በሰሜን ጎንደር ዞን በጦርነት ከወደሙት 207 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ማስተማር የጀመሩት16ቱ ብቻ መሆናቸው ተገለጸ

0
784

አርብ ኀዳር 9 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ውስጥ በጦርነት ከወደሙት 207 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ማስተማር የጀመሩት 16 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸው ተገልጿል።

ወረራ በተፈጸመባቸው የዞኑ አምስት ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ኹሉም ትምህርት ቤቶች ዘረፋ እና ውድመት እንደተፈጸመባቸው ነው የተነገረው።

አድርቃይ ወረዳ ወረራ ከተፈጸመባቸው ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 72 ትምህርት ቤቶች ነበሩት። የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አረጉ ጆርጌ በወረዳው የሚገኙ ኹሉም ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን ጠቅሰዋል። በወረዳው የሚገኙ 28 ሺሕ 536 ተማሪዎች እና 1 ሺሕ 300 መምህራን ለ16 ወራት ከትምህርት ቤት ውጭ ቆይተዋል ብለዋል።

ሀላፊው አዲርቃይ ወረዳ ከወረራ ነፃ ከወጣ ጀምሮ በወረራ ምክንያት የተበላሹትን ትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ የማጽዳት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። ወረዳው ከወረራ ነጻ ከወጣ ጀምሮ እስካሁን 13 ትምህርት ቤቶች ብቻ በከፊል ትምህርት የጀመሩ ሲሆን ቀሪዎችን ለማስጀመር ግን ከወረዳው አቅም በላይ እንደሆነ አረጉ ተናግረዋል ።

በተለይም አገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱትን የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች በቅድሚያ ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከሌሎች የአገሪቱ ተማሪዎች ጋር እኩል ውድድር የሚጠብቃቸው ቢሆንም ከ14 ወራት በላይ ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው የአካባቢውን ተማሪዎች የስነ ልቦና ጫና ውስጥ እንዳስገባቸውም ገልጸዋል።

ሀላፊው እስካሁን ድረስ ለትምህርት ዘርፉ የተደረገ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ድጋፍ እንደሌለም ገልጸዋል። በቀጣይ መንግሥት እና ረጂ ድርጅቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝበው አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርጉ ከሆነ ኹሉንም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መመለስ እንደሚቻል ገልጸዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ አጸደ በሬ በበኩላቸው፤ በዞኑ በጦርነት የወደሙ የትምህርት ቁሳቁሶች አለመተካታቸው ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ እንቅፋት መኾኑን ተናግረዋል። የደረሰውን ውድመት በጥናት በመለየት ትምህርት ለመጀመር የሚያስችል ድጋፍ ለማግኘት በንቅናቄ እየተሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

አጸደ፤ ወረራ በተፈጸመባቸው አምስት ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ የገለጹም ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶች ጥገና እና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸው መደበኛ ትምህርት ለማስቀጠል በዞኑ ብቻ አቅም የማይቻል በመሆኑ የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት አፋጣኝ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ሀሳባቸውን መስጠታቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ከመንግሥት ድጋፍ ጎን ለጎንም ረጂ ድርጅቶች፣ ተቋማት እና ባለሃብቶች የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ በመገንባት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ አጋርነታቸውን ማሳየት አለባቸው ሲሉም ምክትል ሀላፊዋ መልዕክት አስተላልፈዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here