መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብነገረ ጤናለእናቶች ሞት መንስኤ የሆነው የኢክላምሲያ በሽታ

ለእናቶች ሞት መንስኤ የሆነው የኢክላምሲያ በሽታ

ለእናቶች ሞት መንስኤ የሆነው ኤክላምሲያ የተባለው በሽታ ላይ የተደረጉ የተለያዩ ምርምሮች፣ በሽታውን የመመርመሪያ መንገዶችን ብሎም ኢትዮጵያም ይህን በተመለከተ ያለችበትን ሁኔታ በማንሳት ሐይማኖት ግርማይ ከዚህ ቀደም አስነብበውናል። አሁን ደግሞ መለስ ብለው ስለበሽታው ምንነት እና በጉዳዩም ላይ ያለው ግንዛቤ ምን ይመስላል የሚለውን እንደሚከተለው አጋርተውናል።

በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት ወይም ፕሪኢክላምሲያ እና ኢክላምሲያ [Pre-Eclampsia and Eclampsia] ከ5 ወር በላይ በሆኑ ነፍሰጡሮች፣ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ልጅ ከተወለደ በኋላ በእናት ላይ የሚከሰት በሽታ ነው። በሽታው በዓለማቀፍ ደረጃ ከ20 ሳምንት (5ወር) በላይ በሆኑ ነፍሰጡሮች ላይ ከ3 እስከ 7 በመቶ የሚያጋጥም ሲሆን፣ 25 በመቶ ደግሞ ልጅ ከተወለደ ከ4 ቀናት እስከ 6 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ በእናቶች ላይ ይከሰታል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና የማህፀን ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ድልአየሁ በቀለ፣ “እናቶች ላይ የሚከሰት የደም ግፊት እና ተያያዥ በሆኑ ሁኔታዎች የእናትየውን የተለያየ የሰውነት ክፍል የሚጎዳ፣ እንዲሁም በእናት እና በጽንስ ላይ እስከ ሕይወት ማጥፋት የሚያደርስ የሕመም ዓይነት ነው” በማለት በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥመውን የደም ግፊት ገልጸውታል።

በሽታው ፕሪኢክላምሲያ እና ኢክላምሲያ በመባል ለኹለት ይከፈላል። ፕሪኢክላምሲያ የበሽታው የመጀመሪያ ደረጃ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት በሕክምና ከበሽታው የማገገም ሰፊ እድል አለ። ኢክላምሲያ ደግሞ በሽታው ተባብሶ በእናት ወይም በፅንስ ላይ ጉዳት የሚደርስበት ደረጃ ነው። በተጨማሪም፣ ፕሪኢክላምሲያ የከፋ እና ያልከፋ በሚል ደረጃ እንደሚከፈል የሕክምና ባለሙያው ገልጸዋል።

የፅንስ እና የማህፀን ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ደምሰው አመኑ እንደተናገሩት፣ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት በሽታ መንስኤ ከመላምት ባለፈ አይታወቅም። የሕክምና ባለሙያው ያስቀመጧቸው መላምቶች የእንግዴ ልጅ አፈጣጠር [አቀማመጥ]፣ አመጋገብ እና የዘረመል ሁኔታ ናቸው።

ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች፤
የመጀመሪያ እርግዝና ላይ ያለች እናት ከ2ኛ እና ከዛ በላይ ካሉ እርግዝናዎች ጋር ሲነጻጸር በዚህ በሽታ የመጠቃት እድሏ ከፍ ያለ ነው።
በልጅነት ወይም እድሜያቸው ከገፋ በኋላ የጸነሱ እናቶች ተጋላጭ ናቸው።
ከእርግዝና በፊት የተለያየ ሕመም ያለባቸው እናቶች ይበልጥ ተጋላጭ ሲሆኑ፣ እነዚህም የደም ግፊት፣ የኩላሊት እና የስኳር ሕመሞች ናቸው።
በቀደመ እርግዝና ላይ የፕሪክላምሲያ ተጠቂ የነበረች እናት በቀጣይ እርግዝናዋ ላይም በሽታው የመከሰት እድል አለው።
የመንታ ልጆች እርግዝና
የልጅ አባት ሲለወጥ ማለትም ከዚህ ቀደም ከተወለዱት ልጆች አባት ሳይሆን ከሌላ ሰው እርግዝና ሲፈጠር ልክ እንደመጀመሪያ ልጅ እርግዝና ለበሽታው ሊያጋልጥ ይችላል።
ከመጠን ያለፈ ውፍረት
በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት መም ምልክቶች፤
የራስ ምታት ሕመም፣
የዐይን ብዥታ፣
የሰውነት እብጠት [እጅ፣ እግር እና ፊት]
በአጭር ጊዜ ውስጥ የክብደት መጨመር፣
በቀኝ ጡት ስር [ጉበት ያለበት አካባቢ] የሔመም ስሜት መኖር፣
የመተንፈስ ችግር [ትንፋሽ ማጠር]፣
ራስን ስቶ መውደቅ እና ማንቀጥቀጥ፣

በመጀመሪያ ደረጃ ላይ በሽታው ምንም ምልክት ላያሳይ እንደሚችል ዶክተር ድልአየሁ በቀለ ተናግረዋል። ስለሆነም፣ በደም ግፊት መጠን እና በላብራቶሪ የሽንት ምርመራ በሽታው የከፋ ደረጃ ሳይደርስ እንዲታወቅ እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረግ አለባቸው ብለዋል የሕክምና ባለሙያው።

በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የድም ግፊት በሽታ ከሌሎች ከእርግዝና ጋር ተያይዘው ከሚመጡ የሕመም ስሜቶች ጋር እንዴት መለየት ይቻላል? የሚል ጥያቄ ለዶክተር ድልአየሁ አቅርበንላቸዋል።

“የራስ ምታት ሕመም በነፍሰ ጡር እናቶች ላይ ሊያጋጥም ስለሚችል የመመሳሰል ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን፣ በእርግዝና ወቅት በሚያጋጥም የደም ግፊት ምክንያትነት የሚፈጠር የራስ ምታት በቀላሉ የማይለቅ እና በማስታገሻ መድኃኒትም ቢሆን ለውጥ የሌለው ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፤ ባለሙያው። አክለውም፣ ሌሎቹ የበሽታው ምልክቶች ደግሞ ከእርግዝና ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ሕመሞች ጋር የመመሳሰል እድላቸው አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት ሕክምና ሳያገኝ ወደ ኢክላምሲያ ደረጃ ካደገ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው። የደም ግፊት ከፍ በሚልበት ወቅት የእንግዴ ልጅ ከቦታው የመልቀቅ እድል ስለሚኖረው ደም እንዳያስተላልፍ ያደርጋል። ይህም ጽንሱ ሆድ ውስጥ እንዳለ እንዲቀጭጭ ከዛም ጽንስ እንዲቋረጥ ሊያደርግ ወይም የመወለጃ ጊዜ ሳይደርስ ልጅ እንዲወለድ በማድረግ፣ እንዲሁም ከተወለዱ በኋላ በጨቅላ ሕጻናት ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል። በእናት ላይ የኩላሊት፣ የጉበት እና የአተነፋፈስ [የሳንባ] በሽታ ሊያስከትል፣ እንዲሁም አንጎል [ጭንቅላት] ውስጥ ደም እንዲፈስ ሊያደርግ ይችላል። በሽታው ሲባባስ የእናትን ሕይወት ይቀጥፋል።

በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሆኑ አምስት በሽታዎች መካከል ይመደባል። በዚህም በወሊድ ወቅት ከሚያጋጥም የደም መፍሰስ ቀጥሎ በኹለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። በዓለም ላይ በዚህ በሽታ ምክንያት በ1 ዓመት ውስጥ እስከ 63 ሺሕ የሚሆኑ እናቶች ሕይወታቸውን ያጣሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ድንገተኛ የጽንስ እና ጨቅላ ሕጻናት ድጋፍ ሰጪ [Ethiopian National Emergency Obstetric and Newborn Care] መረጃ እንደሚያሳየው፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ 10 በመቶ ለእናቶች ሞት ምክንያት በመሆን የተቀመጠው በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት ነው። በአገሪቱ ከአንድ መቶ ሺሕ ወላድ እናቶች መካከል 412 እናቶች ሕይወታቸው ያልፋል። ሕይወታቸውን ከሚያጡበት ምክንያቶች ውስጥ 19 በመቶውን የሚይዘው በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት ነው። እንዲሁም ዶክተር ድልአየሁ በቀለ እንደተናገሩት፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በተደረገ ጥናት መሠረት በሆስፒታሉ ለእናቶች ሞት ምክንያት በመሆን ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። ለዚህም በዋነኝነት እንደምክንያት ያስቀመጡት የእናቶች የቅደመ ወሊድ ክትትል አለማድረግን ነው።

አዋላጅ ነርስ አሸናፊ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ገጠራማ ቦታዎች እንዲሁም ከተሞች ላይ በሕክምና ሙያ ለ12 ዓመታት ሲሠሩ ቆይተዋል። እናም በዚህ ወቅት ኅብረተሰቡ ለበሽታው ያለው ግንዛቤ እናቶች የሕክምና ክትትል እንዳያደርጉ ምክንያት መሆኑን ታዝቧል። “በክላምሲያ በሽታ እናቶች ራሳቸውን ስተው ሲወድቁ ወይም ሲያንቀጠቅጣቸው ኅብረተሰቡ የሚገምተው የሚጥል በሽታ ስለሆነ ክብሪት ይለኩሳል” በማለት ችግሩን ያለመገንዘብ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል፤ የሕክምና ባለሙያው።

አዋላጅ ነርስ የሆኑት ዋሴ ጉልላት በተመሳሳይ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለበሽታው የተዛባ አመለካከት መኖሩን ተናግረዋል። በደብረ ብርሀን አየር ጤና በሚገኘው ጤና ጣቢያ የሚሠሩት ባለሙያው፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ በሽታውን ከባእድ አምልኮ እና ከሀጢያት ጋር የማያያዝ ሁኔታ መኖሩን አስተውለዋል። ይህ የሚስተዋለው በሽታው ኢክላምሲያ ደረጃ ላይ ደርሶ የማንቀጥቀጥ ወይም የመጣል ሁኔታ ሲኖረው ነው።

ስለሆነም፣ በዚህ ወቅት የሚሰጠው ሕክምና አስፈላጊ እንዳልሆነ በማሰብ ሕክምናውን እንዳይሰጥ የማድረግ [የመከልከል] ሁኔታ አለ። በተለይ ገጠራማ አካባቢ ባለው ማኅበረሰብ ዘንድ ይህ እሳቤ እና ተግባር መኖሩን ነው ባለሙያው የተናገሩት። ለዚህም ታማሚዎች ለከፋ ደረጃ ይዳረጋሉ።

ማንኛውም በሽታ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ አስቀድሞ መከላከል ወይም በሽታው እንዳይከሰት ማድረግ ያስፈልጋል። ስለሆነም፣ ይህ በሽታ እንዳይከሰት አስቀድሞ ለመከላከል መደረግ የሚገባቸው ሁኔታዎችን እንዲያብራሩልን ለዶክተር ድልአየሁ በቀለ ጥያቄ አቅርበንላቸዋል።

- ይከተሉን -Social Media

“በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት እንዳይከሰት አስቀድሞ ለመከላከል በሳይንስ የተገኘ ግኝት ወይም የተረጋገጠ ነገር የለም” ብለዋል ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ። ነገር ግን፣ ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ እናቶች እርግዝና ከተፈጠረበት ወቅት ጀምሮ አስፈላጊውን የቅድመ ወሊድ ክትትል ካደረጉ በሽታው ወደ ከፋ ደረጃ ሳይደርስ ማለትም ኢክላምሺያ ከመሆኑ አስቀድሞ ሕክምና እንዲያገኙ ይደረጋል።

በተመሳሳይ ሁሉም ነፍሰጡር እናቶች ከእርግዝና የመጀመሪያ ወራት ጀምረው የቅድመ ወሊድ የሕክምና ክትትል ማድረግ አለባቸው። በሽታው ጉዳት ከማድረሱ አስቀድሞ ለመከላከል ዋነኛው መፍትሔ አስፈላጊውን የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረግ በመሆኑ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄዱ በማለት የሕክምና ባለሙያው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች