መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበኢትዮጵያ ያለው የደም ክምችት ለሰባት ቀናት ብቻ የሚያገለግል እንደሆነ ተነገረ

በኢትዮጵያ ያለው የደም ክምችት ለሰባት ቀናት ብቻ የሚያገለግል እንደሆነ ተነገረ

በኢትዮጵያ ያለው የደም ክምችት ለሰባት ቀናት ብቻ የሚያገለግል እንደሆነ የኢትዮጵያ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የደም ልገሳ ልምድ እምብዛም የሆነባት ኢትዮጵያ፣ ያላት ለነፍስ አድን ሥራ የሚውል የደም ክምችት ለሰባት ቀናት ብቻ የሚያገለግል እንደሆነ የደምና የቲሹ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ባለፉት ሦስት ወራትም ደም ይለግሳሉ ተብለው ከተጠበቁ 120 ሺሕ ሰዎች መካከል ደም የለገሱት 78 ሺሕ 800 ሰዎች ብቻ እንደሆኑ የገለጹት ሀብታሙ፣ ኢትዮጵያ ያላት የደም ክምችት አናሳ የሚባል እንደሆነ ተናግረዋል።

በቂ የደም ክምችት አለ ተብሎ የሚታሰበው ለ25 ቀናት መሆን የሚችል ክምችት ሲኖር እንደሆነ የተናገሩት ሀብታሙ፣ ከዚህ በፊት በቂ የደም ልገሳ በነበሩባቸው ወቅቶችም ይህንኑ ማሳካት ተችሎ እንደነበር ተናግረዋል። መደበኛ የደም ለጋሾች እጥረት እንዳለም የተናገሩት ሀብታሙ፣ አንድ ሰው በየሦስት ወሩ ደም መስጠት እንደሚችል ተናግረው፣ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ደም ከለገሱ ለጋሾች መካከል 38 በመቶ የሚሆኑት በድጋሚ የለገሱ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የአንድ አገር የደም ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ተሟልቷል ተብሎ የሚታሰበው መደበኛ ደም ለጋሽ ሲኖር እንደሆነ ይነገራል። ይህም አጭር የመጠቀሚያ ጊዜ ያለውን ደም በየጊዜው በመለገስና በመተካት የድንገተኛ የነፍስ አድን ሕክምናዎችን ማገዝ እንደሚገባም ይታመናል። ትምህርት ቤቶችን የትኩረት ቦታዎች በማድረግ መደበኛ ደም ለጋሾችን ለማግኘት እየጣሩ እንደሆነ የተናገሩት ሀብታሙ፣ በመደበኛነት በየሦስት ወሩ ደም የሚለግሱ ግለሰቦችን ማግኘት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በአንድ አገር ውስጥ ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ቢያንስ አንድ በመቶ የሚሆኑት ደም ለጋሽ መሆን እንዳለባቸው ያስቀምጣል። በ2014 በኢትዮጵያ 337 ሺሕ ዩኒት ደም የተሰበሰበ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ዩኒት ደም ከአንድ ሰው የተሰበሰበ ነው ቢባል እንኳን በዓለም ጤና ድርጅት ምጣኔ መሠረት ያነሰ አፈጻጸም እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

ጥቅምት ወር ከገባ ጀምሮ በተለያዩ ዘመቻዎች ደም የመለገስን ልማድ ለማሻሻል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንዳሉ የተናገሩት ሀብታሙ፣ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተሻለ አፈጻጸም እንዳለ ተናግረዋል። ይሁንና እንደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሲዳማ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባሉ ክልሎች ደግሞ የደም ልገሳ አፈጻጸም ጉድለት የታየ ሲሆን፣ የየክልሎቹ የደም ባንኮች እንዲያሻሽሉ አቅጣጫ ተቀምጦ ከጥቅምት ወር ጀምሮ በስፋት እየሠሩ እንደሆነም ተናግረዋል።

በ2015 በመላው ኢትዮጵያ 490 ሺሕ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፣ የክረምት ወራት ከመምጣቱ በፊት አብዛኛውን ደም የመሰብሰብ ሥራ እንደሚሠራም ለማወቅ ተችሏል። በየዓመቱ የደም ተጠቃሚዎች እየጨመሩ እንደመጡ የገለጹት ሀብታሙ፣ የደም አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ተቋማትም እንደጨመሩ የተናገሩ ሲሆን፣ ከተጠቃሚዎች ጋር አብሮ የሚያድግ የደም ልገሳ ልምድ መኖር እንዳለበትም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከአንድ ሺሕ ሰዎች ውስጥ ከኹለት እስከ ሦስት ሰዎች ብቻ ደም የመለገስ ልምድ እንዳላቸው ባንኩ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፣ ደም በመለገስ ሕይወትን ማዳን እንደሚገባም ሀብታሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች