ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራውና በመንግሥት “ሸኔ” ተብሎ በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የካቲት 10/2013 ለክልሉ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ በኦሮሚያ ክልል ለሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን የእርቅ ጥሪ አቅርበዋል። ታጣቂ ቡድኑ “የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” አቋም ብሎ ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በሰለጠነ ንግግር በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደው ጦርነት እልባት እንዲያገኝ የሚጠይቅ ማንኛውም ጥሪ መልካም ዜና መሆኑን የገለጸው ቡድኑ፣ ለቀረበው የሰላም ጥሪ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል፡፡ ለቀረበው የሰላም ጥሪ ባስቀመጠው ቅድመ ሁኔታም፣ ውጤታማ የሰላም አማራጭ ለመከተል ወይም ለመደራድር የሰላም ሂደቱ ገለልተኛ በሆነ ሦስተኛ ወገን መከናወን እንዳለበት ገልጿል፡፡
ትርጉም ያለው የሰላም ሂደት ለመፍጠር የቡድኑ አዛዦች እና ተደራዳሪዎች ከግጭት ቀጠናዎች መውጣት እና መግባት አለባቸውም ብሏል። ለዚህም አስፈላጊዎቹ የደህንነት ዋስትናዎች እና ሎጅስቲክስ ሊገኙ የሚችሉት በአለም ዓቀፍ ደረጃ ብቻ ነው ሲል ቡድኑ ይፋ አድርጓል።
ውጤታማ የስላም ሂደት ለመፍጠር የድርድር ሂደቱ ገለልተኛ በሆነ ሦስተኛ ወገን መመራት እንዳለበት ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው ቡድኑ፣ ከዚህ ውጪ የሚሞከር የሰላም ጥረት በኦሮሚያ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ኤርትራ ላይ እንደተደረገው የከሸፈ ስምምነት ከመሆን አይዘልም ብሏል፡፡
ቡድኑን በአሸባሪነት የተፈረጅኩት በፌደራል መንግሥት ፓርላማ በመሆኑ፣ የሚኖረኝ የሰላም ሂደት በፌዴራል መንግሥት መመራት አለበት ብሏል፡፡ ከቡድኑ ጋር ወታደራዊ ትግል ውስጥ የገባው የፌደራል ሰራዊት እንጂ የክልል ኃይሎች አይደሉም ተብሏል፡፡
በቀረበው ጥሪ መሰረት የሰላም ስምምነት ላይ የሚደረስ ከሆነ፣ ለተፈጻሚነቱ ዋስትና ሊሆኑ የሚችሉት ዓለም አቀፍ ተዋናዮች ብቻ ናቸው ያለው ቡድኑ፤ ይሁን እንጂ በአለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ተግባራዊነቱን ማረጋገጥ የሚችሉት በጣት የሚቆጠሩ አካላት ብቻ ብቻ መሆናቸውን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ በፊትም መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሰላም ጥሪዎችን በተደጋጋሚ ማድረጉንም በመግለጽ፤ የአሁኑ ጥሪ በቅርጽም ሆነ በይዘቱ አዲስ አይደለም፣ በቀደሙት ጥሪዎች ላይም ብዙ አልጨመረም ያለው ቡድኑ በቀጣዮቹ ቀናት ሊወጡ የሚችሉ ዝርዝሮችን እየጠበቀ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ የተፈጠረውን ግጭት አሳሳቢነት ተከትሎ፣ የአገር ውስጥ አሸማጋዮች ያቀረቡትን ጥሪ ታጣቂ ቡድኑ ውድቅ ማድረጉን አስታውሷል፡፡
በአገሪቱ ባለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ገለልተኛ የአገር ውስጥ አስታራቂ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ምንም እንኳን እንደ እድል ሆኖ ገለልተኛ አቀራራቢ አካል ቢገኝ፣ ማንኛውም የአገር ውስጥ አካል በገለልተኛነት እንዲሰራ ከመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ ይሆናል ብሎማ እንደማያምን ቡድኑ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን ጦርነት ለመፍታት ከልቡ ፈቃደኛ ከሆነ፣ ተገቢውን አገራዊና ዓለም አቀፋዊ አሠራር ለመከተል መስማማት አለበት ተብሏል።
ቡድኑ በክልሉ በስፋት የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የትጥቅ ትግል ከጀመረ በኋላ በርካታ ንጹሀን ዜጎችን መግደሉ በየጊዜው ሲገለጸ ቆይቷል፡፡