በአዲስ አበባ ከተማ የመታወቂያ እድሳት አገልግሎት ከኅዳር 1/2015 ጀምሮ በኹሉም ክፍለ ከተሞች እንደሚጀመር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ላይ እያካሄደ ያለው ማሻሻያ እንዲሳካ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ በተቀመጠበት መድረክ ላይ፣ በመጪው ሳምንት ለሚጀመረው የመታወቂያ እድሳት በየደረጃው ያለው መዋቅር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጿል፡፡
በኹሉም ደረጃ የሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ቀደም ተብሎ በተከናወነው የቅድመ ዝግጅት ተግባርና አሰራሩ መሠረት አገልግሎት ፈላጊውን ኅብረተሰብ በቀናነትና በቅልጥፍና ማስተናገድ እንደሚገባቸውም ነው አስተዳደሩ ያሳሰበው፡፡
የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ማሻሻያ ማካሄድ ያስፈለገው ተቋሙ ያጋጠመው ችግር የመልካም አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የሀብትና የአገር ደኅንነት ስጋት ጭምር በመሆኑ ነው ያለው ከተማ አስተዳደሩ፣ ችግሩን በውል ተረድቶ ለመፍትሔው በሚካሄደው ማሻሻያ ኹሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ መወጣት እንዳለበትም ተመላክቷል።
ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015