በህትመት ምክንያት አገልግሎቱ ቆሞ በመቆየቱ በታቀደው መሠረት ሥራውን ማከናወን እንዳልቻለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ በላከው መረጃ አስታውቋል።
ከተቋሙ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው የልደት፤ የጋብቻ፤ የፍቺ፤ የሞት እንዲሁም የጉዲፈቻ ምዝገባና እና መረጃ አሰጣጥ አገልግሎት በህትመት ምክንያት አፈጻጸሙ ከታቀደው በታች ነው።
ኤጀንሲው በጥቅምት ወር 2015 የወሳኝ ኩነት ምዝገባን ከማሳደግ አንጻር ለ35 ሺሕ 404 የልደት ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ ያከናወነው 9 ሺሕ 354 ሲሆን፤ አፈጻጸሙም 26 ነጥብ 42 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።
እንዲሁም፤ ለ2 ሺሕ 232 ሰዎች በዘገየ ልደት ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ክንውን 491፤ አፈጻጸም ደግሞ 22 በመቶ ሲሆን ለ26 ሺሕ 707 ጊዜ ገደቡ ያለፈ ልደት ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ቢታቀድም ክንውኑ 7 ሺሕ 897 ነው።
በህትመት ምክንያት አገልግሎቱ በመቆሙ የጋብቻ ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት አሰጣጥ ክንውን ዝቅተኛ መሆኑንም ሪፖርቱ ያሳያል። ለ5 ሺሕ 433 የጋብቻ ምዝገባ እና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ክንውኑ 1 ሺሕ 252 በመሆኑ አፈጻጸሙ 23 በመቶ ሲሆን፤ ለ374 በዘገየ የጋብቻ ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ቢታቀድም የተከናወነው ግን 119 ብቻ ነው ተብሏል።
እንዲሁም ለ1 ሺሕ 504 የጊዜ ገደቡ ያለፈ የጋብቻ ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ክንውኑ 565 ይህም 37 ነጥብ 57 በመቶ መሆኑን የተቋሙ መረጃ ያመላክታል።
ለ964 የፍቺ ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ቢታቀድም፣ በህትመት አገልግሎት መቆም ምክንያት የተከናወነው 89 ብቻ ሲሆን፤ አፈጻጸሙ 9 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑ ተጠቅሷል። እንዲሁም፤ ለ198 በዘገየ የፍች ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ክንውኑ 26 እና ለ119 የጊዜ ገደቡ ባለፈ ፍች ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ክንውን 42 ነው ተብሏል።
ሌላው በህትመት መቆም ምክንያት ዝቅተኛ ሆኖ የተመዘገበው ክንውን የሞት ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት አሰጣጥ ሲሆን፤ ይኸውም ለ3 ሺሕ 631 የሞት ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ክንውን 476 በመሆኑ በመቶኛ አፈጻጸሙ 13 ነጥብ 11 በመቶ ብቻ መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል።
ተቋሙ በጥቅምት ወር 2015፣ ለ893 በዘገየ የሞት ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ቢያቅድም ከዕቅዱ 159 ብቻ በማከናወኑ አፈጻጸም 17 ነጥብ 81 በመቶ ነው ተብሏል።
እንዲሁም ለ29 የጉዲፈቻ ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ የህትመት አገልግሎት ቆሞ በመቆየቱ ምክንያት ክንውኑ 3፤ አፈጻጸም ደግሞ 10 ነጥብ 34 በመቶ ብቻ በመሆኑ ዝቅተኛ ክንውን ነው ተብሏል።
አገልግሎቱን ማዘመን (ዲጂታላይዝ ማድረግ) ሲቻል ህትመት ላይ ማተኮር ለምን አስፈለገ ለሚለው ጥያቄም አሰራሩን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ተቋሙ የኔትወርክ አገልግሎት ለማግኘት በሂደት ላይ ስለሆነ መሆኑን የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አማካሪ መላክ መኮነን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በተቋሙ ብዙ የተስተጓጎሉ አገልግሎቶች አሉ ያሉት አማካሪው፤ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ቢያንስ ከጥር በኋላ የተሻለ አገልግሎት እንደሚኖርም ጠቁመዋል።
ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015