መነሻ ገጽዜናወቅታዊዓድዋ የጥቁር ሕዝብ የታሪክ ማርሽ ቀያሪ ድል!

ዓድዋ የጥቁር ሕዝብ የታሪክ ማርሽ ቀያሪ ድል!

ከ127 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማንበርከክ፣ አሰፍስፎ የመጣው የጣልያን ወራሪ ጦር ዓድዋ ላይ ድባቅ ተመታ፣ ታሪክም ተቀየረ፡፡ ዓለም ጥቁሮችን የበታች አድርጎ የሚያስብበት ታሪክ በኢትዮጵያ ጀግኖች ተቀልብሶ፣ እነሆ ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ሆነ፡፡

የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያ ለማንበርከክ ቆርጦ የተነሳው፣ ኢትዮጵያ በድርቅ በተመታችበት ወቅት ነበር፡፡ የጣሊያን ጦር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገፋ መምጣቱን ተከትሎ፣ የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ታሪክ የቀየረውን የክተት ዐዋጅ መስከረም 7/1888 በይፋ አወጁ፡፡

የኢጣልያ ጦር እጅግ ዘልቆ ወደ ትግራይ መግባቱን የሰሙት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጦራቸውን ለማንቀሳቀስ ወሰኑ፡፡ የክረምቱ ዝናብ እንዳቆመ መስከረም 7/1888 ባስነገሩት አዋጅ በጥቅምት ወር ወደ ሰሜን እንደሚያቀኑ አስታውቀው፣ ጉልበት ያለው የሸዋ ሰው ጥቅምት ወር ሳያልቅ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 200ኪ.ሜ እርቃ በምትገኘው ወረኢሉ ላይ ተገኝቶ እንዲከት አዘዙ፡፡

ከጎጃም ደምቢያ ቋራ እና በጌምድር የሚንቀሳቀሱት ወታደሮች ጨጨሆ ከተባለው ሥፍራ እንዲሰበሰቡ፣ እንዲሁም ከሰሜን ወልቃይት እና ጠገዴ የሚዘምቱ ወታደሮች ደግሞ መቀሌ እንዲሰበሰቡ ታዘዘ፡፡

የራስ መኮንን ጦር ከሐረር ተጉዞ በጥቅምት መጀመሪያ ሳምንት ከዋናው ጦር ጋር ተቀላቀለ፡፡ የክተት ጥሪው የታወጀው፣ የትጥቅና የስንቅ ዝግጅት የተደረገውም በአዲስ አበባ እንጦጦ ተራራ ላይ በሚገኘው የቀድሞው የንጉሡ ነገሥቱ ቤተ-መንግሥት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እቴጌ ጣይቱ የውጫሌን ውል እንደማይቀበሉ የተናገሩትም በእዚሁ ቤተ-መንግሥት ሆነው ነበር፡፡ ስንቅና ትጥቅ ከተዘጋጀ በኋላ የመጀመሪያዎቹ የመሀል አገር አርበኞች በጥዋት ተሠባስበው ጦርነቱ ወደሚካሄድበት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ጉዞ የጀመሩትም ከዚሁ ቤተ-መንግሥት እንደሆነ ይነገርላቸዋል፡፡

በዘመቻው ወቅት ንጉሠ ነገሥቱና አርበኞች ከተለያዩ የጦር መሣሪያዎች በተጨማሪም ሌሎች ነገሮችን ወደ ቦታው ይዘው መሔዳቸውም ይነገራል፡፡

ለአብነትም በዚሁ ቤተ-መንግሥት አጠገብ ካለችዋ የእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውና በአንድ ወቅት በፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ተመርቆ የተከፈተው ሙዚየም ቤት ውስጥ ያሉ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙትም፣ ንጉሠ ነገስቱና እና ንግሥቲቱ በዓድዋ ዘመቻ ጊዜ ለታቦታቱ ማረፊያና ማስቀደሻ ያሠሩት ድንኳን፣ በእጅ የተጠለፈ የአንድ ግድግዳ መጋረጃ ተቀምጧል፡፡

የዓድዋ ዘመቻ ሲጀመር እና ሠራዊቱ ከአዲስ አበባ ሲነሳ ከተማይቱ የአስር ዓመት እድሜ ብቻ ነበራት፡፡

ዘመቻው ከተጀመረ ከወራት በኋላ በየካቲት 23/1888 የተካሄደውን ጦርነት በተመለከተ በጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ጽሑፍ ላይ እንዲሁ ሠፍሮ ይገኛል፡፡

‹‹ቀኑም ሲነጋ የካቲት 23 ቀን የጊዮርጊስ በዓል ነበር፡፡ ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት ግድም የኢጣሊያ ጦር በድንገት ደረሰ፡፡ 500 ከሚሆኑት በር ከሚጠብቁት ከራስ መንገሻ(ዮሐንስ) ጦር ጋር ገጠመ፡፡

እነዚህም መልሰው ሲዋጉ ኹለት ባሻ ባዙቅ ማረኩና ቢጠይቋቸው ግማሹ የአጼ ምኒልክ ጦር ስንቅ ፍለጋ መሄዱን ስለሰሙ ኢጣሊያኖች በድንገት አደጋ ጥለው ለመዋጋት አራት ዤኔራሎች በአባ ገሪማ በኩል፣ አንደኛው ዤኔራል በማርያም ሼዊቶ በኩል ተሰልፈው ይጓዛሉ ብለው ተናገሩ፡፡

ይኸን ሲሰሙ ከቃፊር ጠባቂዎች አንዱ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ሰፈር እየሮጠ ሲሄድ በመንገድ ቀኛዝማች ታፈሰን አገኘና የያዘውን ወሬ ነገረው፡፡

አጼ ምኒልክም ኢጣሊያኖች ተሰልፈው በጣም ተጠግተው ጦርነቱን ካልዠመሩ በቀር ጦሬን አሰልፌ ኹለተኛ አልወጣም ብለው ስለነበር በከንቱ አሰልፎ ሊያሶጣኝ ሳይሆን ሊዋጋ የመጣ መሆኑን ታምናለህን ብለው ታፈሰን ቢጠይቁት ዛሬስ እርግጥ ነው ብሎ መለሰ፡፡

እቴጌይቱ በዚህ ቀን የሴትነት ባህሪያቸውን ትተው እንደ ወንድ ወታደሮቻቸውን በቀኝና በግራ አሰልፈው ወደ ጦርነት ገቡ፡፡

መድፈኞቻቸውም ከቀኛቸው በኩል ጠምደው እየተኮሱ በመካከል የሚዋጋውን የጠላት ጦር ይመቱት ጀመር፡፡ አቡነ ማቴዎስ የማርያምን ታቦት አስይዘው ከቀሳውስትና ከመነኮሳት ጋር ሆነው የጊዮርጊስን ስብሐተ ፍቅርን እያዜሙ ሲከተሉ ዜማው ሳያልቅ ድሉ ተፈጸመ፡፡

- ይከተሉን -Social Media

የኢትዮጵያም ጦር ከጦርነቱ የሸሸውን የኢጣልያን ጦር የራቀውን በጥይት የቀረበውን በጦርና በጎራዴ እየመታ ፈጀው፡፡››

ጸሐፌ ትዕዛዝ እንደገለጹትም፣ በዕለቱ የሰሌን ቆባቸውን የደፉ ብዙ መነኮሳትም አብረው አርበኞችን ሲያበረቱና ሲያዋጉ ውለዋል፡፡

እቴጌይቱም እንዲሁ ያመነታ ወታደር ሲያዩ ‹‹በርታ! ምን ሆነሀል! ድሉ የእኛ ነው!›› በማለት ያጀግኑት እንደነበር፣ ወታደሩም ኹሉ‹‹ጮማ ላበላኝ ጠጅ ላጠጣኝ ለጌታዬ ለምኒልክ እሞታለሁ›› እያለ ጀብድ ሲፈጽም መዋሉን ጸሐፌ ትዕዛዝ በጹሑፋቸው አስቀምጠዋል፡፡

የጦርነቱን ፍጻሜ ሲገልጹም፣ ‹‹ ዐጼ ምኒልክ ወደ ሠፈር ሲገቡ ጨልሞ ነበር፡፡ ወታደሮቹም ቁስለኛውን በከብት የሞተውን ሬሳ በቃሬዛ አድርገው ወደ ሠፈር መግባት ጀመሩ፡፡  በግራ በኩል ያለው የኢጣልያን ጦር ገና ስላልተሸነፈ በዚያ በኩል ያሉት ጦረኞች እስከ ሌሊቱ አምስት ስድስት ሰዓት ድረስ ሲገድሉ፣ ሲማርኩ ቆይተው በኋላ ተመለሱ›› ይላሉ፡፡

መጨረሻ ላይ ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በዚያ በኋላ ጣልያኖች በጥቁር ተሸነፍን የሚለው ስለሚያሳቅቃቸው የተለያዩ ምክንያቶችን ሲያቀርቡ መኖራቸው ይገለጻል፡፡

እንዲሁም፣ የካቲት 23/1988 ከንጋት ጀምሮ እስከ ዕኩለ ሌሊት በተደረገው ተኩስ ብዙ በውል ያልታወቁ እና በተለያዩ ጸሐፍት ቁጥራቸው ከ4 ሺሕ እስከ 7 ሺሕ የሚደርሱ አርበኞች እንደሞቱ እና 10 ሺሕ የሚደርሱ እንደቆሰሉ በታሪክ ተጽፎ ይገኛል፡፡
እነ ፊታውራሪ ገበየሁን የመሳሰሉ ጀግኖችና ሌሎችም በማለቃቸው በተገኘው ድል ከመኩራት ይልቅ ሐዘን ሆኖ እንደነበርም ይነገራል፡፡

ጸሐፌ ትዕዛዝም ይህን ሲገልጹ ‹‹ ከሰልፍ ላይ ስለቀሩት እጅግ አጥብቆ ሀዘን ሆነ›› ይሉና ስለ ንግሥቲቱ ሐዘን ሲናገሩም ‹‹ብርሃን የመሰለ ፊታቸው አጥላስ (ጥላት) እስኪመስል አለቀሱ›› በማለት አስፍረዋል፡፡

ሆኖም ይህ ኹሉ የደረሰው ዕልቂት ለአገር ነጻነት የተከፈለ ዋጋ በመሆኑ ሐዘኑን ቀለል የሚያደርግ እንደሆነ ይታሰባል፡፡

- ይከተሉን -Social Media

ጸሐፌ ትዕዛዝም ‹‹እንደ ተኩሱ ብዛት፣ እንደ ቀኑ እርዝመት ሰው ሞተ ብሎ ያዘነ የለም፡፡ ባሏም፣ ልጅዋም፣ ወንድሟም የሞተው እንኳን አልጋው ቆመልን ነው እንጂ፣ ባሌ ልጄ ወንድሜ ሞቱብኝ ብሎ ያዘነ የለም›› በማለት የዘመኑ አርበኞች የደረሰውን ጉዳት ከአገራቸው ነጻነት አንጻር እንዴት ቀለል አድርገው እንደገለጹት አሳይተዋል፡፡

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን የነጻነት ጉዳይ ሲሆን፣ ለሌሎች አፍሪካውያን እና በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁሮች ግን እንደ ሠው መቆጠርን ያሳየ መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ብዙ ጥቁሮች ከዚያ ቀድሞ ራሳቸውን እንደ (ነጻ) ሠው ለመቁጠር ይቸገሩ የነበረው ነጭ ቅኝ ገዥዎቻቸው ትክክለኛ የሠው ፍጥረት እኛ ነን በማለት ይሰብኳቸውና ራሳቸውን እንደ ሠው እንዳይቆጥሩ ያስፈራሩዋቸው ስለነበር ነው የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡ በዚህም ኢትዮዮጵያ ከነጭ ወራሪ ጋር ጦርነት ለማድረግ ማቀዷ ሳይቀር ያስደንቃቸው ነበር፡፡

ነጮችም ቢሆኑ በጥቁር መሸነፋቸው ከሚያሳቅቃቸው በላይ፣ ሌሎች ጥቁሮችን ለአመጽ ሊያነሳሳ ይችላል በሚል በቅኝ ግዛት አስተዳደራቸው ላይ ችግር ይፈጥርብናል በማለት ፍርሀት አድሮባቸው እንደነበር ተጽፏል፡፡

የፈሩት ደርሶም ጥቁሮች በጦርነቱም ወቅት ኢትዮዮጵያ የነጭ ወታደር ገድላ እና ማርካ ነጻና ሉዓላዊት አገር መሆኗን ሲያዩ፣ በመላው ዓለም ያሉ ጥቁሮች እሷን አብነት በማድረግ ሠው መሆናቸውን ከመቁጠር ባለፈ ለነጻነታቸው መታገል እንደጀመሩ ታሪክ ያወሳል፡፡

ከኹለት መቶ ዓመት በላይ በቅኝ ግዛት ከኖሩት ደቡብ አፍሪካውያን የተገኙት ኔልሰን ማንዴላም፣ ለነጻነት ትግል እንቅስቃሴያቸው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሱዳን በደረሱ ጊዜ ካዩት ነገር እጅግ ያስገረማቸው ጥቁር አውሮፕላን አብራሪ ኢትዮጵያውያንን ማየታቸው እንደሆነ በወቅቱ ገልጸው እንደነበር ይነገራል፡፡

እንዲሁም፣ከዓድዋ ድል በኋላ በርካታ የአፍሪካ አገራትም የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ቀለማትን በተለያየ መልኩ መጠቀማቸው የድሉ ውጤት መሆኑን ታሪክ አዋቂዎች ያስረዳሉ፡፡

ስለዓድዋ ድል ትልቅነት የሚናገሩ ምሁራን የካቲት 23/1888 ሰውን እንደልኩ፣ እንደዓመሉ፣ እንደኩራቱ በነጻነት የሚያኖር ድል፣ ለጥቁር ህዝቦች ሌላ መወለድ ለዓለም ዳግሞ እንግዳ ክስተት ተፈጸመ ይላሉ፡፡

- ይከተሉን -Social Media

በጦርነቱ ወቅት ከኢጣሊያ የተማረኩ እጅግ በርካታ መድፎች በምኒልክ ቤተመንግሥት ከሰዓት ማማ ስር ተደርድረው ለህዝብ ሲታዩ ነበር፡፡

በድሉ ወቅቱ አጼ ምንልክ የአገሪቱ ጦር አዝማች/መሪ መሆናቸው ይወሳል፡፡ የዓድዋ ድል ንጉሠ ነገሥቱን ታላቅነት የሚያሳይ እንደሆነ የሚታመን ሲሆን፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ እጅግ በሳል አካሄዶችን ይከተሉ እንደነበርም ይነገርላቸዋል፡፡

‹‹ዐጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚለው መጸሐፋቸው ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ይህን ሐሳብ ሲያጠናክሩም፣ ንጉሡ የክርስትያን ደም በከንቱ አይፍሰስ፤ ጦርነት አይበጀንም እያሉ ጣሊያንን ያዘናጉ ነበር ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ይህን ስልት የተጠቀሙትም በቂ የጦር መሣሪያ ለማከማቸት፣ ከራሷ ከጣሊያን የነበረባቸውን አንድ ሚሊዮን የማሪያ ትሬዛ ብድር ለመክፈል እና በደቡብ ያለውን ግዛታቸውን ለማስፋፋት በተለይም አስቸግሮ የነበረውን የወላይታን ገዥ ጦናን ልክ ለማስገባት ነበር ይላሉ ተክለ ጻድቅ በሐተታቸው፡፡

ይህ ኹሉ የንጉሠ ነገሥቱን የላቀ የመሪነት ብቃት እና ለአገራቸው ነጻነት የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ በመሆኑ የዓድዋ ድል በሚታሠብበት ዘመን ኹሉ ዳግማዊ አጼ ምኒልክን አለማንሳት እንደማይቻል ማሳያ ነው፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝብ ብሔራዊ ኩራት ማህተም ይሆን ዘንድ ንግሥተ ነገሥት እቴጌ ጣይቱ ከጦር እቅድ አመንጭነት ጀምሮ በጦር ሜዳ የነበራቸው ሚና እጅግ ግዙፍና የከበረ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

በዓድዋ ጦርነት ወቅት ከነበሩ ታላላቅ የጦር ጀኔራሎች መካከል የጎጃሙ ንጉስ ተክለኃይማኖት፣ ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ እና አባተ ቧያለው ይገኙበታል፡፡

የዓድዋ ድል የተከበረው ከሰባት ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ ይህም አጼ ምኒልክ ምንም እንኳን ድሉ የእኔ ቢሆንም ይህ ኹሉ ህዝብ አልቆ ደስታ የለም በማለታቸው ነው፡፡

ከጦርነቱ በኋላ ኢጣሊያ ወዲያው ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ከፈተች፡፡ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክም በአዲስ አበባ የተከፈተውን የኢጣሊያን ኤምባሲ በአካል ተገኝተው ጎበኝተዋል፡፡

ከአፍሪካ አገራት የድል እንጂ የነጻነት በዓል የማታከብር ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡

አሜሪካ የአጼ ምኒልክን የጦር ስልት በተለይም አስደናቂውን የክተት አዋጅ በጦር ስርዓተ ትምህርት በማካተት በወታደራዊ ትምህርት ቤቶች  ትሰጣለች፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ እስላም ክርስትያን፣ ወንድ ሴት፣ ንጉስና ባሪያ ሳይባባል ከአራቱም መዓዘን ኹሉም ለአገሩ ነጻነት በፍፁም ጀግንነት እንዲሰለፍ ያደረገው የንጉሠ ነገሥቱ የክተት አዋጁ በጦር ጠበብቶች ዘንድ እጅግ ትልቅ ቦታ አለው፡፡

እጅጋየሁ ሽባባው ስለዓድዋ ድል በተጫዎተችው ዘፈኗ ‹‹በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፤ በክብር ይሄዳል ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ›› ስትል የክተት አዋጁ ምን እንደሚመስል ትጠቅሳለች፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ትውልድ ዘንድ የዓድዋ ድል በሚገባው ልክ እየተከበረ እንዳልሆነ ይነሳል፡፡

መንግስት ለድል በዓሉ የሰጠው ትኩረት እናሳ መሆኑን የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዓሉ በየዓመቱ የጭቅጭቅ መንስኤ ሲሆንም ይስተዋላል፡፡

ለአብነት ዘንድሮ ለ127ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓድዋ ድልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ በተለይ የአጼ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱን ምስል የያዘ ቲሸርት ማሳተም በፖሊስ እንደተከለከለ፣ እንዲሁም የንጉሡን እና የንግሥቲቷን ምስል የያዘ ቲሸርት ለብሰው የተገኙ ሰዎች ለእስር መዳጋቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች