ምግብ ቀዳሚ ከሚባሉ የሰው ልጅ ፍላጎቶች መካከል ዋነኛው እንደሆነ ይታወቃል። እያንዳንዱ ሰው በየቀን እንቅስቃሴው ምግብ እንደሚያስፈልገው ኹሉንም የሚያስማማ ጉዳይ ነው። ድህነት በሚስተዋልባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራትም የምግብ ፍላጎትን ማሟላት የነዋሪዎች ቀዳሚ ዓላማ ነው።
በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ መሠረት፣ እ.ኤ.አ በ2022/2023 የእለት የምግብ ወጪን መሸፈን ካለመቻል የተነሳ 10 ሚሊዮን የዕለት ደራሽ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው ሕዝብ እንደሚገኝባት በሚነገርባት ኢትዮጵያ የምግብ ጉዳይ የኹሉንም ሰው ቤት የሚያንኳኳ ነው።
አዲስ አበባ ውስጥ የቀን ሥራ በመሥራት የሚተዳደሩት አባይነሽ ተስፋዬ ከባለቤታቸውና ከኹለት ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩ ሲሆን፣ የቤት ኪራይ ለመክፈልና በልቶ ለማደር ሲባል በየቀኑ እንደሚባዝኑ ይናገራሉ። ‹‹ሥራ ይመጣል ይሄዳል›› የሚሉት አባይነሽ፣ የሚሠሩት ሥራ የምግብና የመጠለያ ፍላጎታቸውን እንዲያሟላ ከመጣር ውጭ ሌላ ሀብትና ንብረት ለማፍራት አስበው እንደማያውቁ ሲናገሩ፣ ‹‹ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ›› ይላሉ። የምግብና የቤት ኪራይ ወጪያቸውን ማሟላት ከቻሉ፣ ሌላው ትርፍ ነው በሚል እሳቤ።
ምንም እንኳን በተከራዩት ቤት እንጀራ መጋገር የሚችሉ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ጊዜ ዳቦ በመግዛት ለመመገብ እንደሚሞክሩ ሲገልጹም፣ ‹‹እንጀራ ለመጋገር የማገዶ ዋጋ ጣራ ነክቷል። የእንጀራ እህሉም ቢሆን ዋጋው ቀላል አይደለም። ባይሆን ሲገኝ እየጋገርኩ ሲጠፋም ዳቦውንም ምኑንም እያልን ነው የምንኖረው።›› ይላሉ። ‹‹ከተገኘ ሸገር ዳቦ ሸጋ ነው። ግን ወረፋ ነው። በዛ ላይ ደግሞ ወረፋ ሳይደርሰንም ዳቦው ያልቃል።›› የሚሉት አባይነሽ፣ የዳቦ ዋጋም እያደር እየጨመረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
እንጀራ በስፋት ለምግብነት በሚውልባት ኢትዮጵያ፣ ዳቦም ለብዙዎች የቀን ከቀን ምግብ ነው። በባህላዊ መንገድ በየሰፈሩ በግለሰቦች ደረጃ ተጋግረው ከሚሸጡት የዳቦ ዓይነቶች ጀምሮ በትልቅ ፋብሪካ ደረጃ ተጋግሮም ለኅብረተሰቡ ይደርሳል፤ ዳቦ። ጠዋትና ማታ ላይም በዳቦ ቤቶች በርካታ ሕዝብ ተሰልፎ ዳቦ ለመግዛት ሲጠባበቅ ማየት የተለመደ ሆኗል።
የዳቦ አቅርቦት
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስንዴ የማምረት አቅም እንዳላት በባለሙያዎችም ሆነ በመንግሥት ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል። ዳቦ ለመጋገር ወይም ለማምረት በዋነኝነት ከስንዴ የሚዘጋጀው ዱቄት አስፈላጊ ነው። የዳቦ አቅርቦት እጥረት ተከሰተ ወይም ዋጋው ተወደደ ማለት፣ በቀጥታ ከስንዴ ከሚዘጋጀው ዱቄት ጋር ይያያዛል።
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በርካታ የዳቦ መሸጫ ቤቶች ለመመልከት እንደሚቻለው፣ የኅብረተሰቡ የዳቦ ፍላጎት ከፍተኛ ነው። ይሁንና የዋጋው ጉዳይ ለብዙዎች ፈተና እንደሆነ ይነገራል። ለተጠቃሚው ዳቦን በዝቅተኛ ዋጋ የሚያቀርበው ሸገር የዳቦ ፋብሪካ ሲሆን፣ ሌሎች የዳቦ አምራቾች ደግሞ የየራሳቸውን ታሪፍ አውጥተው ምርታቸውን ለገበያ ያቀርባሉ።
በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤትነት የሚተዳደረው ሸገር የዳቦ ፋብሪካ በ2012 ተመርቆ በመሥራት ላይ ይገኛል። ዳቦ ለመጋገር የሚጠቀመውን ዱቄትም በራሱ የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ በቀን 1.8 ሚሊዮን ዳቦ የማምረት አቅም አለው። በአሁኑ ሰዓትም ፋብሪካው በቀን ከ1.3 እስከ 1.5 ሚሊዮን ዳቦ በማምረት ላይ ሲገኝ በኅብረተሰቡ ከፍተኛ ተፈላጊነት አለው።
አንድ የሸገር ዳቦ በኹለት ብር ከ10 ሳንቲም ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን፣ በዚህ ዋጋም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአንድ ብር ከ14 ሳንቲም ድጎማ እንዲሁም አምራቹ ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ደግሞ የ36 ሳንቲም ኪሳራ ወይም ድጎማ እንደሚያደርጉ ከዚህ ቀደም ተዘግቧል። ዳቦው ያለምንም ድጎማ ወደ ገበያ ቢቀርብ፣ በትንሹ የሦስት ብር ከ60 ሳንቲም ዋጋ ሊኖረው እንደሚችልም መረዳት ይቻላል።
የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የምርት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አካለወልድ አድማሱ ከዚህ በፊት ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ ሸገር የዳቦ ፋብሪካ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። የኅብረተሰቡን የምግብ ፍላጎት ለማሟላትም የመሰል ድርጅቶችና የሸማች ማኅበራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው እንደሚገባ ተነግሯል።
አካለወልድ እንደሚሉትም፣ ሸገር ዳቦ ካለው የማምረት አቅም አንጻር የኅብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት አይችልም። ይሁንና ያለውን አቅም ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ምርቱን ለኅብረተሰቡ ለማድረስ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በሌሎች ለትርፍ በተቋቋሙ ዳቦ ቤቶች ባለ 75 ግራም ዳቦ ከ5 ብር ባላነሰ ዋጋ ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን፣ ይህ ዳቦም በወረፋ ይሸጣል። በራሳቸው የገበያ ትስስር የስንዴ ዱቄትን የሚያገኙ ዳቦ አምራቾችም የሚያመርቱትን ዳቦ ራሳቸው በሚያወጡት ዋጋ ለገበያ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ብዙ ተቃውሞ ባይነሳበትም የዋጋ ውድነት እንዳለበት ሲነገር ይደመጣል።
በሌሎች የክፍለ አገር ከተሞች
ተመሳሳይ የዳቦ ፍላጎት በሚታይባቸው የክልል ከተሞችም፣ እንደ ሸገር ዓይነት ለትርፍ ያልተቋቋሙ ዳቦ አምራች ድርጅቶች እንዳሉ ሲነገር አይሰማም። ለትርፍ በተቋቋሙ ዳቦ አምራቾችም አዲስ አበባ ላይ እንደሚስተዋለው ኹሉ 75 ግራም ዳቦ የ5 ብር ዋጋ እንዳለው መረጃዎች ያመላክታሉ።
ጳጉሜ 4/2013 ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት በ800 ሚሊዮን ብር በጀት በተለያዩ 10 የአገሪቷ ከተሞች 10 የዳቦና ዱቄት ፋብሪካዎችን ለማስገንባት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። ከተሞቹም ሐዋሳ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ቦንጋ፣ ሐረር፣ ጎንደር፣ ሰመራ፣ ጅግጅጋ፣ ነቀምት፣ አሶሳ እንዲሁም ደሴ ናቸው። በእነዚህ ከተሞችም በቀን 420 ኩንታል ዱቄት እንዲሁም 300 ሺሕ ዳቦ የማምረት አቅም ያላቸው ፋብሪካዎች እንዲገነቡ ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ከእነዚህ ዐስር ከተሞች ቀደም ብሎ የተጀመረው የአጋሮ የዱቄትና ዳቦ ፋብሪካ ደግሞ በተመሳሳይ የማምረት አቅም ተገንብቶ ጥቅምት 13/2015 ተመርቆ ሥራ እንደጀመረ የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሰዒድ መሐመድ ተናግረዋል።
ሌሎች 10 ፋብሪካዎችም የግንባታ ሂደታቸው እየተከናወነ ይገኛል። በምዕራፍ አንድ የፋብሪካዎች ግንባታ ውስጥ የተካተቱት በሐዋሳ፣ በወላይታ ሶዶ እንዲሁም በቦንጋ ከተሞች በመገንባት ላይ ያሉት የዱቄትና የዳቦ ፋብሪካዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሰዒድ ተናግረዋል።
በምዕራፍ ኹለት ግንባታ ውስጥ እየተገነቡ ያሉ የሐረር እና የጎንደር ፋብሪካዎች ደግሞ የግንባታ ሂደታቸው 75 በመቶ እንደደረሰ የተናገሩት ሰዒድ፣ እስከ ጥር ወር ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በተለያዩ አገራዊ ምክንያቶች የመሬት ርክክብ ዘግይቶ በተካሄደባቸው ቀሪ በሦስተኛ ምዕራፍ የፋብሪካዎች ግንባታ የተካቱት ደግሞ ከኹለቱ ምዕራፎች አንጻር ግንባታቸው የዘገየ ሲሆን፣ ሥራው በመፋጠን ላይ እንደሚገኝ ሰዒድ ተናግረዋል። በዚህ ምዕራፍ የተካተቱትም በሰመራ፣ ጅግጅጋ፣ ነቀምት፣ አሶሳ እንዲሁም ደሴ ከተሞች በመገንባት ላይ ያሉ ፋብሪካዎች ናቸው።
ለፋብሪካዎቹ የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎች በሙሉ ቀደም ብለው የታዘዙ ሲሆን፣ የሲቪል ግንባታ ሥራም በሜድሮክ አባል ኩባንያዎች የሚካሄድ መሆኑ ፋብሪካዎችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የተያዘውን በጀት በአግባቡ እንድንጠቀም አድርጎናል ብለዋል፤ ሰዒድ። አያይዘውም የፋብሪካዎችን ግንባታ ለማጠናቀቅ ከተያዘለት የ800 ሚሊዮን ብር በጀት ብዙ ባልበለጠ የገንዘብ መጠን የፋብሪካዎቹ ግንባታ መጠናቀቅ እንደሚችል ተናግረዋል።
እነዚህ ፋብሪካዎች ተገንብተው ከተጠናቀቁ በኋላ የየከተማው አስተዳደሮች ፋብሪካዎችን ተረክበው የማስተዳደር ሥራ የሚሠሩ ሲሆን፣ ዱቄት የማዘጋጀት፣ ዳቦ የማምረት እንዲሁም ለተጠቃሚ የማድረስ ሥራ የከተማ አስተዳደሮች ይሆናል። ይህም ከትርፍ ይልቅ ኅብረተሰቡን ማገልገል ላይ ያተኮረ ሥራ እንዲሠራ የማድረግ ኃይል እንዳለው ይታመናል።
የሚጠበቀው የስንዴ ምርት
ከሰሞኑ፣ ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ ገበያ ልታቀርብ ነው የሚል ንግግር ተደጋግሞ በመሰማት ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያም የስንዴ ግብይትን እንደሚጀምር አስታውቋል። ይህም አገሪቷ የምታመርተው ስንዴ የውስጥ ፍላጎትን አሟልቶ ለውጭ ገበያ ታቀርባለች የሚል ተስፋን በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል። ከዚህ በፊትም ኢትዮጵያ በዓመት ከ15-20 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በእርዳታና በግዥ ከውጭ አገራት ታስገባ እንደነበር ይታወሳል።
ይህ የአገር ውስጥ ፍጆታን ያሟላል የተባለው የስንዴ ምርትም በዳቦ አቅርቦትና ዋጋ ላይ መሻሻል እንደሚያመጣ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በግብዓት እጥረት ምክንያት ከገበያ የወጡና ያቋረጡ የነበሩ ዳቦ አምራቾችን ወደ ገበያው እንደሚመልስ ይጠበቃል።
ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015