ኢትዮጵያ በሦስት ወራት ለነዳጅ ግዢ 77 ቢሊዮን ብር ማውጣቷ ተገለጸ

0
1420

ከ2014 ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር በ35 ቢሊዮን ብር ጨምሯል

ኢትዮጵያ በ2015 የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት ለነዳጅ ግዢ 77.8 ቢሊዮን ብር ማውጣቷን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት 1 ሚሊዮን 5 ሺሕ 490 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ለመግዛት 77.85 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዓለማየሁ ጸጋዬ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በዚህም ድርጅቱ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ካቀደው የነዳጅ ምርት 94 በመቶውን ማስገባት እንደቻለ የተናገሩት ዓለማየሁ፣ ይህም ከ2014 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ7 ሺሕ 698 ሜትሪክ ቶን ወይም የ0.77 በመቶ እድገት እንዳሳየ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት ለነዳጅ ግዢ ወጪ የተደረገው 77.85 ቢሊዮን ብር በ2014 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 997 ሺሕ 792 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ለመግዛት ወጪ ከተደረገው 42.71 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር የ35.14 ቢሊዮን ብር ልዩነት ያለው ሲሆን፣ ይህም በዓለም ዐቀፍ የነዳጅ ዋጋ መናር፣ የውጭ ምንዛሬ እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የመጣ ከፍተኛ ጭማሪ እንደሆነ ዓለማየሁ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ እኤአ 2020/21 በጀት ዓመት 3.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ለመግዛት 72.6 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጋለች። እንዲሁም በ2019/20 በጀት ዓመት 3.9 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ለመግዛት 62.1 ቢሊዮን ብር አውጥታለች። ባለፉት ሦስት ወራት ለነዳጅ ግዢ የወጣው ገንዘብ ካለፉት ኹለት ዓመታት ጋር ሲነጻጻር ከፍተኛ ልዩነት ዐሳይቷል።

በሦስት ወራት ውስጥ ወደ አገር ውስጥ ከገባው ነዳጅ መካከል ነጭ ናፍጣ የ673 ሺሕ 429 ሜትሪክ ቶን ድርሻ በመያዝ ከፍተኛው ሲሆን፣ ቤንዚን ደግሞ የ178 ሺሕ 448 ሜትሪክ ቶን ድርሻ ይዟል።

የከባድ ጥቁር ናፍጣ እንዲሁም የቀላል ጥቁር ናፍጣ የአገር ውስጥ መሸጫ ዋጋ ከሌሎች የነዳጅ ምርቶች አንጻር ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት ዓለማየሁ፣ የምርቶቹ ተጠቃሚዎች የነበሩ ኢንዱስትሪዎች በአብዛኛው የሚጠቀሙትን ምርት ወደ ነጭ ናፍጣ እንደቀየሩ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት በአገር ውስጥ ያለው የጥቁር ናፍጣ ክምችት በቂ ሆኖ ስለተገኘ ቀላል ጥቁር ናፍጣ ከታቀደው 62 በመቶ እንዲሁም ከባድ ጥቁር ናፍጣ ከታቀደው 13 በመቶ ብቻ ግዢ እንደተፈጸመ ገልጸዋል።

ቤንዚንና ነጭ ናፍጣ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ከታቀደው እንደየቅደም ተከተከላቸው 93 እንዲሁም 97 በመቶ ገቢ የተደረገ ሲሆን፣ ለመጠኑ ማነስም ከነዳጅ ሻጮች ጋር ያለው ውል ለግዢ ከተስማሙበት የነዳጅ መጠን እስከ 10 በመቶ ከፍና ዝቅ በማድረግ መገበያየት እንደሚቻል በመቀመጡ መሠረት መሆኑን ዓለማየሁ ገልጸዋል።

መንግሥት ከሰኔ 29/2014 ጀምሮ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ብቻ ተጠቃሚ እንዲያደርግ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ በጊዜ ሂደትም መንግሥት በነዳጅ ላይ የሚያደርገውን ድጎማ ሙሉ በሙሉ እንደሚያነሳም ማሳወቁ ይታወሳል።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here