መነሻ ገጽዜናወፍ በረር ዜናከሥርዓተ ትምህርቱ ውጪ የሚሠሩ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተነገረ

ከሥርዓተ ትምህርቱ ውጪ የሚሠሩ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተነገረ

የአዲስ አበባ ትምህርትና ሥልጠና ቁጥጥር ባለሥልጣን ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ውጪ ያልተጠናና መንግሥት ያልፈቀደው የትምህርት ሥርዓትን የሚከተሉ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቀ።

እንዲሁም፣ ተማሪዎች ከትምህርት ሂደቱ ጋር የማይገናኙ ቁሳቁስ እንዲያመጡ የሚያስገድዱት ላይም እርምጃ እወስዳለሁ ነው ያለው።

የአዲስ አበባ ትምህርትና ሥልጠና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንደገለጸው፣ አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት በተመለከተ የትምህርት ክትትልና ጥራት ፍተሻ እየተደረገ ነው።

በዚህም መንግሥት ያልፈቀደውና ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ውጪ የትምህርት ሥርዓትን የሚከተሉ የትምህርት ተቋማት እንዳሉ በጥናት መረጋገጡ ተገልጿል።

ተቋማቱ መንግሥት ያስቀመጠውን የትምህርት ሥርዓት እንዲከተሉ ባለሥልጣኑ ያሳሰበ ሲሆን፣ ከዚህ ድርጊት የማይቆጠብ ተቋም ካለ በተቀመጠው ሕግና ደንብ መሠረት በቶሎ እርምጃ እንደሚወሰድ ነው የተጠቆመው።

በትምህርት ተቋማቱ ከተገኙት የአሠራር ችግሮች ውስጥ አንደኛው፣ ከሌሎች አገራት የተቀዱ ሥርዓተ ትምህርትን በአገሪቱ የሥርዓተ ትምህርት መመዘኛ መስፈርቶች ሳይጠና ተማሪዎች እንዲጠቀሙ ማድረግ መሆኑም ተመላክቷል።

ይህም ተማሪዎች ከአገር ውስጥ ባህል፣ ሥነ ሥርዓትና ጥበብ ጋር እንዲራራቁ በማድረግ በውጭ አገራት ባህል የሚማረክ ትውልድ እንዲፈጠር ያደርጋል የሚል ሐሳብ ቀርቧል።

ኹለተኛም ተማሪዎች በተገቢው ሰዓት መማር ያለባቸውን የትምህርት ዓይነት በሌሎች የትምህርት ዓይነቶችን እንዲተኩ ማድረግ ሲሆን፣ ይህም ተማሪዎች የትምህርት ፍላጎታቸው እንዲቀንስ እንደሚያደርግና ተደራራቢ የትምህርት ጫና መኖሩም ተማሪዎች ለጭንቀት እንዲዳረጉ የሚያደርግ መሆኑ ነው የተነሳው።

እንዲሁም ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ጋር በተያያዘ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል በአገር ውስጥ ቋንቋ መማር ያለባቸውን ትምህርቶች በእንግሊዝኛ እንዲማሩ የሚያደርጉ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ ያለው ባለሥልጣኑ፣ በአገሪቷ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር መብትን የሚፃረር በመሆኑ ተቋማቱ ከወዲሁ መፍትሔ እንዲያበጁ አሳስቧል።


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

 

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች