አማራ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

0
923

የአማራ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ለአዲስ ማለዳ በላከው ሪፖርት እንደገለጸው፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመቱ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፉ ከሰባት ሺሕ ቶን በላይ ምርት ወደ ውጭ በመላክ ከ19 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። በግብርና፣ አበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም በዕፀ-ጣዕም ደግሞ ከአንድ ሺሕ ቶን በላይ ምርት ወደ ውጭ በመላክ ከ8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የሚልቅ ገቢ መገኘቱን ነው የገለጸው።

በዚህም በአጠቃላይ በኹሉም ዘርፍ ከስምንት ሺሕ ቶን በላይ ምርት ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ከ28 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር የሚበልጥ (ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ) ገቢ እንደተገኘ ተመላክቷል።

ገቢው ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ከ24 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር በላይ (ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ) ብልጫ አለው ነው የተባለው። ምንም እንኳ ክልሉ በጦርነት ቀጠና አካባቢ የቆየ ቢሆንም፣ በተለይ የአገር ውስጥ ባለሀብቱ የኢንቨስትመንት ፍሰት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲልም ቢሮው አክሏል።

በዚህም 2 ሺሕ 165 ባለሀብቶች በ2012፣ 3 ሺሕ 227 ባለሀብቶች በ2013፣ እንዲሁም በባለፈው በጀት ዓመት 2 ሺሕ 872 ባለሀብቶች ፈቃድ መውሰዳቸውን ለማወቅ ተችሏል። በዘንድሮው 2015 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ደግሞ 131 ነጥብ 49 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 1 ሺሕ 180 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማውጣታቸው ተመላክቷል።

ይህ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ870 ባለሀብቶች ብልጫ አለው ነው የተባለው።

ባለሀብቶች ፈቃድ ያወጡባቸው ዋና ዋና ዘርፎችን በተመለከተ፣ 558 ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ 164 ባለሀብቶች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ እንዲሁም 141 ባለሀብቶች በግብርና ዘርፍ ቀሪ 317 ባለሀብቶች ደግሞ በሌሎች ልዩ ልዩ ዘርፎች ማለትም በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና የአገልግሎት ዘርፎች (ጤና፣ ትምህርት፣ በመኖሪያ ቤት ልማት፣ በማሽን ኪራይ …) ፈቃድ ያወጡ መሆናቸው ተገልጿል።

ሆኖም የክልሉ ኢንቨስትመንት ዘርፉ በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ የኃይል አቅርቦት ችግር፣ የብድርና ውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የግንባታ ቁሳቁሶች ግብዓት እጥረት (ሲሚንቶና ብረት) እንዲሁም መሬት የወሰዱ ባለሀብቶች ፈጥነው ወደ ሥራ አለመግባት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል።

በበጀት ዓመቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ300 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ሊፈጥሩ የሚችሉ 3 ሺሕ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲያወጡ ለማድረግ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከ32 ሺሕ ቶን ምርት በላይ ወደ ውጭ በመላክ ከ260 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅድ መያዙንም ቢሮው አመላክቷል።

በግብርናው፣ በአበባ አትክልትና ፍራፍሬ እና ዕፀ ጣዕም ዘርፎች ደግሞ ከ10 ሺሕ ቶን በላይ ለመላክ፣ በአጠቃላይ ከ43 ሺሕ ቶን ምርት በላይ ወደ ውጭ በመላክ ከ307 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ከዘርፉ ለማስገኘት ዕቅድ መያዙ ነው የተገለጸው።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here