ትላንት 100 ብር ሲሸጥ የነበረ ዕቃ ዛሬ 200 መቶ እና 300 ብር ሲሸጥ ይታያል። የቤት፣ የመሬት እና የመኪና ዋጋ ጭማሪው ብሎም የሚጨምርበት ፍጥነት ከፍተኛ ነው።
ከኹለት ዓመት በፊት ከሞሮኮ አገር 250 ዶላር ይመጣ የነበረ የአፈር ማዳበሪያ፣ በዚህ ዓመት ከ1000 ዶላር በላይ ተገዝቶ ነው የገባው። የመማሪያ ቁሳቁሶች፣ የነዳጅ፣ የአልባሳት፣ የቤት ዕቃዎች፣ የኤሌትሮኒክስ መገልገያዎችና የሌሎች ዋጋ በእጅጉ ጨምሯል።
ከላይ ያሉት ለአብነት ተጠቀሱ እንጂ፣ በአጠቃላይ በምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ባልሆኑ ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ አሁን ላይ የሚስተዋለው ግሽበት መነሻው አገሪቱ የተጨማሪ እሴት ግብርን (ቫት) ስታስተዋውቅ የነበረበት ወቅት (ማለትም በ1995/96) ነው። አሁን ላይ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ቀውስ እያስከተለ ያለው ግሽበት በሌሎች አገራት ከተከሰተው ግሽበት የሚለየው በኹለት መሠረታዊ ነገሮች ነው። ይኸውም ለረዥም ጊዜ የቆየ እንዲሁም እየጨመረ የሚሄድ ከፍተኛ መጠን ያለው ግሽበት ነው።
ለኹለት ዐስርት ዓመታት የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ጎታች ኃይል ሆኖ መቀጠሉ የሚነገርለት ይህ ግሸበት፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ለመግታት ፈታኝ በሆነ ደረጃ ላይ መድረሱ ይገለጻል። ለግሽበት መከሰት በርካታ ገፊ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፣ ጦርነትና ግጭቶች፣ ድርቅ፣ ወረርሽኝ፣ የሥርዓት ለውጥ፣ ስር የሰደደ ሙስና እና ሌሎች ይጠቀሳሉ።
በቅርቡ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማኅበር (Ethiopian Economics Association) በእንግሊዝኛ ቋንቋ ‹‹Inflation and the Ethiopian Economy›› በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ የታተመውን መጽሐፉን ባስመረቀበት መድረክ ባለሙያዎች ስለ ግሸበት እና የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በርካታ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል።
በዚህም የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አረጋ ሹመቴ (ዶ/ር)፣ አገሪቱ አሉብኝ ከምትላችው የምጣኔ ሀብት ችግሮች አንዱና ዋናው ግሽበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ችግሩ በፊትም ፈተና ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ አሁንም የሚቀጥል ነው›› ብለዋል። ኢትዮጵያም ከዚምባቡዌ እና ሱዳን በመቀጠል በአፍሪካ ሦስተኛዋ፣ ከዓለም ደግሞ ዐስረኛዋ ከፍተኛ ግሽበት ያለባት አገር መሆኗን አንስተውም፣ ግሽበት ዐብይ የፖሊሲ ፈተናም ሆኗል ሲሉ ተደምጠዋል።
አክለውም፣ ችግሩን ለማስተካከል ባለፉት ኹለት ዓመታት ከ10 ያላነሱ እርምጃዎች (ሰንበት ገበያ፣ ፍራንኮ ቫሉታ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች እገዳ እና ሌሎች) ቢወሰዱም ሊስተካከል አልቻለም ነው ያሉት። ባለፈው ዓመት 2014 ግንቦት ወር ከነበረው የግሽበት ምጣኔ (37.2 በመቶ) አንጻር፣ በዚህ ዓመት 2015 መስከረም ወር ላይ ያለው ምጣኔ (32.5 በመቶ) የተወሰነ የቀነሰ ይመስላል። ሆኖም ገና ብዙ መፍትሔዎችን በመተግበር ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት።
ማኅበሩ ለግሽበቱ ዋና ምክንያት ብሎ ከለያቸው ስድስት ነጥቦች መካከል በአቅርቦት እና በፍላጎት በኩል ያሉ ችግሮች ቀዳሚ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ገበያ፣ በገበያ ላይ ያለው የገንዘብ መጠን፣ የፖለቲካ አስተዳደር እና አካባቢያዊ ተጽእኖዎች ቀሪዎቹ ናቸው። በመሆኑም የአገሪቱ የማምረት አቅም ከፍ እስካላለ ድረስ ግሽበቱ የሚቀጥል ነው ያሉት ባለሙያው፣ ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ የምርት አቅማችን እየቀነሰ ነው የሄደው ብለዋል።
ላለፉት 13 ዓመታት ገደማ ከተከሰተው ግሽበት 53 በመቶ ያህሉን በምግብ ነክ ፍጆታዎች የተከሰተው ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቅሰዋል። ቀሪው 47 በመቶ ግሽበት ምግብ ነክ ባልሆኑ ፍጆታዎች የተከሰተ ነው ያሉት ባለሙያው፣ ከዚህ ውስጥ ከመሬት አጠቃቀም ጋር የተያያዘው አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
ከመሬት ጋር ተያይዞ የዜጎችን ከፍተኛ የቤት ፍላጎት እና የቤት ኪራይ ዋጋ መናርን እንዲሁም ለሌሎች የልማት ሥራዎች የሚሆን የመሬት አቅርቦትን ችግርን በመጥቀስ፣ በዚህ ወቅት መሬትን ለልማት የማግኘት ዕድል በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2008 ዜጎች መሬትን ለልማት የማግኘት ዕድላቸው 96 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 21 በመቶ ደርሷል ብለዋል። ይህም የግሽበቱ አንድ ገፊ ኃይል ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
በተለይ ካለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት ወዲህ የውጭ ምንዛሬ ልዩነት እየሰፋ መሄዱ ሌላው የግሽበት ምክንያት ነው ተብሏል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዝቅተኛ ግብር ከሚሰበስቡ አገራት አንዷ መሆኗ ብሎም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ከጣሉ ቀዳሚ የአፍሪካ አገራት አንዷ መሆኗ፣ እነዚህም ሌሎች መንስኤዎች መሆናቸው ተመላክቷል።
በ2011/12 ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው መግባቱ (ከጠቅላላ ምጣኔ ሀብት 44 በመቶ) እና ይህም እየጨመረ መሆኑ ሌላው ሰበብ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው የተገለጸው። እጅግ ዝቅተኛ የፋይናንስ ተቋማት የቁጠባ ወለድ ምጣኔ፣ ከፍተኛ የማበደሪያ ወለድ እና ውስን የብድር አገልግሎት እነዚህም ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸው ተጠቁሟል።
ዝቅተኛ ኢንቨስትመንት መጠን መኖሩም ሌላኛው የግሽበት ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ በ2012/13 ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መጠን የነበራት ሲሆን፣ እሱም የጠቅላላ አገራዊ ምርት (GDP) 41 በመቶ ድርሻ የነበረው ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ከ31 በመቶ በታች ነው ተብሏል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እድገት፣ የሩስያ ዩክሬን ጦርነት እንዳሉ ሆነው፣ የኅብረተሰቡና የመንግሥት ወጭ ማደግ፣ የአገሪቱ የውጭ ንግድ ውስንነት እንዲሁም ሙስና ተጨማሪ ግሽበት አምጭ ኃይሎች መሆናቸውም ታምኖበታል።
በሌላ መልኩ፣ ግሽበት የምጣኔ ሀብት እድገት ውጤት ነው የሚሉ ባለሙያዎችም አሉ። ግሽበት ከምጣኔ ሀብት እድገት የሚወለድ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ግሽበት ግን ከምጣኔ ሀብት እድገቱ ጋር በእኩል አኃዝ የሚጓዝ ከፍተኛ መጠን ያለው ነው በማለት ሐሳቡን የተቹ ባለሙያዎች አሉ።
በዚህ ሁኔታ ከቀጠለም ምጣኔ ሀብቱ ቆሞ-ቀር ወይም ወደኋላ የሚመልስ ሊሆን ይችላል ነው የተባለው። ከገጠሩ አንጻር የከተማው ማኅበረሰብ በግሽበቱ ምክንያት ተጠቂ ነው። ከዚህም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ዋነኛ ተጠቂ መሆናቸው ተገልጿል።
ከፍተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በችግሩ ከመጠቃት ይልቅ በአንጻሩ በግሽበቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል እንደተፈጠረም ሳይጠቀስ አልቀረም።
የሰሜኑን ጦርነት እና የሩስያ ዩክሬንን ጦርነት ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ማኅበሩ አጠናኹት ባለው መሠረት፣ ደቡብ (20.3 በመቶ)፣ ኦሮሚያ (20 በመቶ) እና ትግራይ (20 በመቶ) ክልሎች በቅደም ተከተል ከፍ ያለ የግሽበት መጠን የሚታይባቸው ክልሎች ናቸው።
ሌላኛው የዘርፉ ባለሙያ ጣሰው ታደሰ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት የድህነት ቅነሳ ዘዴ ደካማ በመሆኑ ግሽበቱን በቀላሉ መቀነስ እንዳልተቻለ አመላክተዋል። አምራቹም ሆነ ተጠቃሚው እንዲሁም በተለይ ሠራተኛው የማኅበረሰብ ክፍል በዚህ ችግር እየተመታ ነው ብለዋል።
ብዙ የገንዘብ መጠን እየታተመ ወደ ምጣኔ ሀብቱ እንዲረጭ መደረጉም የአምራች ዘርፉን አቅም ሊያሳድግ ያልቻለ ድርጊት ነው ሲሉ ገልጸውም፣ በርካታ እርምጃዎች ቢወሰዱም ሊስተካከል አልቻለም ነው ያሉት።
‹‹እድገት አለ፣ ግሽበትም አለ›› የሚሉት ባለሙያው፣ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት አሳየ ከተባለ ሊሆን የሚችለው በአገልግሎት ዘርፉ ነው። ነገር ግን መሪ እንዲሆን የሚፈለገውን የግብርናውና የኢንዱስትሪ ዘርፉ ነው፡፡ ሆኖም የአገልግሎት ዘርፉ እነዚህን ከቀደመ በእርግጥም ምጣኔ ሀብቱ ቢያድግም ግሽበቱም አይቀሬ ነው በማለት አብራርተዋል።
ስለሆነም፣ የአገልግሎት ዘርፉን ከሌሎች ወሳኝ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ጋር ማጣጣም እንዲሚገባ ሳይጠቅሱ አላለፉም።
በጦርነትና በግጭቶች የተነሳ በርካታ አምራች የነበረ የማኅበረሰብ ክፍል ተረጂ ሲሆን፣ እንዲሁም እስከ 50 በመቶ ድረስ ግምት የሚሰጠው የሥራ አጥነት ቁጥር ግሽበቱን ከቁጥጥር ውጭ ሊያደርጉ ከሚችሉ በርካታ ምክንያቶች ውስጥ እንደሚጠቀሱም ነው የተናገሩት።
ግሽበቱ ሊቀንስ ይችላል?
በርካቶች አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለው ከ30 በመቶ በላይ የግሽበት መጠን፣ ሊቀንስ ይችላል ወይ በማለት ይጠይቃሉ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ በተለይም ከአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ማብቂያ ወቅት ጀምሮ አልፎ አልፎ ከፍ ያለ የግሽበት መጠን ይታይ ነበር። የተከሰተው የግሽበት መጠን ከግማሽ በላይ ሲቀንስ፣ በኹለት አኃዝ የተከሰተው የግሽበት ምጣኔ ወደ አንድ አኃዝ ሲቀንስም ታይቷል።
ለአብነትም በ1966፣ 29 በመቶ ግሽበት የነበረ ሲሆን፣ ብዙም ሳይቆይ ግሽበቱ ከተረጋጋ በኋላ እንደገና በ1977ቱ ድርቅ ወቅት 19 በመቶ ነበር። ይህም ግሽበት እንደገና ቀንሶ ሌላኛው የወቅቱ ከፍተኛ የግሽበት መጠን የተባለው፣ ደርግ ተወግዶ ኢሕአዴግ ሲተካ (1993) የተከሰተውና መጠኑም 36 በመቶ የነበረው ነው።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይህም ግሽበት ወደ አንድ አኃዝ የተመለሰ ሲሆን፣ ከኤርትራ ጋር በነበረው ጦርነት፣ በ1990ዎቹ በነበረው ድርቅ እንዲሁም በምርጫ 97 መጠነኛ የግሽበት ለውጦች ተስተውለዋል።
ነገር ግን፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ይህ አኃዝ ወደ 44 በመቶ ከፍ አለ። ወቅቱም ሚሊኒየም (2000) ነበር። እስካሁን ከተመዘገቡ የግሽበት መጠኖች በኢትዮጵያ ሚሊኒየም የተከሰተው ከፍተኛው መሆኑን መረጃዎች ይገልጻሉ።
ሆኖም ይህም ሊቀንስ በመቻሉ፣ በምርጫ 2002 ወቅት የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ግሽበት 32 በመቶ ነበር። ከዚህም በመቀነስ በቀጣዮቹ ዓመታት እስከ 10 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ አሁን ያለው የግሽበት መጠን ከእስካሁኑ የተለየ እንዲባል ያስቻለው ከ2008/09 ጀምሮ አንድ ጊዜም ሳይቀንስ እየጨመረ በመምጣቱ ነው።
ስለሆነም፣ መንግሥት ጠንካራ የመፍትሔ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ ከቻለ ግሽበቱ የማይቀንስበት ምክንያት እንደሌለ ይነሳል።
የመፍትሔ እርምጃዎች
መንግሥት ከዚህ በፊት ተከታታይ እርምጃዎችን የወሰደ ቢሆንም፣ ግሽበቱን በሚፈለገው ልክ መቀነስ ካልቻለ፣ መቀነስ ያልተቻለበትን ምክንያት በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል ሲሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
‹‹ይህን ያህል እርምጃዎች ስለተወሰዱ ግሽበቱ ይስተካከል ብሎ ማሰብ ድክመት ነው። ይልቁንም ግሽበትን በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ ለመፍታት (ከመሬት፣ ከግብር፣ ከግብርና እና ከኢንዱስትሪ እንዲሁም ሌሎች ጋር የተያያዙ) ጠንከር ያሉ የመፍትሔ እርምጃዎችን መተግበር ይገባል›› ሲሉም ጠቁመዋል።
‹‹የጸጥታ ችግር ካልተፈታ ስለሌሎች ነገሮች ብዙ መናገር እርባና ቢስ በመሆኑም፣ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ፣ ምጣኔ ሀብቱን በስሌት ለመምራት ሕዝብና ቤት ቆጠራ ማድረግ፣ የፈጠራ አቅምን ማሳደግ ብሎም ጥቁር ገበያውን መከላከል መቻልና ከመቼውም ጊዜ በላይ በዚህ ወቅት ጫፍ የነካውን ሙስና ማስወገድ ወሳኝ የመፍትሔ እርምጃዎች ናቸው›› ተብሏል።
በተጨማሪም፣ ሰውና አካባቢ ተኮር አስተዳደራዊ ሥርዓትን መዘርጋትና ማዘመን፣ በድለላ የተሞላውን የንግድ ሰንሰለት መቆጣጠር፣ ተቋማዊ ለውጥ እንዲሁም ጠንከር ያሉ የፖሊስ ማሻሻያዎችና አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግም ግድ ሊሆን እንደሚችል ነው ባለሙያዎች የሚመክሩት።
የውጭ ንግድ አቅምን ማሳደግ በሰፊው የታመነበት በመሆኑም፣ ከታች ላለው አምራች/አቅራቢ የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋትም ይገባል ነው የተባለው።
በዘርፉ ባለሙያዎች አገላለጽ፣ ግሽበት ከካንሰር ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። ካንሰር በቶሎ ካልታከመ የሰውነት አካላትን ሲያጠቃ ኖሮ በመጨረሻም ሰውዬውን ለሞት እንደሚያበቃው ኹሉ፣ ግሽበትም በጊዜ መፍትሔ ካልተበጀለት እያንዳንዱን ዘርፍ ሲያዳክም ኖሮ በመጨረሻም ከቁጥጥር ውጭ የሆነና በቀላሉ የማይቃና የምጣኔ ሀብት ውድቀት ሊያስከትል ይችላል።
ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015