መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅአዲስ ማለዳ ወደ ዲጂታል ሚዲያ ተሸጋገረች

አዲስ ማለዳ ወደ ዲጂታል ሚዲያ ተሸጋገረች

እንሆ አዲስ ማለዳ የመጀመሪያዋን የህትመት ብርሃን ካየች 210 ሳምንታት ተቆጠሩ፣ በነዚህ ጊዜዎች ጋዜጣዋ ዜጎችን በመረጃ ለማበልፀግ የቻለችውን ሁሉ ጥረት አድርጋለች፡፡ በዚህም ጋዜጣዋ አንድም ጊዜ ህትመቷን ሳታቋርጥ ለአንባብያን የደረሰች ሲሆን፣ ከአንድ አመት በላይ ደግሞ በቤተሰብና በማኅበራዊ ለውጥ ላይ የሚያተኩር መጽሄት ስታሳትም ቆይታለች፡፡

በነዚህ አራት አመታት፣ አዲስ ማለዳ በምትስራቸው ታዓማኒ፣ የትም ያልተሰሙና አነጋጋሪ ዜናዎቿ ምክንያት ከዜጎች አልፋ የበርካታ መገናኛ ብዙኋን የዜና ምንጭ ሆና ቆይታለች፡፡ ጋዜጣዋ በቻለችው መጠን ሃቀኛ የዜጎች ድምጽ ለመሆን ጥረት አድርጋለች፣ ለዚህም ከአማርኛ በተጨማሪ በአፋን ኦሮሞና አፍ ሶማሊ ቋንቋዎች መረጃዎችን በስፋት ለህዝብ በማድረስ ጥሩ ጅምር አሳይታለች፡፡አዲስ ማለዳ ዘወትር ቅዳሜ በጋዜጣ ከምታትመው በተጨማሪ በማኅበራዊ ትስስር ገፆቿ ወደ 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ) የሚደርሱ አንባቢዎችን ያፈራችን ሚዲያ ናት፡፡

ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ ህትመት ሥትጀምር ብር 6:27 (ስድስት ብር ከሃያ ሰባት ሳንቲም) የነበረው የአንድ ጋዜጣ ህትመት ዋጋ፣ በአሁኑ ሰዓት ከአምስት እጥፍ በላይ (551%) በማደግ ብር 34.85 (ሰላሳ አራት ብር ከሰማንያ አምስት ሳንቲም) ደርሷል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት እንኳን የጋዜጣው የህትመት ዋጋ ከ80% በላይ የጨመረ ሲሆን፣ ይህም በአሳታሚው ድርጅት ላይ ከፍተኛ ጫናን ፈጥሯል፡፡

በሃገራችን ካለው ወቅታዊ የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና አጠቃላይ የንግድና ኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ አንፃር ይህ የህትመት ዋጋ ጭማሬ በምን ያህል ፍጥነት የት እንደሚደርስ እርግጠኛ መሆን ካለመቻላችንም ባሻገር፣ በርካታ ኩባንያዎች የድርጅቶቻቸውን ምርትና አገልግሎት ለማስተዋወቅ ከፍተኛ የአቅም ውስንነት እና የፍላጎት ማጣት ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ አይተናል፡፡ በዚህም ምክንያት በአንድ በኩል የገቢ መቀነስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በከፍተኛ ፍጥነት የወጪ መጨመር ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ይህም ድርጅታችንን በተወሰነ መልኩ ጫና ውስጥ ከቶታል፡፡

የኅትመት ዋጋ በዚህ ልክ መናር ከአዲስ ማለዳ አቅም በላይ በመሆኑ ከዛሬ ጀምሮ የአዲስ ማለዳን ህትመት በማቆም፣ ሙሉ ትኩረታችንን ወደ አዲሱ ትውልድ ሚዲያ (New Media) ለማድረግ የጋዜጣዋ አሳታሚ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በተሻለ አሰራር፣ አስተማሪ፣ አዝናኝና ቁም ነገር አስጨባጭ በሆኑ የዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ለመምጣት ዝግጅታችንን ወደማገባደዱ ደርሰናል፡፡ ለዚህም ይረዳን ዘንድ ከስድስት ወር በፊት የጀመርነውን የስቱዲዮ ግንባታ ያጠናቀቅን፣ የተለያዩ የስቱዲዮ መሳሪያዎችንም ከውጭ ያስገባን ሲሆን፣ ዘርፉ የሚጠይቀውን የሰው ኃይልም በማዘጋጀት ሂደት ላይ መሆናችንን ለክቡራን የአዲስ ማለዳ ቤተሰቦች ማሳወቅ እንወዳለን፡፡

ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ፣ አዲስ ማለዳ የተሟላ የበይነ-መረብ ቴሌቪዥን (Internet TV)  ሆና አገልግሎቷን በአዲስ መልክ ለመጀመር የሚያስችላትን ሙሉ ዝግጅት ወደማጠናቀቅ የተቃረብን ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ ካሁን በፊት ታደርገው እንደነበረ፣ በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞና አፍ ሶማሊ መደበኛ ስራዎቿን ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ትቀጥላለች፡፡

ባለፉት አራት አመታት አብራችሁን የቆያችሁ የጋዜጣዋ ቤተሰቦች፣ አንባቢያን፣ ምርትና አገልግሎታችሁን በጋዜጣዋ ያስነገራችሁ ድርጅቶች፣ የተለያዩ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ ስታደርጉልን የቆያችሁ አጋሮቻችንነበሙሉ፣ ስለነበረን ቆይታ ከልብ እያመሰገንን ከአዲስ ማለዳ ጋር በአዲሱ ሥራዋም አብራችሁን እንደምትሆኑ በዚህ አጋጣሚ ያለንን መተማመን እንገልፃለን፡፡


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች