ብልጽግና ፓርቲ ስለሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ምን ይላል?

0
1222

በኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከሠለጠኑት አገራት ሳይቀር የቀደመ ታሪክ አለው የሚሉት ቤተልሔም ነጋሽ፣ ተሳትፎውን በየዘመኑ ምን መልክ እንደነበራው በጥቂቱ በማቃኘት ይጀምራሉ። ኢሕአዴግ በአባላት ፓርቲዎቹ ውህደት (ከሕወሓት በቀር) የመሠረተውን ብልጽግና ፓርቲ ረቂቅ መመሪያ ደንብንም ከሴቶች ተሳትፎ አንጻር በመቃኘት ይተቻሉ። ይልቁንም ረቂቁ ከአንዲት ቦታ በቀር ‹ሴቶች› የሚለውን ቃል ያልተጠቀመና ሙሉ በሙሉም በወንድ አንቀጽ የተዘጋጀ ስለመሆኑም ጠቁመውናል።

ላለፉት 28 ዓመታት አገሪቱን ሲመራ የነበረው ኢሕአዴግ ባለፈው ሰሞን በይፋ ግብአተ መሬቱ ተፈጽሟል። በሌላ በኩል አጋር ፓርቲ ተብለው የነበሩ ፓርቲዎችን አካትቶ ሕወሓት ሲቀር ቀደምት አባላቱን ጨምሮ የያዘ አዲስ ፓርቲ ‹ብልጽግና ፓርቲ› ተመሥርቷል። አዲሱ ፓርቲ የሴቶችን ነገር እንዴት አይቶታል? የዛሬ ጽሑፌ ርዕሰ ጉዳይ ነው።

በአገራችን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከሠለጠኑት አገራት ሳይቀር የቀደመ ታሪክ አለው። ተሳትፎው ትርጉም ያለው ተሳትፎ ነበር፤ አልነበረም የሚለው ለክርክር የሚተው ሆኖ፣ እንደ አሜሪካና እንግሊዝ ባሉ አገራት ሳይቀር ሴቶች መምረጥና መመረጥ በሕግ ተከልክለው በነበሩበት ወቅት ሳይቀር፣ በአገራችን ዘመናዊ ምርጫ ጅማሬ ተብሎ በታሪክ የተያዘው የመጀመሪው ፓርላማ የአጼ ኃይለሥላሴ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እየተባለ ይጠራ የነበረው ተቋም ሲመሠረት ጀምሮ ሴቶች ለመሳተፍ ክልከላ አልነበረባቸውም።

ነገር ግን በዚያን ጊዜ በተለይ ለመመረጥ የመኳንንት ዘር ወይም የከበርቴው መደብ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር። ይኸውም እንደ ስንዱ ገብሩ ዓይነት አልበገር ባዮች አልፈውት እስኪሔዱና መጠየቅ እስኪጀምሩ ሰጥቶ የመንሳት ያህል እንጂ ትርጉም ያለው ተሳትፎ የሚያደርጉበት እድል አልነበረም። በዚያን ወቅት በነበረው ፓርላማ ከፈረንሳይ ተቀድቶ የወጣው የወንጀለኛ መቅጫና እንደ ዜግነት ሕግ በፍትሐ ብሔር ሕግ ውስጥ ተካትቶ የነበረው የቤተሰብ ሕግ ሳይቀር በወቅቱ ሴቶች በማኅበረሰባቸው ይሰጣቸው የነበረውን ቦታ ተንተርሰው የወጡ፣ የወንድን የበላይነት ለማስጠበቅ የቆሙ ነበሩ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ሕጎቹ ሳይሻሻሉ ሥራ ላይ ለረጅም ጊዜ ቆይተው ነበር።

በወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ያለ ዕድሜው የተቀጨውና የተጠለፈው መሬት ላራሹ ብሎ በዋነኛነት የዘመተው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ አንዱ ጥያቄ የሴቶች እኩልነት ጥያቄ እንደነበር ከታሪክና ከሰነዶች እንረዳለን። በተደራጀ መልኩ ሴቶች አደባባይ ወጥተው ፖለቲካውን ጨምሮ በሁሉም መስክ የመሳተፍ መብታቸውና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የጠየቁበት የመጀመሪያ ክስተትም ተደርጎ ይጠቀሳል።

በወቅቱ በነበረው አመለካከትና ሴቶችን በአብዮታዊው እንቅስቃሴ ለማሳተፍና ደርግ ባስተዋወቀው አባባል ከ “ድርብ ጭቆና” ለማውጣት በሚል ከአብዩታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር መደራጀት ጨምሮ በወቅቱ የደርግ ፓርቲ የነበረው ኢሠፓ፣ ሴቶች በተለያየ ደረጃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥያቄያቸውም የተመለሰ ለማስመሰል ተሞክሯል። ነገር ግን በተለይ ኢሴማ በርካታ ሴቶችን ማንቀሳቀስ ቢችልም፣ ንቅናቄው በወቅቱ ለነበረው እርስ በእርስ ጦርነት ስንቅ አዘጋጅ ከማድረግና በዓል ሲኖር ሰልፍ ከማሰለፍ ያለፈ አልነበረም።

በአንፃሩ ከ40 በመቶ በላይ የትጥቅ ትግል ዘመን ወታደሮቹ ሴቶች እንደነበሩ የሚነገርለት ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ከ 1983 ጀምሮ ሴቶች ትርጉም ባለው መልክ በአገራቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ቀደም ሲል በማኅበረሰቡ ሰርጾ የነበረው የጾታ ልዩነት ምክንያት ይፈጠር የነበረው የተጠቃሚነት ልዩነትና የአመለካከት ችግር ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ረጅም ጊዜና ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ነው። ቢሆንም ባለፉት 21 ዓመታት በተደረገው ጥረት መሠረታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸው የማይካድ ሀቅ ነው።

አንዱ ይበል የሚያሰኘው ተሳትፎ አብላጫ መቀመጫ በፓርላማ ይዞ የቆየው ኢሕአዴግ በወሰደው ተነሳሽነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35 ለሴቶች ቀደም ሲል የነበረውን ያልተመጣጠነ ተሳትፎና ትኩረት ለማሻሻል የድጋፍ እርምጃን ለሴቶች በደነገገው መሠረት፣ ቢያንስ 30 በመቶ የፓርላማ መቀመጫ በሴት ተመራጮች እንዲያዝ ማድረጉ ነው።

በአሁኑ ወቅት 38.8 በመቶ በሴቶች የተያዙት መቀመጫዎች የዚያ ውጤት ሲሆኑ በአፍሪካ በርካታ ሴቶችን በፓርላማ ካሳተፉ አገራት እንድንሰለፍም አስችለውናል። ነገር ግን በዚህ ገጽም ከዚህ በፊት እንደተገለፀውና በተለያዩ መድረኮችም እንደተነሳው ይህ አበረታች ተሳትፎ እንዲቀጥል የሚያስችል የሕግም ሆነ ተቋማዊ መዋቅር አልተቀመጠም። በተለይ ከኢሕአዴግ መፍረስና አዲስ ፓርቲ መመሥረት ጋር ተያይዞ ይህ ጉዳይ ሥጋት የሚያሳድር ሆኗል።

ቀጣዩ ወራት ለአገራዊ ምርጫ ዝግጅት የምናደርግበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። የምርጫ ሕጉ መሻሻሉ ከእነኝህ ተግባራት አንዱ ሲሆን ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ቀደም ሲል ሴት አባላትና እጩዎች የሚያሳትፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ማበረታታቻ ይሰጣቸው የነበረበት በቀድሞው ምርጫ ሕግ ውስጥ የነበረው አሠራር ተሰርዟል። ኢሕአዴግ ፈርሶ አጋር ፓርቲዎችን ጭምር፣ መላው ኢትዮጵያን ያካተተ ሊባል የሚችል ፓርቲ ተቋቁሟል። አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ ለሴቶች ምን ይዟል የሚለውን ጥያቄ ለመጠየቅም ጊዜው አሁን ይመስላል።

አዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ በድረ-ገፁ ላይ ያስነበበው የፓርቲው ረቂቂ የመተዳደሪያ ደንብ (ምንም እንኳን ጥቅል ቢሆንም እንዲሁም በዝርዝር መመሪያዎች የሚደነግጉት ቢኖርም፣ ፓርቲው አጠቃላይ የሚመራበት ማዕቀፍ መሆኑ ሲታይ ዋነኛ ሰነድ መሆኑ አያጠራጥርም) ስለሴቶች ጉዳይ ያለውን አጠቃላይ እይታ በወፍ በረር ለመቃኘት ብሞክር፤

ጠቅላላ ድንጋጌን ባየበት የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ምዕራፍ አንድ ላይ የቃላት ትርጉም፣ ስያሜ፣ ዓርማ ሲዘረዝር በሌሎች ሕጎች ላይ የተለመደው በወንድ ጾታ የተገለፀው ለሴት ፆታም ያገለግላል የሚለው አባባል አልተቀመጠም። በሌሎች ፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንብ ላይ ይህ ጉዳይ የተቀመጠበትን አግባብ ተመልክቼ ስለማላውቅ አጠንክሬ መናገር ባልችልም፤ እንደ አጠቃላይ አስተያየት ግን እስከመጨረሻው ክፍል በወንድ ጾታ አገባብ የተዘረዘረው ቢያንስ ለትእምርታዊ ዋጋው ይህ ሐረግ መቀመጥ ነበረበት ባይ ነኝ። ካልሆነ የወንዶች ፓርቲ ብቻ ያስመስለዋል።

ይህ ጉዳይ ቀላል ቢመስልም ነገር ግን የሴቶችን ጉዳይ አካታች ሆኖ ለመቅረቡ ማሳያ ነጥብ ነው። የብሔሮችና የቋንቋ ስብጥር ትኩረት የተሰጠውን ያህል ትኩረት እንዳልተሰጠውም አመላካች ነው። አንድ ፓርቲ አባላት ሲመለምል የሚያስቀምጠው መስፈርትና የሚመለምልበት አካሔድ የፓርቲው አባላት የሚኖራቸውን ስብጥር የሚለይ ሲሆን ፆታም የዚህ ስብጥር አንድ መልክ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ የአባላት ምልመላን የተመለከተበት ክፍል የሚከተለው ነው።
ምዕራፍ ኹለት – አባልነት
አንቀጽ 9. የፓርቲው አባል ስለመሆን
ከዚህ በታች የተመለከቱትን መመዘኛዎች የሚያሟላ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የፓርቲው አባል መሆን ይችላል።
ሀ) የፓርቲውን ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ተቀብሎ በጽናት ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ የሆነ፣
ለ) መልካም ሥነ ምግባር ያለውና በኅብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያለው፣
ሐ) በኅብረ ብሔራዊነት እና በአገራዊ አንድነት ላይ ፅኑ አቋም ያለውና ዋልታ ረገጥ አመለካከትና ተግባሮችን በፅናት የሚታገል፣
መ) ዜጎችንና ሕዝቦችን በእኩልነት የሚያገለግል፣ የሕዝብ ጥቅምን የሚያስቀድም፣ ከሙስናና ብልሹ አሰራሮች ራሱን ያራቀና ሌሎችንም የሚታገል፣
ሠ) የፓርቲውን ዕሴቶችና ዓላማዎችን ተቀብሎ የተሰጠውን ኀላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ የሆነ፤
ረ) በፓርቲው መመሪያ መሠረት ወርሃዊ የገንዘብ መዋጮ ለመክፈል ፈቃደኛ የሆነ፤
ሰ) ዕድሜው ዐስራ ስምንት ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ፣
ሸ) የሌላ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ፣
ቀ) የፖለቲካ ድርጅት አባል የመሆን መብቱ በሕግ ያልተገፈፈ፤
በ) በዚህ ደንብ በተወሰነው መሠረት የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ የፓርቲው አባል መሆን ይችላል።
ይላል። በዚህ ዝርዝር መሠረት ሴቶች የፓርቲው አባል እንዲሆኑ ልዩ ማበረታቻ አላደረገም። ከላይ እንደጠቀስኩትም ክፍሉን የሚያብራራው አገላለጽ በሙሉ በወንድ ጾታ የተቀመጠ ነው።

ሴቶችን በሚመለከት ቃሉን ጭምር ለመጀመሪያ ጊዜ የምናየው ምዕራፍ ሦስት የፓርቲው አወቃቀርና አደረጃጀት በሚለው ክፍል ሲሆን፣ እንደ ኢሕአዴግ ሁሉ የሴቶች አደረጃጀት የሚባል ዘርፍ የተካተትበት በመሆኑ ነው።
አንቀጽ 14. የፓርቲ አወቃቀርና የአመራር አካላት
1) የፓርቲው ድርጅታዊ አወቃቀር የአገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ፌዴራላዊ አወቃቀር የተከተለ ነው፣
2) ፓርቲው የሚከተሉት ቋሚ አካላት ይኖሩታል።
ሀ) ብሔራዊ ጉባዔ፣ ለ) ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ሐ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መ) ፕሬዝዳንት ሠ) ምክትል ፕሬዝዳንት
ረ) ማዕከላዊ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን፣ ሰ) የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ሸ) የፓርቲው የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች
ቀ) የፓርቲው የአካባቢ አካላት በ) የሴቶች አደረጃጀት፣ ተ) የወጣቶች አደረጃጀት

ቀጣዩ ምናልባት በእኔ አመለካከት የሴቶች ውክልና አስፈላጊ የሚሆንበት የፓርቲው ውሳኔ ሰጪ ከፍተኛ የበላይ አመራር ወይንም ማዕከላዊ ኮሚቴን በሚመለከት አንቀጽ 17. የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በሚለው ሥር፤
1) የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ጉባኤው ሆኖ በጉባዔዎቹ መሀል ፓርቲውን የሚመራ ከፍተኛ አካል ነው።
2) ማዕከላዊ ኮሚቴው በቀጥታ በነጻና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከጉባዔው አባላት በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ በሚመረጡ አባላት የሚመሰረት ነው፤
3) የማዕከላዊ ኮሚቴው አባላት ብዛትና ስብጥር በጉባዔው ይወሰናል፤ ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ በማዕከላዊ ኮሚቴ ይወጣል፤
እያለ ሲሄድ ለሴቶች የተቀመጠ ኮታ የለም።

አንቀጽ 18. የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሚለው ውስጥም እንዲሁ የሴቶች ተሳትፎ ጨርሶ አልተጠቀሰም። ሌላው በፓርቲው አሠራርና የዕለት ተዕለት ውሳኔ ግብዓት እንዲሆን የሴቶችን አተያይ የተለየ ማኅበራዊኅ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ እንዲካተት እድል ሊሆን የሚችለው አጋጣሚ በፓርቲው መማክርት ጉባኤ ሴቶች ውክልና እንዲኖራቸው ማስቀመጥ ሲሆን ይሄም በመተዳደሪያ ደንቡ አልታየም።

አንቀጽ 50. የፓርቲው አማካሪ የመማክርት ጉባዔ 1) ፓርቲው የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማዎቹን ለማሳካት የተለያየ ሙያ ያላቸው ምሁራኖችና ታዋቂ ግለሰቦችን ያቀፈ የፓርቲው መማክርት ጉባዔ በፕሬዝዳንቱ አቅራቢነት በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቋቋም ይችላል።

በአጠቃላይ ብልጽግና ፓርቲ 54 አንቀጾች ባሉት መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ሴቶች የሚለው ቃል የተገለፀው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ታዲያ ፓርቲው አሁንም ያለ ተቋማዊ ድጋፍ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳየነው የ50-50 የሚኒስትሮች የጾታ ተዋጽኦ በመሪዎቹ ችሮታ ሴቶችን ያሳትፋል ብለን እንጠብቅ?

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here