መነሻ ገጽዜናወፍ በረር ዜናኅብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር ኅብር ኢ-ኮሜርስ የተሰኘ የአሌክትሮኒክ ክፍያ አገልግሎት...

ኅብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር ኅብር ኢ-ኮሜርስ የተሰኘ የአሌክትሮኒክ ክፍያ አገልግሎት ጀመረ

ኅብረት ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ የመጀመሪያ የሆነውን ኅብር ኢ-ኮሜርስ የተሰኘና በኢትዮጵያ የሚሠሩ የንግድ ድርጅቶች በኦንላይን ለሸጡት እቃ ክፍያ በዓለም ዐቀፍ የካርድ ክፍያ መንገዶች መቀበል የሚያስችላቸውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ አስተዋወቀ።

በማስተር ካርድ የክፍያ ጌትዌይ የሚሠራው ኅብር ኢ-ኮሜርስ በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ኦንላይን ለዓለም ዐቀፍ ደንበኞች እንዲሸጡና አዳዲስ ደንበኞችንም እንዲያገኙ ያስችላል ነው የተባለው።

ይህ ሥርዓት የአገር ውስጥ ንግዶች አዳዲስ ዓለም ዐቀፍ ገበያዎችን ማግኘት እንዲችሉና ገቢያቸው እንዲያድግ ብሎም ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚው ገበያ እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

በማስተር ካርድ የክፍያ ጌትዌይ አማካኝነት የሚሠራው ኅብር ኢ-ኮሜርስ በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ ተቋማትና ነጋዴዎች በማስተር ካርድና በሌሎች ዓለም ዐቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ካርዶች ክፍያ ከኢትዮጵያ ውጭ ካሉ ደንበኞች መቀበል እንዲችሉ የሚያግዝ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ኅብር ኢኮሜርስ ሻጮች ለሸጡት ምርት ክፍያቸውን በውጭ ምንዛሬ ያለምንም እንግልትና መዘግየት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን፣ የክፍያ ሥርዓቱ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲያድግም አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።

ኅብረት ባንክና ማስተር ካርድ በትብብር ያስተዋወቁት የኢ-ኮሜርስ አገልግሎት ለደንበኞች ደኅንነቱ የተጠበቀ የ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል፣ ባንኩም የደንበኞችን ፍላጎት በማሟላት አዳዲስ ዓለም ዐቀፍና አገር ዐቀፍ ደንበኞችን እንዲያገኝ የሚያግዝ መሆኑ ተጠቁሟል።

ይህ ትብብር ለኢኮሜርስ አገልግሎት ያለው ፍላጎት እያደገ በመጣበት በዚህ ወቅት የተደረገና የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ የሚረዳ ነው የተባለ ሲሆን፣ ከኮቪድ 19 መከሰት በኋላ የኢኮሜርስ አገልግሎት በፈጣን ሁኔታ እያደገ የመጣ በመሆኑ ከዚህም ጋር ተያይዞ ተጠቃሚዎች እ.ኤ.አ በ2020 የ4.29 ትሪሊዮን ዶላር የኦንላየን ግብይቶችን ማከናወናቸው ነው የተገለጸው።

ማስተር ካርድ ግብይቶችን ለማሳለጥ የሚሠራ ዓለም ዐቀፍ የቴክኖሎጂ ድርጅት ነው።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች