣ ከእኛ የተለየ እኛን የማይመስል አድርጎ የመሳሉ ነገር መፍትሔ ይኖረዋል። ስለዚህ ትልቁ እይታ ሌላውን ሰው የምንመለከትበት ነው።
ዓርማችን አልማዝ (ዳይመንድ) ነው። የሰውን ክቡርነት ያመለክታል። ሰው ሁሉ በጣም ውብ ነው፤ ክቡር ነው፤ ቦታ ሊያገኝ ያስፈልጋል በሚል መንገድ ልባችንን ማስፋት፣ አንዳችን ሌላችንን በውድድር መንፈስ ሳይሆን ተደጋጋፊ እንደሆንን ማየት፣ የአንዳችን መኖር የሌላውን ሕልውና የሚያስቀጥል፣ የአንዳችን ጉዳት ለሌላችን ሊሰማን የሚያስፈልግ እንደሆነ ነው የምናምነው። እንቅስቃሴው ይህን እሴት ዳግም ለማንሳት ይጠቅማል። እይታ በተቀየረ ቁጥር ግንኙነታችን ይቀየራል፤ ግንኙነታችን የእይታችን ውጤት ስለሆነ።

ኹለተኛው የድህነታችን ጉዳይ ነው። ድህነታችን የከፋ ነው። በአንድ በኩል እስከዛሬ የተማመንባቸው ትልልቅ የዓለም አቀፍ ተቋማት መጠበቅ የምንችልበት አይደለም። አቅም ቢኖራቸውም እኛ የምንደርስበት ቦታ ሁሉ መድረስ አይችሉም። ስለዚህ መጀመሪያ ደረጃ አጠገባችን ላለ ሰው ባልንጀራችን እንደሆነ ካሰብን፣ የመጀመሪያ ኃላፊነት እንዳለብን ይሰማናል። በዚህ ግላዊ ቸርነት እንለማመዳለን።

ይህ ሲባል በጉድለት መቆም፣ ያለንን ማካፈል ነው፤ ለዚህ መነሳሳት ያስፈልጋል። ‹እኔ የማደርገው ነገር ኢምንት ነው› ከሚል ስሜት መውጣት ያስፈልጋል። እኛ የምናደርገው ነገር በዛ ሰው ሕይወት ውስጥ የሚጫወተው ሚና በቁጥር አይቀመጥም። ብዙዎች የማያስተውሉት ነገር በዜሮ እና በአንድ መካከል ያለው ልዩነት ምንም ይመስላቸዋል። በምንምና በሆነ ነገር መካከል ያለው ልዩነት ግን በቃል የሚገለጽ አይደለም።

ይሄ በግለሰብ ደረጃ የሚደረግ ነው። በተቋማት እየተሳተፍን ያለን ደግሞ ሆነ ብለን የተገፉ ያልናቸውን አካላት፣ ተጠቂ ብለን የምናስባቸውን መደገፍ አለብን። ይህን ሁሉ ለማድረግ መጀመሪያ ተጎድቷል ብለን የምናስበው የእኛ ሰው መሆኑን፣ እንደ እኛ ሰው እንደሆነ ማሰብ አለብን። ባልንጀርነት እይታችንን ቀይሮ ተመሳሳይ ኑሮና ሕልም እንዲኖረን የሚያስችል ነው። እርስ በእርስ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖረን ያደርጋል።

ሦስተኛ ደረጃ የፍትህ ጉዳይ ነው። ለሌላ ሰው ቸርነት ማድረግ እይታው አጭር ነው። የፍትህ ጥያቄ ግን የረጅም ጊዜ ማስተካከያ ነው። ፍትህ የድምጽ ማሰማት ሥራ ነው። ብዙዎቻችን የፍትህ መዛባትን እንመለከታለን፣ ጥንቃቄያችን ግን ያ የፍትህ መዛባት እኛን እንዳያገኘን ብቻ ነው። በእኛ እና በሌሎች መካከል ግድግዳ ስላስቀመጥን፤ ያ እስካልተሰበረ ድረስ ይህ አመለካከት ይቀጥላል።

- ይከተሉን -Social Media

ሁላችን በአምላክ አምሳል የተፈጠርን ክቡራን ነን ብለን የምናስብ ከሆነ፣ ሁላችንም ያለ ማኅበራዊ ኑሮ ልዩነት እኩል ነን ብለን የምናስብ ከሆነ፣ ይህን ግድግዳ መስበር ቀላል ነው። እይታ አስተሳሰብ ላይ ነው። ባልንጀራ አድርገን ስንቆጥር የሌላው ሕመም ስለሚሰማን ድምጽ እንሆናለን።

አዛውንቶችና ትልልቆች ወጣቶችን በመውቀስ ተጠምደናል። በኹለታችን መካከል ድልድይ ካልሠራን ዋጋ የለውም። ችግር ናቸው የምንላቸው ሰዎች የአገራችን ተስፋ ናቸው። በአብዛኛው ስለ ወጣቶች እያወራን እንጂ ወጣቶችን እያወራናቸው አይደለም።

አሁን ወጣቶችን ማውራት ያለብን ጊዜ ላይ ነን። ምንድን ነው የሚፈልጉት፣ ተግዳሮት ምንድን ነው፣ ምንስ ልናግዛችሁ እንችላለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ ትላንትናቸው ውስጥ ያለፉበትን ነገር አስመልክቶ ምክር ቢያስፈልጋቸው በባልንጀራነት ብንንቀሳቀስ በምክር ማገዝ እንችላለን። ዛሬ ላይ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የመከወን ችግር ካለባቸው ደግሞ ልናሠለጥን ልንኮተኩታቸው እንችላለን። አንዳንዶቹ ደግሞ የሚገርም ዓይነት አቅም አላቸው። ያንን የጠየቃቸው ሰው ስለሌለ ግን፣ እነሱም ርዕያቸውን ስለማያውቁ ባሉበት ይቀጥላሉ። ምክር መስጠት ያስፈልጋል። ይህን ባህል መገንባት እንፈልጋለን።

በፌስቡክ ገጽ ላይ ቃል መግቢያ ሰነድ አላችሁና የተለያዩ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችም ‹ፈርመዋል፤ ቃል ገብተዋል› ስትሉ ይታያል። ነገሩ ምንድን ነው?
ያልኳቸውን ውጤቶች ለማምጣት ልንከውን የምንፈልገው ኹለት ነገር ነው። አንደኛ እሴቱን ሰው ተገንዝቦ ቃል እንዲገባ እንፈልጋለን። ለዚህ ነው ድረ ገጻችን ላይ የቃልኪዳን ሰነድ ያለው። ሰነዱ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ እኔ የባልንጀራዬ አምባሳደር እሆናለሁ›› የሚል ነው። አምባሳደርነት የውክልና ጉዳይ ነው።

ይሄ ቃልኪዳን ወደ ተግባር የሚለወጥበትን መንገድ ጭምር ነው ያዘጋጀነው። ተግባሮቻችን ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ የሚጠይቁ አይደሉም። ተግባሮቻችን ሁላችን አሉን የምንላቸው የሰውነት አካሎቻችን ናቸው። ፈጠራ በተሞላበት መንገድ ብንጠቀማቸው ግንኙነታችን ወደተለየ ደረጃ ይወስዳሉ ብለን እናስባለን። ለምሳሌ ባልንጀራዬን ሳየው የሚሰማኝ ስሜትን ሆነ ብሎ በውስጥ መኮትኮት ዓይነት። በዐይናችን ባልንጀራችንን ስናይ ‹የተለየ ሰው አግኝቻለሁ፣ ከሰውነት አላራክሰውም፣ ዘንግቼ አላፈውም፣ ለመገኘቱ እውቅና እሰጣለሁ።› ማለት፤ እንዲሁም ከሰዎች ጋር ባለኝ ግንኙነት ውስጥ ሥማቸውን የማላውቅ የሚመስላቸውን ሰዎች ሥማቸውን ስጠራ የሚፈጥረው ደስታ አለ። ያ ደስታ ደግሞ የሚያስከትለው ትስስር የሚገርም ነው። ይህ ዐይኔን ብቻ የሚፈልግ ነው።

በእጆቼ ሌላውን ለማገዝ እተጋለሁ። በተጨማሪ በቤተሰብ ውስጥ ባለን ድርሻ፣ እንደ እህት፣ ወንድም፣ አባት፣ እናት ወዘተ ተጽእኖ የምናደርግበት መድረክ ነው። በዛ የተሰጠንን ሥልጣን እንዴት ነው አረአያ ለመሆን የምንጠቀመው? ሌላው ጆሮአችንን ብንከፍተው፣ እግሮቻችንን ካሉበት ሰፈር ማውጣት ብንችል እና ሌሎችም። ይህ ሁሉ እይታችን ሲለወጥ ግንኙነታችን ይለወጣል ከሚል እይታ ነው።

ባልንጀራዬ ውስጥ ስንት አባላት አሉ፤ እንዴትስ ተሰባሰባችሁ?
ባልንጀራዬ አምስት ሰዎች ያሉበት ቡድን ነው። የዚህ መሥራች ዳይሬክተር ዶክተር አንድሪው የሚባል አሜሪካዊ ነው። ኢትዮጵያን ከ10 ዓመት በላይ የሚያውቅ ነው። በመምህርነትም ለረጅም ጊዜ ቆይቷል፤ የሚኖረውም እዚህ ኢትዮጵያ ነው። እሱ ባልንጀራ የሚለውን ሐሳብ አነሳ።

እኔም በተመሳሳይ ይህን አስብ ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነት ቆይታዬ ተገናኝተን በወዳጅነት ስናወራ፣ ስናሰላስል የሆነ ነገር ማድረግ አለብን የሚል ሐሳብ ውስጣችን ተፈጠረ። የሆነ ዓይነት እርምጃ መውሰድ አለብን ብለን አሰብን።

- ይከተሉን -Social Media

ችግሮቻችን ራሳቸው የሚፈቱ አይደሉም፤ ጊዜ ይፈታዋል የሚባለው በጊዜ ውስጥ የሚንቀሳቀስ አካል አለ ብለን ስለምንገምት ነው። ያንን አካል ከምንጠብቅ እኛ በጊዜ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው አካል ለምን አንሆንም ብለን ነው። ስለዚህ አጀማመሩ ያለንበትን ሁኔታ ከመገንዘብና ከኹለታችን ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው።

እንቅስቃሴው ከተጀመረ ምን ያህል ጊዜ ሆነ?
ባልንጀራዬ እንቅስቃሴ መቼ ተጀመረ የሚለው ቀላል ጥያቄ አይደለም። ምክንያቱም ልባችን ውስጥ መች ተጀመረ ከሚለው ጋር ይሄዳል። ማሰላሰል ከጀመርን 10 ዓመት በላይ ሆኖታል። ኹለታችን ግን [እኔና አንድሪው] በዚህ ጉዳይ ላይ ሆነ ብለን ንድፍ እየነደፍን እያቀድን ከጀመርን አሁን ኹለት ዓመት አካባቢ ሊሆን ነው። ወደ ማኅበራዊ ሚድያ ከመጣን ደግሞ ኹለት ወር ያህል ነው። ስለዚህ ጅማሬው መልኩ ብዙ ነው።

ምን ዓይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ ነው?
ይህ ሐሳብ ሁሉም ሰው ጋር እንዲደርስ እንፈልጋለን። ሰውን ማግኘት የምንችለው ደግሞ በኹለት መንገድ ነው። አንደኛው ገጽ ለገጽ የሚባለው ነው፤ ፊት ለፊት። ኹለተኛው የእርስ በእርስ ግንኙነታችን በሚድያ አማካኝነት ነው።
ፊት ለፊት የሚባለው አስመልክቶ ስትራቴጂዎች አሉ። አንደኛው ለምሳሌ በሚቀጥለው ወር ወደ ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ እንሔለን። የምንሔደው ቀደም ብለን ያነሳነውን ጽንሰ ሐሳብ ለማስተዋወቅ ነው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የምናገኝበት መድረክ አለ ማለት ነው። እናም በዚህ ዓመት ከ10 ያላነሱ ዩኒቨርሲቲዎችን የመድረስ እቅድ አለን። ወደዚህ በምንሔደበት ጊዜ ብዙዎችን የማግኘት እድል አለን።

ከዚህ ባሻገር ከእምነት ተቋማት ጋር የሚሠሩ አካላት አሉ። ከእምነት ተቋማት ጋር ስንገናኝ ፊት ለፊት ተገኝነት መልእክቶችን እናስተላልፋለን። ለምሳሌ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤቶች አሉ። እነዚህ የአንድነት ትምህርት ቢያስተምሩም ልበ ሰፊ ናቸው። ከዛ ባሻገር በሚድያ የምናስባቸው አሉ። በመደበኛም ሆነ በኢ መደበኛ፣ ሁሉም አሉ። ፌስቡክ፣ ትዊተርና መሰሎቹን ጨምዎ። የራሳችን ድረ ገጽም አለን፤ በዚህ ለምሳሌ የቪድዮ ትምህርት ይኖራል። ይህን እናቀርባለን። ይህም ሰርተፍኬት የሚያሰጥ ጭምር ነው።

በቅርቡ እኔው ያዘጋጀሁት መጽሐፍ አለ፤ ‹ባልንጀራዬ› የተሰኘ። ከይሁዲነት እና ክርስትና ጋር በተያያዘ ባላንጀራ ሁሉም ሰው የሚያብራራ ነው። በእቅድ ደረጃ በድምጽ አዘጋጅተን ለሰው እንዲደርስ ማድረግ ይኖራል።
እንቅስቃሴው ሰዎችን ማነሳሳት ስለሆነ በወር አንድ ጊዜ ባልንጀራ መውደድ 101 የተሰኘ፤ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ባለሙያ ጋር መድረክ አዘጋጅተን ውይይት የሚደረግት መድረክ ይኖረናል። በዚህ ውስጥ ውድድሮች ጭምር ይኖሩናል። እነዚህም አብረውን የሚሠሩም አሉ፤ ለአሸናፊዎች ጊዜ የሚያሳልፉበትን ጊዜ ጭምር ሰጥተውናል። ከእነዚህ ጋር አብረን እየሠራን ባልንጀራነትን የሚያጠናክር፤ በጣም በጎ ሞዴል የሚሆን ሥራ ሠርተው ግን ያልታየላቸው ሰዎች ጭምር ታሪካቸውን ማውጣት እንፈልጋለን።

ከትምህርት ቤቶችም ጋር እንሠራለን። ልጆች ያልሰማናቸው የማኅበረሰብ ክፍል ሲሆኑ ከማስተማር ባላነሰ የምንማርባቸው ናቸው። እንደ አገር እየፈተኑን ያሉ ጥያቄዎች በእነሱ እይታ ምን ይመስላሉ የሚለውን እናያለን።
በባልንጀራዬ አዲስ በሆነ መንገድ ፈጠራ የተሞላበትና ሁሉም ሰው ተሳታፊ የሚያደርግ፤ እኛ ብቻ ሳንሆን ሌላው ሰውም ተሳታፊ የሚሆንበት እንዲሆን ነው የምንፈልገው። እኛ ተናጋሪ ሌለው አድማጭ ሳይሆን ሁላችን በጋራ የምንሠራት ነው። መገናኛ ብዙኀንም ትልቅ ባለድርሻ አካል ነው።

ኃይሌ ገብረሥላሴን ጨምሮ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች እንቅስቃሴያችሁን ሲደግፉ ታይተዋል፤ በምን መልኩ ነው ሊያግዟችሁ የሚችሉት?
ማኅበረሰባችን ውስጥ ትልቅ ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች አሉ። አንዳንዶች ፖለቲካኛ አንዳንዶች አርቲስት ሌሎች በየዘርፉ የተሳካላቸው ናቸው። እነዚህ ሰዎች ካላቸው ስኬት አንጻር ብዙ ተከታይና ሊከተሏቸው የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች የእኛን መልእክት ሲናገሩ በጣም ተደማጭነታችን ያድጋል።

ለምሳሌ ኃይሌ ገብረሥላሴ ካናገርናቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ኃይሌ በዚህ ሐሳብ ደስተኛ ነው። በሚችለው ሁሉ ሊያግዘን ተዘጋጅቷል። ያን የቃልኪዳን ሰነድ ፈርሟል። ያ ማለት የሰውነት አካልን በመጠቀም ይህን ማንነት እንኖራዋለን ነው። ለወደፊት ደግሞ ከተቋማት ጋር የምናስበው አጋርነት አለ። በእነዚህ የአጋርነት መድረኮች ውስጥ እነዚህ ተቋማት በቢሮዎቻቸው ቃል ኪዳን ሰነዱን እንዲሰቅሉ፣ በተቋማቸው ከሠራተኞቻቸው ጋር በዛ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ። እኛም ለምሳሌ ለሠራተኞች ሥልጠና በመስጠት የምንሰጠው ድጋፍ ይኖራል። በዚህ ላይ ወደፊትም ብዙ የምናወራው ይኖራል።

- ይከተሉን -Social Media

በቅርቡ ይህን ሐሳባችንን የምናሳውቅበት ይፋዊ ክዋኔ ይኖረናል። ይህን ሐሳብ ሰው እንዲገዛ እና እንዲኖርበት ነው የምንፈልገው።

ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊ ትስስር እሴት አለን የምንል ሕዝቦች ነንና፤ አሁን ደግሞ እርስ በእርስ የምንተያይበት እይታ ልክ አይደለም እያልን ነው። እንደ ባልንጀራዬም እንደ አንድ ግለሰበም፤ የቱ ጋር ይመስሎታል ይሕ ትስስር የተበጠሰውና እርስ በእርስ እይታችን የተበላሸው?
እንደ እኔ አመለካከት የእርስ በእርስ ግንኙነታችን የሚኖረውም የሚበጠሰውም በአንድ መርህ ላይ ነው። ያ መርህ ምን ያህል እየተገናኘን ነው የሚለው ነው። እርስ በእርሳችን እንዳንገኛኝ የሚያደርጉ ግድግዳዎች በተገነቡ ቁጥር፣ አንዳችን ከሌላችን ጋር ያለንን ልዩነት ስንናገር እንዲህ ያሉ ክፍተቶች መፈጠራቸው አይቀርም። እና ትልቅ ሚና የተጫወተው ብዬ የማስበው መተያየት ማቆማችን፣ የእርስ በእርስ ግንኙነታችን የሚያስተሳስሩ መድረኮቻችን ላይ ጥቃት ስለደረሰባቸው ነው።

ስለዚህ መፍትሔውም ተመሳሳይ ነው። ያሉትን የልዩነት ግድግዳዎች ማፍረስ። ካሰመርነው ክበብ ውስጥ ደፍሮ ለመውጣት መሞከር። ያን ስናደርግ ተመልሰን እንገናኛለን። ይህ መለያየት እንዲኖር አገራዊ፣ ዓለም አቀፋዊም፣ ግለሰባዊም ምክንያቶች አሉ። በግለሰብ ደረጃ ሲታሰብ ከተማ ውስጥ ሁላችን ሩጫ ላይ መሆናችን፣ ግለኝነት በጣም ትልቅ ቦታ ማግኘቱ፣ እየተሳተፍንባቸው ያሉ የሥራ መስኮች በዋነኛነት ከትብብር ይልቅ ለውድድር ትልቅ ቦታ መስጠታቸው፣ የፈጠርናቸው መድረኮች ውስጥ ያሉ እድሎች ትንሽ መሆናቸውና ያን እድል ለማግኘት በምናደርገው ሩጫ መጠላለፋችን ናቸው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የምንኖርበት ቤት፣ ገብተን የምንወጣበት ሰዓት፣ በፖለቲካ ስናስብ ብዙ ነገርን ከብሔር አንጻር የመመለከት እይታችን ማደጉ የሚጫወተው ሚና አለ። ያለንበትን ቡድን ማድነቅ አንድ ነገር ነው። ግን ያንን ለማድረግ ሌላውን መኮነን አይጠይቅም። እርስ በእርሰ ባለን ግንኙነት ዛሬና ነገ ውስጥ ከማተኮር ይልቅ ትላንትና ውስጥ ረጅም ጊዜ መፍጀታችን። በትላንት የእኛ ጀግኖች ስናነሳ፣ ሌሎች ላይ በደል ያደረሱ እንደሆኑ መዘንጋታችን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

አሁንም የዘገየን መስሎ አይሰማኝም። ለማተካከል ትልቅ መንገድ አለ። ያንን ተስፋ ስላደረግን ነው የተነሳነው። እንቀራረብ፣ እንተዋወቅ፣ እንስማማ፣ ያኔ አንዳችን ሌላችንን የምናሟላ ውበት ነን የሚል ዓይነት ስሜት ይመጣል።

ባልንጀራዬ በእርስዎ የግል ሕይወት ላይ የፈጠረው አዲስ እይታ አለ?
አዎን! ባልንጀራዬ በብዙ መንገድ እይታዬን ቃኝቶታል። የማስብበትን መንገድ ብቻ አይደለም፤ ድርጊቶቼን ጭምር ቃኝቷል። የምፈልገውን ምኞቴንም ጭምር። የባልንጀራዬ አመለካከት ልቤ ውስጥ መስረጽ ከጀመረ በኋላ እኩያነት የምወደው እሴት ሆኗል። ከእኩልነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሲነሱ ብዙዎች ቦታቸውን የሚያስለቅቃቸው ይመስላቸዋልና ይፈራሉ። የእኔ ምኞት ግን ብልጫን መናቅ፣ እኩያነትን ማወደስ ነው። ስለዚህ በእያንዳንዱ ግንኙነት ይህን አስታውሳለሁ።

እንዳልኩት መምህር ነኝ። በክፍል ውስጥ እኔ ብቻ መናገርና መሰማት የለብኝም፤ እነሱም [ተማሪዎቼ] መናገር መሰማት አለባቸው። ከዛ ባሻገር በሰዎች ሕይወት ውስጥ ላደርግ የምችለውን በጎ ነገር ማወቅ። ሆነ ብሎ ለሌሎች በጎነትን ማሳየት ሕይወቴ ውስጥ አድጓል። የማይመስሉኝ ሰፈር መሔድና ሰዎችን ማወቅ ለሕይወቴ ደስታ የሚፈጠር ሆኗል።

ልዩነት ለእኔ ተጨማሪ መዋቢያ መንገድ ሆኗል። ድሮና አሁን የሚባል ነገር አለኝ። በመካከል በሕይወቴ ሆኗል ብዬ የማስበው የእይታ ለውጥ ይመስለኛል።

ባልንጀራዬ እንዲህ ባለ እንቅስቃሴ መንገድ ጠራጊ ነው ማለት ይቻላል ወይስ በዚህ መንገድ የሔዱና አረአያ የሆኗችሁ የምታውቋቸው ተቋማት አሉ?
በተቋም ደረጃ የለም። እኛ የምንሠራውን በቀጥታ የሚሠራ ተቋም አናውቅም። ግን እሴቱ ቢሰርጽ ወደፊት በዚህ ላይ የሚሠራ ይመጣል። በርካታ በጎ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ግን አሉ። ለዛ ነው ወደፊት ቀርጸን ከምናሰራጫቸው መካከል አንዱ በጎ የሠሩትን ማውጣት ነው።

ለምሳሌ ሆነ ብለው ሴተኛ አዳሪዎችን የሚቀጥሩ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን እና ከእስር የወጡትን የሚቀጥሩ አሉ፤ አግባብ በሆነ ክፍያ። እነዚህ ሰዎች ታሪካቸው እንዲነገር ያስፈልጋል። የእኛን [የባልንጀራዬን] እሴት እየኖሩት ነው። የእኛ የሚለየው ዓላማችን ማነሳሳት ነው። ሰው እንዲወርሰው፣ ሥሙ ከእኛ ጋር ተያይዞ ብቻ እንዳይቀር ነው የምንፈልጋው። እኛ ዱላ አቀባይ ተብለን እንድንታሰብ ነው በዚህ በጎ ነገር ወስጥ።

ተጽእኖውን በመገንዘብ በዚህ ላይ የሚሠራ ተቋም ካለና ወደፊትም የሚመጣ ከሆነ ግን በደስታ አብረን ለመሥራት ዝግጁ ነን።

ባልንጀራዬ አሁን ያለው መዋቅር በእንቅስቃሴ ደረጃ ብቻ ነው? ምን ታስቧል?
አሁን እንቅስቃሴ ነው። ወደፊት ሲጠነክር ወደ ተቋምነት ማደጉ አይቀርም። አሁን የበጎ ፈቃደኞች የእርስ በእርስ ትብብር መድረክ ነው።

እንዳሉት መሥራቹ አሜሪካዊ ናቸው። ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች የዚህ እንቅስቃሴ መሥራች መሆናቸው የሚፈጥረው ተጽእኖ የለም?
ባልንጀራነት አካታች እንቅስቀሴ ነው። የሚያገልለው አካል ከሌለ የማያገልለው ቀለምም ጭምር ነው። በእንዲህ ዓይነት መንገድ ያለ አግላይነት የምንታገለው ነውና እንደ ችግር አንቆጥረውም። ኹለተኛ የተለያየን ዓለም ሰዎች በእኩል መንፈስ በአንድ ላይ መሥራታችን ለምናመጣቸው ነገሮች ውበት ፈጥሮልናል፤ እይታን ማስፋት ችሏል። በአንጻሩ ሊሆን የሚችለው አንዱ አለቃ ሌላው ተገፊ ሲሆን ነው። እኔ ረዳት ነኝ እንጂ ምክትል አይደለሁም።
አንዳንዴ እኛ አገር ነጮች ያሉበት ነገር ሁሉ ገንዘብ ያለበት ይመስላል። ባልንጀራዬ እንደዛ አይነት እንቅስቃሴ አይደለም። እንደዛ ሊታሰብ ይችላል የሚል ስጋት አለ። የአገር ውስጥ ዋጋ እና የውጪ የሚባል ነገር ስላለ። ግን በሒደት ታግለን ልንሰብረው እንፈልጋለን።

ሌላው ይህ የጋራ የሆነ፣ ዓለም አቀፍ ስምምነት ያለው አገርኛ መልዕክት ነው። አገርኛ ስንል በውጪ ሐሳብ አይዳብርም ማለት ሳይሆን የእኛን ጊዜና ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ነው። የእኛ አገር የሆነን ብቻ እንይዛለን አይደለም። በጣም አጽንዖት መስጠት የምንፈልገው ሰውን ሁሉ የባልንጀራዬ አምባሳደር ማድረግ ነው። ይህ ማለት ደግሞ እሴቶቹን መናገር አይደለም፤ ንግግር ቀላል ነው፤ መኖር ነው። ሰዎች ይህን አምባሳደርነት ጥሪ ስናቀርብ የተለወጠች አገር ማየት ነው።

ይህን ሁሉ ለመተግር የሰው ኃይልም ያስፈልጋልና እንዴት ነው በጎ ፈቃደኞች አሏችሁ?
በጎ ፈቃደኞች አሉ። ቡድኑ ውስጥ ያለን ሰዎች በብዙ መድረክ የምንተዋወቅ፣ ሰፊ ግንኙነት ያለን ነንና ብዙ ወዳጆች አሉን። በማኅበራዊ ሚድያም ጥሩ ተከታዮች አሉን። ጥሩ ትስስር ያለን ስለሆንንም በምን እንርዳችሁ የሚሉን ብዙ ናቸው። ያላጣነው ነገር ቢኖር መልካም ሰው ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች